Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለአማራ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት የቀረቡ ዕጩዎች የብቃትና ታማኝነት ጥያቄ ቀረበባቸው

ለአማራ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት የቀረቡ ዕጩዎች የብቃትና ታማኝነት ጥያቄ ቀረበባቸው

ቀን:

  • ብሔራዊ ባንክ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወስድና ማስተካከያ እንዲያደርግ አቤቱታ ቀርቦለታል
  • ዕጩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ጥያቄው ከሥርዓት ውጪና ባንኩን የማፍረስ እንቅስቃሴ ነው ብለዋል

የባንክ ኢንዱስትሪውን እ.ኤ.አ. ጁን 18 ቀን 2022 ከ185 ሺሕ በላይ በሆኑ ባለአክሲዮኖች የመሠረተውና ኢንዱስትሪውን በከፍተኛ የመመሥረቻ ካፒታል የተቀላቀለው አማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር፣ ለባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት የቀረቡ ዕጩ አባላት የብቃትና የታማኝነት ችግር እንዳለባቸው ተገልጾ፣ ከዕጩ አባልነት እንዲሰረዙና ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ለብሔራዊ ባንክና ለባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምልመላና አስመራጭ ኮሚቴ ጥያቄ ቀረበ፡፡

ጥያቄ የቀረበባቸው የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዕጩ አባላት በበኩላቸው ቅሬታ ማቅረብ መብት መሆኑንና መቅረብም እንዳለበት ተናግረው፣ ነገር ግን በእነሱ ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ወይም የእነሱን ብቃትና ታማኝነት ምክንያት በማድረግ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ፣ ከጀርባው ሌላ ተልዕኮ ያለውና ባንኩን ለማፍረስ የሚደረግ ሴራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ቁጥራቸው ከሃያ በላይ የሆኑ ባለአክሲዮኖች ቅሬታቸውን ለብሔራዊ ባንክ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ለፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ለአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር የዳይሬክተሮች ቦርድ ምልመላና አስመራጭ ኮሚቴ፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሱፐርቪዥን መምርያ እንዳብራሩት፣ ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት ዕጩ ሆነው የቀረቡት አባላት የፋይናንስ ፖሊሲ መሠረታዊ መርሆዎች ማለትም ታማኝነት፣ ሀቀኝነት፣ ኢአድሏዊነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የጣሱ ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አቤቱታ ያቀረቡት የባንኩ ባለአክሲዮኖች ትኩረት ሰጥተው ቅሬታቸውን ያቀረቡባቸው ዕጩ አባላት፣ ባንኩን በቦርድ ሊቀመንበርነት ለሦስት ዓመታት ያገለገሉትና ከሁለት ሳምንታት በኋላ ታኅሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ለተጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ዕጩ ሆነው በቀረቡት አቶ መላኩ ፈንታ፣ ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ፣ አቶ ኃይለ ማርያም ተመስገንን ጨምሮ 29 ዕጩ አባላት ላይ ነው፡፡

ለባንክ ሥራ የወጣው አዋጅ ቁጥር 592/2000 ድንጋጌ፣ ‹‹ማንኛውም በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በውጭ አገሮች እምነት በማጉደል ወይም በማጭበርበር ወንጀል ተከስሶ፣ በፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ የተሰጠበት ሰው፣ የባንክ ዳይሬክተር ወይም ሠራተኛ መሆን አይችልም›› የሚል ሆኖ ሳለ፣ አቶ መላኩ ፈንታ ግን የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መምራት የሙስና ወንጀል ተከስሰውና ጥፋተኛ ተብለው፣ የባንክ ማቋቋሚያ አዋጅንና የኮርፖሬት ገቨርናንስ መርሆዎችን በሚፃረር ሁኔታ የአማራ ባንክ የቦርድ ሰብሰቢ መሆናቸው ሕግን መጣስ መሆኑን ባለአክሲዮኖቹ ያቀረቡት አቤቱታ ያብራራል፡፡

ስለቀረበባቸው ቅሬታና ክስ አቶ መላኩ ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹እኔ የተከሰስኩበት ወይም ተከስሼ የነበረበት ጉዳይ አገርና ሕዝብ የሚያውቀው ነው፡፡ ተከስሼ የነበረው እምነት በማጉደልና በማጭበርበር አይደለም፡፡ የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኃን መምራት በሚል እንጂ፣ ከባንክ ሥራ ሕግ ወይም አዋጅ ጋር በተገናኘ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንድ ግለሰብ ወንጀለኛ የሚባለው በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ የወንጀል ቅጣት ሲጣልበት እንደሆነ መደንገጉን አስታውሰው፣ በእሳቸው ላይ ክስ መሥርቶ የነበረው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ክሱን በማንሳትና በማቋረጥ፣ በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት አለመድረሱን በማረጋገጥ ነፃ መባላቸውን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ባንክን ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር ሲያቋቁሙ ከምንም ነገር ነፃ መሆናቸውን ለብሔራዊ ባንክ ማስረጃ ቀርቦና ተረጋግጦ መሆኑን በማከል፣ ቅሬታና ክስ የሚያቀረቡ ግለሰቦች (ባለአክሲዮኖች) ሆን ብለው ባንኩን ለማፍረስና ስም ለማጠልሸት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አቤቱታና ቅሬታ አቅራቢዎቹ ባለአክሲዮኖች በበኩላቸው በርካታ ቅሬታዎችን በዝርዝር ያቀረቡት፣ ብሔራዊ ባንክና አስመራጭ ኮሚቴው ተገቢውን የማስተካከያ ዕርምጃ በመውሰድ፣ በባንኩና በአገር ላይ ያንዣበበውን ሊተካ የማይችል ውድቀት የሚመለከት ሲሆን፣ በዋነኛነት ተጠያቂ ያደረጉትም አቶ መላኩንና አቶ ኃይለ ማርያም ተመስገንን ነው፡፡ ተፈጽመዋል ያሉት የሥነ ምግባር ጉድለትም ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤን የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ሳያውቅና ሳይፈቅድ፣ የአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አድርገው በመቅጠራቸው ሥልጣናቸውን ያላግባብ ተጠቅመዋል የሚል ነው፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ወ/ሮ መሰንበት ካለባቸው የብቃት ማነስ ችግር በተጨማሪ፣ በሌላ ተቋም የቦርድ አባልና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ቋሚ ሠራተኛ በመሆናቸው፣ የባንኩን የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በአግባቡ ሊመሩ አልቻሉም ብለዋል፡፡ እንዲሁም የባለአክሲዮኖችን መረጃ በተገቢው ሁኔታ በፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በኩል ባለማደራጀታቸውና ለብሔራዊ ባንክ ባለማቅረባቸው፣ በአክሲዮን ሽያጭ የተሰበሰበ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያለ ሥራና ያለ ወለድ ታግዶ መቀመጡን፣ በዚህም ምክንያት ባንኩም ሆነ ባለ አክሲዮኖቹ ከፍተኛ ጥቅም እንዲያጡ ማድረጋቸውን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በርካታ ባለአክሲዮኖች መሥራች አባል እንዳይሆኑና የባንኩ መመሥረቻ ካፒታልም ዝቅ እንዲል ማድረጋቸውን፣ በባንኩ የማበደር አቅምና ተወዳዳሪነት ላይ ቀጥተኛ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ መሠረታዊ የፋይናንስ መርሆዎች መጣሳቸውን አክለዋል፡፡

በወ/ሮ መሰንበት ወይም በፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ምክንያት የአክሲዮን ግዥ መዋጯቸው የታገደባቸው አካላት የባንኩ ባለአክሲዮን ባለመሆናቸው፣ በባንኩ የሥራ አመራር ቦርድ ምርጫ ሒደት ውስጥ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብታቸውን እንዲያጡ መደረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ምንም እንኳን በራሳቸው በተጭበረበረ አካሄድ የተመረጡና ዕጩ ሆነው የቀረቡ ቢሆንም፣ እሳቸውም አቶ መላኩም የባንኩ ባለድርሻ አለመሆናቸውን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጠቁመዋል፡፡ አቶ መላኩ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የባንኩ ባለአክሲዮን ሳይሆኑ መሆኑንና ይህም የተጠያቂነትና የግልጽነት መርህን የጣሰ ከባድ የማጭበርበር ወንጀል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለባንክ ምሥረታ ጉባዔ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ወይም ሕጋዊ ወኪሎች በመቆጣጠሪና በመፈረሚያ ሰነድ ላይ መፈረምና ድምፅ መስጫ ካርድ መውሰድ እንዳለባቸው የሚያስረዱት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ አቶ መላኩ ግን አሠራሩን በመቃረን ሕጋዊ ውክልና ያልሰጧቸውን ባለአክሲዮኖች ሰነድ ላይ በመፈረምና የድምፅ መስጫ ካርዱን በመውሰድ፣ የምርጫ ሒደቱን ማዛባታቸውን አስረድተዋል፡፡ ዕጩ የቦርድ አባላት ምርጫን ለማከናወን ከ3.2 ቢሊዮን ብር በላይ አክሲዮን ያላቸው ባለአክሲዮኖች ቀርበው ውክልና የሰጡ በማስመሰል፣ ከፍተኛ ዋጋ ያለው የመራጭነት ድምፅ ያለ ሕጋዊ ውክልና በሐሰት በተቀነባበረ መንገድ ለራሳቸውና ለሌሎች ግለሰቦች እንዲደለደል መደረጉን ማረጋገጥ መቻሉን ቅሬታ አቅራቢዎቹ  አስረድተዋል፡፡ ይህም የባንክ ሥራ ዘርፍ የሚጠይቀውን የተዓማኒነት መርህን መተላለፋቸውንና የቦርድ መቀመጫዎችን በአብላጫ ድምፅ ለመያዝ ከፍተኛ ርቀት መጓዛቸውን እንደሚያሳይም ጠቁመዋል፡፡ አቶ መላኩ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አብረዋቸው ይሠሩ የነበሩትን አቶ አባቡ እምሩ፣ አቶ በላቸው በየነና አቶ ሰጥቶናል ደሳለኝ (የአማራ ልማት ማኅበርን ወክለው) እሳቸው (አቶ መላኩ) የያዙትን ድምፅ በመጠቀም ዕጩ የቦርድ አባል ሆነው እንዲቀርቡ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ መሠረታዊ የሆነ የኮርፖሬት ገቨርናንስ (Corporate Governance) መርህን በእጅጉ የጣሰ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አቶ መላኩ ባለአክሲዮኖቹ ያቀረቡባቸውን አቤቱታና ቅሬታ በሚመለከት ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ወ/ሮ መሰንበት አገርና ሕዝብ ያወቃቸው፣ የማንንም ድጋፍም ሆነ ይሁንታ የማይፈልጉ፣ ብቻቸውን የሚቆሙና በዘርፉ ብቃት ያላቸው ባለሙያ ናቸው፡፡ ያለ አደራጅ ኮሚቴ ዕውቅና ለአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አድርጎ ‹‹አቶ መላኩ ሾሟቸዋል›› የሚባለው አሳሳች ክስና ማወናበጃ፣ እንዲሁም የሌላ ተልዕኮ ማሳኪያ ማጀቢያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስለወ/ሮ መሰንበት አቀጣጠር በግልጽ የሚያስረዳውን ቃለ ጉባዔ ማየት በቂ መሆኑን የሚናገሩት አቶ መላኩ፣ ቅጥሩ የተፈጸመው በአደራጅ ኮሚቴው ዕውቅና መሆኑንና በሰብሳቢ፣ በምክትል ሰብሳቢ፣ በጸሐፊና በፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አደራጅ ተወስኖ የተፈጸመ ቅጥር መሆኑን አክለዋል፡፡

‹‹የሚገርመው ነገር ከሳሾቻችን በእያንዳንዱ ሰነድ ላይ ፈርመዋል፡፡ በወ/ሮ መሰንበት በኩል ሆነው ከፈረሙት ውስጥ የአሁኑ ከሳሻችን አቶ የልቤ ሞላ አንዱ ናቸው፡፡ ሁሉንም እንቅስቃሴ በሐሰት ፕሮፓጋንዳ እየመሩ ያሉትም እሳቸው ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ሌላው፣ ‹‹ወ/ሮ መሰንበት የተለያዩ ድርጅቶች የቦርድ አባል እንደሆኑና ቋሚ ሠራተኛ እንደሆኑ ተደርጎ የሚናፈሰው ወሬም ሐሰት ነው፡፡ የቦርድ አባልም፣ ቋሚ ሠራተኛም አይደሉም፡፡ ዓባይ ባንክ አክሲዮን ማኅበርን በብቃትና በጥራት ማደራጀታቸው ስለታወቀና ስለተመረጡ እንጂ ዝም ብለው የመጡ አይደደሉም፤›› ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል፡፡

ከመረጃ ጋር በተያያዘ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ወይም ከሳሾቹ የሚያቀርቡት ክስ የማይታወቅ ሳይሆን፣ ጉባዔውም የሚያውቀው ነው ብለዋል፡፡ ባንኩ አክሲዮን የሸጠው በመላው አገሪቱ በሚገኙ ባንኮች መሆኑን ጠቁመው፣ አክሲዮን ገዥዎች ፎርም ሲሞሉ ስማቸውንና የአባታቸውን ስም ብቻ በመሙላት የአያታቸውን ሳይሞሉ የሚዘሉ፣ ፆታ ሞልተው ሌሎች መረጃዎችን ሳይሞሉ ቀርተው ስህተቶች ተፈጥረው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከሰቱና ቀጥሎም የሰሜኑ ጦርነት በመጀመሩ የተወሰኑ ማስረጃዎች ላይ ችግር ተፈጥሮ እንደነበርም አክለዋል፡፡ ለማስተካከል ጥሪ ተደርጎ፣ አደራጁና ቦርዱ በፈረሙት በባለአክሲዮኖች ተረጋግጦ ጉባዔ እንዲካሄድ ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ቀርቦ የሌሎቹ ባለአክሲዮኖች (ሰነድ ተበላሽቶ ያልፈረሙና ውክልና ያልሰጡ) እየተጣራ በሒደት እንዲፈረም ውሳኔ ላይ ተደርሶ የተሠራ እንጂ፣ ከሳሾቹ በሚሉት ሁኔታ እንዳልሆነ አቶ መላኩ አስረድተዋል፡፡

ባንኩ አንደኛውን ጠቅላላ ጉባዔ ሲያደርግ የባንኩን ካፒታል ወደ 20 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ግማሽ ያልከፈሉ እንዲከፍሉና ያልተስተካከሉ የሰነድ ችግሮች እንዲፈቱ ለማድረግ እየተሠራ ባለበት ሁኔታ እንዳይሳካ ለማደናቀፍ፣ በመሸጥ ላይ ያለው አክሲዮን እንዳይሸጥ እንቅፋት ለመሆን ሆን ተብሎ የተጠነሰሰ ሴራ መሆኑን አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡ ከሳሾች ባለአክሲዮኖች ባልተመዘገቡበትና በጉባዔው ባልፀደቀበት ዕጩ ሆነው ቀርበዋል የሚሉት እነሱ እንዳሉት ሳይሆን፣ ከላይ በተገለጸው አግባብ ብሔራዊ ባንክ ፈቅዶና ጠቅላላ ጉባዔ አፀድቆት፣ የከፈሉ ሁሉ ባለአክሲዮን እንደሚሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ጠቅላላ ጉባዔው መጠራቱንና ይህ ደግሞ በማስረጃና በሰነድ የተደገፈ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ወ/ሮ መሰንበት በሌሎች ተቋማት የቦርድ አባል ሆነው ስለመሾማቸውና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ቋሚ ሠራተኛ ስለመሆናቸው ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹እኔ የምክር ቤቱ ሠራተኛ አይደለሁም፡፡ ነጋዴው የሾመኝ የውጭ የሥራ ግንኙነት ለመወከል እንጂ ቋሚ ሠራተኛ አይደለሁም፣ ልሆንም አልችልም፡፡ የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጁም ይከለክላል፡፡ ምናልባት የንግድ ምክር ቤት አመራርን ስለማያውቁት ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበርን ስናቋቁም ብሔራዊ ባንክ የሚያውቀውና የሚያፀድቀው የምንሞላው ፎርም አለ፡፡ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሚሾመው በአደራጅ አባላት ነው፡፡ እኔ ብዙ ልምድ ያለኝና የፋይናንስ ሕግን ጠንቅቄ የማውቅ ብቁ ባለሙያ ነኝ፡፡ ዓባይ ባንክን አቋቁሜ ውጤታማ ሆኖ እየሠራ ያለ ባንክ ነው፤›› ብለው፣ ‹‹ብዙ ባንኮች ጠርተውኝ ነበር፡፡ ነገር ግን የአማራ ባንክ አደራጆች እንድረዳቸው ጭምር ሲጠሩኝ ደስ ብሎኝ ተቀላቀልኩኝ፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ መሰንበት እንደሚጠረጥሩት አዳዲስ አክሲዮኖች ሲቋቋሙ ፍላጎት (Interest) አለ፡፡ በአደረጃጀት ላይ የሚገኙ ጥቅሞች አሉ፡፡ ምናልባት የአሁኑ ቅሬታ የዚያ ውጤት ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡ ‹‹እንደሚመስለኝ ከአደራጆቹ ውስጥ ወደ ቦርድ መምጣት የሚፈልጉ ነበሩ፡፡ ሕዝቡ ደግሞ አልመረጣቸውም፡፡ የዚያ ብሶት አሁን ለደረሱበት ሁኔታ የዳረጋቸው ይመስለኛል፤›› ብለዋል፡፡ እሳቸው ከልጅነት ጀምረው ሥራቸው ከፋይናንስ ጋር የተገናኘ መሆኑን ጠቁመው፣ በሥራቸው ጠንካራና ለምንም ነገር የማይገበሩ በመሆናቸው፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት በተለይ ቦታውን ፈልገውት ሕዝብ ሳይመርጣቸው ከቀሩት አደራጆች ከነበሩትና አሁን ከሳሽ ከሆኑት ተግዳሮቶች እንደነበሩባቸው አልሸሸጉም፡፡ ‹‹ባንኩ አካባቢ ብዙ ችግሮች አሉ፣ በተለይ ከብድር ጋር በተገናኘ፤›› ብለዋል፡፡ ለእሳቸው ወቅቱ ከፍተኛ ተግዳሮት የነበረበት መሆኑን አስታውሰው፣ ከ174 ሺሕ በላይ ባለአክሲኖችን ማደራጀት በጣም ከባድ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኔ ድርጅቱን በጥንቃቄ አደራጅቼ፣ ወጪ ቆጥቤ 471 ሚሊዮን ብር አትርፌ ሰጥቻለሁ፡፡ የተፈተንኩበት ባንክ ቢሆንም በብቃት ማደራጀት በመቻሌ ደስ ብሎኛል፡፡ ሰዎቹ ለምን እንዲህ ሆኑ የሚለው ግልጽ እንዳልሆነላቸውና የተጀመረው አታካራ ይጠናቀቅ እንጂ ምክንያቱን እጠይቃቸውለሁ፤›› ብለው እንደሚያስቡ ወ/ሮ መሰንበት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ባንኩ ዓለም አቀፍ አሠራርን ተከትሎና ሕግና ደንብን አክብሮ የሚሄድ በመሆኑ አስቸጋሪ አይደለም፡፡ እኔ የአዲስ አበባ ልጅ በመሆኔ የጎንዮሽ አካሄድና አፈንጋጭነት አይገባኝም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ለጥቅም መሪነትን የሚፈልግ ሊኖር ይችላል፡፡ ለህሊናዬ የሚቆጨኝ ነገር የለም፡፡ በንፅህናና በብቃት የሠራሁ በመሆኔ እኔን ከብቃት ጋር አያይዞ ማንሳት የአስተዳደግ ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ ስለራሴ መናገር አልፈልግም ሌሎች ቢናገሩ የተሻለ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አንድ ነገር መናገር የምችለው የባንክ ሙያን ከእነ ሕጉና አሠራሩ ጠንቅቄ የማውቀው መሆኑን ነው፤›› ያሉት ወ/ሮ መሰንበት ስለእሳቸው ሥራ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ትልቁ ምስክር መሆኑን፣ ወርቅ ተሸልመው የተሸኙና በብቃት የሠሩ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ወ/ሮ መሰንበት ልማት ባንክን ያላግባብ በመምራት ጉዳት እንዳደረሱበት በመገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል ማለታቸውን አስተባብለዋል፡፡

