Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየሰላም ሚኒስቴር ሰላም ማስፈን ባለመቻሉ ወቀሳ ቀረበበት

የሰላም ሚኒስቴር ሰላም ማስፈን ባለመቻሉ ወቀሳ ቀረበበት

ቀን:

የተመሠረተባቸውን ዓላማዎችና ተልዕኮዎች አላሳካም የተባለው የሰላም ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ሰላም ማስፈን ባለመቻሉ ወቀሳ ቀረበበት፡፡

ሚኒስቴሩ ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ጉባዔ ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት፣ ‹‹ሰላማዊ አገር መፍጠር አልቻለም›› በሚል በምክር ቤቱ አባላት ተተችቷል፡፡ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት የሰላም ሚኒስቴር ህልውናና አስፈላጊነትን ጥያቄ ውስጥ የሚከት አስተያየት ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡

በዕለቱ በምክር ቤቱ በመገኘት ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም፣ ሚኒስቴራቸውን ለመከላከል ጥረት አድርገዋል፡፡

- Advertisement -

ለኢትዮጵያ ሰላም መደፍረስና ቀውስ ሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች እንዳሉ አቶ ብናልፍ ተናግረዋል፡፡ አንደኛው ከለውጡ ጋር ተያይዘው የመጡ ችግሮች መሆናቸውን፣ በሁለተኝነት ደግሞ የፖለቲካ ባህሉ ብልሽት በመጨረሻም ከታሪክና ትርክት ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ውዝግቦች በኢትዮጵያ ሰላም ለመታጣቱ  መሠረታዊ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል፡፡

አንዳንድ የምክር ቤት አባላት የሰላም ሚኒስቴር በ2011 ዓ.ም. ሲቋቋም፣ የኢትዮጵያን ቀውስ ለመፍታትና ሰላማዊ አገር ለመፍጠር ትልቅ ሚና ይኖረዋል የሚል ሰፊ ተስፋ በሕዝብ ዘንድ ሰፍኖ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ተስፋው አለመሳካቱን ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ራዕዩና ተልዕኮው አድርጎ ያስቀመጣቸውን ሰላምና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ እንዲሁም የዜግነት ክብርን ማረጋገጥ አልቻለም ብለዋል፡፡ ሚኒስቴሩ ግጭቶች ሳይፈጠሩ ማስቆምም ሆነ ሲከሰቱም ማስቆም አለመቻሉን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ ሰላማዊ የፖለቲካ ባህል እንዲገነባ ያደረገው በጎ አስተዋጽኦ የለም በሚል ተወቅሷል፡፡ ሰዎች በኃይል ዕርምጃዎች፣ በጥቃት፣ እንዲሁም በመገፋት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን በተስፋ መቁረጥ አይተው ወደ ኃይል አማራጭ ሲገቡ ተቋሙ ለማስቆም በቂ ጥረት አላደረገም ተብሎ ተተችቷል፡፡

በተያያዘም በአማራ፣ በኦሮሚያና በሌሎች ክልሎች ታጥቀው የሚታገሉ ኃይሎችን ወደ ሰላም ለመመለስ፣ ሰላም ሚኒስቴር የሠራው ሥራ ምን እንደሚመስል ማብራሪያ ተጠይቋል፡፡

በተለይ አገሪቱ ከለውጡ ወዲህ በግጭት አዙሪት ውስጥ መውደቋን ያነሱ አንዳንድ ተወካዮች፣ ይህን መታደግ ካልቻለ የሰላም ሚኒስቴር ለምን ያስፈልጋል የሚል ጠንካራ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ሚኒስቴሩ በሕግ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት መወጣት የማይችል ከሆነ፣ የሚመደብለት ውድ የአገር ሀብት ለሌላ ጠቃሚ አገልግሎት ሊውል ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ተቋሙ ሌላው ቀርቶ ሁለት ሚኒስትሮቹን ማጣቱን የጠቀሱ አባላቱ ሚኒስትር ደኤታና የጨፌ ኦሮሚያ አባል የነበሩት አቶ ታዬ ደንደአ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ መታሰራቸውን አውስተዋል፡፡ ሌላኛው ሚኒስትር ደኤታ ሥዩም መስፍን (ዶ/ር) ደግሞ ወደ ውጭ አገር ተሰደዋል ሲሉ ሚኒስቴሩን የህልውና ጥያቄ አንስተውበታል፡፡

በእነዚህና በሌሎችም ጥያቄዎች ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ፣ ከለውጡ ጋር ተያይዞ አገሪቱ በመሠረታዊነት የታጠቁ ኃይሎች አደጋ እንደገጠማት አውስተዋል፡፡ ‹‹በለውጡ ማግሥት ይዋጣልን የሚል የታጠቀ ኃይል መፈጠሩ አገሪቱን ለከባድ ምስቅልቅል የዳረገ ጦርነት እንዲፈጠር አድርጓል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ከ1960 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ የተፈጠረው የፖለቲካ ባህል ብልሽት ፈተና መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ሳይኖር ጭምር መገዳደል፣ መጨራረስ፣ ለሥልጣን መባላት፣ መደማመጥ ወይም መነጋገር ያልተለመደበት ፖለቲካ መንገሡ ዛሬም ፈተና ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ፖለቲካን በታሪክና በትርክት ላይ ያለውን ተቸንካሪነት፣ ለኢትዮጵያ ሰላም መጥፋት ሌላው ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ የእኔ ብቻ እውነት ማለትና ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ ማተኮር አገር መጉዳቱን ተናግረዋል፡፡

ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር መንግሥታቸው ሁሌም ዝግጁ እንደሆነ የጠቀሱት ሚኒስትሩ በአማራ፣ ኦሮሚያም ሆነ በሌሎች ክልሎች ያሉ ታጣቂዎች ወደ ሰላም ድርድር እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር አስፈላጊ ነው ተብሎ በተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ የተቋቋመ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ የሰላም ችግር ስላለ ተቋሙ መመሥረቱን፣ ነገር ግን የሰላም ግንባታ በአንዴ የሚሳካ ሳይሆን ረዥም ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን በመግለጽ የተቋማቸውን አስፈላጊነት ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...