Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኮሜርሻል ኖሚኒስ በኩል የቀጠራቸውን  ሠራተኞች ማሰናበቱ ቅሬታ አስነሳ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኮሜርሻል ኖሚኒስ በኩል የቀጠራቸውን  ሠራተኞች ማሰናበቱ ቅሬታ አስነሳ

ቀን:

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኮሜርሻል ኖሚኒስ በኩል የቀጠራቸው ከ1,300 በላይ ሠራተኞች ከሕግ አግባብ ውጪ መባረራቸው ቅሬታ አስነሳ፡፡ ሠራተኞቹ ቅሬታቸው ባለመሰማቱ ወደ ክስ ሊያመሩ መሆናቸውንም የኮሜርሻል ኖሚኒስ መሠረታዊ ሠራተኛ ማኅበር አስታውቋል፡፡ የተሰናበቱት ሠራተኞች በሹፍርና፣ በፅዳት፣ በመዝገብ ቤት፣ በረዳት ጸሐፊነት፣ በአትክልትነትና በሌሎች የጉልበት ሥራዎች የተሰማሩ እንደነበሩ ተገልጿል፡፡

ባለቤትነቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሌሎች ተቋማት የሆነው ኮሜርሻል ኖሚኒስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (ለባንኩ ሠራተኞቹን የቀጠረው) ሊቀመንበር አቶ ባህሩ መለስ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ባንኩ ያሰናበታቸው 1,378 ሠራተኞች ናቸው፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 መሠረት የውል ጊዜያቸው ሳይጠናቀቅ፣ ያለ ምንም የሥራ ካሳ የተሰናበቱ ናቸው ብለዋል፡፡

ከተሰናበቱ ሠራተኞች ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን የገለጹት አቶ ባህሩ፣ የባንኩ ውሳኔ የኑሮ ውድነቱንና አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ያላገናዘበ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከኮሜርሻል ኖሚኒስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አመራር ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ ባንኩ ባለው ፍላጎት መሠረት ሠራተኛ የመቀነስም ሆነ የመቅጠር መብት እንዳለው በውይይት ወቅት ቢነገራቸውም፣ ማኅበሩ ግን ቅነሳው ከሕግ አግባብ ውጪ መሆኑን ያምናል ብለዋል፡፡

ጉዳዩ በውይይት የማይፈታ ከሆነ፣ ሠራተኞቹ ኮሜርሻል ኖሚኒስን ለመክሰስ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

እንደ ሊቀመንበሩ ገለጻ ጥያቄው ‹‹ሠራተኞቹ ለምን ከሥራ ተሰናበቱ?›› የሚለው እንዳልሆነ፣ በአዋጅ በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት ውሉ ሳይጠናቀቅ የሚሰናበት ሠራተኛ የሥራ ካሳ ሊከፈለው እንደሚገባ የሚገልጽ  ቢሆንም ይህ ሳይተገበር መቅረቱ ነው፡፡

ከተሰናበቱት ሠራተኞች መሀል አንዳንዶቹ ገና ከወለዱ ሦስት ወራት ያልሞላቸው አራስና ነፍሰ ጡር እናቶች መሆናቸውን ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ማኅበሩ በሕግ መሠረት መክሰስ የሚገባው የኮሜርሻል ኖሚኒስን መሆኑን፣ ይህም የሚሆነው ችግሩ በአፋጣኝ በውይይት የማይፈታ ከሆነ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅሬታቸውን በደብዳቤ ከማስገባት በተጨማሪ፣ የባንኩን ኃላፊዎች በአካል ለማግኘትና ለመወያየት ያረጉት ጥረት አለመሳካቱን ገልጸዋል፡፡

የማኅበሩ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አዘዘው አጥላው በበኩላቸው፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራሮች በሠራተኞች ላይ ለተፈጸመው በደል በተደጋጋሚ ቅሬታ ቢቀርብም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም ብለዋል፡፡

‹‹በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብ ባንኩ የሠራተኛ ቅነሳውን ለተወሰኑ ቀናት ያቆመ ቢሆንም፣ ከቀናት በኋላ ቅነሳውን ቀጥሎበታል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

የተቀነሱት ሠራተኞች ነሐሴ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ከኮሜርሻል ኖሚኒስ ጋር ውል የገቡ መሆናቸውን የገለጹት ምክትል ሊቀመንበሩ፣ ውሉ የሚያበቃው ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አዋጁ ለሠራተኞች ከሰጣቸው መብቶች አንዱ ከውል በፊት የትኛውም አሠሪ ተቋም ቀድሞ ውል ካቋረጠ፣ የሥራ ካሳ ሊከፍል እንደሚገባ እንደሚደነግግ ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ባንኩ ሠራተኞችን ሲያሰናብት የትኛውንም የአዋጅ ወይም የሕግ አግባብ የተከተለ እንዳልሆነ አክለዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ከኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽንና ከቱሪዝምና ሆቴሎች ጠቅላላ አገልግሎት ሠራተኛ ማኅበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽንና ከሕግ አማካሪዎች ጋር ውይይት እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ ይህም ውይይት ተገቢውን የሕግ ሥርዓት በመከተል ወደ ክስ ለማምረት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የኮሜርሻል ኖሚኒስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ኮማንደር ጥላሁን ፀጋዬ፣ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሠረት የአንድ ተቋም ሠራተኛ በማስጠንቀቂያና ያለ ማስጠንቀቂያ ሊሰናበት ይችላል ብለዋል፡፡

ይህም የሚወስነው በአገልግሎት ተቋማት ፍላጎት መሠረት እንደሆነ የጠቆሙት ኮማንደሩ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሠራተኛ ቅነሳም በሕግ አግባብ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባንኩ ከተሰናበቱ ሠራተኞች ጋር ግንኙነት እንደሌለውና ማኅበሩ በቀጥታ ቅሬታ ማቅረብ ያሉበት ለኮሜርሻል ኖሚኒስ ነው ብለዋል፡፡

‹‹በዚህ መሠረት እስካሁን ለኮሜርሻል ኖሚኒስ የመጣ ቅሬታ የለም፣ ነገር ግን በወሬ ደረጃ ሰምተናል፤›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ከሥራ ተሰናብቻለሁ ብሎ የመጣ ግለሰብም ሆነ ማኅበር ባለመኖሩና ቅሬታ ባልቀረበበት አግባብ በጉዳዩ ላይ መልስ ለመስጠት እንደሚቸገሩም ተናግረዋል፡፡

ተሰናባች ሠራተኞች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ቅሬታ የማቅረብ ሕጋዊ ምክንያት እንደሌላቸው፣ ነገር ግን ኮንትራት ካላቸው በኮሜርሻል ኖሚነስ ላይ ማቅረብ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

የቱሪዝም፣ ሆቴሎችና ጠቅላላ አገልግሎት ሠራተኞች ማኅበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው አበበ፣ ጉዳዩን በሕግ አግባብ ለመፍታት በጋራ እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከየትኛውም ድርጅት ሠራተኞች የሥራ ውላቸው የሚቋረጥበት አስገዳጅ ሁኔታ ተፈጥሮ ለመቀነስ ቢታሰብ እንኳ፣ የሕግ አግባብነትን ተከትሎ ቅነሳ መድረግ እንደነበረበት ገልጸዋል፡፡ ለፌዴሬሽኑ በደረሰው መረጃ መሠረት ከተሰናበቱት ሠራተኞች ውስጥ አራስ እናቶች አሉ ብለዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ የተሰናበቱ ሠራተኞች ቁጥርና ሌሎችም መረጃዎች በማሰባሰብና ትክክለኛ ሁኔታውን በማጣራት ላይ እንደሚገኙ፣ ከተጠናቀቀም በኋላ ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድ በሒደት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት ከኮሜርሻል ኖሚነስ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ አስፋው፣ በውይይቱ መሠረት ኃላፊዎቹ ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው መናገራቸውን ጠቁመዋል፡፡

የተጻፉ ደብዳቤዎች ሲታዩ ኮሜርሻል ኖሚኒስ የሠራተኛ ቅነሳ ያደረገው፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በመሆኑ፣ የተቀነሱትን የሠራተኞች ቁጥር አጣርቶ ሲያጠናቅቅ ወደ ሕግ ለማምራት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

በሕግ መሠረት ቀጣሪ ድርጅቶች ሠራተኛ የመቀነስ አስገዳጅ ሁኔታ ቢገጥማቸው እንኳን፣ ቅድሚያ ማን እንደሚቀነስና ሌሎች ደረጃዎች እንዳሉት ጠቁመዋል፡፡

አቶ አስፋው ፌዴሬሽኑ ምንም እንኳን ከባንኩ ኃላፊዎች ጋር ያልተነጋገሩ ቢሆንም፣ ‹‹ሠራተኞቹን በሚመለከት ከኮሜርሻል ኖሚኒስ ጋር ተወያይተናል፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የሚገኙ ኃላፊዎችን በስልክ ለማግኘት ጥረት ቢደረግም አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...