Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሶማሊያ ከተሰማራው የኢትዮጵያ ጦር ጋር የተያያዘ ግብታዊ ዕርምጃ እንዳይወሰድ አሜሪካ አሳሰበች

በሶማሊያ ከተሰማራው የኢትዮጵያ ጦር ጋር የተያያዘ ግብታዊ ዕርምጃ እንዳይወሰድ አሜሪካ አሳሰበች

ቀን:

  • ኢጋድ ማንኛውም ስምምነት የሶማሊያ መንግሥትን ፈቃድ ማግኘት አለበት ብሏል
  • ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በድርድር ጥረቷን ትቀጥላለች ብለዋል

ኢትዮጵያና ሶማሊያ በመካከላቸው በተፈጠረው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ምክንያት፣ በሶማሊያ ከተሰማራው የኢትዮጵያ ጦር ጋር የተያያዘ ግብታዊ የሆነ ዕርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠቡ አሜሪካ አሳሰበች።

አሜሪካ ይህንን ማሳሰቢያ የሰጠችው ጥር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. በኡጋንዳ የተካሄደውን የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) አስቸኳይ የመሪዎች ጉባዔ ላይ በታደመችበት ወቅት ነው።

የኢጋድ አባል አገሮች አስቸኳይ የመሪዎች ጉባዔ የተጠራው ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነትን ተከትሎ፣ በሶማሊያና በኢትዮጵያ መንግሥታት መካከል ለተፈጠረው ውጥረትና ለሱዳን የእርስ በርስ ግጭት ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ለማበጀት ነው። 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዚህ የመሪዎች ጉባዔ ላይ በተጋባዥነት የተገኙት የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር (አምባሳደር) ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ውስጥ የተካተተው ይዘት አሜሪካንን እንደሚያሳስባት አስረድተዋል፡፡

ከኢትዮጵያና ከሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነት ይዘቶች መካከል ውጥረት የቀሰቀሰው መሠረታዊ ነጥብ፣ ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ የባህር ይዞታ ውስጥ በሊዝ የባህር በር እንደምታገኝና ኢትዮጵያ ደግሞ በምትኩ ለሶማሌላንድ ራስ ገዝ አስተዳደር ዕውቅና እንደምትሰጥ የሚገልጸው ነው።

የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሐመር (አምባሳደር)፣ የሶማሊያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መከበር እንዳለበትና ይህም የአሜሪካ መንግሥት አቋም መሆኑን አስታውቀዋል። 

በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ማርገብ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በሶማሊያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር ሥምሪት ላይ ግብታዊ ዕርምጃ መውሰድ፣ አሸባሪው የአልሸባብ ቡድን በፍጥነት በሶማሊያ ውስጥ በመቀጠልም ወደ ኢትዮጵያ እንዲያስፋፋ ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

አልሸባብ ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት በመጠቀም፣ አዲስ ተዋጊያዎችን በስፋት እየመለመለ መሆኑን የሚያመላክቱ መረጃዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሊያ መንግሥትና ከሶማሌላንድ ክልል አስተዳደር ጋር ለብዙ ዓመታት በትብብር እየሠራ መሆኑን የገለጹት ልዩ ልዑኩ፣ ይህ ትብብር አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል። 

በአፍሪካ ቀንድ እየተከሰቱ ባሉ የፀጥታና ያለመረጋጋት ሥጋቶች የአካባቢው መንግሥታት የጋራ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሥራ ግንኙነታቸውን መቀጠል፣ እንዲሁም እርስ በርስ የጠበቀ ውይይት ማድረጋቸው ወሳኝ እንደሆነ የአሜሪካ መንግሥት በፅኑ ያምናል ብለዋል። አክለውም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ተጨማሪ ግጭቶች የመሸከም አቅም እንደሌለው አክለዋል፡፡

በኢጋድ የመሪዎች ጉባዔ ላይ የተገኙ ተጋባዥ አገሮችም ሆኑ የኢጋድ አባል አገሮች ከሶማሊያ መንግሥት ጎን በመቆም፣ የሶማሊያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መከበር አለበት ብለዋል። በጉባዔው መጨረሻ ላይ የወጣው የኢጋድ መግለጫም ይህንኑ አቋም አንፀባርቋል፡፡

ኢጋድ በመግለጫው የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን የማክበር ዋና መርሆችን በድጋሚ በማረጋገጥ፣ ማንኛውም ግንኙነት ከላይ የተጠቀሱትን ዋና መርሆችን እንዲያከብር አሳስቧል።

በማከልም ከሶማሌላንድ ጋር የሚደረግ ማንኛውም ስምምነት በሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግሥት ፈቃድ መሠረት መሆን አለበት ብሏል። የኢትዮጵያና የሶማሊያ መንግሥታት የተፈጠረውን ውጥረት በማርገብ በምትኩ ገንቢ ውይይት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ምሥጋኑ አረጋ የኢጋድ መሪዎች አስቸኳይ ስብሰባ በተካሄደበት ዕለት በኡጋንዳ በገለልተኛ አገሮች ንቅናቄ (Non-Aligned Countries Movement) የሚኒስትሮች ስብሰባን እየተካፈሉ የነበረ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ የኢጋድን ጉባዔ በፕሮግራም መደራረብ የተነሳ እንደማትሳተፍ አሳውቃ ሳትካፈል ቀርታለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ ከኢጋድ የመሪዎች ጉባዔ ማግሥት በኡጋንዳ በተካሄደው የገለልተኛ አገሮች ንግናቄ የመሪዎች ጉባዔ ላይ መገኘታቸው ይታወሳል፡፡

በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደብ የሌላቸው አገሮች የሕዝቦቻቸውን በቂና ቀጣይነት ያለው የመተዳደሪያ ፍላጎት ለማሟላትና ዕድገታቸውን ለማረጋገጥ ፈተናዎች እንደሚገጥሟቸው ተናግረዋል።

ወደብ አልባ የሆነችው አገራቸው ኢትዮጵያም ይህንን ፈተና በሰላምና በጋራ ተጠቃሚነት፣ እንዲሁም በድርድር መፍትሔ ለማበጀት ጥረቷን እንደምትቀጥል አስታውቀዋል።

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት መሠረት አድርጋ የሶማሊያን የግዛት ወሰን ለመጠቅለል አልማለች ሲሉ የከሰሱ ሲሆን፣ ሶማሊያ በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሕግን መሠረት ባደረገ መንገድ ከማንኛውም አገር ጋር የንግድና የባህር ወደብ አገልግሎት ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...