Thursday, May 30, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በመጪዎቹ ሦስት ወራት ለኢንቨስተሮች ዝግጁ እንደሚደረግ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባን ግማሽ ወይም የአዳማ ከተማን ስድስት እጥፍ የሚያህል ስፋት ይይዛል የተባለው፣ በአዳማና በሞጆ ከተሞች መካከል የሚገነባው ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን፣ በመጪዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ የመጀመርያውን ዙር መሠረተ ልማት በማጠናቀቅ ለኢንቨስተሮች ዝግጁ ይደረጋል ተባለ፡፡

ከአጠቃላዩ 24,000 ሔክታር መሬት ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ከመንግሥት 2,300 ሔክታር፣ ከግለሰቦች ደግሞ 400 ሔክታር መሬት ካሳ በመክፈል መረከባቸውን፣ በሦስት ወራት ውስጥ ለተጨማሪ 600 ሔክታር መሬት የካሳ ክፍያ ለማጠናቀቅ መታቀዱን የገዳ ዞን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞቱማ ተመስገን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአምስት ዓመታት ውስጥ ዝግጅቱ እንደሚጠናቀቅ ከሚጠበቀው 3,150 ሔክታር መሬት ውስጥ፣ የመጀመርያው ምዕራፍ አካል የሆነው 1,000 ሔክታር መሬት ላይ ልማት እየተከናወነ መሆኑን አቶ ሞቱማ አስረድተዋል፡፡

በመጀመሪያው ዙር የመሠረተ ልማት ከተዘጋጀ በኋላ የአገር ውስጥና የውጭ አልሚዎችና ኢንተርፕራይዞች ዞኑ ውስጥ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

ለመሠረተ ልማት ግንባታ ብቻ ለመነሻ የተያዘው 48 ቢሊዮን ብር በመሆኑ፣ ለግል ባለሀብቶች ምቹ ማድረግ አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በቀጥታ ፕሮጀክቶችን የሚያከናውን ሳይሆን አልሚዎችን በማምጣት ለነፃ የንግድ ቀጣናና የሎጂስቲክስ ሀብት የሚሆኑ መሬቶችን እንዲያለሙ የሚጋብዝ በመሆኑ፣ በግሉ ዘርፍ፣ በመንግሥትና በሁለቱ አጋርነት ግንባታው ይከናወናል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የገዳ ልዩ ኢኮኖሚክ ዞን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ለመገንባት ካሰባቸው፣ የሎጂስቲክስ ማዕከልና የሞጆ ሎጂስቲክስ ግንባታ ጋር ማስተሳሰር በሚቻልበት የመሠረተ ልማት ጉዳዮች ላይ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተጠሪ ተቋማትና ከዞን አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጉን አቶ ሞቱማ ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ዴንጌ ቦሩ መገኘታቸውን፣ ከተጠሪ ተቋማት ጋር የአዋጭነት ጥናት ሰነድን በተመለከተ ጥያቄዎች ተነስተው መወያየታቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ብሔራዊ ሎጂስቲክስ ስትራቴጂን ከማስፈጸም አንፃር እንዴት መሥራት እንደሚችልና የኢኮኖሚ ዞኑ ድረስ ዋና ዋና የግንባታ ፕሮጀክቶችን የማቅረብ ኃላፊነት ስላለበት፣ የመንግሥት አቅም በሚፈቅደው መሠረት እንዴት መሥራትና እንደ ባለድርሻ አካል ምን መሥራት እንደሚቻል ለመለየት ውይይቱ መካሄዱን ገልጸዋል፡፡

በ2050 ዓ.ም. የመጨረሻው ምዕራፍ ተጠናቆ ዕውን ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የገዳ የኢኮኖሚ ዞን ምሥረታ፣ ‹‹ስታርትአፕ›› ከሚባለው የመጀመርያው ምዕራፍ ግንባታ አንስቶ በተለያዩ ምዕራፎች የተከፋፈለ የነፃ ንግድ፣ የወጪ ንግድ፣ የመዝናኛና የኢንዱስትሪ ከተማ ግንባታ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት በየአሥር ዓመታት የሚከናወኑ ሥራዎችን በመለየት፣ ለነፃ የንግድ ቀጣና፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የመኖሪያ አፓርትመንቶች ጨምሮ ለሌሎች ፕሮጀክቶች አስፈላጊው ዲዛይን ተሠርቶ መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች