Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መንግሥት እንቅስቃሴዎችን የሚገድቡ ተግባራትን ያስታግስ

በትራንስፖርት ዘርፍ ከተሰማሩ ትልልቅ ከሚባሉ የግል ኩባንያ ቅጥር ግቢ ከወትሮው በተለየ በተሽከርካሪዎች ተሞልቶ አየሁ፡፡  በሳምንቱ ላይ የተመለከትኩት እንግዳ ነገር በቀጣይ ቀኖችም ተሽከርካሪዎቹ ያለ ሥራ መቆማቸውን ታዝቤያለሁ፡፡

የኩባንያው ቅጥር ግቢ ከዚህ ቀደም ምናልባት አንድና ሁለት የጭነት ተሽከርካሪዎች ይታዩበት ካልሆነ በቀር፣ እንደ ሰሞኑ በብዛት ተሰባስበው ያየሁበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ሁሌም ሥራ ላይ የነበሩ ተሽከርካሪዎች እንዲህ ባልተለመደ ሁኔታ መሰባሰባቸው ብዥታ የሚፈጥር ነበርና ጉዳዩን ለማጣራት ሞከርኩ፡፡ ተሽከርካሪዎቹ ከያሉበት እንዲሰበሰቡ በኩባንያው ቅጥር ግቢ ያለ ሥራ እንዲቆሙ የተደረጉበትን ምክንያትም ለማወቅ ቻልኩ፡፡ ኩባንያው ባልተለመደ ሁኔታ ያሰባሰበው ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ተሽከርካሪዎቹን ለማሰማራት ባለመቻሉ መሆኑን አረጋገጥኩ፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ አንዳንድ ዓውራ ጎዳናዎች በተሽከርካሪዎች ላይ እየደረሰ ባለው ጥቃት ተደጋግመው መስተዋላቸው ኩባንያው ለጊዜው ተሽከርካሪዎቹን እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግን እንደ አማራጭ ሊወስድ ችሏል፡፡  

ለወትሮው ፋታ ያልነበራቸውን እነዚህን ትልልቅ የጭነት ተሽከርካሪዎች የሚሾፍሩ ሠራተኞችም ጊዜያዊ ዕረፍት እንዲወስዱ ተገደዋል፡፡ ተሽከርካሪዎቹን  ከማንቀሳቀስ የተቆጠበው ይህ ኩባንያ የተለያዩ ዕቃዎችን ለማጓጓዝ ውለታ የገባባቸው ሥራዎችን ሁሉ ሰርዟል ተብሏል፡፡

ከሰሞኑ በተከታታይ በተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው አደጋና ውድመት የፈጠረውን ሥጋት ተከትሎ ተሽከርካሪዎቻቸውን እንዲህ ባለ ሁኔታ ከእንቅስቃሴ ያቀቡ፣ ሌሎች ኩባንያዎችና ግለሰብ አገልግሎት ሰጪዎች ተመሳሳይ ዕርምጃ ስለመውሰዳቸውም ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ በግል ያነጋገርኳቸው ከከተማ ውጪ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ ግለሰቦች እንደገለጹልኝ፣ ከሰሞኑ በአንዳንድ ተሽከርካሪዎች ላይ ደረሰ የተባለውን ጥቃት በመስማት እስኪረጋጋ በሚል ተሽከርካሪቻቸውን አቁመዋል፡፡

ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ እንዲህ ያሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ሊበጅላቸው ካልቻለ ችግሩ በትራንስፖርቱ ድርጅቶች ላይ ብቻ የሚወድቅ አይሆንም፡፡ ባደፈጡ ታጣቂዎች እየተፈጸመ ነው የተባለው ጥቃት ንብረት በማውደም ብቻ የሚገለጽም አይደለም፡፡ ከንብረት ውድመቱ ባሻገር የሎጂስቲክስ እንቅስቃሴዎች በማስተጓጎል አጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱ ላይ ችግር ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡

 በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከሚታየው የፀጥታ መደፍረስና አለመረጋጋት ዘላቂ መፍትሔ እስካልተገኘ ድረስ ችግሩ ቀጣይ መሆኑም አይቀርም፡፡ በአንደኛው አካባቢ ተረጋጋ ሲባል በሌላው ክፍል ደግሞ ሌላ ችግር እየሰማን ባልተቋረጠ ሥጋት ውስጥ እያደረግን ያለው ጉዞ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ለመሆኑ አይካድም፡፡

በአንዳንድ የአገሪቱ ዓውራ ጎዳናዎች ላይ ያለ ሥጋት መኪና የማይሽከረከርባቸው ከሆነ፣ ወደ ገበያ መቅረብ የሚገባውን ምርት በአግባቡ ማቅረብ እንዳይችል እያደረገ ነው ማለት ነው፡፡ የገቢና የወጪ ዕቃዎችን በአግባቡ ማንሳትና መጫን የሚቻለው ያለ ሥጋት መንቀሳቀስ ሲቻል ነው፡፡ በሚጓዙበት መንገድ ላይ በተከታታይ የተቃጠሉና የነደዱ ተሽከርካሪዎች የሚመለከቱ አሽከርካሪዎችም ቢሆኑ ይህንን እያዩ እንዴት ሊሠሩ ይችላሉ? ነገ፣ ከነገ ወዲያ ተረኛው እኔ ልሆን እችላለሁ በሚል ሥራውን ለመሥራት ፍላጎት አይኖራቸውም፡፡  

ስለዚህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ሥጋት እየሆነ ያለው ችግር ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ እየከበደ ስለሚሄድ መንግሥት ያልተቋረጠ ምርትና ሸቀጣ ሸቀጦች የሚመላለስባቸው ዓውራ ጎዳናዎችን ከሥጋቱ ነፃ እንዲሆኑ ማስቻል ይኖርበታል፡፡   

የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መስተጓጎል በአጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የሚያስከትለውን ችግር የዋጋ ንረትን የሚያባብስ መሆኑ በዋናነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ እስካሁንም በታጣቂዎች ጥቃት የወደሙ ንብረቶች የተሽከርካሪዎቹን ባለቤቶች ጎድቷል፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያልተጠበቀ ካሳ ክፍያ እንዲከፍሉ አድርጓል፡፡ ተሽከርካሪዎችን ይዘው የነበሩ ሾፌሮች ሥራ አጥ ማድረጉንም መግለጽ ይቻላል፡፡ ባልተጠበቀ ሁኔታ የሚደረጉ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች መጨመር በኢትዮጵያ ባልተለመደ ሁኔታ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከፖለቲካ አመፅና ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶች ለሚሰጡ የኢንሹራንስ ሽፋኖች እየተከፈለ ያለው ካሳ እየጨመረ መምጣት በራሱ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች የሰላም ዕጦት የሚያስከፍለው ዋጋ ቀላል አለመሆኑን ነው፡፡  

ከሁሉም በላይ ግን የሎጂስቲክስ አገልግሎቶችን ሥጋት ላይ የሚጥሉ ተደጋጋሚ አደጋዎች ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በበቂ ሁኔታ እንዳይቀርቡ የሚያደርግና የዋጋ ንረቱን የሚያባብሱ ስለሚሆን መንግሥት ጉዳዩን መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ችግሩ በግብይት ሥርዓቱ ላይ ከሚፈጥረው ተፅዕኖ ባሻገር በተለይ እንደ ኮንስትራክሸን ያሉ ዘርፎችም ሥራቸውን በአግባቡ ለመከወን እንዳይችሉ እያደረገ መሆኑንም ማስታወስ ይገባል፡፡

ከሰሞኑ እንደሰማነውም ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ካሉ ከተሞች ለግንባታ ግብዓት የሚሆኑ አሸዋ፣ ጠጠር፣ ድንጋይና ሲሚንቶ የሚያመላክቱ ተሽከርካሪዎች እንደ ልብ ያለመንቀሳቀሳቸው ተፅዕኖ እያሳረፉ መሆኑን ነው፡፡

ስለዚህ በአጠቃላይ ግን ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ እየተፈጠሩ ያሉት ችግር ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላቂ መፍትሔ የሚያሻው መሆኑን ደግሞ ደጋግሞ ማስገንዘቡ ተገቢ ነው፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት