Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የአስቤዛ የዋጋ ንረት ማቆሚያው የት ነው?

ከዛሬ አራት ዓመት በፊት አንድ ኩንታል ጤፍ መጠነኛ ጭማሪ ተደርጎበት በሦስትና አራት ሺሕ ብር ሲሸጥ፣ ‹‹ኧረ ኑሮ ተወደደ›› ሲባል ነበር፡፡ አንድ ኩንታል ጤፍ አራት ሺሕ መግባቱ በእርግጥም ለብዙዎች ከባድ ነበር፡፡ በወቅቱ በአንድ ኩንታል ጤፍ ከ500 እስከ 1,000 ብር አካባቢ ነው፡፡

በዚያን ወቅት ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ጤፍ እስከ አንድ ሺሕ ብር ሲጨምር ይህ ለምን እንደሆነ እንኳን አውቆ ያሳወቀን አልነበረም፡፡ የጤፍ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎም ሦስትና አራት ብር ይሸጥ የነበረ የእንጀራ ዋጋ በአንዴ ከአምስት እስከ ሰባት ብር ገብቶ አረፈው፡፡ በዚህም ‹‹አጀብ!›› ብለናል፡፡ ‹‹ጎበዝ ማቆሚያው የት ነው?›› ለሚለው ጥያቄ ሁነኛ መልስ ሳናገኝ ይግረማችሁ ብሎ የጤፍ ዋጋ ወደ ሰባት ሺሕ ብር ተሻገረ፡፡ የደረቅ እንጀራም ዋጋ 10 እና 12 ብር ገባ፡፡ አሁንም የዋጋ ጭማሪው ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ነው ወይ? ወይስ በዘፈቀደ የሆነ ነው? የሚለውን ፈትሾ እንቅጩን የሚነግረን ጠፋ፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ በእኛው ገበሬዎች የሚመረት ምርት ከዕጥፍ በላይ ዋጋው ሲያሻቅብ ነገሩን ከሥሩ አጥርቶ፣ ‹‹ወዴት እየሄደ ነው?›› ብሎ መልስ የሚሰጥ አልተገኘም፡፡ ኧረ እንዲያውም ይህ ጥያቄ የአንገብጋቢነቱን ያህል በደንብ አልተመከረበትምና ችግሩ የበለጠ ገፍቶ ወጣ፡፡ በአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል የሚጠቀምበት ይህ ምርት በአንድና በሁለት ዓመት ልዩነት ዋጋው እንዲህ ሲሰቀል ዝም በመባሉ ብቻ አሁንም ግስጋሴው ቀጥሎ ከአንድ ዓመት በፊት በኩንታል 12 ሺሕ ብር የነበረው፣ ከሰሞኑም ደግሞ እስከ 14 ሺሕ ብር ዋጋ ሊጠየቅበት በቅቷል፡፡ ስለዚህ በአራትና በአምስት ዓመት ልዩነት የጤፍ ዋጋ ከአራት እጅ በላይ ለማሻቀቡ ምክንያት ትክክለኛውን ምክንያት አውቆ ለመፍትሔ ባለመሠራቱ ነገም ከዚህ የባሰ ችግር ከፊት ለፊታችን ይጠብቀናል ማለት ነው፡፡

ጤፍም ሆነ ሌላ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች በአንድ ወቅት ተገማች ያልሆነ የዋጋ ለውጥ ሲታይባቸው ወዲያው ‹‹ለምን?›› ብሎ የሚጠይቅ እንዴት ይጠፋል? ዋጋው የጨመረው በምርት እጥረት ወይስ በሌላ ምክንያት ነው፡፡ ተፈጠረ ለሚለው ጥያቄ ፈጣን ዕርምጃ ባለመወሰዱ ዛሬ በእያንዳንዱ ምርቶች ላይ የተጋነነ ዋጋ የምንሰማው፡፡ በእያንዳንዱ ምርት ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ምክንያቱ የምርት እጥረት ከሆነ ይህንን ክፍተት መድፈን የሚችለው ምርታማነትን በመጨመር ከሆነ ይህንኑ አስታውቆ በፍጥነት ወደ ተግባር እንዲገባ ማድረግ ሲገባ ይህ አልተደረገም፡፡ ሁሌም ጊዜያዊ መፍትሔ ፍለጋ ላይ ቆመን መቅረታችን ከማንወጣው ቅርቃር ውስጥ እየከተተን መሆኑ ገበያው እየነገረን ነው፡፡ የሚታረስ መሬት ባልጠፋበት አገር ነጋ ጠባ በዋጋ ንረት የመሰቃየታችን አንዱና ዋነኛ ችግር ለችግሮችን ዘላቂ መፍትሔ እያበጀን አለመጓዛችን መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል፡፡  

ጤፍን ምሳሌ አደረግን እንጂ በሌሎች እኛው በምናምታቸው የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችም በተመሳሳይ መንገድ በጣም በሚያስገርም ሁኔታ የዋጋ ጭማሪዎች መታየታቸውን ተዘንግቶ እንዳልሆነ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ በአቅማችን ያለ ብዙ ድካም አምርተን ልንጠቀምባቸው የሚገቡ እንደ ሽንኩርት ያሉ ምርቶች ሳይቀሩ የኢትዮጵያ ችግር ሲሆኑ ማየት በራሱ ያማል፡፡

 የሌላውን ጊዜ ትተን በሦስትና በአራት ዓመታት ልዩነት እጅግ ተወደደ ተብሎ ከ15 እስከ 20 ብር ይሸጥ የነበረው ሽንኩርት ከሁለት ዓመት በፊት 50 ብር ገባ ተብሎ የተፈጠረውን ትርምስ የምናስታውሰው ነው፡፡ የሽንኩርት ዋጋ የአገር አጀንዳ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀሩ በአደባባይ የተናገሩለት ጉዳይ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡

ዛሬስ? ዛሬ ይለይላችሁ ተብለን አንድ ኪሎ ደቃቃ ሽንኩርት እስከ 150 ብር ያውም ተሠልፈን እየገዛን ነው፣ ይህ የሚያሳዝን ነው፡፡ ሽንኩርት 50 ብር ገባ ተብሎ በሚጮህበት ሰዓት የችግሩን መንስዔ ለይቶ ቢያንስ ዋጋው ባለበት እንዲቆም የሚያስችል ዘላቂ መፍትሔ አልተቀመጠም፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ አንድ ኪሎ ሽንኩርት 150 ብር የምንገዛው፡፡

በነገራችን ላይ ሽንኩርት በጥቂት ዓመታት ልዩነት ከአምስትና ከስድስት እጅ በላይ ዋጋው ሲወጣ፣ ጤፍ በአራት እጅ ጨምሮ ሲሸጥ፣ ሌሎች ምርቶችም በተመሳሳይ መንገድ እያሻቀቡ የመሄዳቸውን ያህል ገቢያችን ያለመጨመሩ ችግሩ ነገሩን የበለጠ የሚያወሳስበው መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ለዚህም ነው በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ያለው ሸክም ከባድና ለመፍትሔውም መደከም ያስፈልጋል የሚባለው፡፡ ከሁሉም በላይ በየዓመቱ እያደገ ከሚመጣው ሕዝብ ቁጥር አንፃር ፍጆታችን በዚያው ልክ እየጨመረ ነው፡፡ ቢያንስ በቀላሉ ልናመርታቸው የሚችሉ ምግብ ነክ ምርቶችን ከማሳደግ አኳያ አገር አቀፍ ንቅናቄ ማድረግ ግድ የሚለው፡፡

አሁን ባለው አካሄዳችን ነገም ከዚህ የባሰ የዋጋ ንረት የሚጠብቀንና ይህም እንዳሁኑ በማማረር ብቻ የምናልፈው እንደማይሆን ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እስከዛሬ የግብርና ምርቶች ዋጋ ባልተጠበቀ መልኩ ዋጋ ሲጨመሩ በቶሎ ዕርምጃ ያለመወሰዳችን እያስከፈለን ያለውን ዋጋ ከዚህም በኋላ መቀጠል ከሌለበት ደግሞ መንግሥት ዜጎች በግብርና ሥራ ላይ እንዲበረታቱ ማበርታት ይኖርበታል፡፡ ፖሊሲዎቹንም ከዚሁ አንፃር መቃኘት የግድ ይለዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ቢሆን ሁሉንም ነገር ለመንግሥት ጥሎ ከማማረር አርሶ ለመብላት ብቻ ሳይሆን አርሶ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ልሁን በሚል መንግሥትን ይሞግት፡፡ ምርታማነትን ማሳደግ የህልውና ጉዳይ ሆኖ መታየት አለበት፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት