Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በሁለንተናዊ እክሎች የታጀበ የድምፅ ብክለት

በአዲስ አበባ ከተማ ከተለያዩ ተቋማትና ከኢንዱስትሪዎች አካባቢ ከደረጃ በላይ የሚወጣው የድምፅ ብክለት ልዩ ልዩ ዓይነት ችግሮችን ማስከተሉ ይስተዋላል፡፡ ይህንንም ችግር ለመከላከል የሚያስችል ሕግ ወጥቶ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ ሕጉንም የማስፈጸም ወይም ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት የተሰጠውም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ነው፡፡ አቶ ለሜሳ ጉደታ የባለሥልጣኑ የአካባቢ የሕግ ተከባሪነት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በድምፅ ብክለት መንስዔ፣ ብክለቱ እያስከተለ ያለው የጤና ቀውስ፣ ቀውሱን ለመከላከል እየተወሰደ ባለው እንቅስቃሴና በሌሎች ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር:- አካባቢ ማለት ምን ማለት ነው? አካባቢና የአየር ብክለት እንዴት ይገለጻል? በካይ ነገሮች የሚባሉት ምንድናቸው? በሚሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ያተኮረ ማብራሪያ ቢሰጡን?

አቶ ለሜሳ፡- አካባቢ ማለት የምንኖርበትን ምድር፣ እንዲሁም ሕይወት ያላቸውና የሌላቸው ነገሮች ከነመኖሪያቸውና ከነመስተጋብራቸው (ኢንተር አክሽን) ጨምሮ አካባቢ ይባላል፡፡ ብክለት ሲባል ደግሞ ሕይወት ያለውና የሌለው ማለትም አፈር፣ መሬት፣ ውኃ፣ ዕፅዋት፣ ሰው በአጠቃላይ አካባቢ የተፈጥሮ ይዘቱን ሲለቅ ወይም በባዕድ ነገር ሲበከል፣ በአጠቃላይ ባዕድ ነገር ወደ ተፈጥሮአዊ ነገር ሲገባ፣ ወይም ወደ ውስጣችን የምናስገባው ንፁህ አየር ውስጥ ሌላ ባዕድ ነገር ሲታከልበት ብክለትን ያመለክታል፡፡ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር የሰው ልጅ ሳይፈጠር ወይም ከመፈጠሩ በፊት አየር መደበኛ ይዘትና መጠን እንዳለው ነው፡፡ ነገር ግን ከተለያዩ የቴክኖሎጂ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ ባዕድ ነገሮች የተነሳ ንፁህና ለጤና ተስማሚ የነበረው አየር ሊበከል ይችላል፡፡ በዚህ መልኩ የተበከለውን አየር በመሳብ ወደ ሰውነታችን ውስጥ ይገባል፡፡

ሪፖርተር:- ከደረጃ በላይ በሚቦርቁ ድምፆች ለተቸገሩ ሰዎች ተደራሽነታችሁ ምን ያህል ነው?

አቶ ለሜሳ፡- ከደረጃ በላይ በሚቦርቁ ድምፆች ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከምናካሂደው እንቅስቃሴ ባሻገር፣ ብዙ ሰዎች በድምፅ ብክለት መቸገራቸውን በባለሥልጣኑ ነፃ የስልክ መስመር እየደወሉና በአካልም እየቀረቡ ሮሮአቸውን አሰምተዋል፡፡ ካቀረቧቸውም ሮሮዎች መካከል ማታ፣ ማታ ልንተኛ አልቻልንም፡፡ ቀን በሥራ የደከመውን አዕምሮአችንና በአጠቃላይ አካላችንን የምናሳርፍበት ቦታ ተቸግረናል፡፡ በተለይ መዝናኛና ጭፈራ ቤቶችና የእምነት ተቋማትን ተጎራብተን የምንገኝ ሰዎች ለከፍተኛ ችግር ተዳርገናል፡፡ በጤንነት መታወክ ምክንያት የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ሰዎች ቀንም ሆነ ማታ ትንሽ እንቅልፍ እንኳን ሸለብ ሊላቸው ተስኗቸዋል የሚሉና ሌሎችም አቤቱታዎች ይገኙባቸዋል፡፡ ሰሞኑን በየጭፈራ ቤቶች ሌሊት ላይ አሰሳ አድርገን ለድምፅ ብክለት መንስዔ ሆነው በተገኙ ላይ ልዩ ልዩ ዓይነት የቅጣት ዕርምጃ ወስደናል፡፡ ባለሥልጣኑ ከሚወስዳቸውም ዕርምጃዎች መካከል ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ ከዚያም እንደየደረጃው ቤቱን የማሸግና ሲቀጥል ደግሞ ከያዘውም የሥራ ዘርፍ እንዲወጣ የማድረግና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡ በዚህም አጋጣሚ አንድ ሳልገልጸው የማላልፈው ነገር ቢኖር በብክለት ቁጥጥር አዋጅ ውስጥ ለድምፅ ብክለት ብቻ ተለይቶ መመርያ ተዘጋጅቶለታል፡፡

ሪፖርተር:- ከፍተኛ የድምፅ ብክለት በሰው ጤንነት ላይ የሚያስከትለውን ዕንከኖች ቢገልጹልን?

አቶ ለሜሳ፡- ከፍተኛ የሆነ የድምፅ ብክለት የጆሮ ታምቡሮችን በመቅደድ የመስማት ችግር ያስከትላል፡፡ ከዚህም ሌላ የደም ግፊት ያባብሳል በተለይ ሕፃናትና አረጋውያንን ለነርቭና ለጨጓራ በሽታዎች ይዳርጋል፡፡ በወንዶችና ሴቶች ላይ መሀንነትን ያስከትላል ወይም ልጅ የመውለድ ችሎታቸውን ያሰነካክላል፡፡ ዓይን የተለያዩ ከለሮችን እንዳያይ ይዳርጋል፡፡ አለመረጋጋትንም ያስከትላል፡፡ ለአካል ጉዳትና ለሥነ ልቦና እክል ይዳርጋል፡፡

ሪፖርተር:- የድምፅ መጠን ደረጃ ወጥቶለታል? ደረጃ ከወጣለት ዘርዘር አድርገው ቢያብራሩልን?

አቶ ለሜሳ፡- ድምፅ በአካባቢያችን ሁለት ነገሮች ሲጋጩ ወይም ሲገናኙ የሚፈጠር ነው፡፡ ጠቅለል ባለ መልክ ሲገለጽ ደግሞ ድምፅ የሚፈጠረው በሚለዋወጠው የአየር ግፊት ሲሆን፣ ይህም የተለያየ መጠን አለው፡፡ መጠኑም በሦስት አካባቢዎች ዙሪያ ተለይቶ ተቀምጧል፡፡ አካባቢዎቹም የኢንዱስትሪ፣ የገበያና የመኖሪያ አካባቢዎች ሲሆን በእነኚህ አካባቢዎች በቀንና በምሽት የሚኖረውን የድምፅ መጠን የሚለካውም ‹‹ዴሲቤል›› ይባላል፡፡ በዚህም መሠረት በኢንዱስትሪ አካባቢ የሚስተጋባው የድምፅ መጠን በቀን 75፣ ማታ ደግሞ 70፣ በገበያ አካባቢ በቀን 65፣ ማታ 55፣ በመኖሪያ አካባቢ በቀን 55፣ ማታ 45 ዴሲቤል መሆን አለበት ነው የሚባለው፡፡ በዝርዝር ከተቀመጡት ደረጃዎች በላይ የሚስተጋባው ድምፅ በካይ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ምሽት ተብሎ የተያዘው ከምሽቱ ሦስት ሰዓት እስከ ንጋቱ ወይም ጠዋት 12 ሰዓት ድረስ ያለው ጊዜ ነው፡፡

ሪፖርተር:- የተጠቀሱትን የድምፅ መጠኖችን በማክበር ረገድ ከኅብረተሰቡና ከተለያዩ አካላት ምን ይጠበቃል?

አቶ ለሜሳ፡- ኅብረተሰቡና የተለያዩ አካላት የሚለቋቸውን ልዩ ልዩ ዓይነት ድምፆች ከተቀመጠላቸው ደረጀ በላይ እንዳያንቧርቁ የማድረግ ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህንን ግዴታቸውን ያልተወጡ ሁሉ የተለያየ ዓይነት ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡ በወንጀልም ያስጠይቃቸዋል፡፡ ከደረጃ በላይ በሚለቀቁ የድምፅ ብክለቶች ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ መብታቸውን ማስከበር ይኖርባቸዋል፡፡ ለድምፅ ብክለት መስንዔ ናቸው የሚባሉት የሃይማኖት ተቋማት፣ የጭፈራና መዝናኛ ቤቶች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ኢንዱስትሪዎች፣ የጦር ጀቶች/አውሮፕላኖች፣ የንግድና የመኖሪያ አካባቢዎች፣ የግንባታ ሥራዎች፣ ወዘተ ናቸው፡፡

ሪፖርተር:- ኅብረተሰቡን ከደረጃ በላይ ከሚለቀቅ የድምፅ ብክለት መከላከል ወይም መጠበቅ የሚችለው እንዴት ነው?

አቶ ለሜሳ፡- የድምፅ ብክለት ባሉባቸው አካባቢዎች የሚኖሩትን የኅብረተሰብ ክፍሎች የተጠቀሰው ብክለት በሌለበት አካባቢ ማስፈር፣ የተለያዩ ተቋማት ድምፅን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙና የሚገነቡት ሕንፃዎች ድምፅን እንዳያሰሙ ማድረግ፣ በአጠቃላይ የድምፅ ብክለትን ለማስቀረት የወጡ አዋጆችንና ደንቦችን ተግባራዊ ማድረግ፣ ለኅብረተሰቡ የድምፅ ብክለትን ለመከላከል ባወጡት አዋጆችና ደንቦች ላይ ትኩረት ያደረገ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ቀጣይነትና ወጥነት ባለው መልኩ ማካሄድ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እስከ ግለሰቦች የሚደርሰው ወገን ፈንድ

ወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሕጋዊ ዕውቅና በማግኘት ከኢትዮጵያና ከተለያዩ አገሮች ልገሳን ለማሰባሰብ ‹‹ወገን ፈንድ›› የሚባል የበይነ መረብ (ኦንላይን) የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድረ...

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...