Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው ደንብ ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታ ቀረበ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው ደንብ ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታ ቀረበ

ቀን:

የትግራይ ክልልያዊ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ያወጣውና ከኅዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ መሆን የጀመረው ደንብ ቁጥር 4/2016፣ ከሕገ መንግሥቱ የሚቃረኑና የዜጎችን መብት የሚገድቡ ድንጋጌዎችን በመያዙ እንዲሻር የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታ ቀረበበት።

አቤቱታው የቀረበው ለፌዴራል የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ሲሆን፣ አቤቱታውን ያቀረበው ደግሞ በሕግ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተመሥርቶ ሕጋዊ ዕውቅና ያገኘው፣ ‹‹ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ›› (Human Rights First) የተባለ አገር በቀል የሲቪል ማኅበር ነው። 

የትግራይ ክልልን ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መመለስና የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ሊያጠናክርና ሊያግዝ የሚችል ዕርምጃ መውሰድን ዓላማው ያደረገው ይህ ደንብ፣ ‹‹ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕጎች ወደ መደበኛ ሕግ ለመመለስ የወጣ የመሸጋገርያ ደንብ ቀጥር 4/2016›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ደንቡ ኅዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ካቢኔ የፀደቀ ሲሆን፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ደንቡን ያወጣው በአዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 15 (1) በተሰጠው ሥልጣን፣ እንዲሁም የሚኒስትሮች ምክር ቤት የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ እስተዳደር ለማቋቋም ባወጣው ደንብ ቁጥር 533/2015 አንቀጽ 5(1) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት እንደሆነ የደንቡ መግቢያ ያስረዳል።

አቤቱታውን ያቀረበው ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ የተባለው አገር በቀል ሲቪል ማኅበር ምክትል ዳይሬክተር አቶ መብርሒ ብርሃነ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያወጣው ድንብ በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይቃረናል ሲሉ ለሪፖርተር አስረድተዋል።

አንደኛው ከሕገ መንግሥቱ ጋር መሠረታዊ ተቃርኖ የሚታይበት በደንቡ የመሸጋገሪያ ክፍል አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ የሠፈረው ድንጋጌ መሆኑን አቶ መብርሒ ገልጸዋል።

የደንቡ አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 3 ድንጋጌ፣ ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ያልተከፈለ የመንግሥት ሠራተኛ፣ የግል ተቋማት ሠራተኛና የግለሰብ ሠራተኛ ውዝፍ ደመወዝን በሚመለከት አዲስ የተመሠረተው ክስ ታግዶ እንዲቆይ፣ እንዲሁም በሒደት ላይ ያሉ ተመሳሳይ ጭብጥ ያላቸው ክሶች፣ ይግባኝና የአፈጻጸም ጉዳዮች በሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ተጠንቶ መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስ ባሉበት እንዲቆሙ ያዛል።

የሕግ መንግሥቱ አንቀጽ 37 (1) ማነኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት እንዳለው ደንግጎ ሳለ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ግን ይህንን የዜጎች ፍትሕ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት ባወጣው ደንብ መገደቡን አቶ መብርሒ አስረድተዋል።

‹‹ሥልጣን ባልተሰጠው አካል ያውም በደንብ ዜጎች ያላቸውን የፍትሕ ጥያቄ በፍርድ ቤት ወይም በሌሎች የዳኝነት አካላት አቅርበው ፍትሕ እንዳያገኙ ተገድቧል፤›› ብለዋል።

በሁለተኛ ደረጃ አቤቱታ የቀረበው በደንቡ የመሸጋገርያ ክፍል አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 2 ሥር የተቀመጠውን ድንጋጌ የተመለከተ ነው። ይህ ድንጋጌ የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንን እንደገና ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 360/2014 ከመደበኛ ሕጎች ጋር ተመዛዝኖ እስከሚሻሻል ድረስ ተፈጻሚነቱ እንዲቀጥል የሚደነግግ ነው።

የሕግ ባለሙያው አቶ መብርሒ እንደሚሉት፣ አዋጅ ቁጥር 360/2014 ነባሩን የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አፍርሶ እንደ አዲስ የሚያቋቁምና የፖሊስ አባላቱም ከትግራይ ሠራዊት ብቻ እንዲሚመለመሉ የሚደነግግ ነው።

የትግራይ ክልል ጦርነት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ከመቀስቀሱ በፊት በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ ፖሊስ ኮሚሽን ሥር ሲሠሩ የነበሩ የፖሊስ አባላት፣ ያለምንም ሕጋዊ ምክንያት ወደ ሥራቸው እንዳይመለሱ እንደተደረጉና ደመወዛቸውም እስከ ዛሬ ድረስ እንዳልተሰጣቸው፣ ከነቤተሰቦቻቸው በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ መሆናቸውን፣ የጥሰቱ ተጠቂ ከሆኑ የትግራይ ፖሊስ አባላት ድርጅት ለማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል። ቁጥራቸው ከ1,000 በላይ የሚሆኑ እስከ 30 ዓመት ያገለገሉ የትግራይ ክልል የፖሊስ አባላት ከሥራቸው እንዲባረሩ ያደረገው ደግሞ፣ ነባሩ የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ፈርሶ፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 360/2014 እንደ አዲስ እንዲቋቋምና የሚመለመሉ የፖሊስ አባላቱም ከትግራይ ሠራዊት ብቻ እንዲመለመሉ የሚደነግግ በመሆኑ ነው ብለዋል።

‹‹ይህ አዋጅ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ተብሎ በፈረሰው የትግራይ ክልል ምክር ቤት የወጣ ነው፡፡ ይህም በፕሪቶሪያው ስምምነት ተቀባይነት አግኝቶ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሠረት ተደርጓል፤›› የሚሉት አቶ መብርሒ፣ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ አይደለም በተባለ ምክር ቤት የወጣ አዋጅ ሕጋዊ ሆኖ ተፈጻሚነቱ ሊቀጥል አይገባም ብለዋል።

በተጨማሪም በጊዜያዊ አስተዳደሩ የወጣው ደንብ በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል ሕጎች መሠረት የተቀጠሩና የሠለጠኑ፣ ለዓመታት ያገለገሉ የፖሊስ አባላት በትጥቅ ትግል አልተሳተፉም በማለት ከሥራ እንዲባረሩ ወይም ወደ ሥራ እንዳይመለሱ የሚከለክል፣ እንዲሁም እንደ ማንኛውም የፖሊስ አባላት የጡረታና የሌሎች ማኅበራዊ ዋስትና ጥበቃ እንዳያገኙ የሚገድብ መሆኑን አስረድተዋል።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የወጣው ደንብ ቁጥር 4/2016 ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 9 (1) እና አንቀጽ 37 የሚቃረን በመሆኑ ደንቡ እንዲሻር፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታ ታኅሳስ 17 ቀን ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ማስገባታቸውን ገልጸዋል።

አቤቱታው ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ መድረሱን ሪፖርተር ማረጋገጥ የቻለ ሲሆን፣ ጉባዔው የቀረበለትን አቤቱታ መቼ እንደሚመለከት ግን ለማወቅ አልተቻለም። ሪፖርተር ጉዳዩን በተመለከተ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች ደመወዝ እንዲከፈላቸው የሚጠይቁ ሰላማዊ ሠልፎችን ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ማካሄዳቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በወቅቱም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የሠራተኞችን ውዝፍ ደመወዝ ለመክፈል የሚያስችል በጀት ከፌዴራል መንግሥት እንዳልተለቀቀለት አስታውቆ ነበር። በተጨማሪም ክልሉ የገጠመውን ከፍተኛ የበጀት እጥረት መቅረፍ እንዲችል የፌዴራል መንግሥት በሁለት ዓመት ውስጥ የሚመለስ አምስት ቢሊዮን ብር እንዲያበደረው ጠይቆ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...