ሌላው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ባለአክሲዮኖች የሥነ ምግባር ጉድለት ፈጽመዋል በማለት ከዕጩ የቦርድ አባልነት እንዲሰረዙ የጠየቁት አቶ ኃይለ ማርያም ተመስገንን ነው፡፡ እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገለጻ፣ አቶ ኃይለ ማርያም የሕግ ባለሙያ እንደመሆናቸው ከባንክ ማደራጀት ጋር የተያያዙ ሕጋዊ አካሄዶች ላይ የድርሻቸውን መወጣት ሲገባቸው፣ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዋ ያለ ውድድርና አደራጅ ኮሚቴው ሳያውቀው ወ/ሮ መሰንበት እንዲቀጠሩ ውል ማዘጋጀታቸውና በሌላ ቦታ በቋሚነት እንደሚሠሩ እያወቁ በዝምታ ማለፋቸው፣ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አለመወጣት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይህም የኮርፖሬት ገቨርናንስ መርሆዎችን መጣስ መሆኑን አክለዋል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም የአደራጅ ኮሚቴው አባል ሆነው እያለ አንተነህ ግርማ (ዶ/ር) የተባሉ ግለሰብ የባንኩ የዲጂታል ባንኪንግ አማካሪ ሆነው እንዲሠሩ የሕግ አስተያየት መስጠታቸው፣ የባንክ ሥራ አዋጅ ቁጥር 592/2000ን የጣሰ ድርጊት መፈጸማቸውን ቅሬታ አቅራቢዎቹ አስረድተዋል፡፡ የአንተነህ (ዶ/ር) ቅጥርን የባንኩ አስተዳደር ‹‹አልፈጽምም›› በማለቱ ባንኩ ያላግባብ ሊያጣ የነበረውን 2.5 ሚሊዮን ዶላር በማዳኑ፣ በሐሰት በተቀነባበረ ሴራ ከባንኩ ማኔጅመንት እንዲባረርና ለቦርዱ እንዲቀርብ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ግለሰቡ እንደማይቀጠር ሲያውቁ አቶ ኃይለ ማርያም፣ የቦርድ አባላትንና የአንተነህን (ዶ/ር) እና የሌሎችን የስማቸውን የመጀመሪያ ፊደል የያዘ ‹‹MHA- PLC›› እንዲቋቋም ተደርጎ፣ ሥራው ያለ ውድድር እንዲሰጣቸውና ቦርዱ በባንኩ ላይ ጣልቃ እንዲገባ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን፣ ይህም እምነት ማጉደልና የባንክ ሥራ አዋጅ ቁጥር 592/2000 እና ብሔራዊ ባንክ ስለኮርፖሬት ገቨርናንስ ያወጣውን ዳይሬክቲሪቭ No SBB/71/2019 ድንጋጌዎችን መተላለፋቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያምን ስለቀረበባቸው ክስ ሪፖርተር አናግሯቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ቅሬታ ማቅረብ ይቻላል፣ መብትም ነው፡፡ ነገር ግን ሥርዓትና ደንቡን ወይም አካሄዱን ጠብቆና አክብሮ መሆን አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ቅሬታ ሲኖር ለቦርድ አስመራጭ ኮሚቴ ቀርቦ ወደ ጠቅላላ ጉባዔ ይሄዳል እንጂ፣ ዝም ብሎ ጉዳዩን በመገናኛ ብዙኃን ማጯጯህና ስም ማጥፋት ተገቢ ለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሕግና ሥርዓት ጠብቆ እስከ መጨረሻው ማቅረብ ሲቻል እንዲህ ማድረጋቸው ሕግን የጣሰና ወንጀል መሆኑንም አክለዋል፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ በሙሉ የጠቀሷቸው ሁሉ ማስረጃ እንደሚቀርብባቸው የገለጹት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ቅሬታ ያለው ባለአክሲዮን ‹‹ጠቅላላ ጉባዔ ይጠራ›› ይላል እንጂ፣ ‹‹እንዴት እንዳይካሄድ ይከላከላል?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ የሠሩት ሁሉ በተቃራኒው መሆኑንም ሲያስረዱ፣ በጠቅላላ ጉባዔ ላይ አጀንዳ አስይዘው በመወያየት መፍታት ሲቻል፣ ማደናገርና ባለአክሲዮኖቹን ግራ ማጋባት ትክልል አይደለም ብለዋል፡፡ የባንኩን ዘላቂ ጥቅም ከማሳካት ይልቅ ችግር ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛ ሕጉና ሥርዓቱ የሚፈቅደውን እያደረግን ወደፊት እንቀጥላለን፡፡ ለቦርድ ምንም ሳያቀርብ በሚዲያ ተፅዕኖ በመፍጠር ብቻ ምንም የሚለወጥ ነገር የለም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ ስም እያጠፉ ጥቅም ለማግኘት መሯሯጥ ባንኩንና ባለአክሲዮኖችን ከመጉዳት የዘለለ ፋይዳ ስለማይኖረው፣ ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ መሆኑን አቶ ኃይለ ማርያም ተናግረዋል፡፡

ቅሬታ የቀረበባቸውና ምንም ዓይነት አክሲዮን ሳይገዙና የባለቤትነት ድርሻ ሳይኖራቸው ዕጩ የቦርድ አባል ሆነው የቀረቡት አምስት ግለሰቦች ኤደን አሸናፊ (ዶ/ር)፣ አቶ አስቻለው ታምሩ፣ አቶ አበባው ጌቴ፣ ወ/ሮ መሠረት ዳምጤና አቶ በላይ ጎንፋ የሚባሉ ግለሰቦች ሲሆኑ፣ ምንም ዓይነት የባንክም ሆነ የፋይናንስ ተቋም ልምድ ሳይኖራቸው በዕጩነት እንዲቀርቡ ማድረግ የኮርፖሬት ገቨርናንስ መርሆችን የጣሰ በመሆኑ እንዲሰረዙ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ባለአክሲዮኖች ጠይቀዋል፡፡ ሐሰተኛ መረጃ በማቀነባበር በተጭበረበ መንገድ ከፍተኛ የሆነ ድምፅ እንዲያገኙ መደረጉ፣ ከፍተኛ የሥነ ምግባር ጉድለት መሆኑንም አክለዋል፡፡ ከባድ የሙስናና ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም ወንጀል መሆኑን ጠቁመው በሕግ እንዲጠየቁም አሳስበዋል፡፡

አማራ ባንክ ከ185 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖችን የያዘ ባንክ በመሆኑና በአንድ ቦታ በሚካሄድ ጉባዔ ማስተናገድ ስለማይቻል፣ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የውክልና ሥርዓትን መጠቀም ብቸኛ አማራጭ በመሆኑ፣ ባለአክሲዮኖች ለፈለጉት የባንኩ አደራጅ ውክልና እንዲሰጡ መደረጉን ቅሬታ አቅራቢዎቹ አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን በአቶ መላኩ ትዕዛዝ አቶ አየልኝ አቦሃይና አቶ ኤልያስ ጥረት መረጃ አጠናካሪ ሆነው እንዲመደቡ በማድረግ፣ የድምፅ ማጭበርበር ሥራ በረቀቀ መንገድ በመሥራት ሕጋዊ ለማስመሰል መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ ለአቶ መላኩ ውክልና ያልሰጡ ሰዎች፣ ውክልና እንደሰጡ በማስመሰል ፊርማቸው እንዲገባ መደጉንና ግለሰቦች የመምረጥና የመመረጥ መብታቸውን መነጠቃቸውን ጠቁመዋል፡፡ እንዲሁም ምርጫው በተጭበረበ ድምፅ እንዲከናወን መደረጉን ገልጸው፣ እንዲሰረዝ ጠይቀዋል፡፡ ሌላው የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ አባል የሆኑ ግለሰቦች የተበደሩትን 400 ሚሊዮን ብር በሚመለከት የኦዲት ሪፖርት እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ፣ ሐሰተኛ የውጭ ኦዲተር ሪፖርት ለባንኩ ማቅረባቸውንም በአቤቱታቸው አቅርበዋል፡፡ ግለሰቡ የተጣለባቸውን ኃላፊነት አለመወጣታቸውንና ይህ የሚያሳየው የባንኩ የቦርድ አባላት የሥነ ምግባር ጉድለትና ተዓማኒነት ችግር ያለባቸው መሆኑንም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በአስቸኳይ ከኃላፊነታቸው እንዲታገዱና በጥፋታቸው ልክ እንዲጠየቁ አሳስበዋል፡፡ በአጠቃላይ የተጠራው ጠቅላላ ጉባዔ እንዲታገድና በሕገወጥ መንገድ በዕጩነት የቀረቡ 29 ዕጩ አባላት እንዲሰረዙ ጠይቀዋል፡፡    

የባንክ ሥራን በሚመለከት የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል በወጣው አዋጁ ቁጥር 1159/2019 እንደተደነገገው፣ የውጭ አገር ዜግነት ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ በራሱም ሆነ በድርጅት አክሲዮን መግዛት የሚችለው በውጭ ምንዛሪ ብቻ ነው፡፡ እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 592/2000 ድንጋጌም በአክሲዮን መዝገብ ላይ ያልተመዘገበ ማንኛወም የአክሲዮን ዝውውር ዋጋ እንደማይኖረው ታውቋል፡፡ በንግድ ሕጉም አንቀጽ 276 አንቀጽ (2) ደግሞ አክሲዮኖች ከመተላለፋቸው በፊት የዳይሬክተሮች ቦርድ ፈቃድ እንዲጠየቅ በመመሥረቻ ጽሐፉ ወይም በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ መወሰን እንዳለበት አስገዳጅ ድንጋጌ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን ኤደን አሸናፊ (ዶ/ር) የውጭ ዜግነት ያላቸው ቢሆንም፣ የባንክ ባለአክሲዮን የሚሆኑበት አክሲዮን በኢትዮጵያ ብር እንደተዘዋወረላቸውና ዕጩ የቦርድ አባል ሆነው መቅረባቸውንም በአቤቱታቸው አስታውቀዋል፡፡ ድርጊቱ አዋጆቹንና የንግድ ሕጉን የጣሰ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲሰርዙ ጠይቀዋል፡፡ በቦርድ ሰብሳቢው አቶ መላኩ ፈቃደኝነት በአግባቡ የተደራጀ የባለአክሲዮኖች መረጃ ለብሔራዊ ባንክ እንዲቀርብ ባለመደረጉ፣ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የውጭ ዜግነት ያላቸው ሰዎች በኢትዮጵያ ብር አክሲዮን እንዲገዙ መደረጉንም አክለዋል፡፡ ኤደን (ዶ/ር) የ15,000 ብር አነስተኛ አክሲዮን ገዝተው የቦርድ አባል ሆነው በዕጩነት መቅረባቸው ሕግን የጣሰ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች ባለአክሲዮኖችንም መናቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አቶ መላኩ በሰጡት ምላሽ፣ ቅሬታ አቅራቢዎቹ እሳቸውንም አክሲዮን እንደሌላቸው እንደተናገሩ ጠቁመው፣ ነገር ግን በነበረውና ከላይ በጠቀሱት የፎርም መበላሸት፣ በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ በተፈጠረ ችግር ስላልፈረሙ እንጂ፣ ባለአክሲዮኖች ናቸው፡፡ የተሰጣቸው ውክልና በጣም ብዙ በመሆኑ ብሔራዊ ባንክ የሚያውቀውና ከሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫም  ጋር ተስማምተው ቲተር ተቀርፆ እየተሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡ እሳቸው በአካል ቀርበው የፈረሙት ነገር እንደሌለ ተናግረው፣ የተወሰኑ የተዘለሉ ስላሉ እየተሠራ መሆኑንና ይህንንም የሚሠራው ሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡ ሁሉም ነገር የተደረገው በብሔራዊ ባንክ ዕውቅና፣ በጉባዔውና በቦርድ አመራሩ ዕውቅና ሆኖ ሳለ፣ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ግለሰብ ለመጉዳት ብለው የተቋማትን ስም ማጥፋታቸው ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

አደራጅ በውክልና እንዲጠቀም የተደረገ ነገር እንደሌለና የተሰጠም ውክልና እንደሌለ አቶ መላኩ ገልጸው፣ ቅሬታ ያለና ያልተፈጠረን ነገር እንደተፈጠረ በማስመሰል ሆን ተብሎ የማደናገር፣ ግርታ የመፍጠርና ከኋላቸው ያነገቡትን ባንኩን አደጋ ላይ የመጣል እንቅስቃሴ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሁሉም ነገር በኦዲተር የተሠራ፣ የሚታይና ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸውው አካላት ቀርበው የሚያረጋግጡት በመሆኑ፣ ሁሉም ባለአክሲዮኖች የሚባለውን ሳይሰሙ የጉባዔውን ውሳኔ እንዲጠብቁ ጠይቀዋል፡፡                       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...