Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ወራጅ አለ!

የዛሬው ጉዞ ከስታዲዮም ወደ ሳሪስ ነው። ከጥምቀት በዓል መልስ ኑሮን ለማሸነፍ ሁሉም ጥድፊያ ውስጥ ነው፡፡ ከተማው አሸብርቆ ሲያዩት ነዋሪው እጅግ አስደማሚ ድሎት ውስጥ ያለ ቢያስመስለውም፣ የታክሲው ወረፋና ሠልፍ ግን እንደ ክፉ ባላንጣ የሕይወታችንን ስንክሳር ሜዳ ላይ አውጥቶ ይዘረግፈዋል። ‹‹አይገርምም ግን የሰው ልጅ ለመኖር ያለው መሬት ይበቃው ነበር፣ ምን ያደርጋል ማደላደሉ ላይ አድሎአዊነት በዛ እንጂ…›› ይላል አንድ ጠውላጋ ተሳፋሪ ከመጨረሻ ወንበር። ‹‹ምን አደላዳዩ ብቻ? እኛስ ራሳችን ስኬት በገንዘብ የሰበሰብናቸው ነገሮች ድምር ውጤት እየመሰለን ካለን በላይ ስንመኝ፣ ከተሰጠን በላይ ስንጠይቅ መቼ የእነሱን ያህል እንቅልፍ ይወስደናል?›› ትለዋለች በግራ በኩል ጥጓን ይዛ የተቀመጠች ወይዘሮ። ወያላው በመሀል የተሳፋሪውን ጨዋታ ያቋርጣል፡፡ ‹‹አሥራ አምስት ብር ብቻ ነው የምትከፍሉት። እንቢ ካላችሁ ግን ይጨምራል ልብ አድርጉ…›› እያለ ያስፈራራል። ‹‹ምን ታስፈራራናልህ? እንዳንተ ዓይነቱ በዝቶ መደንገጥ ካቆምን ቆየን እኮ…›› ወዲያው ከጋቢና አንዱ ይጮህ ጀመር። ይኼን ጊዜ ከሴት ጓደኛው ጋር የተቀመጠ ወጣት፣ ‹‹አልበዛም እንዴ…›› ሲለው፣ ‹‹እናንተ ደስ ስላላችሁኝ አምስት ብር እቀንስላችኋሁ…›› ሲለው ከተሳፋሪዎች መሀል ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተቀመጠ ሌላ ወጣት፣ ‹‹እዚህ አገር እኮ ከዚህ በላይ አስቂኝ ድራማ የለም…›› አለ። ሕይወት እንደ ድራማ በሉት!

መሀል ወንበር ላይ ተደርቦ የተቀመጠ ጎልማሳ ደግሞ፣ ‹‹የሦስት ሺሕ ዓመታት ታሪክ ይዘን አሁንም ለምን ከችጋር እንደማንላቀቅ አይገባኝም…›› ይላል። ዝም ብሎ ማዳመጥ መቻል አንዳንዴ እንዴት ያለ መታደል መሰላችሁ? ከስንት ጭቅጭቅ በኋላ ታክሲያችን መንቀሳቀስ ጀምራለች። ወያላው ሒሳብ እየተቀበለ፣ ‹‹ጎበዝ ቆጥሮ ያልሰጠና ያልተቀበለ ሁለቱም ሌባ ናቸው የሚለውን ብሒል ሳትረሱ፣ በተቻለ መጠን ሒሳባችንን እየተሳሰብን ብንቀባበል ምን ይመስላችኋል…›› እያለ ማስታወቂያ ይለፍፋል። ‹‹አሁን ለእኛ አዝኖ አይመስልም? ስንት ያስገባሉ ስንት ያስወጣሉ ብሎ ሊሰልል እኮ ነው…›› ትላለች መጨረሻ ወንበር የተቀመጠች ጠይም ዓይን አፋር አላስችላት ብሏት። ‹‹ኤድያ የእኛ ደግሞ የትኛው ገቢያችንና ወጪያችን ነው የሚሰለለው? በባዶ ኪስ ኩራቴ እራቴ የሚለው ሁሉ ያለው መሰለሽ? አይምሰልሽ…›› ይላታል ከፊቷ የተቀመጠ ጎልማሳ ከፊል ወደ እሷ ዞሮ። ‹‹እኔ መቼ መሰለኝ አልኩህ፣ ሂድና ገዥዎቻችን አይምሰላችሁ በላቸው። በሰርክ ሩጫችን ኩራታችን አላንበረክከን ብሎን እንጂ ደልቶን እንዳልሆነ አስረዳቸው…›› ስትል ምሬት ያዘለ ድምጿን አሰማች። ሊጀመር ነው ደግሞ!

ሁለቱ ሲዘጋጉ ከፊታችን መሀል መቀመጫ ላይ የተቀመጡ በዕድሜ ጠና ጠና ያሉ ተሳፋሪዎች ጨዋታ ጀምረዋል። ‹‹ሰው ቀዳዳ ሲያገኝ እንደ ደጃዝማች (ስም ጠርተው) ነው የሚናገረው እባክህ…›› ይላሉ አንደኛው። ‹‹ምን አሉ ደግሞ እሳቸው? አንተ ሰውዬ እየቆየህ ስትሄድ ትውስታህ ይጨምራል…›› ይላሉ ወዳጃቸው። ‹‹ነፍሳቸውን ይማርና ደጃዝማች ከሆነ ሰው ጋር ይጋጩልሃል። ንጉሡ ለሆነ በዓል ደግሰው ድንኳን ውስጥ ሲያበሉ ደጃዝማች ጫፍ መግቢያው ላይ ተቀምጠውልሃል። ንጉሡ ያላዩ መስለው ዓይተዋል፣ ኩርፊያቸውም ገብቷቸዋል። እናም ዝናብ መጣል ጀመረ። ይኼኔ ንጉሡ ‹ደጃዝማች ወዲህ ገባ በል እንጂ፣ ዝናቡ ይመታሃል እኮ› ቢሏቸው፣ ‹ኧረ ዝናቡስ ደህና ነው እኛን ያስቸገረን ፀሐዩ ነው› አሏቸው። ይኼውልህ እዚህ ታክሲ ውስጥም አዳዲሶቹ ደጃዝማቾች አሉ ልልህ ነው…›› ብለው ሲያበቁ ሁለቱም ተያይዘው መሳቅ ጀመሩ። እኛም እንዲሁ፡፡ አንዳንዴ እኮ ወደፊትና ወደኋላ መለስ ቀለስ ስንል ስንት አስገራሚ ነገር አለ መሰላችሁ፡፡ እንዲያ ነው!

አንደኛው አዛውንት እየሳቁ ሌላ ጨዋታ ሊያመጡ ሲሉ፣ ‹‹ፋዘር እርስዎና ቢጤዎችዎ በትንሽ ገንዘብ እንደፈለጋችሁ በልታችሁ፣ ጠጥታችሁ፣ ለብሳችሁና አጊጣችሁ ኖራችሁ፡፡ አሁን ግን የሚበቃችሁ አይመስልዎትም…›› ሲላቸው ያ ወጣት በንግግሩ ደንግጠው ወደኋላ ለመዞር ሲንጠራሩ፣ ወንበሩ ሰባራ ነበርና ተኝቶ አስተኛቸው። ወያላው ቶሎ ብሎ ፌዝ በለመደ አንደበቱ፣ ‹‹ለደንበኞቻችን ምቾት አስበን ከአውሮፓ ያስመጣነው ነው። አይዞዎት አባት…›› እያለ ይወሸክታል። አዛውንቱ ግን ወያላውን ችላ ብለው፣ ‹‹የዛሬ ልጆች ትታችሁን አስቀድማችሁ የሚከተለውን ስታውቁ ስትናገሩ ታሳዝኑኛላችሁ። እርስ በርስ ብትከባበሩ እኮ አዛውንት ለማዋረድ አትሽቀዳደሙም ነበር። ከምግብና ከመጠጥ ያለፈ ትልቅ ትልም ቢኖራችሁ እኮ የጊዜውን የኑሮ ክብደት በቀላሉ ታሸንፉት ነበር። ስማ ልጄ ከትችት በፊት የነገሮችን ታሪካዊ ለመረዳት ጥረት አድርግ፡፡ እያንዳንዱ ክንውንም ሆነ ፍፃሜ መጀመሪያ እንደነበረው ለመረዳት ታሪክን መርምር…›› አሉትና ወንበራቸውን ለማቃናት ይታገሉ ጀመር። ትግል ነው የበዛው እኮ!

ውሉ የተወለጋገደ ከመሰለው ጨዋታ እኛም የተቀበልነውን ተቀብለን የተውነውን ትተን ጉዞአችን ቀጠለ። እንዲህ እንዲህ እያልን የዴሞክራሲውን ምኅዳር ሌሎቻችን ካላሰፋነው ከአንድ ወገን ብቻ እንዴት ይሰፋል? እየተጓዝን ነው። ታሪፍ ተቀንሶላቸው የተሳፈሩት ጥንዶች አንዳንድ ሲባባሉ ቆይተው ዓይናችን እያየ አፍ ለአፍ ተያይዘዋል። ‹‹ሥልጣንን ተገን አድርገው በጠራራ ፀሐይ የሚዘርፉን ሳይበቃን፣ አሳቻ ሰዓት ጠብቀው መንገድ ለመንገድ የሚላላሱ መጡ?›› ትላለች ከኋላ ጥጓን ይዛ የተቀመጠች ወይዘሮ። ‹‹አሁን ‹ኪሲንግ› መሀል መላላስን ምን አመጣው? ፍቅር ጠፋ፣ ፍቅር አነሰ፣ ፍቅር ተረሳ እያላችሁ ስንፋቀር ደግሞ መተቸት ምንድነው?›› ይላል አጠገቧ የተሰየመው ጠውላጋ። ‹‹ዘወር በል አንተ ፍቅርን እንዲህ ካለው የሥነ ምግባር ዝቅጠት ጋር አታገናኘው…›› ስትለው መንገድ እንዳገኛት ረስቶና እንደ እኩያው ቆጥሮ፣ ‹‹እንዲያው እኛ ግን ምን ይሻለናል? ስንት የሚወገዝ ነውር ሳለ፣ ዓይን ያወጣ ወስላችነት፣ ስግብግብነት፣ ምቀኝነትና አጭበርባሪነት ነግሶብን በሰው ቆዳ የምንቀበር ይመስል በሰው ፍቅር ደርሰን ድንጉር የምንለው ነገር አይገባኝም?›› አለ ለሁላችን እንደሚያወራ ሆኖ። በቀኝ በኩል ያለው ጎልማሳ ደግሞ ተቀብሎ፣ ‹‹እንደ እሱ አትልም? እነ አምታታው በከተማን የጀግንነትና የአርበኝነት ማዕረግ እየሰጠን ሌባውን ‹እሱ ይችልበታል፣ ቆራጥ ነው፣ ጀግና ነው…› ስንል በምንውልበት አፋችን ደግሞ መልሰን የሞራልና የሥነ ምግባር ጠበቆች ነን ብለን እንመፃደቃለን። ይብላኝልን ለእኛ…›› ብሎ ፊቱን አዞረ። ጉድ ነው!

ጉዟችን ወደ መገባደዱ ነው። ጥንዶቹ ከሁላችን በፊት መውረጃቸው ደርሶ ሲወርዱ፣ ሁለቱ አዛውንቶች ከሾፌሩ ጀርባ ከተቀመጠችው ወይዘሮ ጋር እያወሩ ነበር። ‹‹እኔ መቼ ለየሁሽ ብለሽ ነው? አውቃሃታል? እኛ ጋ ነው እኮ ዕቁብ የምትጥለው፡፡ ባለፈው ዕጣ የወጣላት ናት እኮ…›› ይላሉ አንደኛው አዛውንት። በጉዟችን መገባደጃ እንዲህ የሞቀ ሰላምታ ሲለዋወጡ ከወይዘሮዋ አጠገብ የተቀመጠ ተሳፋሪ ደግሞ በስልክ፣ ‹‹እኔ ከዚህ በላይ አልታገስም ብዬሃለሁ። ነገ ጠዋት ሚስቱ ፊት ነው ቤቱ ድረስ ሄጄ የማዋርደው። ገንዘቤን ይስጠኝ በቃ….›› ብሎ እንደ ኃይድሮጂን ቦምብ ለፈነዳ ተቃርቧል። ቁጣው የረበሻቸው ጋቢና ከተቀመጡ ተሳፋሪዎች አንዱ ዘወር ብሎ፣ ‹‹ወንድም ቀስ ብለህ አውራ። እኛ ቼክ አንጽፍልህ…›› አለው። በዚህ ሁሉ ጫጫታ መሀል መጨረሻ ወንበር ጥጓን ይዛ የተቀመጠች አጭር የጠይም ቆንጆ፣ ‹‹አወይ ልጅነቴ እኔስ ደርሶ ልጅነቴ እየናፈቀ አስቸገረኝ…›› ብላ ድንገት ከአፏ ሲያመልጣት በአካባቢዋ ያሉ ሁሉ ሰሟት። ‹‹እንዴት?›› ሲላት ከጎኗ ተጣቦ የተቀመጠው ጠውላጋ፣ ‹‹አታየውም ኑሯችንን፣ ደስታችን፣ ሰላማችን፣ ሳቃችን፣ ሐዘናችን፣ ጭንቀታችን ምኑ ቅጡ፣ ሁሉ ነገር ከገንዘብ ጋር ተቆራኝቶ ስታይ የምንም ነገር ባሪያ ያልሆንክበት፣ ስለምንም ነገር የማትጨነቅበት ዛሬህን ብቻ የምትኖርበት የልጅነት ዘመን አይናፍቅህም? ሰው መሆን እኮ እንዴት ያለ ክፉ ነገር መሰለህ?›› አለችው። ‹‹እዚህ ጋ ወራጅ አለ፣ አደራ የመጨረሻውን ዓረፍተ ነገር ስትደጋግሚው ሰው እየመረጥሽ፣ መጨረሻ…›› ብሎ ወያላው በሩን ከፈተው። እኛም መጨረሻችን መሆኑን አውቀን ቀስ በቀስ ‹ወራጅ አለ…› እያልን ተግተልትለን ወርደን ተበታተንን። መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት