Sunday, April 14, 2024

ረሃብ ያንዣበባቸው ዜጎች ፈተና

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አለቃ እምባዬ ሰርፀ ይባላሉ፡፡ ከስተው የሰለሉ እጆቻቸው ያስፈራሉ፡፡ ቢጫና ድፍርስ ሆነው የጎደጎዱት ዓይኖቻቸው በረጅሙ ዕድሜያቸው ብዙ ማየታቸውን ይናገራሉ፡፡ በምግብ እጥረትና በሕመም የሚከሰት በሚመስል ሁኔታ ሰውነታቸው ጠውልጎና ከስቶ የሚታዩት እኚህ ጎልማሳ፣ በትግራይ ክልል አበርገሌ ወረዳ የጭላ ከተማ የምግብ ዕርዳታ ያለህ እያሉ ከሚማፀኑ ሰዎች አንዱ ናቸው፡፡ ከመቀሌ ከተማ አበርገሌ ወረዳ ዋና ከተማ የጭላ ከተማ ለመድረስ 120 ኪሎ ሜትር ግማሽ ፒስታና ግማሽ አስፋልት መንገድን መጓዝ ይጠይቃል፡፡ በጦርነት የወደሙ ሽታና ጥላሸት ያለባቸው ከባድ ተሽከርካሪዎችና ታንኮች የሚታይበትን አስቸጋሪ አቧራማ ጥርጊያ መንገድ አቆራርጦ የጭላ ከተማ መድረሱ፣ አካባቢው ያለፈበትን ሰቆቃ በከፊል እንጂ በሙሉ አያሳይም፡፡ ከየጭላ ከተማ 35 ኪሎ ሜትር ተመሳሳይ ጥርጊያ መንገድ ሲጨምሩ ግን አካባቢው የተለያዩ ጉዳቶች እንደተፈራረቁበት ለመመልከት ይቻላል፡፡

ከየጭላ ከተማ ፈለገ ሕይወት ቀበሌ የሚዘልቀው መንገድ በግራም በቀኝም ክው ብለው የደረቁ ማሳዎች የሚታዩበት ነው፡፡ ከጥቅምት እስከ ጥር በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች አዝመራ ሲወቃና እህል ሲታጨድ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ግራና ቀኝ ከሚታዩ ማሳዎች ላይ ግን ባዶ ውድማዎች ብቻ ነው መመልከት የሚቻለው፡፡ ቁጥቋጦ እንኳን የሚናፈቅበት ሆኖ የሚታየው ይህ አካባቢ ሰሊጥ፣ ጤፍ፣ ማሽላና አደንጓሬ አምራች እንደሆነ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የመኸር ዝናብ በመጥፋቱ ይህ ቀበሌ የተዘራው ሳይበቅል በዚያው የቀረበት አካባቢ መሆኑን ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ፡፡

ሪፖርተር ያናገራቸው አለቃ እምባዬ፣ ‹‹ማሳችን እንደታረሰ ነው በዚያው የቀረው፡፡ ሁሉም ሰው የሚበላው ፍለጋ ተሰዶ ነው የከረመው፡፡ ትንሽ ዕርዳታ ይሰጣል ሲባል ነው ከስደት የተመለስነው፡፡ አንድ ዙር አቃምሰውናል፡፡ ተጨማሪ ዕርዳታ ይመጣል ብለን እየጠበቅን ነው፡፡ ዘላቂ መፍትሔ እንድናገኝ መንግሥት ቢረዳን፡፡ ሳምረ የሚባል ቦታ ሄጄ የጉልበት ሥራ ለመሥራት ሞክሬ ነበር፡፡ ልጆቻችንም ወንዝ ወርደው ወርቅ ፍለጋ ሲማስኑ ቆይተዋል፡፡ እዚሁ በቀዬአችን ውኃ በቦቴ መቅረብ በመጀመሩ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሆኖም የምንበላው የለምና በውጭም በአገር ቤትም ያሉ ሰዎች እንዲረዱን ነው የምንጠይቀው፡፡ በረሃብ ሰው እየሞተ ነው፡፡ ሰው ገንዘቡ ተይዞበታል፡፡ ሳር ባለመኖሩ የተነሳ ገንዘብ የሆኑት እንስሶቻችን ሞተውብናል፡፡ በጉ በሙሉ አልቋል፡፡ ፍየልና ከብቶቻችንም ሞተዋል፡፡ ሰውም ቢሆን ይታመማል፡፡ ሕክምና አይሄድም፣ ጥሩ ምግብ አይመገብም፣ በዚያው ይሞታል፡፡ አሁን የታመመው ሁሉ በረሃብ መጎዳቱ በደንብ ይታወቃል፡፡ ግን ሕመም እንጂ ረሃብ አይባልም፡፡ እኔ ራሴ ሰውነቴ መዛሉ ይታወቀኛል፡፡ ሕክምና ልሄድ ብዬ ገንዘብ አጥሮኛል፡፡ ዕርዳታው ጅማሮ ነው፡፡ ትንፋሻችን እንዳይቋረጥ የሚያደርግ እንጂ የሚለውጥ ነገር አይደለም፡፡ ሥራ አለ የሚባልበት አካባቢ ሄደን ነበር፡፡ ጉልበት ያለው በቀን መቶ ብር እየተከፈለው ይሠራል፡፡ እንደ እኔ ያለው ጉልበት የሌለው ግን ከውድማው ሄዶ ነጠላውን ዘርግቶ እህል ይለምናል፡፡ በሁለት እጅ እፍኝ እየተዘገነ ሦስት ጊዜ ይሰጠዋል፡፡ እሷን ይዞ ሕይወቱን ያቆያል፤›› በማለት ነበር አካባቢያቸውንም ሆነ እሳቸውን እየገጠማቸው ያለውን የከፋ ችግር የተናገሩት፡፡ 

አለቃ እምባዬ ‹‹የብዬ›› ሲሉ በጠሩት ባህል መሠረት በዚህ አካባቢ የቸገረው ሰው አዝመራ ወዳለባቸው አካባቢዎች ሄዶ በአካባቢው አገላለጽ ‹‹ዓውድማ ይበርክት›› እያለ እህል በመለመን ሕይወቱን ማቆየቱ የተለመደ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ዕርዱኝ ብሎ እህል የሚለምነው ሰው መብዛቱን የሚናገሩት አረጋዊው፣ አዝመራ ያላቸው ሰዎችም በዚህ ተማረው መስጠቱን እንደተው ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹አበርገሌ የጭላ አሁን የገባው ድርቅ በተለይ አምስት ቀበሌዎችን ክፉኛ ነው ያጠቃው፡፡ እግዚአብሔርን እንጃ ምን እንዳደረግን መቼም በእኛ ኃጢያት ነው የሚሆን ክፉኛ ነው የተጎዳነው፡፡ በየዓውድማው እህል የሚወቁ ሰዎች የሚለምን ሰው ሲበዛባቸው ቤት መግባት ጀመሩ፡፡ በየቤቱ ሲኬድባቸውም ስናፍስ ኑ እያሉ ይመልሳሉ፡፡ ሲታፈስ ስትሄድባቸው ደግሞ አፍሰው ይቆያሉ፣ ወይም ለሊት ያፍሳሉ፤›› ሲሉ ያከሉት አለቃ እምባዬ፣ መንግሥት ዕርዳታ ጀመረ በመባሉ ወደ ቀዬአቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡

የተከዜ ወንዝ በቅርባችሁ እያለ ለምን ተራባችሁ? ወንዙን ጠልፎ በመስኖ መጠቀም ባይቻል እንኳ ዓሳ አስግሮ ችግሩን ለመቋቋም ለምን ተቸገራችሁ ተብለው የተጠየቁት አለቃ እምባዬ ይህ እንደሚከለከል ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹ተከዜ ይጠቅመን የነበረው ግን ባልተገደበ ጊዜ ነበር፡፡ ድርቅ ሲገባ ከብቱም ሆነ ፍየሉና ሰው ወንዙ ዳር ሄዶ ሕይወቱን ያቆያል፡፡ ውኃው ብዙ ቦታ ይይዛል፡፡ እዚያው ሄዶ ለመጠቀም ውኃው ይሞላል፡፡ አሁን ልንጠቀም ብንል አይፈቀድም ነው የሚሉን፡፡ ከጦርነቱ በፊት ዓሳ ነበር፡፡ ወጣቱ ሁሉ ተደራጅቶ ዓሳ ይመረት ነበር፡፡ አሁን ግን አይፈቀድም ነው የሚባለው፡፡ ሰው ግን አደጋውን ተጋፍጦ በረሃብ ከመሞት ብሎ መግባት ጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን እሱም ማን ግባ አለህ የሚል ችግር እያመጣበት ነው፡፡ አሁን ዓሳው አይሠራም ተስፋ ቆርጠን ነው ያለን፡፡ ዓሳው ራሱ ይበላል፣ ተሸጦም እህል ያመጣ ነበር፡፡ ቢፈቀድልን ጥሩ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልል አበርገሌ ወረዳ የተከዜ ወንዝን በተለይም የተከዜ ኃይል ማመንጫ ግድብ ሐይቅን በሰፊው የሚጎራበት ነው፡፡ ከዚህ ውኃ በቅርብ ርቀት ያሉ 13 ቀበሌዎች ያሉት ወረዳው 91 ሰዎች ድርቅ ባስከተለው ረሃብ ሞተው 394 ሰዎች ለጉዳት መዳረጋቸው ታውቋል፡፡ ከ11 ሺሕ በላይ ሰዎችና ከ46 ሺሕ በላይ የቤት እንስሳት ረሃቡን ሽሽት ተሰደዋል ሲሉ የወረዳው ግብርና ቢሮ አደጋ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ክፍል ኃላፊ አቶ ኪሮስ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

ወደ ተከዜ ኃይል ማመንጫ ግድብ ማለፊያ መንገድ የሚያቋርጣቸው ስዬ፣ ተክለወይኒ፣ ፈለገ ሕይወት የመሳሰሉ ቀበሌዎች ከባድ ድርቅ እንዳጠቃቸው ታውቋል፡፡ ግርውርና ሌሎችም የወረዳው ቀበሌዎች በዝናብ እጥረት፣ በውርጭና በተባይ ጉዳት እንዳጋጠማቸው የቢሮው መረጃ ያመለክታል፡፡ በወረዳው በመኸር ወቅት ታረሰ የተባለው መሬት 19 ሺሕ ሔክታር እንደሆነና ከ403 ሺሕ ኩንታል በላይ የሰብል ምርት ተጠብቆ እንደነበር ወረዳው ይገልጻል፡፡ ይሁን እንጂ በድርቁ አደጋ የተነሳ ከ51 ሺሕ ኩንታል ብዙም ያልዘለለ ምርት ብቻ መገኘቱን ነው ያስታወቀው፡፡

በመደበኛው ጊዜ ድርቅም ሆነ ሌላ አደጋ ሳያጋጥመው ራሱን መቻል የሚቸግረውና ከዕርዳታ ተላቆ የማያውቀው ይህ አካባቢ፣ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት በድርቅ መጠቃቱ ጉዳቱን እንዳከፋው የአካባቢው ኅብረተሰብ ይናገራል፡፡ ይህ ሳያንስ አካባቢው በትግራይ ክልል በተደረጉ ጦርነቶች ወቅት ከዋነኞቹ የጦር ግንባሮች አንዱ ሆኖ መቆየቱ የችግሩን ተደራራቢነት ሁኔታውን አሰቃቂ እንዳደረገው ነው የሚገልጹት፡፡   

ሌላ አካባቢ ተወልደው ማደጋቸውንና ወደ ፈለገ ሕይወት ቀበሌ ተሞሽረው አግብተው መምጣታቸውን የሚናገሩት የ75 ዓመቷ የዕድሜ ባለፀጋ እማሆይ ወረደች ተክለ ሃይማኖት፣ ብዙ የሕይወት ውጣ ውረድን እያሳለፉ የኖሩበት አካባቢ ከድርቅና ከተረጂነት ተላቆ እንደማያውቅ ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ሊወድቅ ሲቃረብ ነው አግብቼ ወደዚህ የመጣሁት፡፡ በ77 ብቻ አይደለም ከ73 ጀምሮ ድርቅ አይቻለሁ፡፡ እዚህ አካባቢ ሁሌም በዕርዳታ ነው የምንኖረው፡፡ ዘጠኝ ልጆች ነበሩኝ፣ ከእነሱ ሦስቱ ብቻ ነው በሕይወት የቀሩት፡፡ የልጅ ልጆችን አይቻለሁ፡፡ እዚህ ቦታ ኑሮን የገፋነው ሁሌም በዕርዳታ ነው፡፡ የተሻለ የሚባል ጊዜ ዓይተን አናውቅም፡፡ በእርሻ ያየነው የተሻለ ነገር የለም፡፡ ልጆቼ ተሰደዋል፣ እኔ ብቻዬን እዚሁ ተቀምጫለሁ፡፡ የአሁኑ በጣም ጎድቶናል፡፡ በዚህ ዕድሜዬ ብዙ ነገሮችን እሠራለሁ፡፡ የልጅ ልጄ ብቻ ነው ከጎኔ ሆኖ የሚረዳኝ፡፡ በጦርነቱ የተነሳ ብዙ ሕዝብ አልቋል፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው ያለቁት፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ቁጭ ብለን ነው የምናድረው፡፡ ጥይቱ ሲንጣጣ ተሳቀን ነው ያሳለፍነው፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን አሁን ሰላም አግኝተናል፡፡ ያለፈው አልፏል፡፡ አሁን ፈጣሪ እንኳን መልሶ አፋቀረን፣ እንኳን መልሶ ሰበሰበን፡፡ ፈጣሪ ከክፉ እንዲጠብቀን ጸሎትና ልመና ያስፈልጋል፤›› በማለት ነበር እኚህ እናት ቀዬአቸው ያለፈበትንና የገጠመውን ሁኔታ ለሪፖርተር የተረኩት፡፡

በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ 28.6 ሚሊዮን ዜጎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (UNOCHA) በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡ በኢትዮጵያ 4.6 ሚሊዮን ሰዎች በግጭት፣ በድርቅና በተፈጥሮ አደጋዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል የሚለው ጽሕፈት ቤቱ፣ ይህ ሳያንስ ኢትዮጵያ 942 ሺሕ የውጭ አገር ስደተኞች ማስጠለሏንም ይናገራል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ አክሎም 20.1 ሚሊዮን ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ 4.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ይሁን እንጂ ከዚህ ፍላጎት ውስጥ ማሳካት የተቻለው ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር (ከ30 በመቶ) ያልዘለለ ነው ብሏል፡፡ በኢትዮጵያ የዕርዳታ እህል ተዘረፈ የሚል ሪፖርት ይፋ መሆኑን ተከትሎ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የረድኤት አቅርቦት ሥራዎችን አቋርጠው የቆዩ ዓለም አቀፍ ዕርዳታ አቅራቢዎች ቀስ በቀስ ሥራ እየጀመሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን በበቂ መጠን አለመሆኑ ነው የሚነገረው፡፡

በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከጦርነትና ከግጭት ተደራራቢ ቀውስ በተጨማሪ ድርቅና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ባስከተሉት ጫና ሰዎች ተርበዋል ጉዳት እየገጠማቸው ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ ከትግራይ አበርገሌ ወረዳ ጀምሮ በአፋር፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ ምዕራብና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች መድረሱን የመንግሥት መረጃም አረጋግጧል፡፡ 

ዜጎች በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ፣ እንዲሁም በአየር ንብረት መዛባት የተነሳ ለምግብ እጥረትና ረሃብ ሲጋለጡ ቆይቷል፡፡ መንግሥት የቅድመ ማስጠንቀቅ ሥርዓት በመዘርጋት ኅብረተሰቡንና ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶችን በማስተባበር በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎች የከፋ ጉዳት እንዳይገጥማቸው ሲታደግ መቆየቱ ተገልጿል፡፡ ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) የችግሩን አድማስ በሚከተለው መንገድ ነበር የዘረዘሩት፡፡

‹‹በአማራ ክልል ስምንት ዞኖች፣ በትግራይ ክልል አራት ዞኖች፣ በአፋር ክልል ሦስት ዞኖች፣ እንዲሁም በሌሎች ክልሎች የተለያዩ ኪስ ቦታዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 3.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ዙጎች የድርቅ አደጋ አጋጥሟቸዋል፡፡ በሶማሌ ክልል አፍዴርና ሊበን ዞኖች፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለይ በደቡብ ኦሞ ዞንና ዳሰነች ወረዳ፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ፣ ባሌና ምሥራቅ ባሌ፣ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃምና ማዕከላዊ ጎንደር፣ በጋምቤላ አኙዋና ኑኤር፣ ኢታንግ ልዩ ወረዳና ጋምቤላ ከተማ፣ በአፋርና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል 1.5 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ በጎርፍ አደጋ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በዚህም ወደ 125 ሺሕ ሔክታር የእርሻ መሬትና 123 ሺሕ የግጦሽ መሬት ተጎድቷል፡፡ እስከ 21,500 እንስሳት ሞት አስከትሏል፡፡ ጎርፉ የትምህርት፣ የጤናና የውኃ ተቋማትን አውድሟል፡፡ የኩፍኝ፣ የተቅማጥና የማስመለስ ሕመሞችን አስከትሏል፡፡ ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ ለጎርፍና ለድርቅ ተጎጂዎች በሦስት ዙር ዕርዳታ ማድረስ ተችሏል፡፡ ወደ አንድ ሚሊዮን 725 ሺሕ ኩንታል የዕርዳታ እህል ለተጎጂዎች ማድረስ የተቻለ ሲሆን፣ የአጋር አካላትን ጨምር ድጋፉ በገንዘብ 15.2 ቢሊዮን ነው፤›› በማለት ነው በመላ አገሪቱ አጋጠመ ያሉትን የጎርፍና የድርቅ አደጋ ለመቋቋም እየተሠራ ስለመሆኑ የዘረዘሩት፡፡

ሪፖርተር ከአንድ ወር ቀደም ብሎ በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል አጋጠመ ስለተባለው ድርቅ በሠራው ሰፊ ዘገባ፣ በአማራና በአፋር የደረሰውን ችግር አድማስ ለማሳየት ሞክሮ ነበር፡፡ በወቅቱ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በትንሹ ሦስት ወረዳዎች በከፋ ድርቅ መጠቃታቸው ይፋ ሆኖ ነበር፡፡ የበየዳ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረ ሕይወት በላይነህ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በወረዳቸው 35 ሺሕ ሰዎች በድርቁ የተጎዱ ሲሆን 17 ሺሕ እንስሳት ሞተዋል፡፡ ድርቁ ገና ያልበቀሉ፣ በመብቀል ላይ ያሉና በቅለው ፍሬ ለመስጠት የተቃረቡ ሰብሎችን ጭምር ማውደሙን ኃላፊው አረጋግጠዋል፡፡ በወቅቱ ለ2,100 ሰዎች ዕርዳታ እየቀረበ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረውም ነበር፡፡

በጊዜው በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ብቻ ሳይሆን በዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞንም ድርቅ መከሰቱ ተረጋግጧል፡፡ በዋግህምራ በአራት ወረዳዎች ሥር በሚገኙ 40 ቀበሌዎች ከባድ ድርቅ ተከስቷል፡፡ የዞኑ አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምሕረት መላኩ፣ ከ123 ሺሕ በላይ ዜጎች በድርቁ መጎዳታቸውን በወቅቱ ለሪፖርተር ነግረው ነበር፡፡

በአፋር ክልል አጋጠመ የተባለውን ድርቅ በተመለከተ በዚያው ወቅት መረጃ የሰጡት የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መሐመድ አሊ በበኩላቸው፣ ክልሉ ከአማራና ከትግራይ ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ድርቁ ማጋጠሙን ተናግረው ነበር፡፡ ዞን አራት በሚባለው የአፋር አካባቢ አራት ወረዳዎችን ጨምሮ የአማራና ትግራይ አዋሳኝ የሆኑ የጦር ቀጣና የነበሩና ዝናብ አጠር የሚባሉ አካባቢዎች መጎዳታቸውን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ አደጋው የሚባለውን ያህል አለመሆኑንና ዕርዳታም በተገቢው ሁኔታ እየቀረበ ነው ብለው ነበር፡፡ የአንበጣን መንጋና ተባይ ቢከሰትም እሱንም ቢሆን ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን አስቀድሞ ብዙ ጉዳት ሳይደርስ መከላከል መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

የአማራም ሆነ የአፋር ክልል አመራሮች ድርቁን በተመለከተ አደጋው የከፋ አለመሆኑን መስከረም መገባደጃና ጥቅምት ወር ላይ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ አስፈላጊው ዕርዳታ ስለመቅረቡም ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ቢጠየቁ ይህን ደግመው ስለመናገራቸው በእጅጉ የሚያጠራጥር ነው የሚመስለው፡፡ አማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልልን ያጠቃው የድርቅ አደጋ ጉዳቱ እየሰፋ እንደሄደ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እያመለከቱ ነው፡፡ ይህ ሦስቱን ክልሎችን ያጠቃው ድርቅ በሰሜኑ ጦርነት ክፉኛ የተጎዱ ቀጣናዎች ላይ መበርታቱ ነው የታወቀው፡፡ ጦርነትና ድርቅ ተከታትለው ባስከተሉት ጉዳትም ይህ ቀጣና ክፉኛ መጎዳቱ ይነገራል፡፡

የሁኔታው ከባድነት ሳይነገር ቢቆይም ነገር ግን በቅርቡ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጠንከር ያለ መግለጫ ነው ይፋ ያደረገው፡፡ ከሳምንት ቀደም ብሎ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ በሦስት ዞኖች ከባድ ድርቅ አጋጥሟል ብሏል፡፡ በሁለት ዞኖች ጊዜውን ያልጠበቀ ውርጭና ዝናብ የተከሰተ ሲሆን፣ በሁለት ዞኖች ደግሞ የበረሐ አምበጣና ተባይ መከሰቱን ነው ይፋ ያደረገው፡፡   

በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ክልል ያጋጠመው ድርቅ በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት እያደረሰ እንደሚገኝ እየተነገረ ነው፡፡ ከመስከረም 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በረሃብ የተነሳ 860 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን ነው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ረዳኢ ሃለፎም የተናገሩት፡፡ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከአማራም ሆነ ከአፋር ክልል አመራሮች በተለየ ሁኔታ ክልሉ አጣዳፊ ዕርዳታ እንዲደረግለት ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ከክልሉ ሕዝብ ውስጥ 91 በመቶው ለሰብዓዊ አደጋዎች የተጋለጠ መሆኑንም ተናግሯል፡፡ በትግራይ ዘንድሮ የጋጠመው ድርቅና ረሃብ ከ1977 ዓ.ም. የድርቅና የረሃብ አደጋ የከፋ መሆኑን በይፋ የገለጸው ክልሉ የውጭ ዕርዳታ ድርጅቶች ሥራ ከማቋረጣቸው ጋር ተዳምሮ የከፋ ጉዳት በሕዝቡ ላይ እንዳይደርስ፣ የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ዓለም አቀፍ ለጋሾች የሚጠበቅባቸውን የሞራል ግዴታ እንዲወጡ ነው ያሳሰበው፡፡

ይህ የትግራይ ክልል መግለጫ ግን የፌዴራል መንግሥቱን ያስቀየመ ነው የሚመስለው፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ጥሪ ተከትሎ በሁለት ቀናት ልዩነት መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ (ዶ/ር)፣ የትግራይ ክልል መንግሥት የመንግሥት ሀብትና በጀትን በንዝህላልነት ላልተገባ ወጪዎች እያዋለ ዕርዳታ የሚጠይቅበት የሞራል ድፍረቱ ሊኖረው እንደማይገባ በጠንካራ ቃላት ምላሽ ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ የተሻለ ምርታማ የሆነችበት ወቅት ላይ እንደምትገኝ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ በአንዳንዶች ግምት ባለፉት ዓመታት አገሪቱ የገጠማትን ሁኔታ የሚቃረን የሚመስልም መረጃ ሰጥተዋል፡፡   ‹‹የክረምቱ የተስተካከለ የዝናብ ሁኔታ ተጨምሮበት መልካም የሰብል ምርት የታየበት ሆኖ አልፏል፡፡ በአብዛኛው የአገራችን አካባቢዎች የመኸር ምርት ተሰብስቦ ተጠናቋል፡፡ የበጋ ግብርና ሥራዎች ተጀምረዋል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ 

ይህ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትሩ መረጃ ግን ዓምና የግብርና ግብዓት በጊዜ ባለመድረሱ አርሶ አደሮች በተለያዩ ክልሎች ለተቃውሞ አደባባይ እስኪወጡ ድረስ መማረራቸውን ያላገናዘበ ነው እየተባለ ነው፡፡ በማዳበሪያና በሌሎች ግብዓቶች እጥረት ምርታማነት በኢትዮጵያ እንደሚቀንስ ተገምቶ ሳለ ምርታማ የመኸር ወቅት አሳልፈናል መባሉ በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ አስነስቷል፡፡ በሌላ በኩል በየአካባቢው ባለው ጦርነትና ግጭት የተነሳ አርሶ መብላት ፈታኝ በመሆኑ፣ በብዙ ክልሎች የምርት ሥራ መሰናክል እንደገጠመው እየተነገረ መንግሥት ምርታማነት አደገ ማለቱ ይህን ሀቅ የሚቃረን መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡

ባለፉት ዓመታት የደረሱ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ፣ የድርቅና ጎርፍ አደጋዎችን ጨምሮ በቅርቡ ያጋጠመው ወፍ መንጋ ሁሉ በኢትዮጵያ የተስተካከለ የምርት ሥራ ማካሄድን ሲፈታተኑ መቆየታቸውን ብዙዎች ያወሳሉ፡፡ ይህ ሁሉ ከጦርነት የዞረ ድምር ጋር ተዳምሮ በአማራ፣ በአፋርም ሆነ በትግራይ ክልሎች ዘንድሮ የተከሰተው የድርቅ አደጋ ጉዳቱ የሰፋ ሊሆን እንደሚችል በርካቶች ይሞግታሉ፡፡ ይህን ፍፁም የሚቃወሙትና በተለይ በትግራይ የደረሰው ረሃብ ከ1977 ዓ.ም. የከፋ ነው መባሉን የኮነኑት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ (ዶ/ር)፣ መንግሥት ለረሃቡ በቂ ምላሽ አልሰጠም መባሉ ተቀባይነት የሌለው ስለመሆኑ በመግለጫቸው ተከራክረዋል፡፡ 

‹‹ከሰሞኑ በትግራይ ክልል ከ1977 ዓ.ም. ረሃብና ድርቅ ጋር የሚስተካከል ድርቅና ረሃብ ተከስቷል በሚል የተሰጠው መግለጫ ፈፅሞ ስህተት ነው፡፡ አንደኛ እንዲህ ዓይነት ቀውስ ሲኖር ማወጅ ያለበት በፌዴራል መንግሥት በኩል የአደጋ ሥጋት አመራር ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ መሥፈርቶችን ማዕከል በማድረግ ተገምግሞ የሚደረስበት እንጂ፣ ፖለቲካና ሰብዓዊ ጉዳይን በማያያዝ የሚወሰን አይደለም፡፡ ምክር ቤቱ በትግራይ ክልል በአራት ዞኖች ድርቅ መከሰቱን ቢያረጋግጥም፣ ከ1977 ዓ.ም. ረሃብና ድርቅ ጋር ይስተካከላል የሚል ማረጋገጫ እስካሁን አላወጣም፡፡ ሁለተኛ አጋር አካላት የዕርዳታ አቅርቦት ቢያቆሙም መንግሥት ፕሮጀክቶችን አጥፎና አስፈላጊውን በጀት መድቦ፣ ከሌሎች አካባቢዎች በተሻለና በበቂ መጠን ለትግራይ ክልል ዕርዳታ እያቀረበ ይገኛል፡፡ ሦስተኛው ሕዝብን ቀጣይነት ወዳለው የልማት ሥራ ከማስገባት ይልቅ፣ በግምገማ ስም ለወራት ስብሰባ የሚቀመጥ አመራር በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ባለሙያን በታጣቂ ስም ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት በተመደበ በጀት እየቀለቡ በምን ሞራል ነው ስለትግራይ ሕዝብ ሥቃይ መናገርስ የሚቻለው? በሕዝብ ሽፋን የሚደረግ የትኛውም ዓይነት ፕሮፓጋንዳ ተቀባይነት የለውም፡፡ መንግሥት የሰብዓዊ ዕርዳታ እህል አቅርቦትና ፖለቲካ መቀላቀል እንደሌለባቸው በፅኑ ያምናል፡፡ የሰብዓዊ ዕርዳታ ቅድመ ሁኔታ የማያስፈልገው ሰውን ያህል የተከበረ ፍጡር ከአደጋ ለመታደግ የሚሰጥ ነው፡፡ በአገራችን ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች፣ ክረምት ከበጋ የሚፈሱ ወንዞች፣ ከአጥጋቢ በላይ ዝናብ የሚያገኙ ትርፍ አምራች አካባቢዎች፣ የመስኖ ልማት መሠረተ ልማት ያላቸው ከግማሽ ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬትና በማምረት ሥራ መሰማራት የሚችል ሰፊ ወጣት ሕዝብና ዕምቅ አቅም ያለን በመሆኑ ሰብዓዊ ድጋፍን በአመዛኙ በአገር በቀልና አካባቢያዊ አቅም ለመሸፈን መረባረብ ይገባል ብሎ መንግሥት በትኩረት እየሰጠ ይገኛል፤›› በማለት ነበር ለገሰ (ዶ/ር) በመግለጫቸው ያስታወቁት፡፡

ለዚህ የፌዴራል መንግሥት መግለጫ ምላሽ የሰጡት የትግራይ ከልል ጊዜያዊ አስተዳደር የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር)፣ ‹‹ከፌዴራል አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን፣ ከክልሎችና ከፌዴራል አመራሮች ጋር ከመስከረም ጀምሮ ውይይትና የጉዳቱን አድማስ የተመለከተ ሪፖርት ሲቀርብ ነበር፡፡ በክልላችን በአምስት ዞኖች፣ በ36 ወረዳዎችና በ213 ቀበሌዎች እንደ ደረጃው ጉዳት ማጋጠሙ ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ወደ 141 ሺሕ ሔክታር መጎዳቱ፣ ወደ 114 ሺሕ ቤተሰቦች በአጠቃላይ ወደ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች መጎዳታቸው በጊዜው ቀርቦ መግባባት ላይ ተደርሷል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ እየቀረበ ያለው ዕርዳታ በቂ ካለመሆኑ ጋር ተዳምሮ ችግሩ እየበረታ መሄዱን የሚናገሩት ኃላፊው፣ ክልሉ ከ77 ረሃብ ጋር የሚነፃፀር አደጋ እየመጣ ነው ማለቱ የፌዴራል መንግሥቱን ለመወንጀል ወይም ለሌላ ፖለቲካዊ ዓላማም አለመሆኑን ተከራክረዋል፡፡

በጀትም ሆነ ዕርዳታን ክልሉ ለሌላ ዓላማ እያዋለ ነው የሚለውን ጉዳዩ ተገቢነት የሌለውና ከእውነት የራቀ እንደሆነ ነው የተናገሩት ገብረ ሕይወት (ዶ/ር) ክልሉ የሚመጣ ዕርዳታን ለተጎጂዎች እያደረሰ መሆኑን ያወሱት ኃላፊው፣ ዕርዳታ አቅራቢዎች የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ የአገር ውስጥና የውጭ ለጋሾች ራሳቸው በቀጥታ ለተጎጂዎች በመስጠት ጭምር የዕርዳታ አቅርቦቱን ማስተዳደር የሚችሉበት ዕድል ክፍት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የትግራይ ክልል ሕዝብ ያጋጠመው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ የፖለቲካ ሽኩቻውን ትቶ ለተረጂዎች ዕርዳታ ማቅረብ ይበጃል ነው ያሉት፡፡    

የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ በአካባቢ ሀብት በመጠቀም በመስኖና በሌላም ድርቅን በዘላቂነት የመቋቋም ሥራ መሥራት እንደሚበጅ በመግለጫቸው ማሳሰባቸው አይዘነጋም፡፡ ሪፖርተር ተከዜን ተጎራብቶ በሚገኘው ፈለገ ሕይወት ቀበሌ ያሉ ነዋሪዎች ይህንኑ የተመለከተ ጥያቄ አንስቶላቸው የነበረ ሲሆን፣ ትኩረት የሚሹ ነጥቦችን ከነዋሪዎቹ አንዱ እንደሚከተለው ገልጸው ነበር፡፡

‹‹የኃይል ማመንጫ ግድቡ ውኃ አይቆነጠርም ይባላል፡፡ ኃይሉ ይቀንሳል ይባላል፡፡ እኛ ውኃውን ጥለፉት ቢሉንስ በምን አቅም የለን፣ በምን ሞተር ነው የምንሠራው? ውኃው ሲወርድ በነበረ ጊዜ ፍየሉና ከብቱን እዚያው አውለን እንጠቀም ነበር፡፡ ድርጅቱ እዚህ ከመጣ በኋላ የተጠቀምነው ነገር የለም፡፡ አንድ ወፍጮ ቤት ነው በርቀት ያለን፡፡ እሱም በነዳጅ ነው፡፡ እኛ ጋ መብራት የለም፡፡ የተጠቀምነው አንድ ነገር ጥርጊያ መንገድ እዚህ መግባቱ ነው፡፡ መብራቱ ሌላ ቦታ ነው የሚሄደው፡፡ በሐይቅ ተሸፍነን የምንጠቀመው ነገር የለም፡፡ በአካባቢያችን በንብና በማር እንዳንጠቀም እንኳን ተክል የሚባል በሙሉ ደርቋል፡፡ የነበረው ቀፎ ራሱ ንቦቹ ተሰደው ባዶውን ቀርቷል፡፡ ዕጣን የሚባል እኛ አካባቢ የለም፡፡ ተፈጥሮው ደረቅ ዛፍ የሚበቅልበት ነው፡፡ ማዕድን አለ ይባላል ነገር ግን አልተፈተሸም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ገብተው ይመረምራሉ፣ ነገር ግን እስካሁን ለእኛ የመጣ ጥቅም የለም፡፡ ቦታውማ ወርቅ ነው የሚባል፤›› ያሉት ነዋሪው በአካባቢያቸው ዘላቂ ልማት እንዳልተተኮረበት ገልጸዋል፡፡

አበርገሌ የጭላ ከተማና በዙሪያው የሚገኙ እንደ ፈለገ ሕይወት ያሉ ቀበሌዎች የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የቀይ መስቀል ዓርማ የለጠፈ የውኃ ቦቴ ውኃ ሲቀርብላቸው መመልከት ተችሏል፡፡ በየቦታው በተቀመጡ የሸራ ማጠራቀሚያ ታንከሮች በቦቴ ውኃ ሲቀርብ ይታያል፡፡ በየቦታው የምግብ ዕርዳታ ይሰጠን የሚሉ ሰዎች ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህን ዓይነት አሰቃቂ ሁኔታ ደግሞ ደረጃው ቢለያይም በሌሎች ክልሎችና አካባቢዎችም መኖሩ ነው ብዙ መረጃዎች እያረጋገጡ የሚገኘው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -