Sunday, April 14, 2024

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ ሥጋቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ባለፉት አምስት ዓመታት በከፍተኛ ውጣ ውረድ ውስጥ እያለፈ ባለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በትንሹ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በርካቶች ቆስለዋል፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፣ ለአገር ተስፋ የነበሩ አገር ጥለው ተሰደዋል፣ በርካታ ቢሊዮን ብሮች የሚገመት የአገር ሀብት ወድሟል፡፡

በተዛባ ትርክት ምክንያት አብረው ለዘመናት ተጎራብተው፣ ተጋብተውና ተዋልደው ቤተሰብ መሥርተው ይኖሩበት ከነበረ አካባቢ በአንድ ምሽት መሣሪያ ባነገቡ ታጣቂዎች በድንገት ተፈናቅለዋል፡፡ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ የተፈናቀሉ ዜጎች መካከል አብዛኛዎቹ ጊዜያዊ መጠለያ ካምፕ ውስጥ ሆነው ከእነ ልጆቻቸው የመንግሥትን እጅ ለዕርዳታ እየጠበቁ ሲሆን፣ የተቀሩት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተበታትነው ጎዳና ላይ ለምፅዋት ጠባቂነት ተዳርገዋል፡፡

በተለይ በዋነኝነት ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከቀድሞው ደቡብ፣ ከትግራይና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በጦርነትና በመሬት ይገባኛል ጥያቄ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በአዲስ አበባ ከተማ አዳራቸውን በጎዳና አድርገው እጃቸውን ለምፅዋት የዘረጉ ዜጎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቁጥራቸው እያሻቀበ ነው፡፡

የዚህ ችግር ሰላባ ከሆኑት ከእነዚህ ወገኖች መካከል ብዙዎቹ ችግራቸው መፍትሔ አግኝቶ፣ መንግሥት ወደ ቀዬአቸው እንደሚመልሳቸው ተስፋ እንዳላቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ አሁንም የብዙዎች ጥያቄ ሆኖ የሚነሳው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የተፈናቀሉ ዜጎች ፍትሕ አግኝተውና ተስፋቸው ለምልሞ፣ ካሳ ተደርጎላቸው፣ የደረሰባቸው የሰባዓዊ መብት ጥሰት ተጣርቶላቸውና እውነተኛ ዕርቅ ተካሂዶ ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ የፖለቲካ ፍላጎት፣ የመንግሥት ቁርጠኝነትና ለመፈጸም የሚያስፈልግ ሀብት አለ ወይ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት የጋራ ምርመራ ቡድን፣ በትግራይ ክልል በተካሄደው ጦርነት ተፈጽመዋል የተባሉትን የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ የሰብዓዊነትና የስደተኞች ሕግጋት ጥሰቶች በተመለከተ ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. የምርመራ ሪፖርት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ሁለቱ አካላት በሪፖርቱ ካስቀመጧቸው ምክረ ሐሳቦች መካከል፣ ‹‹አገሪቱ የሰብዓዊ መብቶች መርሆችን የሚያሟላ፣ ሁሉን አቀፍና ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት እንድታቋቁም›› የሚል ነበር፡፡

የፌዴራል መንግሥት ከሕወሓት ጋር ሲያካሂድ የነበረው ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በተደረገ ስምምነት በሰላም እንዲገታ ከተደረገ በኋላ፣ በታኅሳስ 2015 ዓ.ም. በፍትሕ ሚኒስቴር ውስጥ በተዋቀረ የ15 ባለሙያዎች ቡድን የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች ሰነድ ይፋ መደረጉ አይዘነጋም፡፡

የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን የቅድመ ረቂቅ ፖሊሲ ሕዝባዊ ምክክርና የግብዓት ማሰባሰብ ሥራዎችን ከየካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ሁሉንም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በማሳተፍ ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፣ በምክክሩ ወቅት በሕዝብ አስተያየት ግብዓቶች የተገኙ ዋና ዋና ግኝቶችንና የቡድኑን ምክረ ሐሳብ አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የባለሙያ ቡድኑ ግኝቶች እንደሚያመላክቱት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄዱ 58 መድረኮች ከተሳተፉ 3,391 ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ክስ የመስማትና ውሳኔ የመስጠት ተግባር ያለውና በሽግግር ፍትሕ የሚታዩ ጉዳዮችን የሚዳኝ ልዩ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም፣ ጉልህ በሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወይም ወንጀሎች ላይ ያተኮረ የክስ ሒደት ሊኖር እንደሚገባ፣ የምርመራና የክስ ሒደቶችን የሚያስተባብርና ልዩ ነፃና ገለልተኛ የምርመራና የክስ ሥራ የሚያከናውን ተቋም እንዲቋቋም ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም እውነታን የማፈላለግና የዕርቅ ሥራን ወይም ሒደትን፣ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ውክልናና ተሳትፎ ባረጋገጠ መንገድ በሚመሠረት አዲስ የእውነት አፈላላጊ ተቋም አማካይነት እንዲካሄድ፣ ከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ ባላቸው አጥፊዎች ላይ ያተኮረ የክስ ሒደት ሊኖር እንደሚገባም ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

ምሕረት የመስጠት ኃላፊነት በሚመለከት አዲስ በሚቋቋም የ‹‹ሀቅ›› አፈላላጊ ኮሚሽን አማካይነት ሊሆን እንደሚገባ፣ በመርህ ደረጃ ለሁሉም ተጎጂዎች እንደ የጉዳቱ ዓይነትና መጠን ማካካሻ መስጠት እንደሚያስፈልግ፣ የጅምላ ግድያ በተፈጸመባቸው ቦታዎች ሐውልት፣ ማስታወሻ ወይም ሙዚየም በመሥራትና የገንዘብ ካሳን በሚያካትት አግባብ ሊከናወን እንደሚገባ፣ የማካካሻ ሥርዓቱም እንደ አዲስ በሚቋቋም ኮሚሽን አማካይነት ሊመራ ይገባል የሚል ምክረ ሐሳብ መቅረቡን የባለሙያዎች ቡድን አስረድቷል፡፡ የባለሙያዎች ቡድን አባላትም ይህንኑ የተሳታፊዎች አስተያየት እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

የባለሙያዎች ቡድኑ ይህን ምክረ ሐሳብና የተሳታፊዎች የውይይት ወጤት መሠረት በማድረግ በመጪዎቹ ጥቂት ሳምንታት ረቂቅ ፖሊሲ እንደሚያዘጋጁ አስታውቀዋል፡፡ በረቂቁ ውስጥ እንዲካተቱ የቀረቡትን ገለልተኛ ተቋማትን በማቋቋምና አሁን የሚታየውን የፀጥታ ችግር በመፍታት ለፖሊሲው መፈጸም ሰላማዊ ሁኔታን ለመፍጠር የሚኖረው የመንግሥት ቁርጠኝነት፣ በሽግግር ፖሊሲው አፈጻጸም ላይ ከሚቀርቡ አስተያየቶች በአመዛኙ በብዙዎች ዘንድ ጥርጣሬና ሥጋትን ያዘለ ቁልፍ ጉዳይ ነው ተብሏል፡፡

የሽግግር ፍትሕ የጊዜ ማዕቀፍ ከየት ይጀመር ለሚለው ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እውነት ለማፈላለግ፣ ዕርቅ ለማስፈንና ካሳ ለመስጠት መረጃና ማስረጃ እስከተገኘበት ጊዜ ሊዘረጋ ይገባል የሚል ሐሳብ መነሳቱን የቡድኑ አባላት ሪፖርት ያመላክታል፡፡ ዓለም አቀፍ የመብት ተቆረቋሪ ተቋማት በአመዛኙ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጸሙ ያሏቸውንና ዓለም አቀፍ ባህሪ ያላቸውን ወንጀሎች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ ቢያቀርቡም መንግሥት ግን አልተቀበለውም፡፡

በቅርቡ ኢሰመኮና ተመድ በጋራ ባወጡት ሪፖርት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መከላከልና በኢትዮጵያ ተደጋግሞ የሚስተዋለውን አጥፊዎችን ተጠያቂ ያለማድረግ ልማድ (Culture of Impunity) እንዲያበቃ በማድረግ፣ መንግሥት ወሳኝ ዕርምጃዎችን እንዲወስድ ጠይቀዋል።

በሪፖርቱ መንግሥት የሽግግር ፍትሕ ሒደትን የሚመሩና የሚተገብሩ አካላትን፣ በተለይም እንደ የወንጀል ተጠያቂነትና እውነት የማፈላለግ የመሳሰሉ ሒደቶች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የሚያሟሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባውም አሳስበዋል። ለዚህም ሲባል የወንጀል ተጠያቂነት፣ እውነት የማፈላለግና መሰል ሒደቶችን የመምራትና የመተግበር ኃላፊነት የሚወስዱ አካላት ከፖለቲካ ጫና የፀዳ፣ ገለልተኛ፣ ተዓማኒ፣ ሕጋዊና ብቃት ያላቸው መሆናቸው በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሒደት በአመዛኙ የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ተጠያቂነትን የማስፈን ጉዳይ ሲሆን፣ በዚህ ሒደት ያለፉ አገሮች ልምድ እንደሚያሳየው ጠንካራ የምርመራና የክስ ሒደቶችን የሚያስተባብር፣ እውነታን የማፈላለግና የዕርቅ ሥራን የሚተገብር ልዩ፣ ነፃና ገለልተኛ ተቋም እንዲቋቋም ብዙዎች የሚጠብቁት በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡

አርጀንቲና እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ፈላጭ ቆራጭ ከነበረው ወታደራዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ለመቀየር በነበረው ሒደት፣ ተከታታይና ጠንካራ የሽግግር ፍትሕ ዕርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረጓ ይወሳል፡፡

በዚህ ሒደት የወንጀል ፈጻሚዎችን የሚዳኝ ፍርድ ቤት የማቋቋም፣ የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽንና የማካካሻ ፕሮግራሞችን ተጠያቂነትን ያጎለበቱ፣ ያመረቀዙ ታሪካዊ ቁስሎችን ያደረቁና ወደፊት የሚደርሱ በደሎችን ለመከላከል መሠረት መጣላቸውንና ሒደቱም በአመዛኙ ውጤታማ እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

በተመሳሳይ በካምቦዲያ እ.ኤ.አ ከ1975 እስከ 1979 በነበረው የኮሙዩኒስት አገዛዝ ዘመን፣ ለሁለት ሚሊዮን ያህል ዜጎች መገደል ምክንያት እንደሆነ በሚነገርለት ፈላጭ ቆራጭና አምባገነናዊ ሥርዓት የተከሰተውን የዘር ማጥፋት ወንጀልና ሌሎች የተፈጸሙ ወንጀሎችን ፍትሕ ፊት ለማቅረብ፣ በካምቦዲያና በዓለም አቀፍ ተቋማት ጥምረት ተቋቁሞ የነበረው ፍርድ ቤት አዝጋሚና ከፍተኛ ወጪ የመጣበት መሆኑ ይነገራል፡፡ ነገር ግን ዕርቅን በማሳካት ረገድ የነበረው እንቅስቃሴ በነበረው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሳቢያ መስተጓጎሉ አሁንም የክርክር ርዕስ ነው ይባላል፡፡

በኮሎምቢያ ለበርካታ አሠርት ዓመታት በአገሪቱ መንግሥትና ፋርክ በሚሰኘው የሽምቅ ተዋጊዎች ቡድን መካከል ሲካሄድ የነበረውን ውጊያ ለማስቆም፣ እ.ኤ.አ. በ2016 በተፈረመው የሰላም ስምምነት የተጀመረው የሽግግር ፍትሕ አፈጻጸም አሁንም በመካሄድ ላይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሒደቱ ባልተወከሉ ሲቪክ ተቋማት ምክንያት፣ በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ውስጥ ባሉ አንዳንድ ድንጋጌዎች ባልተደሰቱ የፖለቲካ ኃይሎች ተቃውሞ፣ በአገሪቱ በርካታ አማፂ ቡድኖች በሒደቱ አለመካተታቸውና በፀጥታ ችግር፣ እንዲሁም በመንግሥት የፖለቲካ ቁርጠኝነት አለመኖር ሳቢያ አሁንም ሒደቱ ሥጋት ያጠላበት መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ሒደቱ ምን ሊሆን ይችላል ተብሎ ጥያቄ የቀረበላቸው የሕግ ባለሙያውና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች (Lawyers for Human Rights) የተሰኘው ድርጅት ዳይሬክተር አቶ አመሐ መኮንን፣ ጦርነትና ሰላም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት አይሠራም ባይባልም አፈጻጸሙ ግን ውስንነት ስላለበት የታሰበውን ዓላማ ሊያሳካ አይችልም ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የሰላም ድባብ በሌለበት ሁኔታ የሽግግር ፍትሕን ለመፈጸም ከባድ እንደሚሆን፣ ውጤታማነቱንም ጥያቄ እንደሚያስነሳበት ገልጸዋል፡፡ አክለውም በሽግግር ፍትሕ ሒደት ውስጥ የሚከናወኑት እውነትን ማፈላለግ፣ መተማመንን መፍጠር፣ ተጠያቂነትን ማስፈን፣ የሕግና የተቋማት ማሻሻያ የሚባሉት ተግባራት ሰላም በሌለበት ውስጥ ሥራውን ፈታኝ እንደሚያደርጉ አቶ አመሐ አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ የሽግግር ፍትሕ ሁሉን አቀፍ ሰላምና ፍትሕ እንዲያመጣ ከታሰበ የሁሉም አካላት ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ፣ በጦርነት ውስጥ ያሉ አካላት አለመሳተፍ አሁንም ጎዶሎነትን የሚፈጥር ማነቆ ስለሆነ ሰላም በሌለበት መካሄዱ ሒደቱን ሙሉ እንደማያደርገው ተናግረዋል፡፡

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ተቋማትና ግለሰቦች በሽግግር ሒደቱ በተለይም በአገር ውስጥ ተቋማት እምነት አንደሌላቸው በመጥቀስ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ ሒደቶችና የፍትሕ አሰጣጥ ሥራዎች ገለልተኛ በሆኑ የውጭ ተቋማት መከናወን አለባቸው የሚል ሐሳብ እንዳላቸው የተናገሩት አቶ አመሐ፣ ሒደቱን በውጭ ተቋማት ለማከናወን መሞከሩ ጥቅም ቢኖረውም በዚያው ልክ የሚፈጥረው አሉታዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ለአብነትም በተለይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ በውጭ ተቋማት ይከናወን ቢባል ዓለም አቀፍ ተቋማት ሊያከናውኑ የሚችሉት የገዘፉና በመንግሥት ኃላፊዎች ዘንድ የተፈጸሙ ወንጀሎችን እንጂ፣ በአብዛኛው ሕዝብ ላይ የደረሰውን በደል ታች ወርዶ የማየትና ፍትሕ የማስፈን ጉዳይ አጠያያቂ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ጫና ሊያስከትል እንደሚችል፣ የአገር ውስጥ ተቋማት ልምድ እንዳይኖራቸውና ለቀጣዩ ሒደት ትምህርት እንዳይወሰድበት ያደርጋል ብለዋል፡፡

በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ክፍል የሰብዓዊ መብት ፕሮግራም ዳይሬክተር  አባድር ኢብራሂም (ዶ/ር) ጦርነት ባለበት አንድ አገር ውስጥ ጦርነት ሳይቆም ወደ ሽግግር ፍትሕ መግባት የማይታሰብ ጉዳይ ከመሆኑም በላይ፣ የትግራይ ክልልን ጨምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ቡድኖችና ታጥቀው ጫካ የገቡ በርካታ ኃይሎች በሒደቱ ደስተኛ አለመሆናቸውን በመጥቀስ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚከናወን ሥራ ወጤታማ እንደማይሆን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በቅድሚያ ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ሽግግር ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት አባድር (ዶ/ር)፣ አገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነት እየተናጠች ስለምትገኝና የሽግግር ፍትሕ ከግጭት ጋር አብሮ መሄድ ስለማይችል ሒደቱን የበለጠ የተወሳሰበ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጭ አርቃቂ ቡድን ዋና ሰብሳቢ ታደሰ ካሳ (ዶ/ር)  ሰላም በሌለበት ማካሄድ ይቻላል ወይ ተብሎ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ አሁን በመላው አገሪቱ የሚስተዋሉት የሰላም ችግሮች ትልቅ ማነቆ ሊፈጥሩ ይችላሉ ብለዋል፡፡

ዋና ሰብሳቢው፣ ‹‹በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ ያሉት ችግሮች የራሳቸው ተፅዕኖ እንደሚኖራቸው ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ሰላም ከሌለ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነህ ዕርቅ ማካሄድ፣ ምሕረት መስጠት፣ ስለክስ ማውራትና መፈጸም የምትችልበት ዕድል የለም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ሰላም ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ ወደ ሥራ ሲገባ ድኅረ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ያለ ኅብረተሰብ አስፈላጊ ነው የሚሉት ካሳ (ዶ/ር)፣ ይህ ባልሆነበት ወደ ሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ መግባቱ ሥራውን ፈታኝ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታዩ ግጭቶች በተጨማሪ የትግራይ ክልል በቅርቡ በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ከጅምሩ ክልሉ ተሳትፎ ያላደረገበትና በሒደቱ ላይ እምነት እንደሌለው በመግለጽ በድጋሚ እንዲታይ ጠይቋል፡፡ እንዲሁም አንዳንድ የአገር ውስጥና የውጭ ተቋማት መንግሥት  ለፖለቲካ ፍላጎት ማሟያ እንጂ፣ ፍትሕና ሰላም ለማስፈን በማሰብ የጀመረው ተግባር አይደለም ሲሉ ወቀሳ ሲያቀርቡ ይደመጣሉ፡፡

መሠረታዊውና ትልቁ የሽግግር ፍትሕ ግብ ፍትሕና ሰላም በማስፈን መካከል ያለውን ሚዛን መጠበቅ መሆኑን፣ በኢትዮጵያ የተጀመረው ሒደት ወጥ በሆነ መንገድ ፍትሕን አስፍኖ ሰላምን ማረጋገጥ ይቻላል ወይ የሚለው ጥያቄ፣ ወደፊት ይተገበራል ተብሎ በሚጠበቀው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አፈጻጸም ላይ የተመሠረተ እንደሚሆን ግን ብዙዎችን ያስማማል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -