Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ሁለት አሠርታት የተሻገረው የካንሰር ተራድኦ

ትኩረቱን የሕፃናት ካንሰር ላይ በማድረግ ነበር ሥራውን ከ20 ዓመታት በፊት የጀመረው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ተላላፊ ላልሆኑ ሕመሞች አጋላጭ የሆነውን ትምባሆን መከላከልን ጨምሮ የተሟላ ሕክምና በሚገኝበት ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሠራ ይገኛል፡፡ የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ የካንሰር ሶሳይቲ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የሚኖሩ የካንሰር ሕሙማን ለካንሰር ሕክምና ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የሚገጥሟቸውን የመጠለያ፣ የምግብ፣ የትራንስፖርትና የሥነ ልቦና ችግሮችን ለመቅረፍ ለሕሙማኑና አስታማሚዎቻቸው ሙሉ የትራንስፖርት ወጪያቸውን በመሸፈን፣ ነፃ የመኝታና የማረፊያ አገልግሎት እንዲሁም ሕክምና የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት ላይ ይገኛል፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የማይገኙ የምርመራና የመድኃኒት ወጪዎችንም በመሸፈን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ሶሳይቲው በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረገው ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች ቁጥጥርና ዕርዳታ ለሚሹ የካንሰር ሕሙማን ድጋፍ በማድረግ በኩል በተለይም ካንሰርን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ በሚደረገው እንቅስቃሴ ከተለያዩ የመንግሥት አካላት ጋር፣ በተለይም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሠራ ነው፡፡ ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የተመሠረተበትን 20ኛ ዓመት በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች በማክበር ላይ ይገኛል፡፡ የማኅበሩን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴና የእስከዛሬ ጉዞው አበርክቶዎችን በተመለከተ፣ የማነ ብርሃኑ የሶሳይቲውን መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንዱ በቀለን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ሲመሠረት ይዞ የተነሳቸው ዓላማዎች ምንድናቸው?

አቶ ወንዱ፡- ሶሳይቲው ሚያዝያ 9 ቀን 1996 ዓ.ም. ትኩረቱን የሕፃናት ካንሰር ላይ በማድረግ የተቋቋመ ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ዘንድ ስለካንሰር ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ በመቀየር፣ የመከላከያና የመታከሚያ አማራጮችን እንዲያውቅ ማድረግ፣ በአገሪቱ የካንሰር ሕክምና ተሟልቶ የሚሰጥበትን አመቺ ሁኔታ መፍጠር፣ አቅሙ ለሌላቸው ሕሙማን የሥነ ልቦናና ማቴሪያል ድጋፍ መስጠት የሚሉት ቀዳሚ ዓላማ ናቸው፡፡ በተጨማሪም የካንሰር ሕክምና ተሟልቶ የሚሰጥበት፣ ምርምርና ሥርፀት የሚካሄድበት የካንሰር ኢንስቲትዩት እንዲቋቋም መርዳትና ማበረታታት፣ በአገራችን የሚገኙ የሕክምናና የትምህርት ተቋማት በካንሰር ላይ ምርምር እንዲያደርጉ ማገዝ ይዞ የተነሳቸው ሌሎች ዓላማዎቹ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ሶሳይቲው የተቋቋመለትን ዓላማ ዕውን ከማድረግ አንፃር እስከ ዛሬ ያከናወናቸው ሥራዎች ምን ይመስላሉ?

አቶ ወንዱ፡- ሶሳይቲው ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሃያ ዓመታት የካንሰር ሕሙማንን ስቃይ በመቀነስና ታክመው የሚድኑበትን አመቺ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ግንባር ቀደም አስተዋጽኦ ሲያበረክት ቆይቷል፡፡ እስካሁን ሶሳይቲው ከ2,500 በላይ ለሚሆኑ ከተለያዩ ክልሎች ለመጡ ሕፃናትና ሴቶች የካንሰር ሕሙማን እንዲሁም አስታማሚ ቤተሰቦቻቸው ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ የምግብ፣ የመጠለያ፣ የምርመራና የመድኃኒት እንዲሁም የትራንስፖርት ወጪዎችን በመሸፈን የመቋቋሚያ፣ የትምህርት፣ የሕክምናና የሥነ ልቦና ድጋፎችን በመስጠት ላይም ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ሶሳይቲው በእስከዛሬ ጉዞው አገር አቀፍ የካንሰር መከላከልና ቁጥጥር ዕቅድ፣ የብሔራዊ የሕፃናትና ታዳጊዎች ካንሰር መቆጣጠሪያ ዕቅድ፣ የማኅፀን በርና የጡት ካንሰር መከላከልና ድጋፍ፣ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞችን የመከላከልና የቁጥጥር ሥርዓት እንዲዘረጋ፣ የትምባሆ፣ የአልኮልና የመድኃኒት ቁጥጥር አዋጅ እንዲፀድቅ አስተዋጽኦ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡  

ሪፖርተር፡- የብሔራዊ የሕፃናትና ታዳጊዎች ካንሰር መቆጣጠሪያ ዕቅድ ላይ የእናንተ ሚና ምን ነበር? የማኅፀን በርና የጡት ካንሰርን በመከላከል ረገድ ያደረጋችሁት አስተዋጽኦስ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ወንዱ፡- በአገራችን በሥራ ላይ ያለው ብሔራዊ ካንሰር መቆጣጠሪያ ዕቅድ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው ለጡትና ማኅፀን በር ካንሰር ነው፡፡ ይህንን በመገንዘብ ሶሳይቲው ከአጋር ድርጅት ያገኘውን ድጋፍ ተጠቅሞ ከአገራችን ስድስት ዩኒቨርሲቲዎችና ከአሜሪካ በዘርፉ ዕውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች በማስመጣት የተለያዩ የምክክር ስብሰባዎችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ለሁለት ዓመታት ሲደረግ የነበረው ይኼው ጥረትም ተሳክቶ የኢትዮጵያ ሕፃናትና ታዳጊዎች ካንሰር መቆጣጠሪያ ዕቅድ ለጤና ሚኒስቴር ቀርቦ እንዲፀድቅ ሶሳይቲው ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ የማኅፀን በርና የጡት ካንሰርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር፣ የማኅበረሰቡንም የግንዛቤ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴዎችን ሲያካሂድ የቆየ ሲሆን፣ በዚህ ረገድ የተጀመረው ጥረት ጎልብቶና ሥራውንም መንግሥት አስፋፍቶት የማኅፀን በር ካንሰር ምርመራና ሕክምና ከ1,300 በላይ በሚሆኑ የመንግሥት ጤና ተቋማት ውስጥ በነፃ እንዲሰጥ፣ 14 ዓመት የሆናቸው ልጃገረዶች በአገር አቀፍ ደረጃ ክትባት እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ሶሳይቲው ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት ወስዶ ተንቀሳቅሷል፡፡  

ሪፖርተር፡- የትምባሆ፣ አልኮልና የመድኃኒት ቁጥጥር አዋጅ እንዲፀድቅ ያደረጋችሁት አስተዋጽኦ ምን ይመስላል?

አቶ ወንዱ፡- በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በፀደቀው የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር አዋጅ ቀጥር 1112/2011 ላይ ከረቂቁ ጀምሮ እስከፀደቀበት ድረስ ሶሳይቲው ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ አዋጁን የኢትዮጵያ መድኃኒትና ምግብ ቁጥጥር ባለሥልጣንና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን ጨምሮ የተለያዩ የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረጉበት ነው፡፡ አዋጁም የትምባሆንና የአልኮል አጠቃቀምን በተለያየ መንገድ ለመቀነስ ታሳቢ ያደረጉ ጠንካራ አንቀጾችን ይዟል፡፡ ሶሳይቲያችንም በዚህ ጉዳይ ገና ከጅምሩ የትምባሆ ቁጥጥር ረቂቅ ሕግ እንዲዘጋጅና እንዲፀድቅ በማስቻል ረገድ ከፍተኛ የገንዘብና የሙያ ድጋፍ አበርክቷል፡፡

ሪፖርተር፡- የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ በሕፃናት ካንሰር ዙሪያ እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች ምንድናቸው?

አቶ ወንዱ፡- በሶሳይቲያችን የማኅበረሰብና የሥነ ልቦና ማዕከል ውስጥ ለሕፃናት ካንሰር ሕሙማን ከምንሠራቸው ሥራዎችና ከምንሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል የትራንስፖርት፣ የምግብና የማረፊያ፣ የምርመራ እንዲሁም የመድኃኒት ወጪዎችን መሸፈን፣ ሆስፒታል በሚተኙበት ወቅት ለጥቃቅን ወጪ መሸፈኛ በወር 500 ብር እንሰጣለን፡፡ የበሽታ መከላከል አቅማቸውን ከፍ ለማድረግ የፍራፍሬ፣ የወተት አቅርቦት እናደርጋለን፡፡ ለተመረጡ የካንሰር ሕሙማን ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶች ማሟላትና የትምህርት ክፍያ በወር 500 ብር መሸፈን፣ ሕፃናቱ በማዕከሉ በሚቆዩበት ጊዜ የተለያዩ የልጆች መጫወቻ እንዲያገኙ ማድረግ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለሕፃናት ካንሰር ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ኢበስና ብሮኖስኮፒ የተባሉ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ መሣሪያዎችንም ገዝተን አስረክበናል፡፡    

ሪፖርተር፡- ካንሰር ላይ ከትምሠሩት ሥራ በተለየ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞችን በመከላከልና በመቆጠጣጠር ረገድ ያበረከታችሁት አስተዋጽኦ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ወንዱ፡- በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች ትኩረት ሳይሰጣቸው በመቆየታቸው እጅግ ፈጣን በሆነ ሁኔታ ለመስፋፋት ዕድል አግኝተዋል፡፡ እያደገ ያለውን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባትና ሕመሞቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን አገር አቀፍ ጥረት በመደገፍ በኩል ሶሳይቲው ጉልህ ድርሻ አበርክቷል፡፡ በአገራችን ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞችን ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለው ጥረት በቂ አለመሆኑን በመገንዘብ ሰብሰቢውን ከጤና ሚኒስቴር፣ ፀሐፊውን ደግሞ ከዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ያደረገ ብሔራዊ የቴክኒክ ቡድን እንዲቋቋምና ኮሚቴው ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ሕመሞችን በመቆጣጠር ረገድ በመንግሥት አካላት በኩል የታየውን ተስፋ ሰጪ ድጋፍ ከግምት ውስጥ በማስገባት አጋር ድርጅቶችን ያሳተፈ ገንቢ ውይይቶችን በማድረግ የኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች ኅብረት እንዲቋቋም አድርገናል፡፡ የጤና ሚኒስቴር ለመጀመሪያ ጊዜ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች ቡድን እንዲያዋቅርና እንዲኖረው በማስቻል ረገድ ሶሳይቲው የላቀ ሚና ተጫውቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ካንሰርና ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞችን በመከላከልና በመቆጣጠር ከሚሠሩ ሌሎች ተቋማት ጋር ያላችሁ የሥራ ግንኙነት ምን ይመስላል?

አቶ ወንዱ፡- የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ከጤና ሚኒስቴርም ሆነ ከሌሎች ተመሳሳይ ሥራ ከሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ እየሠራ ይገኛል፡፡ ሶሳይቲው በኢትዮጵያ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ኅብረት ጋር በቅንጅት የሚሠራ ሲሆን፣ እኔም የኅብረቱ አስተባባሪ ነኝ፡፡ ኅብረቱ የኢትዮጵያ ስኳር ሕመምተኞች ማኅበር፣ የልብ ሕሙማን ማኅበር፣ የኩላሊት ሕሙማን ማኅበርና የካንሰር ሕሙማን ማኅበር በጥምረት የመሠረቱት ሲሆን፣ ከእነዚህ ማኅበራት ጋር መልካም የሥራ ግንኙነት በመፍጠር አብረን በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ሶሳይቲው ለመሥራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ያለው ምንድነው?

አቶ ወንዱ፡ ትልቁና የረዥም ጊዜ ዕቅዳችን ጤናማ የአፍሪካ የልህቀት ማዕከል መመሥረት ነው፡፡ ሕሙማን በአገራቸው መታከምና መፈወስ እየቻሉ መሞትና ወደ ውጭ አገር ለሕክምና መሄድ እንዲሁም ከአቅማቸው በላይ ገንዘብ ማውጣት የለባቸውም ብሎ ሶሳይቲያችን ያምናል፡፡ ስለሆነም ሰዎች ገንዘብ ከፍለው የሚታከሙበት፣ አቅም የሌላቸው ዜጎች ደግሞ በድጎማ ነፃ አገልግሎት የሚያገኙበት ማዕከል እንገነባለን ብለን አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ሕዝቡንና ባለሀብቱን በማስተባበር ይህንን ማዕከል እንገነባለን ብለን ስንነሳ፣ ማዕከሉ በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች ሕክምና እና በተለይም ካንሰር ላይ ዓይነተኛ ለውጥ እንደሚያመጣ ትልቅ ተስፋ ይዘንና በሙሉ ልብ በመተማን ነው፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እስከ ግለሰቦች የሚደርሰው ወገን ፈንድ

ወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሕጋዊ ዕውቅና በማግኘት ከኢትዮጵያና ከተለያዩ አገሮች ልገሳን ለማሰባሰብ ‹‹ወገን ፈንድ›› የሚባል የበይነ መረብ (ኦንላይን) የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድረ...

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...