Wednesday, May 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልበገና ትውፊቱና ተግዳሮቱ

በገና ትውፊቱና ተግዳሮቱ

ቀን:

ኢትዮጵያ ታሪካዊና ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ መሣሪያዎች ቢኖሯትም ዕውቅናቸው ወንዝ ሳይሻገርና አገልግሎታቸው ሳይሻሻል ዘመናት ተቆጥረዋል። አገር በቀል የሙዚቃ መሣሪያዎች ትኩረት ተነፍጓቸው በኤሌክትሮኒክስ የሙዚቃ መሣሪያዎች በመተካታቸው ጎልተው ካለመታየት ባለፈ የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ይነገራል።

በአገር በቀል የሙዚቃ መሣሪያዎች ላይ በቂ የሆነ ጥናትና ምርምር ባለመደረጉ በዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ዋሽንት በፍሉት፣ ክራር በጊታር፣ ማሲንቆ ደግሞ በቫዮሊንና በመሳሰሉት በመተካት ላይ እንደሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ያወሳሉ።

ለአገር በቀል ሙዚቃ መሣሪያዎች ተብሎ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወይም ኮሌጆች አለመኖራቸው ደግሞ ለመቀዛቀዛቸው እንደ ምክንያት ይነሳል። አገር በቀል የሙዚቃ መሣሪያዎች  ከሚባሉት በቤተ ክርስቲያን በተለይ ደግሞ ዓብይ ፆምን (ሁዳዴ) ጠብቆ የሚሰማው በገና አንዱ ሲሆን፣ ብዙ ጊዜ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ነው የሚውለው።

- Advertisement -
በገና ትውፊቱና ተግዳሮቱ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በበገና ስሪት ላይ ያጠኑት ብርሃኑ ግዛው (ዶ/ር)
ፎቶ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ

ከዚህ ባሻገር በንጉሣውያን ዘመን ነገሥታት ሐዘንና ደስታቸውን በበገና በማጀብ   ይገልጹበት እንደ ነበር ታሪክ ይናገራል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ የበገናና የክራር ሥልጠናዎች ቢኖሩም ነገር ግን በጣም ዝቅተኛ መሆናቸው ይነሳል።

በተለይ ደግሞ አገልግሎቱ ከቤተ ክርስቲያን ጋር መንፈሳዊና ታሪካዊ ቁርኝት ያለው በገና የተለያዩ ተግዳሮቶች እያጋጠሙት ነው ተብሏል።

በገና በኢትዮጵያ ያለው ታሪክና ዕድገት፣ እንዲሁም እያጋጠመው ስላለው ፈተና  ታኅሣሥ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ሙያዊ ማብራሪያ  ተሰጥቷል።

ምንም እንኳን በገናን በተለያዩ ዘመናት ከሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር በማጣመር ለዓለማዊ ሙዚቃ መሣሪያነት ለመጠቀም የተሞከረ ቢሆንም፣ ሳይሳካ እንደቀረና ይልቁንስ ተስማሚነቱና ተገቢነቱ ፈጣሪን ለማመሥገን እንደሆነ ዋቢ ምክንያቶችን እያስደገፉ የተናገሩት የበገና ደርዳሪው መጋቤ ስብሐት ዓለሙ አጋ ናቸው።

ቅዱስ ዳዊት አምላኩን በዝማሬ ለማመሥገን ሲጠቀምበት የነበረው ባለ አሥር አውታር በገና፣ ሲወርድ ሲዋረድ መጥቶ ዛሬም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፈጣሪን ለማመሥገን እየተጠቀመችበት እንደሚገኝ መጋቤ ስብሐት ዓለሙ ተናግረዋል።

በቤተ ክርስቲያን መነፅር የበገና አውታር አሥር የሆነበት አሠርቱ ትዕዛዛትን ለማመልከት እንደሆነ የሚናገሩት መጋቤ ስብሐት፣ ሁለቱ ቋሚዎች በቀኝ በኩል ያለው ቅዱስ ሚካኤልን፣ በግራ ያለው ቅዱስ ገብርኤልን ሲያመለክት፣ ከላይ በኩል አውታሮቹ የታሰሩበት ‹ጋድም› ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ፈጣሪ የሁሉ በላይ ነው የሚል ምሳሌ እንደሚሰጥ፣ እንዲሁም ከታች ያለው የድምፅ ሳጥን ‹ገበቴ› ደግሞ በድንግል ማርያም የተሰየመ ነው ይላሉ።

በእነዚህ ምክንያቶች በገና እንደ ቅዱስ መሣሪያ ወይም እንደ ንዋያተ ቅዱሳን ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ ለዓለማዊ ሙዚቃ መጫወቻ አልተፈቀደም ሲሉ ያስረዳሉ። ምን አልባትም ከአሥር በታችና ከአሥር በላይ አውታሮች ያለው በገና ለሌላ አገልግሎት ሊውል እንደሚችል አክለዋል።

 ‹‹በገና ለዓለማዊ ሙዚቃ መሣሪያ አልተፈቀደም፤›› የሚለውን ሐሳብ በማጠናከር የተናገሩት ደግሞ በአኩስቲክስ ኢንጂነሪንግ ላይ መሠረት በማድረግ የበገና የዜማ መሣሪያ ላይ ሙያዊ ጥናት ያጠኑት ብርሃኑ ግዛው (ዶ/ር) ናቸው።

 ‹‹ከሰው መርጦ ለሹመት ከእንጨት መርጦ ለታቦት›› እንዲሉ በገናን ለመሥራት የራሱ የሆነ ጥበብን የሚጠይቅ ሲሆን፣ የሚሠራበት ቁስም የተመረጠና የተለየ መሆን እንዳለበት ያስረዳሉ። እንደ ብርሃኑ (ዶ/ር) ገለጻ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለምሥጋናና ለዝማሬ እየተጠቀመችበት ያለውን በገና ለመሥራት ከዋልድባ ገዳም የዝግባ እንጨት የሚመጣ ሲሆን፣ ቆዳው ደግሞ ባሌ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙ ድኩላዎች አርጅተው ሲሞቱ ከሚገኘው ቆዳ እንደሆነ ያብራራሉ።

ከከብት ወይም ከበግና ከፍየል ቆዳ ቢሠራ ምን ጉዳት አለው? ለሚለው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ ቀደም ሲል የሚሠራው በእነዚህ ቆዳዎች እንደነበር ተናግረው፣ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ጮማ ስለሚበዛበት በገናው በሚያወጣው ድምፅ ላይ ከፍተኛ ልዩነት በመፍጠሩ እንደሆነ አብራርተዋል።

 በዚህም አንድ በገና ለመሥራት ለቁሳቁስ ብቻ እስከ 25 ሺሕ ብር እንደሚፈጅ፣ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በገና ደረጃውን ባልጠበቀ መልኩ እየተሠራ ለገበያ እንደሚቀርብ ገልጸው፣ ይህ ደግሞ ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነ አክለዋል።

በሌላ በኩል በገና ከምሥጋናና ውዳሴ ውጪ ለዓለማዊ አገልግሎት ፈጽሞ የማይስማማ እንደሆነ ሲናገሩም ‹‹በገናን ከሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር ቀላቅሎ ለመጠቀም መሞከር ጥሩ የዶሮ ወጥ ከተሠራ በኋላ በላዩ ላይ ሽሮ እንደመጨመር ወይም ለአነባበሮ በተዘጋጀ እንጀራ ላይ ሽልጦ እንደመደረብ ይቆጠራል፤›› ሲሉ  በገና  ለሌሎች ጭፈራና አካላዊ እንቅስቃሴ ከሚያሳዩ ሁነቶች ጋር ጥምረት እንደሌለው ያመለክታሉ።

 ተግዳሮቶቹ ከፍ እያሉ መጥተው በአሁኑ ወቅት በዜማው ላይም ችግሮች እየታዩ እንደሆነና በአንዳንድ ሙዚቃዎች ጀርባ እየቀላቀሉ እየተጠቀሙ እንደሆነ ማስተዋላቸውን ብርሃኑ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

‹‹በገናን ለዓለማዊ ሙዚቃ ለመጠቀም የተሞከረው ዛሬ ሳይሆን ቀደም ሲል ነው፤›› የሚሉት መጋቤ ስብሐት ዓለሙ፣ አፄ ቴዎድሮስና አፄ ምኒልክ በገናን ይደረድሩ እንደነበር ተናግረው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በገና ደርዳሪዎች የበዙበትና አንፃራዊ ዕድገትም የታየበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳሉ።

በተለይ አፄ ቴዎድሮስ ሲከፋቸውና ሲተክዙ ደስታቸውን የሚመልሱት በበገና ነበር። በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ንጉሡን ጨምሮ በርካታ ትልልቅ ሰዎች በገናን መደርደር ይችሉ እንደነበር መጋቢ ስብሐት ይናገራሉ፡፡

በበገና አውታር የሚቀኙ ግጥሞችና ዜማዎች ሁለት ባህሪያትን የያዙ ሲሆን  የመጀመርያው ስለታሪክ፣ ስለአገር፣ ስለነገሥታትና ለመሳሰሉት በሚቀኝበት ወቅት በገና የሚደረደር ሲሆን፣ ቀጣዩ ደግሞ በሰምና ወርቅ ታጅበው በአዝማች እየተደረደሩ ፈጣሪ በሚመሠገንበት ወቅት የሚቀርብ ነው።

ነገር ግን በገናን እንደ መሰንቆ፣ ክራርና የመሳሰሉት ዓለማዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር በማጣመርም ሆነ ራሱን አስችሎ ለመሥራት ታስቦ ሳይሳካ መቅረቱን መጋቤ ስብሐት ያስታውሳሉ።

በገና እንኳን ከዓለማዊ ሙዚቃ ጋር ሊዋሃድ ቀርቶ ከቅዱስ ያሬድ የዜማ መሣሪያዎች ጋር ውህደት ሊፈጥር አይችልም የሚሉት መጋቤ ስብሐት በዘመነ ደርግ አንድ የኦርኬስትራ ቡድን በገናን ከሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር ቀላቅሎ ሊጫወትበት ፈልጎ ሳይሳካ እንደቀረ ያስረዳሉ፡፡

በገና በደርግ ዘመን ሊጠፋ የተቃረበበት ወቅት እንደነበር የተናገሩት መጋቤ ስብሐት፣ በወቅቱ ያስተምሩበት የነበረው የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የበገና ትምህርት እንዳይሰጥ ማድረጉን ያስታውሳሉ። በገናም ከመንፈሳዊ አገልግሎት ይልቅ ለአብዮቱ መፈክሮች ማጀቢያ እንዲሆን ትልቅ እንቅስቃሴ ተደርጎ ነበር ብለዋል።

በወቅቱ የበገና ደርዳሪዎች ቁጥር ተመናምኖ የነበረ ቢሆንም፣ የደርግን  መውደቅ ተከትሎ በተፈጠረው የተሻለ እንቅስቃሴ በተለይ በቤተ ክርስቲያን በገና ደርዳሪዎችን በማሠልጠን የተሻለ እንቅስቃሴ ታይቶ ነበር የሚሉት ብርሃኑ ግዛው  (ዶ/ር)  በአሁኑ ወቅትም ከአሥር ሺሕ በላይ በገና ደርዳሪዎች እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...