Sunday, April 14, 2024

ሦስት አሥርት ዓመታትን ከፈጀው የሶማሌላንድ የዕውቅና ጥያቄ ጀርባ ድንገት የተገኘችው ኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሪፖርተር ጋዜጣ የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማ በሶማሌላንድ ተገኝቶ ያኔ የአገሪቱ ገዥ ፓርቲ የነበሩትንና የመንግሥትነት ሥልጣንን ለመረከብ ጥቂት ወራት ብቻ የቀራቸውን የዛሬውን የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የማነጋገር ዕድል አግኝቶ ነበር።

ከሪፖርተር ጋር የአሁኑ የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ከሙሴ ቢሂ አብዲ በወቅቱ አድርጎት በነበረው አጭር ቆይታ፣ ከሶማሊያ ተገንጥላ የራስ ገዝ አስተዳደር ከመሠረች ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረችው ሶማሌላንድ እንደ አገር ዕውቅና ለማግኘት ፅኑ ፍላጎትና ጥረት ብታደርግም፣ ሊሳካ ያልቻለበት ምክንያት ላይ ያተኮረ ነበር።

የአሁኑ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ በወቅቱ በሰጡት ምላሽ የተለያዩ ምክንያቶችን የደረደሩ ቢሆንም፣ በዋናነት ግን ጣታቸውን ኢትዮጵያ ላይ ቀስረው ነበር።

ሦስት አሥርት ዓመታትን ከፈጀው የሶማሌላንድ የዕውቅና ጥያቄ ጀርባ ድንገት የተገኘችው ኢትዮጵያ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሶማሌላንድ እንደ ነፃና ራሷን የቻለች አገር እንዳትታወቅ ካደረጓት መካከል ዋነኞቹ ጎረቤቶቿ ናቸው፣ ‹‹በተለይም ኢትዮጵያ›› ሲሉ ምላሽ የሰጡት የአሁኑ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ በዋነኛነት ኢትዮጵያን የወቀሱበትን ምክንያትም አስረድተው ነበር።

‹‹ኢትዮጵያ የአካባቢው ታላቅ (Big Brother) ናት። ሶማሌላንድ ዕውቅና እንድታገኝ ከፍተኛ ሚና መጫወት የነበረባት ቢሆንም፣ የተለያዩ ምክንያቶችን በመሰንዘር ሶማሌላንድን ከማገዝ ትሸሻለች፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ምላሽ ሰጥተው ነበር።

ኢትዮጵያ እንደ አካባቢው ኃያልነቷ ማድረግ የሚገባትን ለማድረግ ካልፈለገችባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ፣ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ያለው የቆየ ጠላትነት ዳግም ያገረሻል የሚል ሥጋት መሆኑን ያስረዱት ሙሴ ቢሂ፣ ኢትዮጵያ የሶማሌላንድ የዕውቅና ጥያቄ ከማገዝ የምትሸሽባቸው ምክንያቶች መካከል፣ ሌላኛውና በኢትዮጵያ መንግሥት በግልጽ የተነገራቸው የአፍሪካ ኅብረት ዋና ጽሕፈት ቤት፣ በአዲስ አበባ መገኘቱ እንደሆነም በወቅቱ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ አስረድተው ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት (በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ይመራ የነበረው) ለሶማሌላንድ የዕውቅና ድጋፍ ጥያቄ በተደጋጋሚ ይሰጥ የነበረው ምክንያት፣ ‹‹ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ ኅብረት መቀመጫነቷ በአፍሪካ ጉዳዮች ገለልተኛ መሆን አለባት፤›› የሚል እንደሆነ ሙሴ ቢሂ በወቅቱ ተናግረዋል።

አክለውም፣ ኬንያና ጂቡቲም ‹‹ለሶማሌላንድ ዕውቅና በመስጠት የመጀመርያ አገር መሆን አይፈልጉም፤›› ያሉት የአሁኑ የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ፣ ሌላኛውና ለሁሉም መሠረታዊ ነው የሚሉት ምክንያት ደግሞ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች የመገንጠል ጉዳይን በፍርኃት መራቃቸው ነው። ‹‹እውነቱ ይህ ነው። እንኳን ሌላው አፍሪካዊ አገር የመገንጠልን መብት በሕገ መንግሥቷ የጻፈችው ኢትዮጵያ እንኳ የመገንጠል ጉዳይን ትፈራለች፣ በሩቁ ትሸሸዋለች፤›› ሲሉ ተናግረው ነበር።

ይህ ሁኔታ መቀየር አለበት ብለው በጽኑ እንደሚያምኑና ሶማሌላንድ ዕውቅና አግኝታ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የምትታወቅ ነፃ አገር እንድትሆን ማድረግ የፕሬዚዳንትነት መንበሩን ከተረከቡ በኋላ የሚኖረው የሥልጣን ዘመናቸው ዋነኛ አጀንዳ እንደሚሆን ገልጸው ነበር።

ይህንን በተናገሩ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እ.ኤ.አ. በመጋቢት 2018 ላይ የበርበራ ወደብን ለማልማት ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የረዥም ዓመታት የውል ስምምነት ያደረጉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የዚህን ስምምነትን ፖለቲካዊ አንድምታ በቅርበት በመከታተል ጫና ለማሳደር በመሞከሯ ስምምነቱ በድጋሚ በመከለስ የሶማሌላንድ ድርሻ እንዲስተካከል ተደርጎ ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ ላይ የ19 በመቶ ድርሻ እንድታገኝ መወሰኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት በስምምነቱ መሠረት የሚጠበቅበትን የ19 በመቶ ድርሻ መዋጮ ባለማድረጓ እስከ ቅርብ ወራት ድረስ በበርበራ ወደብ ላይ የባለቤትነት መብትን ሳታገኝ ቆይታለች።

ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ ላይ የተፈቀደላትን የ19 በመቶ ድርሻዋን ለመያዝ ያልፈለገችው ጉዳዩ ከሶማሊያ የፌዴራል መንግሥት ጋር ሊያጋጫት እንደሚችል በመሥጋት ሲሆን፣ በወቅቱም ኢትዮጵያ የስምምነቱ አካል የመደረጓ ዜና ሲሰማ ከመቋዲሾ መንግሥትና የማዕከላዊ ሶማሊያ የፖለቲካ ልሂቃን የተቃውሞ ድምጾችን ሲያሰሙ እንደነበር ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ያስታውሳሉ።

በማሳያነትም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ሶማሌላንድ በርበራ ወደብን ለማልማት ስምምነት ከመፈጸማቸው አንድ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ከሌሎች የኢጋድ አባል አገሮች መሪዎች በተለይም ከኬንያ ጋር በመሆን በሶማሊያ የፌዴራል መንግሥት ሥርዓትን ብሎም ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት እንዲመሠረት አበክራ እየሠራች እንደነበር እነዚሁ ቅርበት ያላቸው ዲፕሎማቶች አስታውሰዋል።

እ.ኤ.አ. በ2017 ወደ ሥልጣን የመጡት የቀድሞው የሶማሌ ፕሬዚዳንት መሐመድ ፋርማጆ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በአዲስ አበባ ተገናኝተው ስለሁለቱ አገሮች ትብብርና ግንኙነት ከተወያዩ በኋላ የጋራ መግለጫ ሰጥተው ነበር። በወቅቱ መግለጫውን የታደሙ የሶማሊያ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሊያ ክልላዊ መንግሥታት ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ተገቢነትን የተመለከተ ጥያቄ አቅርበውላቸው ነበር። 

የቀደሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም በወቅቱ በሰጡት ምላሽ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ፈቃድ ሳትጠይቅ ምንም ዓይነት ግንኙነት ከሶማሊያ ክልላዊ መንግሥታት ጋር አድርጋ እንደማታውቅ ገልጸዋል።

አክለውም፣ የሶማሊያ የውጭ ግንኙነትን የመምራትና ሶማሌ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን የማስከበር ኃላፊነት ያለው ብቸኛው አካል የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት መሆኑን አስረድተዋል።

‹‹ያለ እኔ ፈቃድ ማንኛውም አገር ከኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥታት ጋር ግንኙነት እንዲያደርግ እንደማልፈቅደው ሁሉ፣ የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ፈቃድ ሳይሰጥ ከሶማሊያ ክልላዊ መንግሥታት ጋር ግንኙነት መፍጠር የአገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጣስ እንደሆነ በግልጽ እረዳለሁ›› ያሉት ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ‹‹ኢትዮጵያን ጨምሮ ማንኛውም የውጭ መንግሥት ከሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ፈቃድ ሳያገኝ፣ ከሶማሊያ ክልላዊ መንግሥታት ጋር ግንኙነት ማድረግ አይችልም›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተው ነበር።

ሶማሌላንድ ዕውቅና እንድታገኝ ማድረግ የሥልጣን ዘመናቸው ዋነኛ ግብ መሆኑን ለሪፖርተር የገለጹት የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ፣ ያቀዱትን ለማሳካት የቀራቸው የሥልጣን ዘመን በወራቶች ዕድሜ ብቻ የሚቆጠር ነው። ይሁን እንጂ በቀራቸው ጥቂት ጊዜ ውስጥ ትልማቸውን ለመፈጸም ወይም መሠረቱን ለመጣል በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ጥረት ውስጥ ናቸው።

ሶማሌላንድና የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ቀደም ሲል ጀምረውት በነበረው የሁለትዮሽ ውይይት ለመፍታት ስምምነት ተፈራርመዋል። ሁለቱ ወገኖች በጂቡቲ ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ ሸምጋይነት ለሁለት ቀናት ውይይቶችን ካካሄዱ በኋላ እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 29 ቀን 2023 ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊዊ መንገድ ለመፍታት ስምምነት ተፈራርመዋል። በጂቡቲው ስምምነት መሠረት ሁለቱ ወገኖች በድርድር ፍኖተ ካርታ ላይ እንዲሁም በ30 ቀናት ውስጥ ውይይት ለመጀመር የተስማሙ ሲሆን፣ በፀጥታና የተደራጁ ወንጀሎችን በመዋጋት፣ በግጭት ቀጣናዎች ሰላምና መረጋጋት ላይ በጋራ ለመሥራት ጭምር የተግባቡት ነው። የስምምነት ፊርማው የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድና የሶማሌላንድ መሪ ​​ሙሴ ቢሂ አብዲ በተገኙበት የተፈጸመ ነው።

ይህ ስምምነት በተፈረመ በሦስተኛው ቀን ወደ ኢትዮጵያ ያቀኑት የሶማሌላንዱ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 1 ቀን 2024 ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ጋር ሁለቱን አገሮች በትብብር ለማልማት እንዲሁም ሁለቱም የጋራ ሰላማቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።

በመግባቢያ ስምምነቱ ዋና ዋና ይዘቶችን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ‹‹ሶማሌላንድ ለኢትዮጵያ ወታደራዊ ካምፕ የምታቋቁመበት የባህር መዳረሻ በሊዝ ለመስጠት ፈቅዳለች። የበርበራ ወደብን ደግሞ ኢትዮጵያ ለንግድ አገልግሎት በስፋት እንድትጠቀምና መሠረተ ልማቶችን እንድታለማ ተስማምታለች፤›› ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቀደም ብሎ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በኢትዮጵያ አየር መንገድም ሆነ በኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ ለሶማሌላንድ ድርሻ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለምታገኘው ወታደራዊ ካምፕ የምትከፍለው የ50 ዓመት የሊዝ ክፍያ መጠን ምን ያህል ነው የሚለውና ሶማሌላንድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወይም በኢትዮ ቴሌኮም የሚኖራት ድርሻ በቀጣይ በሚካሄድ ዝርዝር ውይይት እንደሚወሰንም ተናግረዋል።

የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሄ አብዲ በይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ደግሞ፣ ‹‹የሶማሌላንድ ሪፐብሊክ መንግሥትና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ ሪፐብሊክ በይፋ ዕውቅና የምትሰጥ ሲሆን ሶማሌላንድ ደግሞ ለኢትዮጵያ ለባህር ኃይል አገልግሎትና ለንግድ አገልግሎት የሚውል ባህር መዳረሻ ለ50 ዓመታት በሊዝ ሰጥታለች፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ የዕውቅና ጥያቄ ጀርባ መገኘት 

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው አንድ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት፣ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የጀመረችው ጥረት ተገቢነት ያለው፣ ወቅታዊና ቋሚ የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ መሆን እንደሚገባው ያምናሉ። ይሁን እንጂ፣ ይህንን የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ትልቅ ጥንቃቄና በየወቅቱ በሚደረግ ጥልቅ ትንታኔ መታገዝ እንዳለበት ይገልጻሉ።

‹‹ነገር ግን አሁን የተካሄደበት መንገድ በጥልቅ ትንታኔና በጥንቃቄ ያልተመራ እንዲሁም ቅደም ተከተሉን ያልጠበቀ ነው፤›› ይላሉ።

ኢትዮጵያ ይህንን የመግባቢያ ሰነድ ከሶማሌላንድ ጋር ስትፈራረም የአፍሪካ ኅብረት የተመሠረተበት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ላይ የተቀመጠውን የኅብረቱ አባል አገሮች በማናቸውም የአፍሪካ አገሮች ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሊጠብቁ ይገባል የሚለውን መርህ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር አንቀጽ 2(4) እና አግባብነት ያለው የመንግሥታቱ ድርጅት ውሳኔ ቁጥር 2625 መጣሷን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቀደም ሲል የስምምነቱን ይዘት አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ ውስጥ ያልገለጸውን የሶማሌላንድ የዕውቅና ጉዳይ ጫና ሲበረታበት ባለፈው ረቡዕ ባወጣው ተጨማሪ መግለጫ ውስጥ አካቶ ማቅረቡን ዲፕሎማቱ ገልጸዋል። ይህም ሒደቱ በጥልቅ ትንታኔና ልምድ ባካበቱ የአገሪቱ ጉምቱ ዲፕሎማቶች ያልተመከረበት ስለመሆኑ ዓይነተኛ ማሳያ ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጣው ተጨማሪ ማብራሪያ የሚሰጥ መግለጫ ላይ፣ ‹‹ሶማሌላንድ ዕውቅና ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ለመያዝ በማሰብ ጥልቅ ግምገማ እንዲያካሂድ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች በመግባቢያ ስምምነቱ ሰነድ ውስጥ ተካተው ይገኛሉ፤›› የሚል መልዕክት ሰፍሯል።

ይሁን እንጂ ‹‹ሶማሌላንድ ዕውቅና ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ላይ አቋም ለመያዝ›› የሚለው አገላለጽ ምን ማለት እንደሆነና ይህ ከስምምነት ተግባራዊነት ጋር የሚኖረውን ቁርኝት እንደማያስረዳ ዲፕሎማቱ ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ ዕውቅና ስትሰጥ በምትኩ ሶማሌላንድ ለኢትዮጵያ ባህር ኃይል መቀመጫ የባህር ሠፈር በሊዝ እንደምትሰጥ የአገሪቱ ባለሥልጣናት በይፋ እየተናገሩ መሆኑን የጠቀሱት ዲፕሎማቱ፣ ኢትዮጵያ ዕውቅና ሳትሰጥ በስምምነቱ የተፈቀደላትን ጥቅም ለማግኘት እንደማትችል አስረድተዋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ተጨማሪ ማብራሪያዎችን አካቶ ባወጣው በዚህ መግለጫ ውስጥ ‹‹ከሰማሌላንድ ጋር በተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ የትኛውም ወገን ወይም አገር አይነካም። እንዲሁም በመግባቢያ ሰነዱ ምክንያት የተሸረሸረ መተማመን ወይም የተጣሰ ሕግ የለም›› በማለት ያስተላለፈው መልዕክት ስምምነቱን ተከትሎ የበረታበትን ውግዘትና ጫና ለማርገብ የቀረበ እንደሆነ መረዳት ይችላል ሲሉም ዲፕሎማቱ አስረድተዋል።

በአጠቃላይ ይህ ጉዳይ ተቋማዊ በሆነ መንገድ እንዳልተመራ የገለጹት እኚህ ዲፕሎማት፣ አጠቃላይ ሒደቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተይዞ መመራቱን ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የረዥም ዓመታት ልምድና ዕውቀት ያላቸው ዲፕሎማቶች የመከሩበት አይመስልም። እንዲያውም ስምምነቱ ከተፈረመና ለሕዝብ ይፋ ከተደረገ በኋላ ጉዳዩን የመሩት ሰዎች በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተገኝተው ለዲፕሎማቶችና ለተቋሙ ሠራተኞች ስለይዘቱ ማብራሪያ መስጠታቸውን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በዚህ የመግባቢያ ስምምነት ዙሪያ ዓርብ ማምሻውን እንደመከረበትና የባህር በር ጉዳይ የፓርቲውም አጀንዳ በመሆኑ እንደሚደግፈው፣ ነገር ግን እንዲህ ያሉ የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳዎች በጥንቃቄና በጥልቅ ትንታኔ ሊመሩ ይገባል የሚል አቋም መያዙን ሪፖርተር ከውስጥ ምንጮቹ ለማረጋገጥ ችሏል።

እንዲህ ያሉ የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳዎች በሚተገበሩበት ወቅ ሥጋትና ጫና መፈጠሩ የማይቀር መሆኑን የገመገሙ የኢዜማ ትይይዩ ካቢኔ እንደዚህ ያሉ ሥጋቶችን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነትና በጋራ ሆኖ መወጣት አለበት የሚል አቋም መያዙን ነገር ግን የመግባቢያ ሰነዱ ዝርዝር ይዘት በይፋ ያልተገለጸ በመሆኑ፣ ኢዜማ ፓርቲም መግለጫ ማውጣት ተገቢ ሆኖ እንዳለገኘው የውስጥ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ለአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኢቢሲ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ ሶማሊያና ሶማሌላንድ ተነጋግረው ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ እንዲሁም በሶማሊያ ሰላምን ለማጽናት ኢትዮጵያ ብዙ ጥረት ስታደርግ መቆየቷንና በዚህም ጥረት የሕይወት ዋጋ ጭምር መክፈሏን አስታውሰው፣ ከዚህ የበለጠ ተጨማሪ ዕገዛ ለማድረግ እንድትችል ኢትዮጵያ ራሷ በእግሯ መቆምና ህልውናዋን ማስጠበቅ አለባት ብለዋል።

የተሰሙ የተቃውሞ ድምጾችና ጂኦፖለቲካዊጋቶች

የሶማሊያ የማስታወቂያ ሚኒስትር ዳውድ አዌይስ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በሶማሊያ ሕዝብ ስም ሊደረጉ የሚገባቸው ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን የመፈጸም ኃላፊነት ያለው ማዕከላዊ መንግሥት፣ በሶማሌ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ውስጥ መኖሩ ይታወቃል። ይህ እየታወቀ ከሶማሌላንድ ክልላዊ መንግሥት ጋር ዓለም አቀፍ ስምምነት መፈረም፣ ዓለም አቀፍ የሕግ ጥሰትና የሶማልያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለመናድ የተደረገ ጥቃት ነው ብለዋል። 

በዚህም ምክንያት የሶማሊያ መንግሥት የተፈረመውን ስምምነት ውድቅ ያደረገ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ከፀብ አጫሪ ድርጊቱ እንዲቆጠብ አስጠንቅቋል። በተጨማሪም የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ማለትም ተመድ፣ የአፍሪካ ኅብረት የተቋቋሙበትን ዓለም አቀፍ ሕግ የማስከበር ተልዕኮ ተንተርሰው ጉዳዩን እንዲመለከቱትና የሶማሊያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንዳይጣስ ዕርምጃ እንዲወስዱ አሳስበናል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ኢትዮጵያ ስምምነቱን ተግባራዊ አደርጋለሁ የምትል ከሆነ፣ የሶማሊያ መንግሥት ሉዓላዊነቱንና የግዛት አንድነቱ እንዳይደፈር ያደርጋል። ከማንኛውም አገር ጋር ወደ ግጭት መግባት አንፈልግም፣ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ይፈታል ብለን እናምናለን። ይህ ካልሆነ ግን ማንኛውንም አማራጭ በመጠቀም የሶማሊያ ሉዓላዊ ግዛት እንዳይደፈር ከማድረግ ውጭ አማራጭ የለንም።

ሶማሌላንድ ከሶማሊያ ጋር የሚኖራትን ግንኙነት በተመለከተ እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ ውይይት ሲደረግ የቆየ ቢሆንም በስምምነት የተጠናቀቀ ጉዳይ የለም። ባለፈው ዓመት ወደ ሥልጣን የመጣው የሶማሊያ መንግሥት ይህንን ውይይት ከቆመበት በማስቀጠል መፍትሔ ለመስጠት በማለም ከሶማሌላንድ መሪዎች ጋር በጅቡቲ ወይይት ባደረገ በቀናት ልዩነት ነው ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነቱን የተፈራረመችው። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ እጇን በማስገባት የሶማሌላንድ ጉዳይ በውይይት ሰላማዊ መፍትሔ እንዳያገኝ ጥራለች የምንለው። ሶማሌላንድ የሶማሌ አካል ነች ይህንን እውነታ የሚቀይር ሕጋዊ መሠረት የለም፣ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ሕግ በመቃረን የሶማሊያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚጥስ ተግባር ፈጽማለች የምንለው። ነገር ግን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን የሶማሊያ እውነታ በመረዳትና በዚህ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ይወጣል የሚል እምነት እንዳለቸው ገልጸዋል።

የሶማሊያ የማስታወቂያ ሚኒስትር ዳውድ አዌይስ ይህንን በተናገሩበት ወቅትም በርካታ የዓለም አገሮችና በአገሮች የተመሠረቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ በኢትዮጵያና የሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነትን በመቃወም ከሶማሊያ ጎን እንደሚቆሙ በይፋ አስታውቀዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማት ሚለር በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹አሜሪካ በ1960 የድንበር መሠረት ለሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ዕውቅና ሰጥታለች፤›› ሲሉ፣ የቱርክ መንግሥት በበኩሉ ‹‹የሶማሊያ መንግሥት ሳያውቀውና ሳይፈቅድ አዲስ አበባ ላይ በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል የተፈረመው የአጋርነትና የትብብር የመግባቢያ ስምምነት ላይ የተሰማትን ሥጋት መግለጽ ትፈልጋለች። ለሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ግዛታዊ አንድነት ቁርጠኝነታችንን እናረጋግጣለን›› ብላለች።

የዓረብ ሊግ የሶማሊያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በመጣስ የኢትዮጵያ መንግሥትና የሶማሊያ አካል ከሆነችው ሶማሌላንድ ጋር የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ውድቅ በማድረግና በማውገዝ ከሶማሊያ መንግሥት ጎን መቆሙን ያሳወቀ ሲሆን፣ ግብፅ ደግሞ የሶማሊያን ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሙሉ በሙሉ ማክበር አስፈላጊነት በማሳየት የሶማሊያን ሉዓላዊነት የሚጎዳ ማንኛውንም ጥቃት እንደምትቃወም በይፋ አስታውቃለች።

የአፍሪካ ኅብረት ባወጣው መግለጫ፣ የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክን ጨምሮ የሁሉም የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሙሉ ለሙሉ ማክበር አስፈላጊ እንደሆነ አስታውቋል። በተመሳሳይ የአውሮፓ ኅብረት ባወጣው መግለጫ፣ በሶማሊያ ሕገ መንግሥት፣ በአፍሪካ ኅብረትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተሮች መሠረት፣ የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ማክበር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሶ ‹‹ይህም ለመላው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላምና መረጋጋት ቁልፍ ነው፤›› ብሏል።

በጂኦፖለቲካዊና በአፍሪካ ጉዳዮች ትንታኔያቸው የሚታወቁት መሐሪ ታደለ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ በሶማሌላንድና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ባሉ አገሮች የውስጥ፣ የጂኦፖለቲካልና የዲፕሎማሲ መልክዓ ምድሮች ላይ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ትኩረቱን ከጦርነት፣ ከረሀብና ከኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሊያዞር እንደሚችል፣ በሶማሌላንድ በኩል የስምምነቱ መፈረም ለአገሪቱ አስፈላጊ የሆነውን ዕውቅና ለማግኘት በሮችን የመክፈት ዕድል ሊያመጣ እንደሚችል፣ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ሶማሌላንድና የሶማሊያ ጦር በተማዘዙበት በላሳኖድና ሶል ግዛቶች ያለውን ግጭቶችን ሊያባብስ እንደሚችል ገልጸዋል። በሌላ በኩል የሶማሊያ የውስጥ ፖለቲካ የሶማሌላንድን የነፃነት ጥያቄ በማውገዝና የውጭ ጣልቃገብነት ተቃውሞን በማጠናከር ሥልጣን ላይ ለሚገኘው የአገሪቱ መንግሥት ተቀባይነት አዎንታዊ ፋይዳ ሊያስገኝ እንደሚችል ገልጸዋል።

የመግባቢያ ሰነዱ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮችን ሊያጦዝ እንደሚችል፣ በዚህ ውስጥም የባህረ ሰላጤው የዓረብ አገሮች በከፍተኛ ደረጃ መሳተፋቸው አይቀሬ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ተግባራዊ ከሆነ፣ የኢትዮጵያ የባህር ኃይል ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ስትራቴጂካዊ ጥቅም ጋር በሚጣጣም መልኩ፣ በቀይ ባህርና በኤደን ባህረ ሰላጤ አካባቢ የመስፈርና የመንቀሳቀስ ሁኔታን እንደሚፈጥር የገለጹት መሐሪ (ዶ/ር)፣ ይህ የጂዳው የቀይ ባህር ምክር ቤት አባል የሆኑት አገሮችን ማለትም ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ግብፅ፣ ኤርትራና የሱዳን ብሔራዊ ጦር በአንድ በኩል እንዲሰለፉ፣ ኢትዮጵያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ደግሞ በተቃራኒ አሰላለፍ ውስጥ ገብተው እንዲፋጠጡ ሊያደርግ እንደሚችል ገልጸዋል። ይህ ደግሞ በአካባቢው አደገኛ ሁኔታን ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁመዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -