Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንብ ባንክ ነባር የቦርድና ማኔጅመንት አባላት በአዲስ እንዲተኩ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በባንኩ የቦርድ አባላት መካከል መከፋፈል መኖሩ ተረጋገጠ
  • ባለፈው ሒሳብ ዓመት 1.5 ቢሊዮን ብር ማትረፉ ተጠቁሟል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በነባሩ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት መካከል፣ ጤናማ ያልሆነና የባንኩን ጥቅም መሠረት ያላደረገ መከፋፈል መፈጠሩን ጠቁሞ ፣ ባንኩ አሁን ያለበትን ችግርና ወደፊት በሥራ ላይ ሊያጋጥም የሚችልን ችግር ፣ አሁን ባለው ቦርድና ማንኔጅምንት ይፈታል የሚል እምነት እንደሌለው ተናግሮ በሌላ መተካት እንዳለበት አስታወቀ፡፡

ብሔራዊ ባንክ ይህንን ያስታወቀው፣ ታኅሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ንብ ባንክ ቀደም ብሎ ባካሄደው የዳይሬክተሮች ቦርድ አስመራጭ ኮሚቴ መካከል ተፈጥሮ በነበረው ችግር ምክንያት ዕገድ በመጣል፣ ባካሄደው ምርመራ ያገኘውን ውጤት ይፋ ባደረገበትና ቀድሞ ተመርጠው የነበሩ የንብ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት በአዲስ እንዲተኩ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስፈጻሚነት የተካሄደው የንብ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ፣ አዳዲስ የቦርድ አባላት በከፍተኛ ድምፅ ሲመረጡ፣ ከቀድሞው የቦርድ አባላት ውስጥ አንዳቸውም ሳይካተቱ መቅረታቸው ታውቋል፡፡

ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት በተለየ ሁኔታ በብሔራዊ ባንክ አስፈጻሚነት በተካሄደው የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ፣ በብሔራዊ ባንክ አስመራጭ ኮሚቴ እንዲያካሂድ ተደርጓል፡፡

አስመራጭ ኮሚቴው ከጠቅላላው ጉባዔተኛ የተጠቆሙትን 24 ዕጩዎች በመያዝ ድምፅ እንዲሰጥባቸው አድርጓል፡፡ እስከ ምሽት ድረስ በቆየው ምርጫ ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት 12 ዕጩዎች ተመርጠዋል፡፡

በምርጫው በሥራ ላይ ከነበሩት የቦርድ አባላት መካከል ዳግም ለመወዳደር ዕጩ ሆነው የተጠቆሙ ቢኖሩም፣ ለአሸናፊነት የሚያበቃ ድምፅ ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት የንብ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ ማካሄድ የነበረበትን አስመራጭ ኮሚቴ በማገድ፣ በብሔራዊ ባንክ አማካይነት እንዲካሄድ የተፈለገበትን ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለጠቅላላ ጉባዔ አሳውቋል፡፡ በዕለቱ የተደረገውንም ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በራሱ መንገድ ለማካሄድ የወሰነበትን ምከንያትና በንብ ባንክ ውስጥ በምርመራ ደርሼበታለሁ ያላቸው ጉዳዮች በዝርዝር ለባለአክሲዮኖች ቀርቧል፡፡

ለባለአክሲዮኖች በንባብ የቀረበው መግለጫ፣ በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ 24ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የባንኩን የአስተዳደር ሥርዓት አስመልክቶ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባዘጋጀ መግለጫ እንደተብራራው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀጽ 4 ከተሰጡት ቁልፍ ኃላፊነቶች መካከል፣ የፋይናስ ዘርፉን ጤናማነትና አስተማማኝነት በማረጋገጥ፣ ዘርፉ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለልማት ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ማስቻልና የገንዘብ አስቀማጮችን፣ ባለአክሲዮኖችንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ጥቅም ማስጠበቅ አንዱና ዋነኛው ኃላፊነት መሆኑን ገልጿል፡፡

የባንክ ሥራ በአብዛኛው በባህሪው በቁጠባ መልክ ከሕዝብ የሚሰበሰብ ገንዘብ በመሆኑ፣ ባንኮች በአግባቡና ጤናማ በሆነ መልኩ ለታለመለት ዓላማ ስለማዋላቸው ማረጋገጥና በዚህ ሒደት የገንዘብ አስቀማጮችን ጥቅምና መብት እንዲጠበቅ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁሞ፣ ይህንን ለማሳካት ብሔራዊ ባንክ በትኩረት ከሚከታተላቸው መካከል ባንኮች መልካም የኩባንያ አስተዳደር (Good Governance) ሥርዓትን በመዘርጋት፣ ሥራቸውን ሕግንና ጤናማ አሠራርን መሠረት ባደረገ መልኩ መሥራታቸውን ማረጋገጥ መሆኑንም አመልክቷል፡፡  

ከዚህ በተቃራኒ ባንኮች የመልካም አስተዳደር ሕጎችና መመርያዎች በሚፃረር መልኩ የሚመሩና የሚንቀሳቀሱ ከሆነ፣ ገንዘብ አስቀማጮችን ጨምሮ የበርካታ አካላትን ጥቅም አደጋ ላይ ስለሚጥል፣ ብሔራዊ ባንክ እነዚህን ጉዳዮች በቸልታ እንደማይመለከታቸውም የብሔራዊ ባንክ መግለጫ ይጠቅሳል፡፡  

‹‹ንብ ባንክ ላለፉት 24 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየና ከተለያዩ መለኪያዎች አንፃር ከፍተኛ ዕድገት በማስመዘገብ በኢንዱስትሪው ውስጥ ትልቅ ከሚባሉ ባንኮች ተርታ የተሠለፈ መሆኑ ይታወቃል፤›› የሚለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መግለጫ፣ ይሁን እንጂ ብሔራዊ ባንክ በባንኩ ላይ ባካሄደው ተከታታይ ምርመራ፣ ባንኩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ መልኩ የመልካም አስተዳደር ችግር እየተስተዋለበት ነው ይላል፡፡ የባንኩን የገንዘብ አከል ንብረት ሥጋትን (ሚስ ማኔጅመንት) ጤናማና ተገቢ በሆነ መልኩ የማስተዳደር ችግር እየገጠሙት መሆኑን ለመገንዘብ መቻሉንም በማመልከት፣ ባንኩ ምርጫውን በራሱ ለማካሄድ አለመቻሉን የሚጠቁም ነው፡፡

የባንኩ ባለአክሲዮኖች የጠራ ግንዛቤ ይኖራቸው ዘንድም የተከሰቱትን ችግሮች በዝርዝር ለባለአክሲዮኖቹ ያቀረበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ተከሰቱ ያላቸውን ችግሮች በአራት ከፍሎ አቅርቧቸዋል፡፡  

‹‹የባንኩ ቦርድ ከጠቅላላ ጉባዔ የተሰጠውን አደራ፣ እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ የኩባንያ አስተዳደርና አግባብነት ካላቸው ሌሎች ተዛማች መመርያዎች መሠረት ለአንድ ዓላማና የባንኩን ዘለቄታዊ ጥቅም መሠረት ባደረገ መልኩ ኃላፊነቱን መፈጸም ሲገባው፣ ይህ አለመደረጉ አንዱ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቦርድ አባላት መካከል ጤናማ ያልሆነና የባንኩን ጥቅም መሠረት ያላደረገ መከፋፈል ከመፈጠሩም በላይ፣ ልዩነቱ የባንኩን የዕለት ተዕለት የሥራ ክንውን ወደሚያውክበት ደረጃ መሸጋገሩን ብሔራዊ ባንክ ማረጋገጥ መቻሉን ከቀረበው መግለጫ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ቦርዱ የባንኩን የአደጋ ሥጋት (ሪስክ ማኔጅመንት) በአግባቡ ማስተዳደር፣ የማኔጅመንቱን የሥራ አፈጻጸም በመገምገም ለውጥ እንዲመጣ በማስቻልና ባንኩን ሕግ አክብሮ እንዲሠራ በማድረግ ረገድ ኃላፊነቶቹን በሚገባ መወጣት አለመቻል በመለየት፣ የታዩትን ችግሮች በመግለጫው አመላክቷል፡፡

ብሔራዊ ባንክ በዚህ መግለጫው አፅንኦት የሰጠው ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ፣ ንብ ባንክን የተመለከቱ ውሳኔዎችና የሥራ አቅጣጫዎችን እንዲሰጡ ለማስቻል፣ ባንኩ በሕግ የተቀመጠና ዕውቅና ያለው የኩባንያ አስተዳደር፣ እንዲሁም ይህንን እንዲያስፈጽሙ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት፣ ኃላፊነታቸውን መወጣት ያለመቻል መሆኑን ነው፡፡ ይህም ጉዳይ በመግለጫው ጠቅላላ ጉባዔ፣ ቦርድና ማኔጅመንት የተሰየመለት ቢሆንም፣ ከዚህ በተለየና ወጣ ባለ መንገድ የባንኩን ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች ስብስብ በሚል ስያሜ አንዳንድ ባለአክሲዮኖች በጥንቃቄ መያዝ የሚገባቸውን የባንኩንና የባንኩን መረጃዎች ባልተገባ ሁኔታ በእጃቸው እንዲገባ በማድረግና የተለያዩ መድረኮች በማዘጋጀት፣ የኩባንያውን አጠቃላይ አስተዳደርና የሥራ አፈጻጸም መገምገምን ጨምሮ፣ ሌሎች ጉዳዮችን የተመለከቱ አጀንዳዎች ላይ ስብሰባ በማድረግና አቅጣጫ በማስቀመጥ፣ ሕጋዊ የሆኑ የባንኩ አስተዳደር አካላት ሥራቸውን ገለልተኛና ካላስፈላጊ ጫና ነፃ በሆነ መንገድ እንዳያከናውኑ ችግር ተፈጥሯል በሚል አስቀምጦታል፡፡

አንዳንድ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ከባንኩ መደበኛ አሠራር ተፃራሪ በሆነ መንገድ አላስፈላጊ ጫና በባንኩ ማኔጅመንት ላይ በማሳደር፣ እንዲሁም ሌሎች አካላትን እንደ መሣሪያ በመጠቀም፣ የራስን ጥቅም ለማሳካት እየጣሩ እንደነበር የተስተዋለ መሆኑን በማመልከትም፣ የባንኩ ማኔጅመንትም የዚህ ጫና ተጋላጭ መሆኑን ስለማረጋገጡም ብሔራዊ ባንክ በመግለጫው አስታውቋል፡፡  

‹‹አንድ ባንክ አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት ከተለያዩ አካላት፣ ከደንበኞቹና ከባለአክሲዮኖች ጥቆማ፣ ወይም የቅሬታ አቤቱታ ሊቀርብበት የሚችል ቢሆንም፣ በንብ ባንክ ላይ ያለው ሁኔታ ከዚህ ወጣ ያለና ተደጋጋሚ በሚባል ደረጃ ቅሬታና ጥቆማ የሚቀርብበት ባንክ ሆኗል፤›› በማለትም፣ የታዩትን ችግሮች በመግለጫው አብራርቷል፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ የሚቀርቡ ቅሬታዎችንና አቤቱታዎችን በተመለከተ ብሔራዊ ባንክ ማጣራት እያደረገ፣ እንደ አስፈላጊነቱና እንደ እንደ አግባብነቱ ምላሽና ማስተካከያ ዕርምጃዎች እየወሰደ የሚገኝ መሆኑንም መግለጫው አስታውሷል፡፡ የእነዚህ ቅሬታዎች ባለማቋረጥ መምጣት ደግሞ የባንኩ የተረጋጋ የኩባንያ የመልካም አስተዳደርና ጤናማነቱን በተመለከተ ጥያቄ የሚያጭር ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል ብሏል፡፡ አያይዞም ‹‹በመጨረሻም በባንክ አሠራር ውስጥ የሚጠቀሱ ቁልፍና ወሳኝ ተግባራት መካከል አንድ ሊያጋጥም የሚችልን የገንዘብ አከል እጥረት ሥጋት (ሊኪውዲቲ ማኔጅመንት) ጤማና ብቃት ባለው ሁኔታ ማስተዳደር የሚያስችል ሥርዓት ዘርግቶ ተፈጻሚ ማድረግ ቢሆንም፣ ባንኩ በተለየ ሁኔታ ይህንን ተግባር ለመወጣት እየተቸገረ መሆኑን ማስተዋል መቻሉንም ከቀረበው መግለጫ መገንዘብ ተችሏል፡፡ እንዲህ ያሉ የባንኩ ችግሮች እንዲከሰቱ በመሠረታዊነት ተግባርና አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል ዋነኛው የባንኩ ቦርድና ማኔጅመንት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸው ሲሆን፣ በዚህም ባንኩ ለተለያዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሊጋለጥ መቻሉን ከመግለጫው መገንዘብ ተችሏል፡፡

ይህም በባንኩ ጤናማ አካሄድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲፈጠር ከማድረግ ባለፈ፣ የባለአክሲዮኖችን ጥቅም የሚነካ ድርጊት ሆኖ እንዳገኘው አመልክቷል፡፡ ምንም እንኳን እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ ብሔራዊ ባንክ የማስተካከያ ዕርምጃ እየወሰደና ለውጥ እየተገኘ መሆኑን በመግለጫው ጠቅሷል፡፡ ሆኖም ብሔራዊ ባንክ በቀጣይ የሚያደርገው የቦርድ ማፅደቅ ውሳኔ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ባንኩ አሁን ያለበት ችግሮችና በቀጣይ ሊሚያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን በሥራ ላይ ባሉት የቦርድ አባላትና የባንኩ ከፍተኛ አመራር ይፈታል የሚል እምነት ስለሌለውና በአዲስ መተካት ወይም መለወጥ አለባቸው የሚል ፅኑ እምነት ያለው መሆኑን ለጉባዔተኛው አስገንዝቧል፡፡

የንብ ባንክ የዳይሬክተሮች የቦርድ አስመራጭ ኮሚቴ ሲያከናውን የነበረው ዕጩዎችን የመቀበልና የመለየት ሥራን በተመለከተ፣ ብሔራዊ ባንክ ባደረገው ምርመራ፣ የኮሚቴው ኃላፊነት በብሔራዊ ባንክ ኮርፖሬት ገቨርናንስ መመርያ፣ በባንኩ የቦርድ ጥቆማና አስፈጻሚ የምርጫ ማስፈጸሚያ መመርያ፣ እንዲሁም ኮሚቴው ራሱ ለባለአክሲዮኖች ካስተላለፈው ማስታወቂያ ጥሪ ውጪ በሆነ መልኩ እንደነበር ማረጋገጥ እንደቻለ አሳውቋል፡፡

በዚህም ምክንያት ኮሚቴው የሠራው ሥራና የዕጩዎች ዝርዝር በብሔራዊ ባንክ ውድቅ እንደተደረገም አክሏል፡፡ ይህንን ተከትሎ የቦርድ ምርጫው በዕለቱ ታኅሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. በብሔራዊ ባንክ አስፈጻሚነት እንዲካሄድ ውሳኔ ሊተላለፍ እንደቻለ ገልጿል፡፡ ስለሆነም በብሔራዊ ባንክ የቀረበውን መግለጫና በባንኩ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች በመሠረታዊነት እንዲቀረፉ ማስቻል አስፈላጊነትን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ በዕለቱ በሚካሄደው የቦርድ ምርጫ በትምህርት ዝግጅታቸውና በሥራ ልምዳቸው ብቃት ያላቸውን፣ ከተለያዩ የትምህርትና የሙያ ዘርፎች የተውጣጡ ነፃና ገለልተኛ የሆኑ፣ በተለይም ከምንም በላይ የባንኩን ጥቅምና ዓላማ ዕውን ለማድረግ የሚሠሩ ዕጩ የቦርድ አባላት፣ በፍፁም የኃላፊነት ስሜት ባለድርሻዎች እንዲመረጡ ማሳሰቡንም በመግለጫው አሳውቋል፡፡

አጋጣሚን በመጠቀም አላስፈላጊ ድርጊቶችን ለመፈጸም የሚንቀሳቀሱ ካሉ ዕርምጃ የሚወስድ ስለመሆኑም ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡ ይህንንም ‹‹በዚህ አጋጣሚ የራስን ጥቅም በመሻትና በማስቀደም፣ ባንኩ በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት እንዳይሠራ የምታደርጉና ጫና ለመፍጠር የምትንቀሳቀሱ አንዳንድ ባለአክሲዮኖችና ግለሰቦች ከዚህ ድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ ብሔራዊ ባንክ በጥብቅ ያስጠነቅቃል፤›› በማለት ገልጾታል፡ የገንዘብ አስቀማጮችን ጥቅምና የፋይናንስ ሥርዓቱን ጤናማነት ለማስጠበቅ፣ ወደፊት አስፈላጊውን ሕጋዊ ዕርምጃ የሚወስድ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ በዚሁ መግለጫ አስገንዝቧል፡፡

በመግለጫው ማጠቃለያ ላይም የባንኩ ባለአክሲዮኖች በዕለቱ በሚያካሂዱት ጉባዔ ጠንቃቃና ብቃት ያለው ቦርድ መምረጥ ከቻሉ፣ ባንኩ አንጋፋነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሚጠበቅ መሆኑንም ገልጿል፡፡ ብሔራዊ ባንክ በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት ከመወጣትና ንብ ባንክ ጤናማና ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችለውን ኃላፊነቱን ከመወጣት ጎን ጎን፣ ባንኩ በሚያካሂደው ቀጣይ እንቅስቃሴ ላይ የብሔራዊ ባንክ ድጋፍ እንደማይለየውም ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡    

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለጠቅላላ ጉባዔው መግለጫውን በንባብ ካሰማ በኋላ፣ ምርጫው ተካሄዶ የምርጫ ውጤቱ ታውቋል፡፡ ሆኖም ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ ድምፅ ያላቸውን ተመራጮች ውጤት እንደገና አጣርቶ ውሳኔ የሚሰጥበት ሲሆን፣ አዲሱ ቦርድ ሥራ ሊጀምር የሚችለውም ውጤቱ በብሔራዊ ባንክ ሲፀድቅ ነው፡፡

ንባ ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስሪ ውስጥ በአንጋፋነታቸው ከሚጠቀሱ የግል ባንኮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ አሁን አጋጥሞታል የተባለው ችግር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እየወሰዳቸው ባሉ ዕርምጃዎች እንደሚፈቱ እምነታቸውን ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ እስካሁን የሄደበት መንገድም ባንኩን ካጋጠሙት ችግሮች ለማላቀቅ ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ እንደሠራም እምነት ያለ ሲሆን፣ ንብ ባንክ ወደ ቀደመው ከፍታው እንዲመለስ አዲሱ ቦርድ ብዙ ሥራ እንደሚጠብቀው ሪፖርተር ካሰባሰበው አስተያየት ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከቦርድ ዳይሬክተሮች ምርጫ ቀደም ብሎ የባንኩን የ2015 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም የተመለከተው ሪፖርት እንደሚያሳው ከሆነ፣ ንብ ባንክ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 1.97 ቢሊዮን ብር ያተረፈ መሆኑን ነው፡፡ ከታክስ በኋላ ያስመዘገበው ትርፍ ደግሞ 1.5 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ከታክስ በኋላ የተገኘው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት 168.2 ሚሊዮን ብር ወይም በ29.2 በመቶ ብልጫ አለው፡፡

በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 77 ቢሊዮን ብር መድረሱን የሚያመለክተው የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት፣ አጠቃላይ የብድር ክምችቱ 53.3 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የሰጠው ብድር 14.3 ቢሊዮን ብር መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በ19.3 በመቶ በማሳደግ 59.4 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉ ተጠቅሷል፡፡  

በሒሳብ ዓመቱ የዘጠኝ ቢሊዮን ብር ገቢ ያሰባሰበ ሲሆን፣ ይህ ገቢ ከቀዳሚው ዓመት በ27.5 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡ ንብ ባንክን ከ25 ዓመት በፊት ለማቋቋም 22 የአደራጅ ኮሚቴ አባላት ተሰባስበው የመጀመሪያውን ስብሰባቸውን በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገቡ ይጠቀሳል፡፡ በዚያም ግንቦት 19 ቀን 1991 ዓ.ም. የባንኩ በይፋ መመሥረቱ ይታወቃል፡፡

በ717 ባለአክሲዮኖች በተዋጣ 27.6 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታልና 27 ሠራተኞች ይዞ ሥራውን በይፋ የጀመረውም ጥቅምት 18 ቀን 1992 ዓ.ም. እንደሆነም የባንኩ መረጃ ያመለክታል፡፡

የ2015 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በ27.6 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ንብ ባንክ፣ አሁን ካፒታሉ ስድስት ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የባንኩ ሠራተኞች ቁጥርም ከ7,661 በላይ የተሻገረ ሲሆን፣ በመላ ኢትዮጵያ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 441 አድደርሷል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች