Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአማራ ባንክ ያስመዘገበው ኪሳራና የፕሬዚዳንቱ በጠቅላላ ጉባዔ ዋዜማ መነሳት በባለአክሲዮኖች ጥያቄ አስነሳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰኔ 2014 ዓ.ም. ተመሥርቶ ሥራ የጀመረው የአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር በተጠናቀቀው የ2015 ሒሳብ ዓመት ከ306 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ለማስመዝገብ አቅዶ ያልተጣራ 460 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ማስመዝገቡ፣ እንዲሁም የባንኩ ፕሬዚዳንት ከጠቅላላ ጉባዔው ጥቂት ቀናት በፊት ከኃላፊነት መነሳት በባለአክሲዮኖች ጥያቄ አስነሳ፡፡

የአማራ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነትን ለመተካት የቀረቡ ዕጩዎች ላይ የብቃትና ታማኝነት ጥያቄ ስመቅረቡ፣ እንዲሁም ከአፈጻጸም ማነስ የተነሳ ባንኩን ለኪሳራ ዳርገዋል በሚል የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩትን አቶ ሔኖክ ከበደና የኮርፖሬት አገልግሎት ዋና መኮንን አቶ ክንዴ አበበ ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ከሁለት ሳምንት በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የባንኩ የባለአክሲዮኖች ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ሐሙስ ታኅሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. 40 ሺሕ ያህል ባለአክሲዮኖች በተገኙበት በጎልፍ ክለብ ተካሂዷል፡፡

ለጠቅላላ ጉባዔው የቀረበው የባንኩ የ2015 ሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ባንኩ በዓመቱ መጨረሻ ላይ 1.8 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ አግኝቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 967 ሚሊዮን ብር ከብድር ወለድ፣ 578 ሚሊዮን ብር ባንኩ በሌሎች ባንኮች ካስቀመጠው ተቀማጭ ገንዘብ ተቀማጭ ወለድና 155 ሚሊዮን ብር ከኮሚሽንና ከአገልግሎት ክፍያዎች፣ እንዲሁም ቀሪው ከሌሎች የገቢ ምንጮች የተገኘ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ የባንኩ አጠቃላይ ወጪ ከቅርንጫፍ መስፋፋት፣ ከሠራተኛ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም፣ ከቢሮ ኪራይና አስተዳደራዊ ወጪዎች፣ እንዲሁም ከተቀማጭ ገንዘብ ጠቅላላ ወለድ ክፍያ ጋር ተዳምሮ 2.3 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

ከዋና ዋና ወጪዎች መካከል ለቅርንጫፎች የቢሮ ኪራይ 214 ሚሊዮን ብር፣ ለአስተዳደራዊ ወጪ፣ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅምን ጨምሮ 521 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም 432 ሚሊዮን ብር ለተቀማጭ ገንዘብ የተከፈለ ወለድ ነው፡፡  

ባንኩ በወለድ ክፍያ በደመወዝና ጥቅማ ጥቅም፣ በቢሮ ኪራይና በአስተዳደራዊ ወጪዎች ማደግ ምክንያት በዓመቱ መጨረሻ ያስመዘገበው የኪሳራ መጠን ከታክስ በፊት 481 ሚሊዮን ብር መሆኑን፣ ይኼው ኪሳራ ከታክስ በኋላ ወደ 145 ሚሊዮን ብር ዝቅ ማለቱ ተገልጿል፡፡ በዚህም ምክንያት በእያንዳንዱ አክሲዮን የተመዘገበው ኪሳራ ሦስት በመቶ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በሰኔ 2015 ዓ.ም. የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 28.4 ቢሊዮን ብር፣ የቅርንጫፎቹ ብዛት 267፣ የባንኩ አጠቃላይ የቋሚ ሠራተኛ ቁጥር ደግሞ 4,659 መድረሱን ባንኩ አስታውቋል፡፡

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ 14.9 ቢሊዮን ብር ብድር ማቅረቡ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 38.4 በመቶ ለአገር ውስጥ ለንግድና አገልግሎት፣ 21.2 በመቶ ለወጪ ንግድ፣ 16.3 በመቶ ለአምራች ኢንዱስትሪ የቀረበ ነው ተብሏል፡፡ እነዚህ ዘርፎች በአመዛኙ የአጠቃላይ ብድሩን 75.8 በመቶ ወይም 11.4 ቢሊዮን ብር ድርሻ መያዛቸው ተመልክቷል፡፡

የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታ በጉባዔው ባደረጉት ንግግር ባንኩ በተቋም ግንባታ ሒደት ወጣ ገባ መንገዶች ቢበዙበትም፣ ‹‹እንሻገራቸዋለን›› የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

አቶ የሺጥላ ሰዋሰው የተባሉ ባለአክሲዮን ጉባዔው ላይ ባነሱት ጥያቄ ባንኩ አርሶ አደሮች፣ መምህራንና ምሁራን ትልቅ ተስፋ የሚጥሉበትና ብዙ ሕዝብ በአባልነት ያቀፈ በመሆኑ አንድነት፣ ፍቅርና ትብብርን ያመጣል ተብሎ የታሰበ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሪፖርቱ የተገለጸው ኪሳራ በምን ምክንያት የተመዘገበ ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹እባካችሁ አንድነትንና ፍቅርን የምናሳይበት መንገድ ላይ ባንኩ ቢሠራ፤›› ብለው ‹‹ከሁሉም በላይ፣ ከገንዘቡም በላይ ቦርዱ መሰባሰባችንን ቅድሚያ ይስጥ፡፡ ከመቀነቷ ፈታ የሰበሰበችውንና ያልፍልኛል ብላ የቆጠበችውን እናትና እህታችን ወይም አርሶ አደሩን ወንድማችንና አባታችንን አንርሳ፤›› ብለዋል፡፡

ሌላኛው የጉባዔው ተሳታፊ ‹‹እኔ በበኩሌ ብዙ ትርፍ ጠብቄ ነበር፣ ነገር ግን ሪፖርቱ ላይ እንደተቀመጠው ትልቁ ገቢ ከወለድ የተገኘ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ለሠራተኛ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ወጥቷል፡፡ ይህ ማለት ባንኩ በዓመቱ ካገኘው ገቢ ውስጥ 68 በመቶ የሚሆነውን ለሠራተኛው ነው የከፈለው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን መጠየቅ የምፈልገው ባንኩ ለባለአክሲዮኖች ስንት በመቶ የትርፍ ድርሻ እከፍላለሁ ብሎ ነበር የሠራው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አክለውም የባንኩን ፕሬዚዳንት ከጉባዔው መካሄድ ጥቂት ቀናት ቀድሞ የተሰናበቱበት መንገድ ግልጽ አለመሆኑን ጠቁመው ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡

አቶ ማናለኝ ፈረደ የተባሉ ባለአክሲዮን በበኩላቸው ባንኩ በ2014 ሒሳብ ዓመት ከ197 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉንና በዚህም ለእያንዳንዱ ባለአክሲዮን አራት በመቶ ብር የትርፍ ድርሻ መክፈሉን አውስተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህኛው ዓመት ሪፖርት 145 ሚሊዮን ብር የተጣራ ኪሳራ ባንኩ እንዳጋጠመውና በዚህም የተነሳ አንድ ሺሕ ብር የሚያወጣ የባንኩ አንድ አክሲዮን ሦስት በመቶ መክሰሩን በመግለጽ፣ ‹‹ባለፈው ዓመት ያተረፈ ባንክ በዚህ ዓመት ለምን ከሰረ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም የባንኩን የቦርድ አባላትና ፕሬዚዳንት በተመለከተ በጋዜጣ የወጣው ጉዳይ ለባለአክሲዮን በግልጽ እንዲቀርብ ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ በጉባዔው የተገኙት አቶ አበባው ካሳ የተባሉ ባለአክሲዮን፣ ‹‹አፍሪካዊ ባንክ ይሆናል የሚል ራዕይ ሰንቆ የተነሳው ባንክ በአጭር ጊዜ የምንቀየርበት የመሰለን ሰዎች ብዙ ነን፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን አንድ ተቋም ሲቋቋም የመጀመርያዎቹ ዓመታት ኪሳራ ማስመዝገቡ በቢዝነስ ዓለም የሚታወቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የዚህ ባንክ ፕሬዚዳንት የነበረ ግለሰብ ጉባዔ ሊጠራ ትንሽ ቀን ሲቀረው ለማባረር ለምን ተጣደፋችሁ? እኛንስ አያደናግረንም ወይ?›› የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

አቶ ጌታዬ ማሞ የተባሉ ባለአክሲዮን የባንኩ የበላይ ኃላፊዎች፣ ‹‹ታሪካዊ ኃላፊነት አለባችሁ ታሪካዊ ሥራ ሥሩ፣ የውስጥ ሽኩቻ በመቀነስ በኃላፊነት ካልሠራችሁ ታሪካዊ ስህተት ጥላችሁ ትሄዳላችሁ፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ማኅበረሰቡን ሊያሻግር የሚችል ሥራ እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባልና የባንኩ ባለአክሲዮን ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ባንኩ ከሰረ መባሉ ሊያጋጥም የሚችል ነው ብለዋል፡፡ አገራዊ ወቅታዊ ሁኔታና በሰፊው ቅርንጫፍ ለማስፋፋት የተሄደበት ርቀት ግምት ውስጥ መግባት እንዳለበትና በጥንካሬ ሊታይ የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ነገር የሚገንበት ግለሰብ ወይም ተቋም መኖሩን የጠቀሱት ሲሳይ (ዶ/ር)፣ ከሰሞኑ ገዳ ባንክ በተመሳሳይ 87 ሚሊዮን ብር ከሰረ ተብሎ እንደነበር ነገር ግን ይህን ያህል ሲጮህ እንዳልነበር ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የባንኩን የበላይ ኃላፊ ጠቅላላ ጉባዔው ሲካሄድ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ማንሳት የተፈለገበት ምክንያት እንዲብራራ ጠይቀዋል፡፡

‹‹የባንኩን ችግር ሁሉ ወስዶ ፕሬዚዳንቱ ላይ ከመዘፍዘፍ›› በፕሬዚዳንቱ ዙሪያ ያለው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሚና በግልጽ እንዲብራራ ጠይቀዋል፡፡

ወ/ሮ ማርታ ሀብቴ የተባሉ የባንኩ ባለአክሲዮን በየቅርንጫፉ በርካታ ቁጥር ያለው ሠራተኛ የሚቀጠር ከሆነ፣ ባለአክሲዮኖች ኪሳራ ውስጥ እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ባንኩ ገና ከጅምሩ የሚከስር ከሆነ ተጨማሪ አክሲዮን አልገዛም፣ ለምንድነው የምገዛው? እኔ እንዲያውም ቢቻል የአክሲዮን ድርሻዬ ተሰጥቶኝ ብወጣ ይሻለኛል፤›› የሚል ቅሬታ አቅርበዋል፡፡

የአማራ ባንክ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አቶ ጫንያለው ደምሴ በማብራሪያቸው በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 307 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ ዕቅድ የነበረ ቢሆንም ኪሳራ መመዝገቡን ጠቅሰው፣ በዘንድሮ የሒሳብ ዓመት ግን 437 ሚሊዮን ብር የማትረፍ ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል፡፡ ባንኩ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከፍተኛ ወጪ ያወጣበት የቤት ኪራይና የሠራተኛ ቅጥር መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይ ወጪ ቆጣቢ ፖሊሲ እንደሚከተሉ አስረድተዋል፡፡

የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታ በበኩላቸው የፕሬዚዳንቱ ከኃላፊነት መነሳት ለጉባዔ ቀርቦ የሚፀድቅ ወይም ውድቅ የሚደረግ አለመሆኑን፣ ጠቅላላ ጉባዔው ለቦርዱ በሰጠው ሥልጣን መሠረት ሠራተኞችን የመቅጠርና የማሰናበት የቦርዱ ኃላፊነት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹የቦርዱን ኃላፊነት ጉባዔ ላይ በማምጣት እገሌ ሊነሳ ነው እገሌ ሊሾም ነው የሚል አሠራር ወደፊትም አይኖርም፣ ሊኖርም አይገባም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በመሆኑም አምናችሁ የመረጣችሁት ቦርድ ባንኩን ሊመራልን ይችላል ብሎ ያመነበትን የመመደብ፣ የመቀያየር፣ የማዘዋወር ኃላፊነት አለው፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ ስህተት ከተሠራ ቦርዱ ሊጠየቅ ይችላል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አክለውም የባንኩ ፕሬዚዳንት ለምን ተነሳ የሚለው ጥያቄ ለጉባዔው የሚጠቅም እንዳልሆነ፣ ዋናው ባለአክሲዮኖች መጠየቅ ያለባቸው ከትርፍና ኪሳራው ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡

ባንኩ ኪሳራ ያስመዘገበው ከሠራተኛ መብዛትና ከቅርንጫፍ መስፋፋት ጋር መሆኑን ጠቅሰው፣ ባንኩ ከጅምሩ ሲነሳ የነበረው አስተሳሰብና በተጨባጭ በተግባር ያለው የተለያዩ በመሆናቸው አንዳንድ አካባቢዎች ባሉ ቅርንጫፎች የሰው ቁጥርና የአገልግሎት መጠን በመቀነስ ወጪ ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹በሕግና በሥርዓት ማመን እንጂ ከሕግና በሥርዓት ውጪ የሆኑ መንገዶች ለማንም አይጠቅሙም፤›› በማለት ለባለአክሲዮኖች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች