Monday, April 15, 2024

ወርቅ – የግለሰቦችና የታጣቂ ቡድኖች ሀብት?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከቡና ቀጥሎ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቁን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከሚያስገኙት የኤክስፖርት (ወጪ ንግድ) ምርቶች መካከል አንዱ የወርቅ ማዕድን ነው። ይህ የወርቅ ሀብት አጠቃላይ ኢኮኖሚው በከፍተኛ ደረጃ በውጭ ምንዛሪ እጥረት በተመታበት በአሁኑ ወቅት ለኢኮኖሚው ምርኩዝ መሆን አልቻለም።

ኢትዮጵያ ከፍተኛና ጠቃሚ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ልታገኝ የምትችልበት ይህ የወርቅ ሀብቷ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከእጇ እያመለጣትና ከኤክስፖርት የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢም እየነጠፈባት ነው፡፡ 

አገሪቱ የተፈጥሮ ሀብቷ ከሆነው የወርቅ ማዕድን ተገቢውን ጥቅም ማግኘት ያልቻለችው ደግሞ፣ የወርቅ ክምችቱ ነጥፎ ወይም ሳይመረት ቀርቶ አይደለም። ነገሩን እጅግ አሳሳቢ የሚያደርገው እውነታም ይህ ነው። 

የ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡት የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ፣ የአገሪቱ ወርቅ እየተመረተ ቢሆንም ወርቅ የመግዛት ብቸኛ ሥልጣን ለተሰጠው ብሔራዊ ባንክ እየቀረበ ያለው መጠን ትርጉም ባለው ሁኔታ መቀነሱን ተናግረዋል።

‹‹የወርቅ ምርት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ቁልፍ ሚና ከሚጫወቱ የኤክስፖርት ምርቶች መካከል አንዱ ነው፤›› ያሉት አቶ ማሞ፣ ‹‹እንደምታስታውሱት ከጥቂት ዓመታት በፊት ከወርቅ ኤክስፖርት ብቻ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት ችለን ነበር፤›› በማለት አስታውሰዋል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የወርቅ ኤክስፖርት መሠረታዊ በሚባል ደረጃ መቀነሱን አስረድተዋል። 

በተመሳሳይ የ2016 ዓ.ም. የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸማቸውን ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና የማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡት የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር)፣ ‹‹እኛ በዘንድሮ ሩብ ዓመት ከወርቅ ሽያጭ የጠበቅነው ገቢ ከ112 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው፣ ነገር ግን ያገኘነው በጣም ትንሽ ነው፤›› ብለዋል።

በ2016 ዓ.ም. ሩብ ዓመት በኩባንያዎችና በባህላዊ አምራቾች ተመርቶ ለገበያ ከቀረበው የወርቅ ሽያጭ የተገኘው ገቢ 63.6 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በ2015 ዓ.ም. ሩብ ዓመት የተገኘው 58.57 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን፣ በ2014 ዓ.ም. ሩብ ዓመት ደግሞ 134 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቶ እንደነበር ጠቅሰዋል።

የተመረተው ወርቅ ወዴት ሄደ?

የአገሪቱ የወርቅ ክምችት ባልነጠፈበትና ወርቁም እየተመረተ ሳለ፣ እንዴት ከዚህ የተፈጥሮ ሀብቷ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት ተሳናት? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ነው። 

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ለቋሚ ኮሚቴው በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹የአገሪቱ ወርቅ ተመርቷል፣ ነገር ግን ወደ ብሔራዊ ባንክ እየመጣ አይደለም። ተጨማሪ ወርቅ ተመርቶ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲመጣ መፈለጋችን ይቅርና የሚታወቀው የተመረተው ወርቅ እንኳ ወደ ትክክለኛው ገበያ ወደ ብሔራዊ ባንክ ቢመጣ፣ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ ጫና በብዙ መልኩ ያቃልለዋል፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችታችንንም ያሻሽለዋል፤›› ብለዋል።

ነገር ግን የተመረተው ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ እየቀረበ እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ ማሞ፣ ለብሔራዊ ባንክ መቅረብ የነበሩበት የወርቅ ምርት ለምን ቀነሰ ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

‹‹ወደ ብሔራዊ ባንክ መምጣት የነበረበት ወርቅ ለምን ቀነሰ ከተባለ አንደኛው ምክንያት በወርቅ አምራች አካባቢዎች ያለው ሕገወጥ የወርቅ ግብይትና ኮንትሮባንድ ነው። እንዲሁም በወርቅ አምራች አካባቢዎች ያለው የፀጥታ መደፍረስ ነው፤›› ብለዋል። 

አቶ ማሞ አክለውም፣ ‹‹ብዙ ሰዎች ከወርቅ ኮንትሮባንድ ንግድ የሚያገኙትን ገቢ ወርቅ በሚመረትባቸው አካባቢዎች ያለውን ግጭትና የፖለቲካ አለመረጋጋት ለማስቀጠል፣ ብሎም ለማስፋፋት መልሰው ጥቅም ላይ እያዋሉት ነው። በዚህ ተግባር ውስጥ ደግሞ አንዳንድ የመንግሥት አካላት ጭምር ተሳትታፊ ናቸው፤›› ብለዋል። 

የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት መዋቅሮች የተመረተው የወርቅ ሀብት የአገሪቱ ብቸኛ የወርቅ ገዥ ወደ ሆነው ብሔራዊ ባንክ እንዲመጣ የማድረግ ኃላፊነት ቢኖርባቸውም፣ ይህንን ኃላፊነት እየተወጡ አይደለም ሲሉ ወቅሰዋል። ‹‹በተለይ አንዳንድ የክልል መንግሥታት ተገቢውን ሚና እየተጫወቱ አይደለም፣ ይህም መስተካከል አለበት፤›› ሲሉ ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ተናግረዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴርና ለዚህ ሚኒስቴር ተጠሪ የሆኑ ተቋማት በጋራ ሆነው የዘንድሮ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸማቸውን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅትም እየተንሰራፋ የመጣው ከፍተኛ የኮንትሮባንድ ንግድ ትልቅ የመወያያ አጀንዳ ነበር። 

በዚህ ውይይት ወቅትም የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ የወርቅ ኮንትሮባንድ ንግድን አስመልክቶ ለቋሚ ኮሚቴው ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ በወቅቱም የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የሚታየው የወርቅ ኮንትሮባንድ ንግድ የከፋ እንደሆነ ተናግረዋል።

‹‹ለምሳሌ ኦነግ ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የወርቅ ኮንትሮባንድን እንደ ገቢ ምንጭ እየተጠቀመበት ነው፡፡ በመሆኑም የኮንትሮባንድ ቁጥጥሩ ከጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ ሳይሆን ከፌዴራል ፖሊስ አቅም በላይም የመሆን ሁኔታን ፈጥሯል፤›› ሲሉ የነገሩን አሳሳቢነት አስረድተዋል።

ኮሚሽነር ደበሌ አክለውም፣ ወርቅ የሚመረትባቸው ክልሎች አመራሮችን ተጠያቂ አድርገዋል።

በተመሳሳይ፣ የዘንድሮውን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡት የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ (ኢንጂነር)፣ ለወርቅ ኤክስፖርት ገቢ መቀነስ የክልል መንግሥታትን ተጠያቂ አድርገዋል።

ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ አገሪቱ በየዓመቱ ከምታመርተው ወርቅ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው በባህላዊ የወርቅ አምራቾች የሚመረተው ነው።

ሪፖርተር ያገኘው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያስረዳው፣ አገሪቱ በየዓመቱ ከምታገኘው ወርቅ ውስጥ 70 በመቶው በባህላዊ የወርቅ አምራቾች የሚመረት ነው። የአገሪቱ የወርቅ ከፍተኛ ክምችት የሚገኘው በአምስት ክልሎች ሲሆን እነዚህም ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ትግራይና የቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ናቸው። በእነዚህ ክልሎች የተመሠረቱ ባህላዊ የወርቅ አምራች ማኅበራት ብዛት ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን በላይ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። 

በ2016 ዓ.ም. ሩብ ዓመት የሆነው ግን ከዚህ የተለየ ነው። የማዕድን ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፣ በ2016 ሩብ ዓመት በከፍተኛ የወርቅ አምራች ኩባንያዎች 996.1 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማምረት ታቅዶ የተመረተው 719.6 ኪሎ ግራም ነው። ከዚህ ውስጥም 700 ኪሎ ግራም የሚሆነው የተመረተው በአንድ ኩባንያ ማለትም በሚድሮክ ጎልድ ኩባንያ ብቻ ነው። በሌላ በኩል ባህላዊ ወርቅ አምራቾች በሩብ ዓመቱ 500 ኪሎ ግሬም ወርቅ ያመርታሉ ተብሎ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ የተመረተው ግን 202 ኪሎ ግራም መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በዚህም መሠረት በዘንድሮው የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከተመረተው አጠቃላይ ወርቅ መጠን ወስጥ 78 በመቶ የሚሆነውን ያመረቱት ከፌዴሬል መንግሥት ፈቃድ የወሰዱ ከፍተኛ ወርቅ አምራች ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ በባህላዊ አምራቾች የተመረተው ወርቅ መጠን ድርሻ ግን 22 በመቶ ብቻ ነው። በሩብ ዓመቱ ከተመረተው አጠቃላይ የወርቅ ምርት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 63.6 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን የሚኒስትሩ ሪፖርት ያመለክታል።

