Monday, April 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከድህነት አዘቅት ውስጥ የሚያወጡ አማራጮች ላይ ይተኮር!

ለረዥም ጊዜ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ያጠኑ፣ በትምህርትና በምርምር የታገዙ ሐሳቦችን ያቀረቡ፣ በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ያስተማሩ፣ እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ በማገልገል ልምድ ያካበቱ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በተለያዩ ጊዜያት ጠቃሚ ልምዶችን ለማካፈል ጥረት አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ እጅግ የከፋ ደረጃ ላይ ያለውን ድህነት ለማስወገድ ውስብስብ ከሚያደርጉት ችግሮች መካከል፣ ኢኮኖሚው የማደግ ተስፋ ቢኖረውም በተለያዩ ተፅዕኖዎች ምክንያት በበርካታ እንቅፋቶች ተከቧል፡፡ በኮቪድ ወረርሽኝ፣ በሰሜን ጦርነት፣ በተለያዩ አካባቢዎች በሚካሄዱ ግጭቶች፣ በዋጋ ንረት፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረትና መጠናቸው እየጨመረ በመጣ የዕዳ ክፍያዎች ምክንያት ኢኮኖሚው ተጎሳቁሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን በርካታ ታዳጊ አገሮች በከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የዕዳ ሽግሽግና ተጨማሪ ብድርና ዕርዳታ በመስጠት እንዲታደጋቸው እየወተወቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ጥያቄ በማቅረብ ከአበዳሪዎች ጋር ውይይቶችን በማድረግ፣ ሊከተል ከሚችለው ቀውስ ራሷን ለመከላከል ጥረት እያደረገች መሆኗን መንግሥት አስታውቋል፡፡ ጥረቱ ተስፋ እንዳለውም እየተነገረ ነው፡፡

ከዚህ ጥረት ጎን ለጎን ደግሞ መንግሥት ምርጥ ተሞክሮዎች ባላቸው ባለሙያዎች ዕገዛ፣ ከድህነት አዘቅት ውስጥ ሊያወጡ የሚችሉ የተለያዩ አማራጮችን መቃኘት ይጠበቅበታል፡፡ ባለሙያዎች እንደሚሉት የመጀመሪያው ትኩረት መሆን ያለበት ግብርና ነው፡፡ የግብርናው ዘርፍ ዘመኑ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ አኳያ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በመጠቀም የተትረፈረፈ ምርት ማስገኘት ይኖርበታል፡፡ ለዚህም ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዱ እንደ የመስኖ እርሻ፣ ድርቅ መቋቋም የሚችሉ ዘሮች፣ የአፈር ጥበቃና እንክብካቤ፣ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና ፀረ አረሞችን በስፋት ሥራ ላይ ማዋል ይጠቀሳሉ፡፡ በሁሉም የግብርና ሥራዎች እነዚህ በሙሉ አቅም ተግባራዊ ሲደረጉ በምግብ ራስን ከመቻል ታልፎ ለአርሶ አደሮች ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም የእሴትና የአቅርቦት ሰንሰለቱን በማጠናከር፣ የግብርና ምርቶችን ለማቀነባበሪያዎችና ለገበያ እንዲደርሱ በማድረግ ከፍተኛ ገቢና ሥራ መፍጠር ያስችላል፡፡ የመሬት ሥሪቱን በማስተካከል አርሶ አደሮች ባለቤትነት ተሰምቷቸው የበለጡ እንዲሠሩ በማስቻል፣ ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ ገበያዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይረዳል፡፡

ሌላው በባለሙያዎች ምክረ ሐሳብ የሚቀርብበት ኢኮኖሚው ባለብዙ ዘርፍ ሀብት አመንጪ እንዲሆን ነው፡፡ ለምሳሌ የማኑፋክቸሪንግና የኢንዱስትሪ ዘርፍን በከፍተኛ መጠን ማነቃቃት ይጠቀሳል፡፡ ለጨርቃ ጨርቅና ለአልባሳት ኢንዱስትሪ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከአገር ውስጥ አልፎ በውጭ ገበያ ተፎካካሪ ማድረግ ይገባል፡፡ ይህንን ክፍለ ኢኮኖሚ በሙሉ ኃይሉ እንዲንቀሳቀስ መደገፍ ከተቻለ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አልፋ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምርቶች ማቅረብ ትችላለች፡፡ በተጨማሪም የብረታ ብረት፣ የአውቶሞቲቭ፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግና ሌሎች ቀላል ኢንዱስትሪዎችን በብዛት ማሠራት ከተቻለ ከፍተኛ ጥቅም ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ በቱሪዝምና በአገልግሎት ዘርፍ ከተሠራባት ከፍተኛ ሀብት ይጠብቃታል፡፡ ከኢትዮጵያ እጅግ አስደናቂ የቱሪስት መስህቦች ለመጠቀም ለመሠረተ ልማቶች መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ያስፈልጋል፡፡ ኢንቨስትመንቱን ማሳካት ከተቻለ ከፍተኛ ገቢ አመንጪና ሥራ ፈጣሪ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም የሆቴል፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ የፋይናንስ፣ የትምህርት፣ የጤና፣ እንዲሁም ሌሎች መሰል ዘርፎች ከተሠራባቸው ኢኮኖሚውን ለመደገፍ የሚያስችል ከፍተኛ ሀብት ያስገኛሉ፡፡

ሌላው በጣም ጠቃሚው ተብሎ በባለሙያዎች የሚጠቀሰው የሰው ኃይል ልማት ነው፡፡ ለአገር ዕድገት ግንባታ የሚያግዘው የሰው ኃይል በትምህርትና በሥልጠና መገራት አለበት፡፡ በሁሉም የትምህርት እርከኖች ጥራት ያለው ትምህርት መስጠት ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ መሆን ሲኖርበት፣ በዚህ መሠረት የሚሰጡት ትምህርቶች በሥራ ገበያ ውስጥ ተፈላጊ እንዲሆኑ ትኩረት መደረግ አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ ሲቻል ዜጎች ለማደግ ተስፋ ባለው ኢኮኖሚ ውስጥ ተሳትፏቸው ይጨምራል፡፡ የጤና አጠባበቅ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ይሻል፡፡ የጤና መሠረተ ልማቶችን በእጅጉ በማሻሻል የጤና አገልግሎትን ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ ጤናማ ዜጋ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ስለሚኖረው ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ሌላው አፅንኦት ሊሰጠው የሚገባ ዋነኛ ጉዳይ የፆታ እኩልነት ነው፡፡ የፆታ እኩልነትን በተግባር በማረጋገጥ ሴቶች ብቁ ሆነው እንዲገኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል፡፡ የሴቶች ተሳትፎ ይበልጥ ሲጠናከር አገራዊ ኢኮኖሚው የበለጠ እንዲያድግ ከፍተኛ ዕድል ይፈጠራል፡፡ በሁሉም የሥራ መስኮች ሴቶች ተሳትፏቸውና ገቢያቸው ሲጨምር አስገራሚ ለውጥ ይገኛል፡፡

ለኢኮኖሚ ዕድገትም ሆነ ለአገር ህልውና በባለሙያዎች ጠቃሚ ከሚባሉት ውስጥ አንደኛው ተቋማትን ማጠናከርና መልካም አስተዳደር ማስፈን ነው፡፡ በዚህ መስክ ውጤታማ የሆነ ለውጥ ማስመዝገብ የሚቻለው በመጀመሪያ ሙስናን ለማስወገድ የሚረዱ ዕርምጃዎች ላይ በማተኮር ነው፡፡ ሙስናን ለመዋጋት ግልጽነትና ተጠያቂነት የግድ መሆን አለባቸው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሚረጋገጡት ተቋማት ሲጠናከሩ ነው፡፡ የጠንካራ ተቋማት መኖር መተማመን ለመፍጠርና ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያግዛል፡፡ ተቋማት ሲጠናከሩና መልካም አስተዳደር ሲሰፍን ኢኮኖሚው የሚያመነጨው ሀብት የጥቂት ምርጦች ሳይሆን፣ የሁሉም ዜጎች እንደሆነ በተግባር ይረጋገጣል፡፡ ሙስናን መቆጣጠርና መልካም አስተዳደር ማስፈን ሲቻል ዜጎችን እርስ በርስና ከገበያ ጋር የሚያገናኙ የትራንስፖርት አውታራት መገንባት፣ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን ማዳረስና የመሳሰሉት በፍትሐዊነት ይከናወናሉ፡፡ እንዲሁም ኮንትሮባንድና መሰል ሕገወጥ ንግዶችን በተቀናጀ ቁጥጥር አደብ ማስገዛት፣ ጉቦና መሰል ኢሞራላዊ ድርጊቶችን ማስወገድና በሕግና በሥርዓት መመራት የግድ ይላል፡፡

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው የከፋውን ድህነት አስወግዶ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ረዥም ጊዜ የሚፈጅ ተግባር መሆኑን ነው፡፡ ባለሙያዎች እንደሚሉት ችግሮችን ለማቃለል የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅዶች አስፈላጊ ናቸው፡፡ በእነዚህ ቅደም ተከተሎች መሠረት የሚፈለገውን ግብ ለመጨበጥ ግን አስተማማኝ ዕቅድ፣ ድርጊትና ቁጥጥር አስፈላጊ መሆናቸው ይሰመርበታል፡፡ መንግሥት ዕቅዶችን ሲያወጣም ሆነ ወደ ተግባር ሲገባ በባለሙያዎች ሲታገዝ፣ የሚያስበው ውጤት ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ አማራጮች በሚገባ ስለሚመረመሩ ተስፋ ሰጪ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በሁሉም ዘርፎች ውስጥ ተዋንያን የሆኑ ባለድርሻ አካላት፣ የመንግሥት ሴክተር መሥሪያ ቤቶች፣ የሲቪል ማኅበረሰቦች፣ የሙያ ማኅበራት፣ የንግዱ ማኅበረሰብና ተሳትፏቸው አስፈላጊ የሆነ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ተወካዮችን ማካተት ለሚፈለገው የዕድገት ትልም ያግዛል፡፡ በሁሉም መመዘኛዎች እጅግ በጣም ዝቅተኛ በሆነ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሕዝባችን ከድህነት ጋር እየታገለ መኖር ሰልችቶታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች በብዙ መመዘኛዎች በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ድህነትን ከኢትዮጵያ ምድር ለማስወገድ ውስብስብና ረዥም ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም፣ ከድህነት ውስጥ የሚያወጡ አማራጮች ላይ ማተኮር ጊዜ ሊሰጠው አይገባም! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...