Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበመመርያና በደንብ የተገደበው የኢትዮጵያ ስፖርት ዕድገት

በመመርያና በደንብ የተገደበው የኢትዮጵያ ስፖርት ዕድገት

ቀን:

በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያላቸው ወደ 200 የሚጠጉ ስፖርቶች እንዳሉ ስፖርት ፖዲየም ይገልጻል፡፡ በኦሊምፒክ መድረክ ያሉት ስፖርቶች ደግሞ በጠቅላላው 40 ሲሆኑ፣ ከእነዚህም 32ቱ በመጪው ሐምሌ በሚካሄደው የፓሪስ 2024 ሰመር ኦሊምፒክ የሚኖሩ ሲሆን፣ ስምንቱ ደግሞ ከሁለት ዓመት በኋላ በሚላኖ ኮርቲና የ2026 ዊንተር ኦሊምፒክ ተወዳዳሪዎች ይሳተፉበታል፡፡      

አገሮች የሚስማሟቸውን ስፖርቶች የሚያስተዳድሩበት የተለያዩ ሥልቶችን ይከተላሉ፡፡ ይህም የፌዴሬሽን፣ የማኅበር፣ ወይም የኮንፌዴሬሽን አስተዳደር ሒደትን ሊመርጡ ይችላሉ፡፡

በመመርያና በደንብ የተገደበው የኢትዮጵያ ስፖርት ዕድገት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 32 የስፖርት ፌዴሬሽኖች ሲኖሩ፣ አብዛኞዎቹ በአማተሮች ይመራሉ፡፡ በአንፃሩ እነዚህ ፌዴሬሽኖች መንግሥት ባለሙያና በጀት መድቦላቸው የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፣ ዓመታዊ ውድድሮችን ከማስተናገድ በዘለለ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ውስን መሆኑን ዕሙን ነው፡፡

በተለይ በኦሊምፒክና በዓለም ሻምዮናዎች ከአትሌቲክስ በስተቀር ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግ እምብዛም ነው፡፡ በእግር ኳስም ቢሆን በአኅጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ የማጣሪያ ውድድሮች ከመሳተፍ በዘለለ አመርቂ ውጤት ሲያመጣ አይስተዋልም፡፡

ፌዴሬሽኖች ለዓመታዊ ሪፖርት ፍጆታ የሚውል እንቅስቃሴ ከማድረግ በዘለለ ብዙም ውጤታማ ሲሆኑ አይስተዋልም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በርካታ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ብቁ በሆኑ ባለሙያዎች አለመምራትና የተሻለ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች በአግባቡ የመጠቀም ክፍተት በቀዳሚነት ይነሳል፡፡ ይህም በተለይ ፌዴሬሽኖች በራሳቸው አቅም የገቢ ምንጭ ፈጥረው፣ ብቁ ስፖርተኞችን በማፍራት በዓለም አቀፍ መድረክ መሳተፍ የሚችሉ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት እንደሚገባቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ይህም በተለይ ሙያው ያላቸውና፣ ስፖርቱን ሊለውጡና ሊጠቅሙ የሚችሉ ባለሙያዎችን ወደ አመራርነት በማምጣት ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ማድረግ እንደሚገባ ይነገራል፡፡

የተለያዩ አገሮች ስፖርታቸውን ለማሳደግ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረክ ተፎካካሪ ለመሆን ውጤትን ግብ አድርገው ይሠራሉ፡፡ ለዚህም ከአገራቸው ዜጎች በዘለለ የውጭ አገር ዜጎች ሳይቀር አምጥተው ሲጠቀሙ ይስተዋላል፡፡

በአንፃሩ በኢትዮጵያ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ የትውልደ ኢትየጵያውያን ሙያን ከመጠቀም አንፃር ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ ይተቻል፡፡ ዳያስፖራው በስፖርቱ ከሚያጋራው ልምድ በዘለለ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ አቅም እንዳለው ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ጥምር ዜግነት ከማይፈቅዱ አገሮች መካከል አንዷ በመሆኗ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በስፖርቱ ሊኖራቸው ከሚችለው ድርሻ ጋር በተያያዘ ውዝግብ ሲፈጠር ይስተዋላል፡፡

ይህም ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ ሊኖራቸው ስለሚችለው መብትና ግዴታ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ቢቀመጥም ተግባራዊነቱ ላይ ግን ወጥነት እንደሚጎድለው በርካቶች ሲተቹ ይደመጣል፡፡

የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎች በትውልድ አገራቸው በተለያዩ መብቶች ተጠቃሚ ለማድረግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 270/1994 አንቀጽ 6  በዝርዝር ያስቀምጠዋል፡፡

በዚህ አዋጅ አንቀጽ 6 የተደነገገው ቢኖርም፣ የኢትዮጵያ ተወላጅነት መታወቂያ ካርድ የያዘ የውጭ ዜግነት ያለው ሰው በማንኛውም የመንግሥት ደረጃ በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ መብት እንደማይኖረው ይደነግጋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በአገር መከላከያ፣ አገር ደኅንነት ወይም በውጭ ጉዳይና መሰል የፖለቲካ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በመደበኛነት ተቀጥሮ መሥራት እንደማይችልም ያስቀምጣል፡፡

በአንፃሩ ወደ ስፖርቱ የሚመጡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ላይ ወጥ የሆነ አሠራር ባለመኖሩና የአዋጁ አፈጻጸም ክፍተት ምክንያት በተለያዩ ፌዴሬሽኖች ውዝግቦች ሲነሱ እየተስተዋለ ነው፡፡ ይህም ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ፌዴሬሽን ውስጥ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዳይመረጡ ክልከላ ሲደረግ ይታያል፡፡

‹‹አዋጁ አንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ በሙያው የስፖርት ፌዴሬሽን መምራት አይችልም አይልም፡፡ ስለዚህ የአዋጁ አፈጻጸምና አረዳድ ክፍተት አለበት፤›› በማለት ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የጁዶና ጁጂትሱ የሙያ ማኅበር የበላይ ጠባቂ ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡

ስፖርቱን ከዜግነት ጋር በማያያዝ ፌዴሬሽን ለመምራት ክልከላ መደረጉ፣ የዓለም አቀፉን የፌዴሬሽኖች ልምድ ካለመረዳት የመነጨ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡  

‹‹አንድ ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያ ዜጋ የተለያዩ ነገር ናቸው፡፡ አንድ ሰው የትም አገር ሄዶ ቢኖር ኢትዮጵያዊነቱን አይቀይርም፡፡ ማንኛውም ሰው የፈለገውን ያህል ዜግነት ቢሰጠው ኢትዮጵያዊነቱን ሊቀየር አይችልም፤›› በማለትም ያብራራሉ፡፡

ጥምር ዜግነት በብዙ አገሮች የሚተገበር ሲሆን፣ የአፍሪካ ኅብረት አንዱ ስትራቴጂ መሆኑ ይነገራል፡፡ ከ160 በላይ አገሮች ጥምር ዜግነት የሚተገበር ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ጥምር ዜግነት በሚፈቅዱ አገሮች ተከባ ትገኛለች፡፡ እነዚህም ኬንያ፣ ማላዊ፣ ማሊ፣ ሱዳንና ኤርትራ ይጠቀሳሉ፡፡

በተለይ አንድ ኤርትራዊ ሦስትና አራት የሌላ አገር ዜግነት ቢኖረው፣ ወደ ኤርትራ ሲገባ ያው ኤርትራዊ ይሆናል ይባላል፡፡ ሌላው አገር ጂቡቲ ስትሆን ጥምር ዜግነት ያለው ሰው በብሔራዊ ምርጫ መሳተፍ ይችላል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ መታወቂያ ማደስ ካልተቻለ ኢትዮጵያዊነቱን ይነጠቃል፡፡ ጥምር ዜግነት ኢትዮጵያውያንን የበለጠ የሚያቀርብ ነው፡፡ አብዛኛው ለወንጀል የተጋለጠ ነው የሚል ጥርጣሬ ቢኖርም፣ ጥምር ዜግነት ያለውን ሰው የበለጠ ለመቆጣጠር ያስችላል፤›› ሲሉ ፀጋዬ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩል ዜግነት ማለት አንድ ሰው በሚኖርበት አገር መብቶቹንና ግዴታዎቹን በዚያ አገር እንደ ተወለዱት ያገኘዋል ማለት እንጂ፣ የግለሰቡን ማንነት ይቀይራል ማለት አይደለም የሚሉ አሉ፡፡

‹‹በአሜሪካ የተወለደ ሰው ‹ከየት መጣ?› ተብሎ ሲጠየቅ፣ ከቴክሳስ፣ ከዳላስ እንደሚባለው፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊውም ‹ከኢትዮጵያዊ መጣሁ› ነው የሚለው፡፡ በአውሮፓውም ያሉ፣ ‹ከኢትዮጵያዊ መጣን› ነው የሚሉት በማለት ፀጋዬ ይናገራሉ፡፡

ስፖርት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ቢኖረውም በአሳሪ መመርያዎችና ደንቦች ስፖርቱ በተፈለገው መንገድ ማሳደግ እንዳልተቻለ ይተቻል፡፡

ከጥምር ዜግነት ጋር እንዲሁም ከትወልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በተያያዘ የሚጠቀሱ ምክንያቶች ሲኖሩ፣ ይህም የአገር ሉዓላዊነት እንዲሁም ሚስጥር አሳልፎ መስጠት በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

ከዚህም በላይ ወንጀል ሠርቶ ከኢትዮጵያ ማምለጥ ይችላል፡፡ ሌሎች አገሮች ኢትዮጵያ ላይ ጫና ያደርጋሉ ብሎ ማሰብና ኢትዮጵያን መርዳት ካልፈለገ የግድ ዜጋ መሆን አይጠበቅበትም የሚሉ አስተያየቶች ይሰጣሉ፡፡

አንድ ዜጋ አገሩን ለቆ ወደ ሌላ አገር ካመራ በኋላ የሚሄድበትን አገር ቋንቋ ተምሮ፣ በትምህርት ራሱን አብቅቶ፣ ጥሮ ግሮ ንብረት ካፈራ በኋላ፣ ከወንጀል ነፃ ሲሆን ነው ዜግነት የሚያገኘው ይላሉ፡፡

ይህም ሒደት ያስፈለገው ከሌላው የአገሪቱ ዜጋ ጋር እኩል ለመሆን እንደሆነ ይነሳል፡፡ በኢትዮጵያ በርካታ ወጣቶች ቢኖሩም በስፖርቱ መድረክ ምቹ ሁኔታ ስላልተፈጠረላቸው ብቻ ያልተገባ ቦታ ለመዋል ይገደዳሉ፡፡ ይህም በተለይ ፌዴሬሽኖች ስፖርቱን ለማስፋፋት በቂ እንቅስቃሴ ባለማድረጋቸው  የመጣ መሆኑ ዕሙን ነው፡፡

በሌላ በኩል  በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አማካይነት የሚወሰኑ ውሳኔዎች ወጥ ያለመሆናቸውንና አግላይ መሆናቸው፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለይ ስፖርቱን በገንዘብም ሆነ በሙያ እንዳይረዱ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...