Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በጥሬ ገንዘብ የሚደረግ ግብይት በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መምጣቱ ተጠቆመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ በጥሬ ገንዘብ የሚደረጉ የገንዘብ እንቅስቃሴዎች እየቀነሱ መሆኑን መረጃዎች እያመለከቱ ነው፡፡ በአብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ባንኮች የሚደረጉ የገንዘብ እንቅስቃሴዎች በተለያዩ የዲጂታል አማራጮች እየተተገበሩ ነው፡፡ በተለይ በ2015 ሒሳብ ዓመት እንደ ሪከርድ የሚቆጠር አፈጻጸም መታየቱም ይገልጻል፡፡

በ2016 ሒሳብ ዓመትም ቢሆን በዲጂታል ባንክ አገልግሎት የሚንቀሳቀሱ የገንዘብ መጠን እያደገ ስለመምጣቱ እየወጡ ያሉ መረጃዎች እያመላከቱ ነው፡፡ 

በጥሬ ገንዘብ የሚደረግ ግብይት በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መምጣቱ ተጠቆመ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይፋዊ መረጃ እንደሚያሳየውም፣ በተጠናቀቀው የ2015 ሒሳብ ዓመት በዲጂታል የክፍያ አማራጮች የተንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን ከ4.7 ትሪሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ይህ የገንዘብ መጠን ከቀዳሚው ዓመት የ2014 የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር፣ ከ3.1 ትሪሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡ በግብይት መጠንም ቢሆን በ2014 የሒሳብ ዓመት የተፈጸመው ትራንዛክሽን ወይም ግብይት 345.7 ሚሊዮን ሲሆን፣ በ2015 ሒሳብ ዓመት ግን 1.24 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ 

በተለይ በሞባይል ባንክ አገልግሎት እየተደረገ ያለው የገንዘብ ዝውውር ከሌሎች አማራጮች በተለየ ከፍተኛ አፈጻጸም የታየበት ሆኗል፡፡ 

የብሔራዊ ባንክ መረጃም የ2015 የሒሳብ ዓመት ብቻ ከ479.9 ሚሊዮን በላይ ትራንዛክሽኖች ከ3.44 ትሪሊዮን ብር በላይ በሞባይል የባንክ አገልግሎት ማንቀሳቀስ መቻሉን ነው፡፡  

በሞባይል የባንክ አገልግሎት በሒሳብ ዓመቱ የተደረገው የገንዘብ ዝውውር ከሌሎች የዲጂታል አማራጮች አንፃር ሲታይ ከ80 በመቶ የሚሆነውን ሊይዝ ችሏል፡፡ 

ይህም ከሞባይል ባንክ አገልግሎት ጋር ተያይዘው ካሉ የቀደሙት ዓመታት እንቅስቃሴዎች አንፃር፣ ሲታይ በእርግጥም በኢትዮጵያ በጥሬ ገንዘብ ይደረግ የነበረ እንቅስቃሴን የለወጠ ስለመሆኑ ያሳያል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ያሳየው ዕድገትም በተገልጋዮች ዘንድ አገልግሎቱ እየተለመደ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን ነው፡፡ 

በ2015 በሞባይል ባንክ የተደረገው ትራንዛክሽን ከ2014 ሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ390 ሚሊዮን በላይ ብልጫ አለው፡፡ የተንቀሳቀሰውም የገንዘብ መጠን ከ2014 ጋር ሲነፃፀር ከ2.2 ትሪሊዮን ብር በላይ ብልጫ ማሳየቱ፣ ከዲጂታል የክፍያ አማራጮች የሞባይል ባንክ አገልግሎት ሰፊ በሆነ ልዩነት እያደገ መምጣቱን ነው፡፡  

በሞባይል የባንክ አገልግሎት በ2014 የሒሳብ ዓመት የነበረው የትራንዛክሽን መጠን 88 ሚሊዮን ሲሆን፣ በዚህ ትራንዛክሽን የተንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን 1.16 ትሪሊዮን ብር ነበር፡፡ በ2011 የሒሳብ ዓመት በሞባይል ባንክ በ4.5 ሚሊዮን ትራንዛክሽን መጠን 16.8 ቢሊዮን ብር የገንዘብ ዝውውር ተደርጓል፡፡ ይህ የገንዘብ መጠን በ2012 ወደ 68.3 ቢሊዮን ብር ከዚያም በ2013 ደግሞ 326.6 ቢሊዮን ብር ማንቀሳቀስ መቻሉን ዕድገቱን በተጨባጭ ያሳያል፡፡  

ከሞባይል ባንክ አገልግሎት ሌላ በኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት የተንቀሳቀሰውም የገንዘብ መጠን በ2015 ከፍተኛ ዕድገት መሆኑን የሚጠቁመው መረጃ፣ በኢንተርኔት የተንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን 380.3 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በዲጂታል የባንክ አገልግሎት ከፍተኛ የሚባለውን ገንዘብ እያንቀሳቀሰ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት በዓመት ከሚያንቀሳቅሰው ገንዘብ ውስጥ አብዛኛው በዲጂታል አማራጮች የተፈጸሙ መሆኑን በጥሬ ገንዘብ የሚደረገው እንቅስቃሴ እየቀነሰ ለመምጣቱ አመላካች ነው፡፡  

የኢትዮጵያ ንግድ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከ64 በመቶ በላይ የሚሆነው የገንዘብ እንቅስቃሴው በዲጂታል የባንክ አገልግሎት የተሳለጠ መሆኑንና አሁንም በዚህ አገልግሎት የሚደረገው እንቅስቃሴ እየጨመረ መሄዱን አመላክቷል፡፡ ሰሞኑንም የ2016 የሒሳብ ዓመት የዲጂታል የባንክ አገልግሎቱን በተመለከተ ይፋ ያደረገው መረጃ፣ በዲጂታል የባንክ አገልግሎት ዕድገት ቀጣይነት ያሳየ ሆኗል፡፡ 

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መረጃ መሠረት በ2016 የሒሳብ ዓመት ግማሽ ዓመት ብቻ ከ2.8 ትሪሊዮን ብር በላይ በዲጂታል የባንክ አገልግሎት ገንዘብ ማንቀሳቀስ ችሏል፡፡ ይህ ገንዘብ እንቅስቃሴ ከ494 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆኑ ግብይቶች ወይም ትራንዛሽኖች የተፈጸመ ነው፡፡ ይህ አፈጻጸም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር፣ በግብይት የ35 በመቶ በገንዘብ መጠን ደግሞ የ118 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ 

በቀዳሚው ዓመት በሙሉ የሒሳብ ዓመት 3.2 ትሪሊዮን ብር ማንቀሳቀስ ችሎ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የስድስት ወራት 2.8 ቢሊዮን ብር ማንቀሳቀስ የቻለው ከ12 ሚሊዮን በላይ የኤቲኤም ተጠቃሚ፣ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ የሞባይል ባንክና ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆኑ ደንበኞች በመያዝ እንደሆነ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሌሎች ባንኮች የተለየ ይህንን አገልግሎት ማስፋት የቻለው፣ በተለይ ከ2013 ሒሳብ ዓመት ወዲህ በአገልግሎቱ ዙሪያ ባካሄደው ማስፋፊያ ነው፡፡ ይህም የማስፋፊያ ፕሮጀክት በ2013 የሒሳብ ዓመት ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ ማድረስ አስችሎታል፡፡ 

እንደ ብዙዎች ባንኮች በሞባይል ባንክ አገልግሎት ከፍተኛ ገንዘብ ያንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በሞባይል ባንኪንግ ብቻ 2.4 ትሪሊዮን ብር በሞባይል ገንዘብ ማዘዋወር ተችሏል፡፡ 

በኤቲኤም ማሽን ደግሞ 308 ቢሊዮን ብር፣ በኢንተርኔት ባንኪንግ 260 ቢሊዮን ብር፣ በሲቢኢ ብር 19 ቢሊዮን ብርና በፓስ ማሽን 17 ቢሊዮን ብር ግብይት ተከናውኗል፡፡ 

እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁሉ ሌሎች ባንኮችም በዲጂታል የባንክ አገልግሎት የሚያንቀሳቀሱት የገንዘብ መጠን እያሳደጉና አብዛኛውንም የገንዘብ እንቅስቃሴ በዚሁ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት እያካሄዱ መሆናቸውን እያመለከቱ ነው፡፡ 

የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ዝውውር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ለመምጣቱ የተለያ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በዋናነት ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴን ተግባራዊ ያደረገው መመርያ ተጠቃሽ ነው፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የግል ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ዲጂታል የባንክ አገልግሎት የህልውና ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡ 

የዲጂታል የገንዘብ እንቅስቃሴ መጠን ዕድገት መታየት የጀመረውም ከባንኮች በጥሬ ገንዘብ የሚወጣው እንዲገደብ ማድረግ ነው፡፡ ከግንቦት 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው መመርያ በጥሬ ገንዘብ የሚደረግ ግብይትን ለመቀነስ አስችሏል፡፡ 

ይህ መመርያ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ከባንኮች ይወጣ የነበረው ገንዘብ ገደብ አልነበረም፡፡ በመሆኑም በጥሬ ገንዘብ የሚደረግ ክፍያ ላይ ገደብ በመጣል ለግሰለብ መጀመሪያ በቀን እስከ 200 ሺሕ ብር፣ በወር እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ ማውጣት የሚቻልና ከዚያ በላይ ያለውን ገድቧል፡፡ ለኩባንያዎችም በቀን እስከ 300 ሺሕ ብርና በወር እስከ 2.5 ቢሊዮን ብር ድረስ ብቻ ማውጣት እንደሚቻል ደንግጓል፡፡ ይህ መመርያ ግን እንደገና ተሻሽሎ ለግለሰብ እስከ 50 ሺሕ ብር ዝቅ ብሏል፡፡ ለኩባንያዎችም እስከ 100 ሺሕ ብር እንዲሆን ተወስኖ፣ ከዚህ በላይ ገንዘብ ማንቀሳቀስ ከተፈለገ ግን ዲጂታል የባንክ አገልግሎት ከአካውንት ወደ አካውንት ማስተላለፍ ወይም በሌሎች እንደ ቼክ መሰል አገልግሎት እንዲጠቀሙ ማስገደዱ ለዲጂታል የገንዘብ ዝውውሩ ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ 

ሌላው ምክንያት መንግሥት ከፍተኛ የገንዘብ ልውውጦች የሚደረግባቸው ግብይቶች በዲጂታል የባንከ አገልግሎት እንዲከናወኑ በመወሰኑ ወደ 200 የሚጠጉ የመንግሥት ኩባንያዎች በዚህ አሠራር ውስጥ እንዲያልፉ መደረጉ ነው፡፡ በዓመት ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ይፈጸምበታል የተባለው የነዳጅ ግብይትና ሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎች በአስገዳጅነት በዲጂታል ክፍያ እንዲፈጽሙ መደረጉ ለዕድገቱ በተጨባጭ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡  

ዲጂታል የባንክ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ አጋዥ ይሆናሉ ከተባሉ መተግበሪዎች መካከል አንዱ የሆነው ኤቲኤም ሲሆን፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ባንኮች በመላ አገሪቱ 7,858 የኢቲኤም ማሽኖች ሥራ ላይ መዋላቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ ያመለክታል፡፡ 

አውቶሜትድ ገንዘብ መክፈያ (ፖዝ) ማሽኖች ቁጥር ደግሞ በ12 ሺሕ በላይ መድረሳቸውን ያመለክታል፡፡ በእነዚህ ማሽኖች የተደረገው የገንዘብ ዝውውር ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱንም ይጠቁማል፡፡ እንደ መረጃው ሥራ ላይ ባሉት የኤቲኤም ማሽኖች በ2015 የሒሳብ ዓመት ብቻ ከ356.3 ሚሊዮን በላይ በሆነ ሁኔታ ከ478.3 ቢሊዮን ብር በላይ መንቀሳቀስ ተችሏል፡፡ በፖዝ ማሽኖች ደግሞ ከ6.6 ሚሊዮን በሚሆን ትራንዛክሽን ከ40.8 ቢሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈጸም መቻሉን ያመለክታል፡፡ 

በእነዚህ የዘመናዊ ግብይትና የዲጂታል የገንዘብ እንቅስቃሴ መተግበሪያዎች የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥር እያደገ መሄድ የገንዘብ እንቅስቃሴውም እንዲጨምር እያደረገ ነው፡፡ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት መረጃዎች እንደሚጠቅሱትም፣ የተገልጋዩን ፍላጎት መጨመር ተከትሎ የኤቲኤም ማሽን ቁጥሮች በየዓመቱ እየጨመረ ነው፡፡

በ2013 ሒሳብ ዓመት የኢትዮጵያ ያሉ የኤቲኤም ማሽኖች 9,208 የነበረ ሲሆን፣ ይህም ቁጥር በ2014 ሒሳብ ዓመት ወደ 11,760 ሊደርስ ችሏል፡፡ የፖስ ማሽኖችንም ቁጥር በ2013 የሒሳብ ዓመት 6,343፣ በ2014 ደግሞ ወደ 6,902 በማደግ፣ በ2015 ሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ወደ 7,878 ሊደርስ ችሏል፡፡        

የዲጂታል የባንክ አገልግሎት በዚህን ያህል ደረጃ እያደገ መምጣት ባንኮችና ሌሎች አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማት ገቢን እየጨመሩ መሆኑም ይታመናል፡፡ በእያንዳንዱ የገንዘብ ዝውውር እየተጠየቀ ያለው የአገልግሎት ክፍያ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መጨመር ከዋና ዋና ባንኮች ገቢዎች መካከል አንዱ ወደ መሆን ተሸጋግረዋል፡፡ 

የዲጂታል የባንክ አገልግሎት አሁን የደረሰበት ደረጃ ይህንን ቢመስልም የአገልግሎት ክፍያው ግን ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ በተለይ ከአንድ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ የሚደረግ የገንዘብ ዝውውር ላይ እየተጠየቀ ያለው የአገልግሎት ዋጋ ከፍተኛ ነው የሚሉ የደንበኞች አስተያየት ጎልቶ እየተሰማ ነው፡፡ አንድ ደንበኛ ከሆነበት ባንክ ገንዘብ ሲያንቀሳቅስ እየተከፈለ ያለው የአገልግሎት ዋጋ ፍትሐዊ አይደለም የሚሉ ተጠቃሚዎች በተለይ የገንዘብ መጠኑ በጨመረ ቁጥር ለአገልግሎቱ የሚከፍሉት የገንዘብ መጠን ከፍተኛ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡

ከራስ ባንክ በኤቲኤም ገንዘብ ለማውጣት በአንድ ሺሕ ብር ሁለት ብር የአገልግሎት እየተቆረጠ ነው፡፡ ከባንክ ወደ ሌላ ባንክ ገንዘብ ለማዘዋወርም በአንድ ሺሕ ብር አምስት ብር ይከፈላል፡፡ ይህ የአገልግሎት ዋጋ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከ50 ሳንቲም እስከ አንድ ብር የሚከፈልበት የነበረ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተደረገው ጭማሪ ከፍተኛ ሊባል የሚችል እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው አንድ የባንክ የሥራ ኃላፊ፣ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ዕድገት ያሳየበት አንዱ ምክንያት ባንኮች ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ለአገልግሎቱ አጋዥ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ማካሄዳቸው ነው፡፡ 

በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ማቅረብ ግድ በመሆኑ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በዚህ ረገድ ብዙ ሥራዎች መሠራታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ ተቋማት በሞባይል የባንክ አገልግሎት ዘርፍ እያከናወኑ ያሉ እንቅስቃሴዎች ግን በዲጂታል ባንክ አገልግሎት ለመስፋፋት ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ 

በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ የረዥም ጊዜ ልምድ ያላቸው ሌላው የባንክ ባለሙያ በሰጡት ትንታኔ፣ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት ለተገልጋዩም ሆነ ለባንኮች እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ተገልጋዩ በቀላሉ ገንዘብ በማንቀሳቀስና ክፍያዎችን መክፈል እያስቻለው ነው፡፡ ‹‹ባንኮች ወደ ዲጂታል የባንክ አገልግሎት እያዘነበልን ያለነው ወጪን ለመቀነስ ነው፤›› ይላሉ፡፡  

በአሁኑ ወቅት አንድ ቅርንጫፍ ከፍቶ አገልግሎት መስጠት ባንኮችን ለከፍተኛ ወጪ እንደሚዳርግ በመሆኑም ባንኮች የዲጂታል የባንክ አገልግሎታቸውን ማስፋፋት ተመራጭ እያደረጉ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

አሁን የዲጂታል ባንክ አገልግሎት መተግበሪያዎች ተደርገው ከሚወሰዱት የተለያዩ አማራጮች ውስጥ አንዱ ኤቲኤም መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን እየታየ ካለው የሞባይልና የኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር ዕድገት አንፃር፣ ኤቲኤም ድርሻ እየቀነሰ የሚሄድ ስለመሆኑም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ በመሆኑም ዲጂታል የባንክ አገልግሎትን ከማስፋት አንፃር የሞባይል ኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት የዲጂታል ባንክ አገልግሎቱ ዋነኛ መሣሪያ ሆነው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

ከዲጂታል የገንዘብ ዝውውር ጋር ተያይዞ ከተገልጋዮች የሚነሳ የአገልግሎት ክፍያ ከፍተኛ ነው ለሚባለው አስተያየትም፣ እኚሁ የባንክ ኃላፊ ክፍያው ለአገልግሎቱ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ሌላው ከዲጂታል የባንክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ከተገልጋዮች እየቀረቡ ከሚገኙ ጥያቄዎች መካከል በተለይ ከአንድ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ ከፍ ያለ መጠን ያለው ገንዘብ ሲንቀሳቀስ አንዳንድ ባንኮች በቶሎ ገንዘቡን ለተቀባይ ያለማድረስ ችግር ነው፡፡

አንዳንድ ባንኮች ባለባቸው የገንዘብ እጥረት ማስተላለፍ የሚገባቸውን ገንዘብ በተጨባጭ በቶሎ ያለማድረስ ተገልጋይ ላይ ጫና እያሳረፉ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ አስተያየት እንዲሰጡ የጠየቅናቸው የባንክ ኃላፊዎች ችግሩ በተወሰኑ ባንኮች ላይ የሚንፀባረቅ ነው ይላሉ፡፡ 

ከዲጂታል የባንክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ከዚህ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ አሁን ያለው ትልቁ ችግር ሳይበር ሲኪውሪቲ ነው ይላሉ፡፡ ብዙ የማጭበርበር ሙከራዎች ይኖራል፡፡ ስለዚህ ይህንን ሥጋት ለመቀነስ የሚደረጉ ጥረቶች ለባንኮች ተግዳሮት ሆነው የሚቀጥሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ 

ሌላው በዘርፉ ያለው ተግዳሮት ቴክኖሎጂው በጣም ወጪ የሚጠይቅ ከመሆኑ በተጨማሪ ለሳይበር ሴኪውሪቲ የሚወጣው ወጪ ደግሞ አጠቃላይ ወጪውን የበለጠ ያንረዋል። በተጨማሪም በየጊዜው ሲስተሙን ለማሻሻል የሚጠየቀው ወጪ ውድ መሆኑን ጠቁመዋል።

በብሔራዊ ባንክ እምነት ደግሞ የዲጂታል የክፍያ ሥርዓት በ2011 የሒሳብ ዓመት ከነበረበት 139.6 ቢሊዮን ብር፣ በ2015 የሒብ ዓመት 4.7 ትሪሊዮን ብር መድረስ ዘርፉ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፣ በተለይ ያለ ማስያዣ ለሚሰጡ ብድሮች መሠረት የጣለ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች