Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹በኢትዮጵያ የሚወጡት የስፖርት መመርያዎች ከሕግ ጋር የሚጣረሱ ናቸው›› ፀጋዬ ደግነህ ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ...

‹‹በኢትዮጵያ የሚወጡት የስፖርት መመርያዎች ከሕግ ጋር የሚጣረሱ ናቸው›› ፀጋዬ ደግነህ ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የጁዶና ጁጂትሱ የሙያ ማኅበር የበላይ ጠባቂ

ቀን:

ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማኔጅመንትና በአስተዳደር፣ እንዲሁም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ አግኝተዋል። በጀርመን መርሴዲስ ቤንዝ በተለያዩ የፕሮጀክት ማኔጅመንትና ኢንተፕራይዝ አርክቴክቸር ላይ በማኔጅመንትና በበርካታ የሥራ መደቦች ላይ የረዥም ዓመታት ዓለም አቀፍ ተሞክሮ በመቅሰም፣ በአሁኑ ጊዜ በሰው ኃይል የዘላቂ ልማትና የብዝኃነት ማናጀር፣ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ ሌክቸረር ናቸው፡፡ ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር) በስፖርቱ በጁዶና ጁጂትሱ በስድስተኛ ዲግሪ ዳን ሲኖራቸው፣ ስፖርቱን ወደ ኢትዮጵያ በዘመነ መልክ አስገብተዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ጁጂትሱ ፌዴሬሽን በሥነ ምግባር ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንትነትና በዘላቂ ልማት ኃላፊነት፣ በአፍሪካ የጁዶ ዮኒየን በማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ኮሚሽን እየሠሩ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ያለው የሙያ ማኅበር የበላይ ጠባቂ ናቸው። ዳዊት ቶሎሳ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ስላለው የስፖርት እንቅስቃሴና ከስፖርት ፖሊሲ፣ እንዲሁም የስፖርት ሕግ ጋር በተያያዘ ከእሳቸው ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ የሚወጡት የስፖርት መመርያዎች ከሕግ ጋር የሚጣረሱ ናቸው›› ፀጋዬ ደግነህ ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የጁዶና ጁጂትሱ የሙያ ማኅበር የበላይ ጠባቂ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የስፖርት ሕግ አለ?

ፀጋዬ (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የስፖርት ሕግ የሚባል የለም፡፡ ይህንን በተመለከተ እኔም በግሌ በተለያዩ ጊዜያት ንድፈ ሐሳብ ጽሑፍ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አቅርቤ ነበር፡፡ በአሁን ጊዜ ያለው የስፖርት መመርያ ነው፡፡ ይህም መመርያ ሲተገበር ግን ልክ ሕግ ተደርጎ ሲወሰድ ይስተዋላል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ይህንን መመርያ የጣሰ ሰው ወይም መመርያ የማይቀበል ከሆነ ሕግ እንደጣሰ ተደርጎ የሚወሰድበት የተዛባ አመለካከት አለ፡፡ ሕግ የሚወጣው በተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ደንብ ደግሞ በሚኒስቴሮች ምክር ቤት የሚወጣ ሲሆን፣ ያንን ለማስፈጸም መመርያ ይወጣል፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚወጡት የስፖርት መመርያዎች ከሕግ ጋር የሚጣረሱበት ነጥቦች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የስፖርት ሕግ ቢኖር ፋይዳው ምንድነው?

ፀጋዬ (ዶ/ር)፡- የስፖርት ሕግ ሲኖር በርካታ ጥቅሞች ይኖሩታል፡፡ የስፖርት ማኅበራት ነፃነት፣ ትክክለኛ አሠራርን ማስከበር ያስችላል፣ እያንዳንዱን የስፖርት ተጠቃሚ መብት የሚያስከብርና በአገር የልማት እንቅስቃሴ ውጤታማነትን የሚያበረታታ ይሆናል፡፡ በተለይ በስፖርት ላይ የሚፈጸመው የሕግ መተላለፎችን የሚዳኝና የሚደነግግ የስፖርት ሕግ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በአማተር ስፖርት ላይ የሚሰጥ ድጎማ በስፖርት እንዴት ኦዲት እንደሚደረግ ይደነግጋል፡፡ የገንዘብ መጓደሎች ሲያጋጥሙ እንዲሁም ግጭቶች፣ በደጋፊዎች የሚነሱ ሁከቶች ሲመጡ በስፖርት ሕግ መዳኘት ያስችላል፡፡ ይህም ከገንዘብ የቅጣት ጣሪያ ጀምሮ እስከ እስራት ያለን አሠራር ያስቀምጣል፣ ቅሬታዎችን የሚሰማና የሥነ ምግባር አሠራሮች መደንገግ ያስችላል፡፡ ከዚህም ባሻገር በፌዴሬሽን በክለቦች ስፖንሰር፣ እንዲሁም ድጎማ ዓለም አቀፍ ተቋማት በስፖርት እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በባህልና በስፖርት ሚኒስቴር ሥር አገር አቀፍ የስፖርት ማኅበራት ስለሚቋቋሙበት ተሻሽሎ የወጣው መመርያ ምን ይመስላል?

ፀጋዬ (ዶ/ር)፡- ተሻሽሎ የወጣው መመርያ ቁጥር 50/2014 ነው፡፡ መመርያው በራሱ መኖሩ ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ፌዴሬሽኖችና ማኅበራት እንዲዋቀሩ መሠረት ያስቀምጣል፡፡ በአንፃሩ በ2003 ዓ.ም. ታኅሳስ ላይ የወጣው የተሻሉ ነጥቦችን የያዘ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ለምሳሌ ያህል ለመጥቀስ በ2014 ዓ.ም. የወጣው መመርያ በክፍል ሁለት አንቀጽ 6፣ አንድ ፌዴሬሽን ማለት አንድን የስፖርት ዓይነት በመላ አገሪቷ ለማሳደግና ለማስፋፋት የተቋቋመ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ይኼ ሲታይ ስፖርቶችን የሚለያይ ይመስላል፡፡ በአንፃሩ በሌሎች አገሮች ሁለትና ሦስት ስፖርቶችን በአንድ ላይ አጣምረው የሚያስተዳድሩ የተለያዩ አገሮች ፌዴሬሽኖች አሉ፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ የበጀት እጥረት ያለባቸው አገሮች ለእያንዳንዱ ስፖርቶች አንዳንድ ፌዴሬሽኖች ማቋቋም ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል፡፡ ‹‹የትኞቹን ስፖርቶች አጣምሬ ብሠራ ይሻላል? ያጣመርኳቸውን ስፖርቶች ደግሞ የትኛዎቹ ዓለም አቀፍ ስፖርት ፌዴሬሽኖች ይቀበሉታል? የሚለውን ማስቀመጥ ይሻላል እንጂ፣ ይህንን አስቀድሞ በመገደብ አንድ ፌዴሬሽን ብቻ ነው ማቋቋም የምችለው ብሎ በሕግ/በመመርያ ማጠር አያስፈልግም፡፡ ለምሳሌ በዓለም ላይ በተመሳሳይ ስፖርት ከተጣመሩ ፌዴሬሽኖች መካከል ጆዶና ጁጁትሱ፣ ኪክ ቦክስ፣ የቴኒስ ዓይነቶች የክላይምፒንግ ስፖርቶችና ሌሎች የማርሻል አርት ስፖርቶችን አንድ ላይ አጣምረው የሚወስዱ አገሮች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በመመርያው በተለይ በስፖርት ፌዴሬሽኖች ውስጥ ሥራ አስፈጻሚ ሆነው መመረጥ የሚችሉት ኢትዮጵያውያን ዜጎች ብቻ መሆን እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡ ይህም በተደጋጋሚ የመከራከሪያ ርዕስ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

ፀጋዬ (ዶ/ር)፡- በተፈጥሮ አንድ ዜግነት የሚገኝባቸው መሠረቶች በደም (Right of Blood) ሲሆን፣ ከትውልድ ትውልድ የሚወራረስ ነው፡፡ ሌላው ዜግነት በአንድ አገር ግዛት ውስጥ በመወለድ የሚገኝ ነው፡፡ ግን በኢትዮጵያ የጥምር ዜግነት ስለሌለ የትውልደ ኢትዮጵያ ሕግ ነው የወጣው፡፡ በ1994 ዓ.ም. የወጣው ሕግ አማራጮችን ያስቀመጠና ገደብ ያስቀመጠ ነው፡፡ እስከ ዛሬ የነበረው መታወቂያውን ሰው እስካወጣ ድረስ በብሔራዊ ምርጫና በፓርላማ የሚደረገውን ምርጫ መምረጥና አለመምረጥ በስተቀር በየትኛው ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ መሥራት ያስችለዋል ይላል፡፡ ለምሳሌ ለአንድ የስፖርት ፌዴሬሽን መሆን አይቻልም የሚል ስለሌለው መሆን ይቻላል ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ዝም ብሎ የሚገኝ ሳይሆን በየአምስት ዓመቱ 300 ዶላር በመክፈል ካርድ እያደሰ የሚያወጣው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፓርላማ ትውልደ ኢትዮጵያውያኖች ከአገራቸው ጎን እንዲቆሙ የሚያስችለውን አዋጅ በግልጽ የተፃረረ መመርያ የተመለከትነው ግን በስፖርት መመርያ የወጣው ነው፡፡ የስፖርት መመርያው 50/2014 ላይ አንቀጽ 46 ትውልደ ኢትዮጵያዊ ፕሬዚዳንት ወይም ምክትል ፕሬዚዳንት አይሆንም ይላል፡፡ አንዳንድ ፌዴሬሽኖች ሥራ አስፈጻሚ ሆኖ መመረጥ እንዳይችል አድርገዋል፡፡ ይህ ትልቅ የሕግ ጥሰት ነው፡፡ የዓለም አቀፍ ፈዴሬሽኖች ስለማይቀበሉ ነው የሚለው ማሳመኛም የትም አይሠራም። ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው ውጤት ነው፡፡ ማንም ሰው ቢሆን በውጤቱ ብቻ ሊገመገም የሚገባው፡፡ እንዲያውም በውጭ አገር ያሉ ዳያስፖራዎችን መጋበዝ እንጂ ማራቅና ማግለል አይገባም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ግለሰቦች በራሳቸው የገንዘብ አቅም መንቀሳቀስ የሚችሉ ስለሆኑ ሊጠቅሙ ይችላሉ እንጂ ሊጎዱ አይችሉም፡፡ ለምሳሌ በጀርመን አገር በአመራር ላይ ያሉ ሰዎች 20 በመቶ የሚሆኑትና በአመራር ላይ ያሉት ሰዎች የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ በመመርያዎቹ ስፖርቱን የሚጠቅሙ ሰዎችን ማራቅ ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም፡፡.

ሪፖርተር፡- ጥምር ዜግነት ያለው ሰው በስፖርት ፌዴሬሽን ውስጥ መመረጥ እንደማይችል ሲነገር ይሰማል፡፡ ይህንን እንዴት ይመለከቱታል? ሌሎች ገደቦችስ?

ፀጋዬ (ዶ/ር)፡- በመሠረቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥምር ዜግነት የለም፣ ከዓለም ዕድሜያቸው ለአቅመ አዳም ሲደርስ መወሰን አለባቸው ይላል፣ በ1996 የወጣው የዜግነት ሕግ። በ2014 ዓ.ም. የወጣው መመርያ ላይ ኢትዮጵያ ዜጋ ብቻ ከማለቱም በላይ በማሳሰቢያ ጭምር ትውልደ ኢትዮጵያን ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት መሆን አይችሉም ብሎ ያስቀምጣል፡፡ ይህ ደግሞ ማንኛውም በውጭ አገር የሚኖርን ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሆኖ በውጭ አገር የሚኖር ዜጋ ‹‹እጅህን ከኢትዮጵያ ስፖርት አንሳ›› ወይም ‹‹ትዳር መመሥረት ትችላለህ አባት መሆን ግን አትችልም ዓይነት›› የሚል መልዕክት ያለው ያስመስላል፡፡ በ1994 ዓ.ም. የወጣውን መመርያ ሙሉ በሙሉ የሚፃረር ነው፡፡ ሌላው ስፖርቱን ለመምራት እንደ ፖለቲካ ሹመት በተወሰኑ ዓመታት መገደብም ተገቢ አይደለም፣ ግን ዴሞክራሲያዊ መሆን ይኖርበታል፡፡ ስፖርት ለማሳደግ በቂ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ በተጨማሪ የታዘብኩት ነገር በስፖርቱ ገደብ ማስቀመጥ ይታይበታል፡፡ በተለይ በመከልከል ባህል የታጀበ መመርያ ወይም አመራር ተገቢ አይደለም፡፡ በመመርያ የታዘብኩት ሁሉንም ነገር ቆልፎ ማስቀመጥ አባዜ ያለበት ነው፡፡ በዓለም ላይ 101 የስፖርት ዓይነቶች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ስንቱ ገቡ? ሌላው መመርያ ላይ ያለው ክፍተት አዲስ የስፖርት ዓይነት ማስገባት ወይም ማኅበር መመሥረት የማይሞከር መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ በኢትዮጵያ አንድ የስፖርት ፌዴሬሽን ወይም ማኅበር ለማቋቋም የተቀመጡት መሥፈርቶች ካልተከተለ አንድን ስፖርት ሕገወጥ ማስባል የሚያስኮንን ነው፡፡ ስፖርትን ለማሳደግ ከተፈለገ አንድ ክለብ እንኳን ቢኖር መታወቅና በኢትዮጵያ የበረዶ ተንሸራታች ማኅበር ተብሎ አንድ ስፖርተኛ ነበር፡፡ በአንፃሩ መመርያው መሰል ስፖርቶችን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት እንዳይችል ያሳያል፡፡ በቀላሉም በማኅበር ተደራጅቶ እንቅስቃሴ እንዲደረግበት አይፈቀድም፡፡ ግን ስፖርቱ ከዓለም አቀፍ የስፖርት ፌዴሬሽኖች ጋር ያለው ግንኙነት ከታየና ስፓርታዊ እንቅስቃሴው ጥሩ ከሆነ መደገፍ ያሻል የሚል እምነት አለና፡፡ በዚህም መሠረት መመርያው ብዙ መሻሻል ያለበት ነገር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ሌላው አከራካሪው ጉዳይ የስፖርት ማኅበራት አደረጃጀት ነው፡፡ የስፖርት ማኅበራት እንዴት መደራጀት ይኖርባቸዋል?

ፀጋዬ (ዶ/ር)፡- በኢትዮጵያ የስፖርት ማኅበራት አደረጃጀት እንደ መመርያው በርካታ ውስብስብ ጉዳዮች ያሉበት ነው፡፡ ለምሳሌ ጀርመን አገር 98 የስፖርት ማኅበራት አሉ፡፡ የኦሊምፒክ ስፖርቶች የሆኑ እና ያልሆኑ በድምሩ 101 ናቸው፡፡ ስለዚህ ጀርመን የኦሊምፒክ ስፖርት ለማሟላት ሦስት ስፖርቶች ይቀሩታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ስፖርት ብዝኃነት ያለው ሲሆን፣ ከታች የሚመሠረት ሆኖ፣ ከላይ የአሠልጣኞችን መብት መጠበቅ አለበት፡፡ ከዚህም ባሻገር የባለሙያዎችን መብት መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ ስፖርት መንግሥት ጣልቃ የሚገባበት አይደለም፡፡ የመንግሥት ኃላፊነት ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ ድጎማ መስጠትና ፈቃዶችን መስጠት ነው፡፡ ሁሉም ስፖርቶች በባህሪያቸው የተለያዩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከቻይና የመጡና ከጃፓን የመጡ ስፖርቶች አሉ፡፡ የኦሊምፒክ የሆኑና የኦሎምፒክ ስፖርቶች ያልሆኑ አሉ፣ የተናጠል እና የቡድን፡፡ አደረጃጀቱም በጥልቀት ሊታይ የሚገባውና የሌሎች አገሮችን አደረጃጀትን ፌዴሬሽኖች ልምድ ማየት ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ አደረጃጀትን በተመለከተ የሚቀመጡ ቁጥሮች አሉ፡፡ ይህም አንድ ፌዴሬሽን ለማቋቋም በአምስት ክልሎች ስፖርቱ መዘውተር እንደሚገባው ተቀምጧል፡፡ መልሶ ደግሞ የሚጣረሱ አሠራሮች ሲተገበሩ ይስተዋላሉ፡፡ ለምሳሌ ‹‹ስፖርቱ ባለባቸው አካባቢዎች ወይም ክልሎች ብቻ ነው ፌዴሬሽን ማቋቋም የሚቻለው›› የሚል ይነሳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስፖርቱ በሌለባቸው ቦታዎች ፌዴሬሽኖች ሲመሠረቱ ይስተዋላል፡፡ በአጠቃላይ ዝብርቅርቅ ያለ አሠራር ይስተዋላል፡፡ ይህንን ለማስተካከል ጥረት ሲደረግ ደግሞ አላስፈላጊ ንትርኮችና ክርክሮች ያጋጥማሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ችግር እንዴት መፍታት ይቻላል?

ፀጋዬ (ዶ/ር)፡- ይህንን ችግር መፍታት የሚቻለው ባለሙያ በማደራጀት፣ ተፈላጊ ችሎታ እንዳለው በማሳየትና በማረጋገጥ ፌዴሬሽን በማዋቀር፣፡ ጠያቂ እና ተጠያቂነት ያለበት ስረዓት በመፍጠር ነው።  ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ ግርታ የሚፈጥረው ስፖርትን ከሲቪክ ማኅበረሰብ ለይቶ የማየት ነገር አለ፡፡ በአንፃሩ ዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሆኑ የተለያዩ አገሮች የስፖርት ፌዴሽኖቹም ሆኑ ስፖርቱን የሚገልጹት አትራፊ ያልሆነ የሲቪክ ማኅበር ብለው ነው፡፡ ስለዚህ ስፖርት አደረጃጀቶቹ በዚህ መልኩ መቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የስፖርት ፖሊሲው ምን ይመስላል?

ፀጋዬ (ዶ/ር)፡- ከ20 ዓመታት በፊት በ1990 ዓ.ም. የወጣ የስፖርት ፖሊሲ አለ፡፡ መስተካከል የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩትም ለጊዜው እንደ ጥሩ ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡ የስፖርት ባለስልጣናትም ለማስተካከል ሲጥሩ ታይቷል። በአንፃሩ ግን አንድ ዕርምጃ ወደፊት፣ ሁለት ዕርምጃ ወደ ኋላ እየተጓዘ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው፡፡ የስፖርት ፖሊሲን ስንመለከት የአንድ አገር ስፖርት መስፋፋት ዋነኛው ጉዳት መኖሩ የሚታየው ስፖርት በትምህርት ቤቶች መዳከምና የስፖርት ማዘውተሪያዎች ያለመኖር ይጠቀሳል፡፡ ፖሊሲው ላይ ባህላዊ ስፖርቶችን ማካተት፣ የክሊን ስፖርቶችንና የፕሮፌሽል ስፖርቶችን በፖሊሲው ላይ መጨመር ያስፈልጋል፡፡፡ በተለይ የክሊን ስፖርት፣ ስፖርት ለአካባቢ ጥበቃና ለአረንጓዴ ልማት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ፖሊሲው ላይ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ በገጠር ያለው ማኅበረሰብ በባህላዊ፣ ዘመናዊ ስፖርት እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ በትምህር ቤቶች እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት መስጠት ይኖርበታል፡፡ የትምህርት መጠናቀቂያ ላይ እንደ መውጫ መግባት ይኖርበታል፡፡ ሌላው በበጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረቱ የስፖርት እንቅስቃሴዎችና አመራር ለሚያደርጉ የማኅበረሰቡ አካላት ማበረታታትና መሸለም፣ እንዲሁም ዕውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ስፖርት ለሁሉም›› የሚል የስፖርት ተደራሽነት የስፖርት ጥናት ምርምር ዓለም አቀፋዊ ልምዶችን የሚያጠና፣ ለባለሙያዎችና ለመምህራን ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ለአትሌቶች የትስስር መረብ የሚፈጥር መሆን ይገባዋል፡፡ ሌላው በውጭ አገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊ (ዳያስፖራዎች) በስፖርት እንዲሳተፉና እንዲረዱ የሚያስችልና ያለ እንቅፋት የስፖርት የዕውቀት ሽግግርን መተግበርን የሚያስችል መፍጠርና በፖሊሲ ማስገባት ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት በስፖርቱ ውስጥ ሊኖረው የሚችለው ሚና እስከ ምን ድረስ ነው?

ፀጋዬ (ዶ/ር)፡- መንግሥት በስፖርት ውስጥ ያለው ሚና ቀዳሚ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው፡፡ የተለያዩ የስፖርት ማኅበራት ተደራጅተው ሲቀርቡ በቀላል መንገድ ዕውቅና የመስጠት ኃላፊነት አለበት፡፡ ወጥ የሆነ አንድን የስፖርት አሰልጣኝ አሰልጣኝ የሚያደርገው የስልጠና ፣ የፈቃድ ስረዓት ይዘረጋል። ሌላው እንደ አስፈላጊነቱ ድጎማ ያደርጋል፡፡ በአብዛኛው ጊዜ ችግር የሚገጥመው መንግሥት ድጎማ ካደረገ ቁጥጥር ስለሚያደርግ ነው፡፡ ድጎማ ያላደረገበት ነገር ላይ ግን መቆጣጠር አይቻልም፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በማኅበራት አሠራር ውስጥ ጣልቃ ሊገባ አይችልም፡፡ ሌላው ወደ ዓለም አቀፍ ስፖርት ፌዴሬሽኖች ጨምሮ ጣልቃ በመግባት ዕውቅና እንዲሰጡ ጫና ማድረግ የኦሊምፒክ ቻርተርን መፃረር ነው፡፡ መንግሥት የመከልከል ባህል ሳይሆን የመፍቀድ፣ መቻቻል፣ የማስታረቅና የመሸምገል ባህል መሥራት ይጠበቅበታል፡፡  መንግሥት በምንም ዓይነት ምክንያት በስፖርት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት አይኖርበትም፡፡..

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...