‹‹ይህ የወርቅ ምርት አቅርቦት ሁኔታን የሚገልጽ አይደለም፣ ምክንያቱም እስከ ዛሬ ድረስ ከፍተኛ ወርቅ አምራች ኩባንያዎች ከሚያመርቱት በእጥፍ የሚበልጥ ወርቅ የሚመርተው በባህላዊ ወርቅ አምራቾች ነው፤›› ብለዋል።

ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች ይገኝ የነበረው የወርቅ ምርት በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ ጤነኛ አይደለም ያሉት ሚኒስትር ሀብታሙ (ኢንጂነር)፣ ወርቅ በሚመረትባቸው አካባቢዎች ያለውን ግጭት ተጠልሎ የተፈጠሮ ሀብቱን የመቀራመት ተግባር መኖሩን ተናግረዋል። 

ሚኒስትሩ አክለውም፣ ‹‹ተጠያቂነት መኖር አለበት፣ ይህ ደግሞ የክልሎች ኃላፊነት ነው። ወዴትም ልንወስደው አንችልም፣ ምክንያቱም ፈቃድ የሚሰጡትና የሚያስተዳድሩት ክልሎች ናቸው፤›› ብለዋል።

በአጠቃላይ ከላይ ከተጠቀሱት የመንግሥት ባለሥልጣናት ገለጻ መረዳት የሚቻለው፣ በባህላዊ ወርቅ አምራቾች የሚመረተው ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ በታጣቂዎችና በኮንትሮባንድ አንቀሳቃሾች ቁጥጥር ወስጥ መውደቁን ነው።

በደህናው ጊዜ በባህላዊ አምራቾች ከሚመረተው ወርቅ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በአማካይ 400 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህ ዓመታዊ የወርቅ ገቢ ውስጥ ግማሹ ብቻ በታጣቂዎች እጅ ቁጥጥር ውስጥ ቢገባ፣ በአገሪቱ ደኅንነት ላይ ሊፈጥር የሚችለው አደጋ ቀላል አለመሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

የጥቁር ገበያ ተፅዕኖ 

የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ እንዳሉት፣ የወርቅ ምርት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ቁልፍ ሚና ከሚጫወቱ የኤክስፖርት ምርቶች መካከል አንዱ ነው። ‹‹ከጥቂት ዓመታት በፊት ከወርቅ ኤክስፖርት ብቻ ከ600 ሚሊዮን ድላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፤›› ብለው እንደገለጹትም፣ በ2014 ዓ.ም. ከወርቅ ኤክስፖርት ብቻ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 672 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን በማዕድን ሚኒስቴርና በብሔራዊ ባንክ ይፋ ከተደረጉ የሰነድ መረጃዎች ለመገንዘብ ተችሏል። 

በ2014 ዓ.ም. ብቻ ሳይሆን ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2006 ዓ.ም. ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ከወርቅ ኤክስፖርት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል። በእነዚህ ከፍተኛ ገቢ በተገኘባቸው ዓመታት በባህላዊ የወርቅ አምራቾች ተመርቶ ለገበያ የቀረበው የወርቅ መጠን በአማካይ 9,000 ኪሎ ግራም የነበረ ሲሆን፣ አልፎ አልፎም እስከ 12 ሺሕ ኪሎ ግራም ተመርቶ ለብሔራዊ ባንክ ቀርቦ እንደሚያውቅ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከ2010 እስከ 2011 ዓ.ም. ጨርሶ ምርት አለተመረትም በሚያስብል ደረጃ አንድ ሺሕ ኪሎ ግራም ብቻ ነበር የተመረተው።  በ2015 ዓ.ም. ግን በእጅጉ በማሽቆልቆል 3,900 ኪሎ ግራም ወርቅ ብቻ ነው ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው። 

የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ (ኢንጂነር) ከ2000 ዓ.ም. አንስቶ ለ15 ዓመታት በባህላዊ አምራቾች የተመረተውን የወርቅ ምርት መጠን መረጃ በመዳሰስ፣ ለዓመታት የቀረበውን የወርቅ ምርት መጠን ሁኔታ ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል። በዚህም መሠረት ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ለብሔራዊ ባንክ የሚያቀርቡት የወርቅ መጠን ቋሚ ሳይሆን በየዓመቱ የሚዋዥቅ ነው።

የ15 ዓመታት የወርቅ ምርት አቅርቦት ሁኔታን በመዳሰስ ባቀረቡት ሪፖርትም፣ ባህላዊ አምራቾች ለብሔራዊ ባንክ የሚያቀርቡት የወርቅ መጠን በሕጋዊና በጥቁር ገበያው መካከል ባለው የውጭ ምንዛሪ ተመን ልዩነት እንደሚወሰን አስረድተዋል።

ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ባለፉት 15 ዓመታት በባህላዊ ወርቅ አምራቾች ተመርቶ ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው ትልቁ የወርቅ መጠን 12 ሺሕ ኪሎ ግራም ሲሆን፣ ትልቁ ዓመታዊ አማካይ ደግሞ 9,000 ኪሎ ግራም ነው። ከዚህ የወርቅ መጠንም በአማካይ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ተገኝቷል። 

ለብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ ወርቅ በቀረበባቸው በእነዚህ ዓመታት በሕጋዊና በጥቁር ገበያው መካከል የነበረው የውጭ ምንዛሪ ተመን ልዩነት ጠባብ እንደነበረ፣ በተጨማሪም ብሔራዊ ባንክ በዓለም የወርቅ ዋጋ ላይ እስከ 35 በመቶ ማበረታቻ ጭማሪ በማድረጉ ከፍተኛ ወርቅ እንደቀረበለት አስረድተዋል።

በአንፃሩ፣ የጥቁር ገበያው የምንዛሪ ተመን ከሕጋዊ ገበያው በከፍተኛ ልዩነት በጨመረባቸው ዓመታት፣ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ መጠን እጅግ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

የማዕድን ሚኒስትሩ ሲያጠቃልሉም፣ ‹‹የባህላዊ የወርቅ ምርትን ችግር ውስጥ የከተተው በሕጋዊና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው የውጭ ምንዛሪ ተመን መስፋት ነው፤›› ብለዋል።

መፍትሔው ምንድነው?

በወርቅ ኮንትሮባንድ ረገድ ያሉትን ችግሮች በየመልካቸው ተረድቶ ከክልሎች ጋር ለመሥራት ያደረጉት ጥረት ቀላል አለመሆኑን የተናገሩት የጉምሩክ ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ፣ አንደኛው መፍትሔ ለወርቅ አምራቾች ፈቃድ በሚሰጡ ክልሎችና በአምራቾቹ መካከል ያለውን ግንኙነት የጠራ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ‹‹ፈቃድ የተሰጠው አምራች በየዓመቱ ምን ያህል ወርቅ የማምረት ዕቅድ እንዳለው ታውቆ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል፤›› ሲሉ ኮሚሽነሩ ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል። 

የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ በበኩላቸው፣ የሚመረተው ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲመጣ ለማድረግ የተለያዩ የአጭር ጊዜ የመፍትሔ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ገልጸዋል። አንደኛው ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀራርቦ መሥራት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ከዓለም የወርቅ ገበያ ዋጋ በተጨማሪ ከ60 እስከ 70 በመቶ ጭማሪ በማድረግ ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲመጣ ማድረግ ነው። 

በመሠረታዊነት ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የማዕድን ዘርፍ እንቅስቃሴ ለማሳደግ ብሔራዊ የማዕድን ካውንስል የተቋቋመ መሆኑን፣ ይህም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማቀናጀት የተሻለ ሥራ ለማከናወን መታቀዱን ገልጸዋል።

የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ (ኢንጂነር)፣ የተቋቋመው ብሔራዊ የማዕድን ምክር ቤት በዘርፉ ላሉት መሠረታዊ ችግሮች መፍትሔ ይሰጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። በዚህ ምክር ቤት የመጀመሪያ ውይይት ላይም በማዕድን ዘርፍ ያለውን ኮንትሮባንድና የፀጥታ ችግር መፍትሔ ለመስጠት የማዕድን ፖሊስ ሠራዊት እንዲደራጅ መወሰኑን አክለዋል።

በዘላቂነት ደግሞ የወርቅ ሀብቱ ኃላፊነት በሚሸከሙ ከፍተኛ ወርቅ አምራች ኩባንያዎች እንዲመረት ማድረግ፣ የአገሪቱን ጥቅም መጠበቅ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -