Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበመሬት አስተዳደር ተቋማዊ አደረጃጀት ላይ ያተኮረ ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጀ

በመሬት አስተዳደር ተቋማዊ አደረጃጀት ላይ ያተኮረ ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጀ

ቀን:

የኢትዮጵያ የመሬት አስተዳደር ባለሙያዎች ማኅበር፣ በመሬት አስተዳደር ተቋማዊ አደረጃጀት ላይ ያተኮረ ረቂቅ ሰነድ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ መሬትን በባለቤትነት ሊመራና ሊያስተዳድር የሚችል ራሱን የቻለ ተቋም እንዲኖር ለማስቻል ማኅበሩ የመነሻ ሐሳብ ረቂቅ በማዘጋጀት፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ውይይት እንዲያደርጉበት ይፋ የተደረገ መሆኑን፣ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቻምየለህ ጋሹ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የከተማና የገጠር መሬት አጠቃቀሙ ልዩነት ቢኖረውም፣ ገጠርም ሆነ ከተማ ያለው መሬት በአንድ ሕግና በአንድ ወጥ በሆነ ተቋም ለመምራት ‹የመሬት አስተዳደር ተቋማዊ አደረጃጀት› በመፈተሽና ክፍተቶችን በመለየት፣ ሊሻሻል የሚችልበትን የሐሳብ ሰነድ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን አቻምየለህ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

በማኅበሩ የተዘጋጀው የመነሻ ሰነድ ሐሙስ ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም. የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ተወካዮችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው በክልል የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ በርካታ ባለድርሻ አካላት የተለያዩ አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን፣ ‹‹በርካታ የመሬት ሥርዓት ችግሮች ባሉበት ወቅት የሁሉም ችግር መፍቻ አደረጃጀት ነው የሚለው ብቻ መሆኑ አጠያያቂ ነው፤›› ሲሉ፣ በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የመሬትና ካዳስተር ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙዓለም አድማሱ ተናግረዋል፡፡

‹‹በተጨማሪም አሁን ካለው አሠራር በመለወጥ ከዚህ ወደ እዚህ መሸጋገር አለበት የሚሉ ቀላል ቃላት በመጠቀም ማሸጋገር ስለማይቻል፣ የሽግግር ሒደት እንዴት መሆን እንዳለበት በግልጽ መቀመጥ አለበት፤›› ብለዋል፡፡

አምስት አባላት ባሉት ቡድን የተካሄደው ጥናቱ፣ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የመሬት ጉዳይ የገጠር መሬት አስተዳደርና የከተማ መሬት አስተዳደር ተብሎ ሁለት ቦታ ተከፍሎ መመራቱ፣ ለተለያዩ መልካም አስተዳደር ችግሮች መፈጠር ምክንያት ሆኗል ሲሉ የጥናት ቡድኑና የማኅበሩ አባል ዘርፉ ኃይሉ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ 

እንደ አገር ትክክለኛ የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት  ባለመከተል ለምርት የሚሆነውን መሬት ለመኖሪያ፣ ለመኖሪያ የሚሆነው ለምርት በማድረግ የተዘበራረቀ አጠቀቃቀም በመስፋፋቱ፣ ረቂቅ ሰነዱ መሬትን በአግባቡ ለመምራትና ለመጠቀም የሚያስችልና ለመንግሥት የመሬት የፖሊሲ አማራጭ እንደ ግብዓት ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

መሬት የሀብቶች ሁሉ ምንጭ ውድ ሀብት በመሆኑና በሰው ልጆች መካከል በጋራና በተናጠል ለተከሰቱትም ሆነ ወደፊት ለሚከሰቱ ግጭቶች ሁሉ መነሻው ከመሬት ሀብት ጋር የተገናኘ ነው ሲል ማኅበሩ ገልጿል፡፡

የጥናት መረጃዎች እንደሚያሳዩት የመሬት ፖሊሲና አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት በአግባቡ ካልተመራ በአገር ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ በመፍጠር የመልካም አስተዳደር ችግር መነሻ ስለሚሆን ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጥ በሚያስችል መንገድ ማከናወን እንደሚገባ ማኅበሩ በሰነዱ ጠቅሷል፡፡

በመንግሥት ሪፖርት ከሚገለጹ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መካከል፣ መሬት ተቆጥሮና ተለክቶ በመረጃ ሥርዓት ያልተያዘ መሆንና የመጠቀም መብትን ያለ ሥጋት ለማረጋገጥ ቀሪ ሥራዎች ያሉት መሆን፣ ሕገወጥ የመሬት ወረራ በስፋት መዘውተር፣ በከተሞች አካባቢ የመኖሪያ ቤት እጥረት በስፋት መኖር፣ በልማት ሰበብ ዜጎች ከመሬታቸው ያለ በቂ ካሳና መልሶ ማቋቋም ከቤት ንብረታቸው መፈናቀል፣ ያነሰ ካሳ ክፍያ ለልማት ተነሺዎች የመክፈል ሁኔታ መኖር፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ የመሬት ፖሊሲ አለመኖር፣ በዘርፉ የሠለጠነ ባለሙያና አመራር እጥረት በአገሪቱ በስፋት የሚታዩ ችግሮች መሆናቸው ማኅበሩ ይፋ ባደረገው ሰነድ ገልጿል፡፡

የተለያዩ የክልል መስተዳድሮች በገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 456/1997 መሠረት፣ የገጠር መሬት መብት፣ ግዴታና አስተዳደር መደንገጉን ማኅበሩ በሠራው ጥናት አስቀምጧል፡፡

‹‹መሬት የሕዝብና የመንግሥት በመሆኑ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት የሚመራበትን ማለትም መሬት ማልማትን፣ አጠቃቀሙን የመወሰን፣ የተጠቃሚነት መብትን ማረጋገጥና ማስተላለፍን፣ የልማት ተነሺዎችን በተገቢው ሕጋዊ መንገድ ማስተናገድንና መልሶ ማቀቋቋምን፣ የመሬት ነክ መረጃዎች ማመንጨትና መተንተን፣ ማከማቸትና ማሠራጨት፣ ወዘተ ሲያጠቃልል፣ ሁለተኛው ደግሞ መንግሥት የመሬት ገበያ ጉድለት ወይም መዛባት ሲፈጠር እንዲፈታ እንዲቃና በሕጋዊ መንገድ ጣልቃ የሚገባበት ክንውኖች መሆናቸው›› በሰነዱ የተካተቱ ሐሳቦች ናቸው፡፡

መንግሥት ከመሬት ጋር የተያያዙ መብቶችና ግዴታዎችን ለማስከበርና ከፍ ብሎ የተገለጹትን ኃላፊነቶች ወጥ በሆነ መንገድ ለመከወን፣ ተግባሩንና ኃላፊነቱን የሚመጥን ተቋማዊ አደረጃጀት ያለው አስፈጻሚ አካል እንደሚያስፈልገው የሚተነትነው ሰነዱ፣ የገጠርም ሆነ የከተማ የመሬት አስተዳደር ሥርዓትን ለመገንባትና ዘርፉንም በተሻለ መንገድ መምራት እንዲቻል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን፣ በተለይም በገጠር የመሬት አስተዳደር ዘርፉ መጠነኛ የሆነ ውጤት መገኘቱን በሰነዱ መቀመጡን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

በአማራ፣ በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች የመሬት ተቋምን ወጥ በሆነ አደረጃጀት ለመምራት በመወሰን ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጸው ማኅበሩ፣ በፌዴራል ደረጃ የከተማ መሠረተ ልማት የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ ሥር የከተማና የገጠር መሬት ተቋማዊ አደረጃጀትን ወደ አንድ ማምጣት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ተግባራት መካከል አንዱ እንደሆነ ማስቀመጡን፣ እንዲሁም በግብርና ዘርፍ የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ በተመሳሳይ ሁኔታ ጠንካራ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ተቋም መመሥረት፣ የሚመሠረተውም ቀድሞ በአንድ ሴክተር ተፅዕኖ ሥር መዋል የሌለበት መሆኑን እንደሚያሳይ ማኅበሩ ገልጿል፡፡

የመንግሥትን ጥረት በመረዳትና የመሬት ዘርፉም ያለበትን የተቋምና አደረጃጀት ተግዳሮት በዘላቂነት ለመቅረፍና የፖሊሲ ጥረቱን ወደ ተግባር የመለወጥ ጥረት ከሙያ አንፃር ለማገዝ እንዲቻል፣ ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያ የመሬት አስተዳደር ባለሙያዎች ማኅበር የተለያዩ ጥረቶችን ማድረጉን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

ከበርካታ ጥረቶቹ መካከል የመሬት አስተዳደር ዘርፉ ተቋማዊ አደረጃጀት ያለበትን ሁኔታ መረዳት የሚታይበትን ተግዳሮት መለየትና አገራዊ ሁኔታውን ከዓለም አቀፍ ልምዶችና ለተግባሩ ምቹ ከሆኑ መርሆዎች ጋር በማዛመድ፣ የመሬት አስተዳደር አወቃቀሩ ሊሻሻል የሚችልበትን አገራዊ የምክረ ሐሳብ ሰነድ ማዘጋጀቱን ማኅበሩ አስረድቷል፡፡

የኢትዮጵያ የመሬት አስተዳደር ባለሙያዎች ማኅበር በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት፣ ታኅሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በመመዝገብ ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ የተቋቋመ የሙያ ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩ በአሁኑ ጊዜ በትምህርት ተቋማት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ በርካታ ባለሙያዎችን በመያዝ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...