Monday, April 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከዕዳ ማጥ ውስጥ ለመውጣት ብልኃት ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ከ28 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ዕዳ ታንቃ የተያዘች ምስኪን አገር ናት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዕዳ ክፍያ ሽግሽግ እንዲደረግላት ከተለያዩ አበዳሪ አገሮችና ተቋማት ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች አድርጋለች፡፡ በይፋ ብድር ከሚሰጧት አበዳሪዎች በተጨማሪ ዩሮ ቦንድን ጨምሮ ከሌሎች የግል አበዳሪዎች ጋር ውይይት በመጀመር፣ ወጥነት ያለው የዕዳ ክፍያ ሽግሽግ እንዲደረግላት ጥረት መጀመሯን መንግሥት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ለምሳሌ በዚህ ወር የዩሮ ቦንድ 33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ክፍያ መፈጸም ባለመቻሏ ምክንያት፣ ዕዳ መክፈል የማትችልበት ደረጃ ላይ ደረሰች ተብሎ የዓለም አቀፍ ሚዲያ መነጋገሪያ መሆኗ አይዘነጋም፡፡ መንግሥት ግን የዩሮ ቦንድ ወለድ ላለመክፈል የወሰነው የኢትዮጵያ አቅም ክፍያውን ለመፈጸም ስለማይችል ሳይሆን፣ ሁሉንም አበዳሪዎች በእኩልነት ማስተናገድ አስፈላጊ ስለሆነና ከሌሎች አበዳሪዎች ጋር እየተካሄዱ ያሉ ውይይቶች እንዳይደናቀፉ ታስቦ መሆኑን ገልጿል፡፡ ለዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች የቀረበው የዕዳ ሽግሽግ ምክረ ሐሳብ የተነደፈው የጋራ ማዕቀፍ የብድር ሽግሽግ ሲጀመር፣ ሊያጋጥም የሚችለው ድጋሚ የሽግሽግ ጥያቄ እንዳይፈጠር ታሳቢ በማድረግና ሊኖሩ የሚችሉ ሥጋቶችን ለመቀነስ እንደሆነም አስታውቋል፡፡

መንግሥት በጋራ ማዕቀፍ የብድር ሽግሽግ (Common Framework for Debt Treatment) መሠረት፣ የቦንድ ባለቤቶችን በማሳመን ችግሮችን መፍታት ከቻለ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ከቦንዱ ባለቤቶች ለሚቀርቡለት ጠንካራ ጥያቄዎች አሳማኝ ምላሽ ለመስጠት ያለው ዝግጁነት ያሳስባል፡፡ ኢትዮጵያ በዩሮ ቦንድም ሆነ በይፋዊ አበዳሪዎች የምታገኛቸው ብድሮች የታሰበላቸው ልማት ላይ ስለመዋላቸው ጥያቄ ቢነሳ፣ ምላሹ በዚያው ልክ መሆን ካልቻለ የወደፊት ታሳቢ ብድሮችን ለማግኘት አሳሳቢ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ የብድር ዕዳና ወለዱን በተገቢው ጊዜ ለምን መክፈል አቃተ ሲባል ጥያቄውን የሚመጥን ምላሽ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ አበዳሪዎችን የማያሳምን ምላሽ ይዞ አደባባይ መውጣት የራሱ ጣጣ እንዳለው መገንዘብ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ ዕዳዎችና እንደ ዩሮ ቦንድ ያሉ ብድሮች፣ በዕዳ ክፍያ ሽግሽግ ውይይቶች ላይ የሚስተናገዱበት ማዕቀፍ እንደ ቅደም ተከተላቸው መሆኑን ነው፡፡

ኢትዮጵያ በጣም ከፍተኛ የተፈጥሮ ፀጋዎችና የወጣት ሰው ኃይል ባለቤት ሆና፣ ሕዝቧ በድህነት እየማቀቀ የሚኖርባት አገር መሆኗ አንገት ያስደፋል፡፡ ዓመታዊ በጀቷ ለረዥም ጊዜያት ከፍተኛ ጉድለት እያስመዘገበ ለዕርዳታና ለብድር ስታንጋጥጥ ኖራለች፡፡ በርካታ ሚሊዮኖች የዕርዳታ ጥገኛ ሆነው መቀጠላቸው አሁንም በስፋት ቀጥሏል፡፡ በፈረቃ እያሰለሰ ከሚከሰተው ድርቅ ጀምሮ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ ሕዝባችን መከራውን እያየ ነው፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲንከባለል የመጣው የውጭ ዕዳ ጫና ኢኮኖሚውን በእንፉቅቅ እያስኬደው ነው፡፡ ምንም እንኳ ኢኮኖሚው በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው ኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ከፍተኛ መንገጫገጭ ቢያጋጥመውም፣ ላለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶችና ጦርነቶች ምክንያት አከርካሪው ተመቷል ቢባል የተጋነነ አይሆንም፡፡ በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት የነጠፈ ሲሆን፣ ጦርነቱን ተከትሎ የመጣው የዋጋ ንረት ታክሎበት የብድር ዕዳ የመክፈልን አቅም አሟጦታል፡፡ ይህ ሁሉ ጫና ነው የብድር ሽግሽግ ጥያቄ ማቅረብ ደረጃ ያደረሰው፡፡

እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት መንግሥት ለዩሮ ቦንድ ወለድ የሚፈለግበትን 33 ሚሊዮን ዶላር መክፈል አቃተው ሲባል፣ መንግሥት ደግሞ መክፈል አቅቶኝ ሳይሆን ሁሉንም አበዳሪዎች በእኩልነት ለማስተናገድ ፈልጌ ነው ሲል ሊፈጠር የሚችለው ተቃርኖ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ የተበዳሪነት አስተማማኝነቷ (Credit Worthiness) በዓለም አቀፍ የብድር ደረጃ ሰጪ ኤጀንሲዎች (Credit-Rating Agencies) ያሽቆለቁላል፡፡ ይህም የሚፈጥረው አሉታዊ ገጽታ ትልቅ ጠባሳ ይፈጥራል፡፡ የዛሬ አሥር ዓመት ገደማ ከዩሮ ቦንድ ከተገኘው ብድር ውስጥ ከሦስት-አራተኛው በላይ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ መዋሉ ሲነገር፣ ከእነዚህ ዓመታት በኋላ ብድርና ወለዱን መክፈል አለመቻል አገር ካለችበት የፀጥታ ችግር ጋር እየተሸራረበ አሉታዊ ገጽታው መበላሸቱ ይቀጥላል፡፡ ችግሩ በዚህ ሁኔታ ሲቀጥል ኢትዮጵያ የምትጠብቃቸው የውጭ ኢንቨስተሮች መተማመን አጥተው ስለሚቀሩ፣ እነሱን አባብሎ ለመሳብ እንቅፋት ያጋጥማል፡፡ ኢንቨስተሮች ሁኔታውን አይተው ሲሸሹ አበዳሪዎችም ጀርባቸውን መስጠት ይጀምራሉ፡፡ ችግሮች ሲከፉ የመንግሥት ወጪ በእጅጉ ይቀንሳል፣ ክፍያዎችን መፈጸም ያዳግታል፣ የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ ለማኅበራዊ ቀውስ ይዳርጋል፡፡

መንግሥት ከአበዳሪዎች ጋር እያደረጋቸው ያሉ ውይይቶች ሁሉን አቀፍ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ እንዲሆኑ፣ በተለይ ዕዳ እንዳይከፈልና ኢኮኖሚው እንዲጎሳቆል ምክንያት የሚሆኑ ችግሮች ላይ ማተኮር ይጠበቅበታል፡፡ ኢትዮጵያ ለማመን የሚያዳግቱ የተፈጥሮ ሀብቶችና ወጣት የሰው ኃይል ባለቤት ሆና በተባበረ አገራዊ ስሜት ፊትን ወደ ልማት ማዞር እየተቻለ፣ ከአንድ አውዳሚ ጦርነት ወደ ሌላው የሚገባባቸውን አጓጉል አባዜዎች ማስወገድ የግድ መሆን አለበት፡፡ አበዳሪዎች የኢትዮጵያን ዕምቅ ሀብት ተረድተው ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ የሚሆኑት፣ መንግሥት በበኩሉ ለሰላምና ለመረጋጋት የሚረዱ ተግባራትን በግልጽ ማሳየት ሲችል ነው፡፡ ግብርናው፣ ኢንዱስትሪው፣ ንግዱ፣ ኢንቨስትመንቱ፣ ማዕድኑ፣ ቱሪዝሙና ሌሎች ዘርፎች በሙሉ ኃይላቸው እንዲሠሩ ለማድረግ የሚያስችል ከባቢ መፍጠር የግድ መሆን አለበት፡፡ መንግሥት ከአበዳሪዎች ጋር የሚያደርጋቸው ውይይቶችም ሆኑ ድርድሮች በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ማተኮራቸው የሚጠበቅ ሲሆን፣ አበዳሪዎች በተለይ ሰላምና መረጋጋት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ምንም ዓይነት ውጤት እንደማይገኝ ስለሚያምኑ አስገዳጅ ሁኔታዎች መደንቀራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የመንግሥትን የፖሊሲ ቅኝቶችንም ይመረምራሉ፡፡

መንግሥት ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አለው ወይ የሚለው አንዱ ነው፡፡ ውጤታማ የብድር አከፋፈል ሥርዓት ሊኖር የሚችለው መንግሥት ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ሲኖረው እንደሆነ በአበዳሪዎች የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ የብድር ጫናው ሲበረታ አበዳሪዎች ሥጋት ስለሚገባቸው የመንግሥት አቅም በዚህ መስክ መፈተሹ አይቀሬ ነው፡፡ ብድሮች ሥራ ላይ ውለው አትራፊ መሆን ለምን እንደሚያቅታቸውም ጥያቄ ይነሳል፡፡ ሌላው አገሪቱ ያሏትን ዕምቅ ሀብቶች ለመጠቀም ለምን አልቻለችም ተብሎም ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ይቃኛሉ፡፡ በምግብ ራስን አለመቻልና የዕርዳታ ጥገኝነት አባዜም እንዲሁ፡፡ ከዚህ በተረፈ ደግሞ የፖለቲካ ምኅዳሩን አስተካክሎ ሰላም ማስፈን ያልተቻለባቸው ምክንያቶችም ይዳሰሳሉ፡፡ አበዳሪዎችም ሆኑ ኢንቨስተሮች ሀብታቸውን ከግጭት መውጣት ያቃተው አገር ውስጥ ማባከን ስለማይፈልጉ፣ እያንዳንዱን ችግር ለማወቅ የሚሄዱበት ርቀት የዕዳ ጫናውን ሸክም የበለጠ አድካሚ ያደርገዋል፡፡ የቀጥታ ኢንቨስትመንት ድርቅና የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማሽቆልቆል ከፀጥታ ችግርና ከፖሊሲ ተግዳሮት ጋር እየተመጋገቡ፣ አበዳሪዎች የበለጠ ጫናቸውን እንዲያጠናክሩ እንደሚያደርጋቸው ይታሰብበት፡፡ ለዚህም ሲባል መንግሥት ብልህ ይሁን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...