Wednesday, May 29, 2024

የኢትዮ ሶማሌላንድ ስምምነትን ወደ እጅ አዙር ግጭት ለመቀየር የሚደረግ ሩጫ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም፣ ሉዓላዊነታችንን ጥሳለች ያሏትን ኢትዮጵያን ለመበቀል ላይ ታች ማለታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሰውየው ከካይሮ እስከ አስመራ፣ ከኡጋንዳ እስከ ጂቡቲና ዓረብ ሊግ በተለያዩ መድረኮች በአካልም በወኪልም በመገኘት ለሶማሊያ አጋሮችን ለማሰባሰብ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ የግብፆችን ድጋፍ ለማግኘት ከሰሞኑ ካይሮ በተገኙበት አጋጣሚ የተፈጠረው ሁኔታ ግን የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ እሳቸው ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ግብፅ ከሶማሊያ ጎን እንደምትቆም ብዙ ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱ መሪዎች መግለጫ በሰጡበት መድረክ አልሲሲ ሲናገሩ የተደመጠው ጉዳይ፣ ግብፆች ለሶማሊያውያን ያላቸውን ንቀትና የወረደ አመለካከት የሚያሳይ በሚል መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

የኢትዮ ሶማሌላንድ ስምምነትን ወደ እጅ አዙር ግጭት ለመቀየር የሚደረግ ሩጫ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ
መሐመድ በዓለ ሲመት ለመታደም ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ሞቃዲሾ
በተገኙበት ወቅት የሐሳብ ልውውጥ ሲያደርጉ

‹‹ወንድሜንም ሆነ ሶማሊያውያንን ማስቀየም አልፈልግም፤›› በማለት ንግግራቸውን በይቅርታ የጀመሩት አልሲሲ፣ የሶማሊያ ቀውስ እ.ኤ.አ. ከ1990 ጀምሮ ላለፉት 30 ዓመታት መዝለቁን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹አገሮች አንዴ አይውደቁ እንጂ ከወደቁ በኋላ ለመነሳት ከባድ እንደሚሆንባቸው ሶማሊያ ምሳሌ ናት፤›› ነበር ያሉት፡፡

አልሲሲ ንግግራቸውን በማስረዘም፣ ‹‹ሶማሊያ 25 ሚሊዮን ሕዝብ እያላት ኢኮኖሚዋ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ ይህች አገር በቀውስ ውስጥ ባትዳክርና ባለፉት 30 ዓመታት ኢኮኖሚዋ በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር ዕድገት ቢያስመዘግብ ኖሮ ዛሬ ዕድገቷ የት በደረሰ ነበር፤›› ሲሉ ለሶማሊያውያን ፍፁም የተቆረቆረ የሚመስል የማዋረድ ንግግር አደረጉ፡፡ ‹‹ሶማሊያ በቀውስ ስትዳክር ብዙ የማደግ ዕድልን አጥታለች፣ ዛሬ ከዜሮ በመነሳት እንደ አዲስ ራሷን እየገነባች ነው፤›› ሲሉ የተደመጡት አልሲሲ፣ ለሶማሊያ የወገኑ መስለው ጉራና ተመፃዳቂነት የተሞላበት ሐዘኔታ ማሳየታቸውን ብዙዎች መታዘባቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ላይ ጠላት ለማሰባሰብ ካይሮ ያቀኑት የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ከዚያ ይልቅ፣ የራሳቸውንም የአገራቸውንም ክብር የሚያዋርድ የለበጣ ከንፈር መጠጣ አፍርተው መመለሳቸውን ብዙዎች እየገለጹ ነው፡፡

ለዚህ የሶማሊያ መሪ ላይ ታች ማለትና ግብፅ ድረስ ሄዶ መዋረድ በተለያዩ መንገዶች መልስ እየሰጡ ያሉት የሶማሌላንድ ሰዎች በበኩላቸው፣ የሶማሊያ ባለሥልጣናት መዋረድ ልምዳቸው መሆኑን በመጥቀስ እየተሳለቁባቸው ነው፡፡ የሶማሌላንድ ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ለመፈጸምም ሆነ በጋራ ለመሥራት የሶማሊያ ፈቃድም ሆነ ድጋፍ እንደማያሻቸው በይፋ እየገለጹ ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንት አልሲሲ ግብፅ ከሶማሊያ ጋር ተባብራ ፀረ ኢትዮጵያ ዕርምጃ እንደምትወስድ ቃል በገቡ፣ እንዲሁም ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ግብፅ የሶማሊያ ሉዓላዊነት እንዳይደፈር ላደረገችልን ያልተቆጠበ ድጋፍ እናመሠግናለን ብለው በተናገሩ ማግሥት፣ የሶማሌላንድ  መንግሥት የሁለቱንም አፍ የሚያዘጋ የምላሽ መግለጫ ነበር ያወጣው፡፡ 

ከትናንት በስቲያ የወጣው የሶማሌላንድ መንግሥት መግለጫ፣ ግብፆች በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ጉዳይ ተጨንቀውና ተጠበው ከሶማሊያ ጋር እንነጋገር ማለታቸውን በቅን ልቦና እንደሚመለከተው በመጥቀስ ነው ሀተታውን የጀመረው፡፡

የሶማሌላንድ መንግሥት በዚህ መግለጫው ሲቀጥልም፣ የሶማሌላንድ ጉዳይን  ለሶማሌላንዶች መተው በጣም አስፈላጊ እንደሆነ አስምሮበታል፡፡ ‹‹በዚህ ጉዳይ ፍላጎት አድሮብናል  የምትሉ ሁሉ እሱን ተውትና ጎረቤታችሁ ባለው እንደ የሱዳን፣ የሊቢያና የጋዛ ቀውስ በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጋችሁ ብትተጉ የተሻለ ነው፤›› ሲል ነው መግለጫው ከሶማሊያ ጀርባ አለን ለሚሉት ግብፆች ጠንከር ያለ አፀፋ የሰጠው፡፡

ሶማሌላንዶች ከኢትዮጵያ ጋር ያደረግነውን ስምምነት በሚመለከት፣ ሶማሊያውያንም ሆኑ ከጀርባ ሆነው የሚነዷቸው ግብፆችና ሌሎች የውጪ ኃይሎች እንደማያገባቸው ፍርጥም ያለ አቋም በማንፀባረቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢሳ ከይድ (ዶ/ር) አገራቸው የማንንም የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበል አጠንክረው ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሩ ለሶማሌያውያንና በጉዳዩ ያገባናል እያሉ ላሉ ሁሉ ‹‹ይውጣላችሁ›› በሚል ይመስላል፣ በሶማሊያና በሶማሌላንድ መካከል በሕግ የፀደቀ አንድነት ኖሮ እንደማያውቅ በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ይፋ አድርገዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይፋ ያደረጉት መግለጫ፣ ‹‹እ.ኤ.አ. በ1960 የተደረገውን ሕገወጥ ውህደት አንቀበለውም፡፡ በ1961 በወጣው ሕገ መንግሥት ሶማሌላንድ ያቀረበችው የሕግ ውሳኔ ውድቅ ተደርጎ የሶማሊያ ፍላጎት ነው የፀደቀው፤›› በማለት ያስረዳል፡፡

መግለጫው በሕገወጥ መንገድ ከሶማሊያ ጋር እንድትዋሀድ በተደረገችው ሶማሌላንድ እ.ኤ.አ. በ1988 በተነሳ የሕዝብ ተቃውሞና የነፃነት ጥያቄ ሳቢያ፣ የሶማሊያ መንግሥት 50,000 ንፁኃን ዜጎችን በመግደል በሶማሌላንድ ላይ ታሪክ የማይረሳው የዘር ማጥፋት ወንጀል ስለመፈጸሙም ይዘረዝራል፡፡

‹‹እ.ኤ.አ. 1991 በተካሄደው በቡርኮ ኮንፈረንስ፣ እንዲሁም በሕዝበ ውሳኔ 97 በመቶ የሶማሌላንድ ሕዝቦች ነፃነትን እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ግንቦት 31 ቀን 2011 ከሕገ መንግሥቱ ጎን መቆማቸውን አንፀባርቀዋል፤›› በማለትም ይኼው መግለጫ ይዘረዝራል፡፡

ሶማሌላንድ እንደ አገር ሉዓላዊና ነፃ ሆና ለመቆም ብዙ መሥፈርቶችን ብታሟላም ዓለም ዕውቅና ሳይሰጣት ለ33 ዓመታት መዝለቋን በርካቶች በይፋ እየተናገሩ ነው፡፡

የሶማሌላንድ ዕውቅና ጉዳይን በተመለከተ ከሰሞኑ በአልጄዚራ ኢንሳይድ ስቶሪ ፕሮግራም ላይ የተናገሩት የቀድሞ የአፍሪካ ቀንድ የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ዳይሬክተርና የሳሀን ጥናት ተቋም ስትራቴጂካዊ አማካሪው ማት ብራይደን፣ መላው ዓለም ሊጠይቀው የሚገባ ጉዳይ አንስተዋል፡፡

‹‹ከሶማሊያ ጋር መስማማት ወይም ግንኙነት ማጠናከር ዓለም አቀፍ ሕግ፣ ወግና ልማድ መጣስ ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡ ይሁን እንጂ የቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ካበቃበት እ.ኤ.አ. 1960 ጀምሮ ብዙ አዳዲስ የዓለም አገሮች እየተፈጠሩ ናቸው፡፡ ሶማሌላንድ ከሶማሊያ ተዋህዳ ከኖረችበት ጊዜ በላይ ለሆኑ ዓመታት ተገንጥላ ቆይታለች፡፡ በሕግም በፖለቲካም ከሄድን ሶማሌላንድ አገር የመሆን ተክለ ቁመና አላት፡፡ ከኤርትራም፣ ከደቡብ ሱዳንም በተሻለ አገር የመሆን መሥፈርትን ታሟላለች፡፡ ሶማሌላንድ ልገንጠል ከምትልበት ከእናት አገር ሶማሊያ ድጋፍ ከማጣቷ በዘለለ፣ አገር ለመሆን የማታሟላው መሥፈርት የለም፤›› በማለት ነበር ማት ብራይደን ያስረዱት፡፡

ከግብፅና ከኤርትራ ጉብኝት መልስ ኢትዮጵያ ላይ የጂኦ ፖለቲካ ጫና ለመፍጠር እየሞከሩ ያሉት የሶማሊያ ፕሬዚዳንት፣ ‹‹ማንም ሶማሊያን ቆርሶ እንዲወስድ አንፈቅድም፡፡ አባቶቻችንም አልፈቀዱም፣ እኛም አንፈቅድም፤›› በማለት ከሰሞኑ ሲፎክሩ ተደምጠዋል፡፡

የሶማሊያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሳላ ጁማ በበኩላቸው ይህን አቋም ከፍ አድርገው፣ ‹‹ወደ እጅ አዙር ጦርነት እንድንገባ ኢትዮጵያ እያስገደደችን ነው፤›› የሚል ይዘት ያለው ንግግር አድርገዋል፡፡ ሰውየው ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት በአስቸኳይ ካልቀደደች ሲሉም ዝተዋል፡፡

‹‹ለወትሮው በግጭት፣ በብሔር ፖለቲካ አክራሪነት፣ በምግብ እጥረት፣ በአየር ንብረት ለውጥና በሌላም ችግሮች የሚሰቃየው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በኢትዮጵያ ዕርምጃ የተነሳ ወደ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ግጭት ሊገባ ይችላል፡፡ በአልሸባብ ሽብር ቡድን ቀጣናው በሚታመስበት በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ በንዝህላልነት ከሶማሌላንድ ጋር ስምምነት መፈረሟ ከአፍሪካ ቀንድ አልፎ በትሪሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ንግድ የሚፈስበትን የቀይ ባህር ባብኤል መንደብ መተላለፊያ ደኅንነት ጭምር አደጋ ላይ የሚጥል ነው፡፡ ችግሩ ካልተቀለበሰ የእጅ አዙር ግጭት በተፎካካሪ ኃይሎች መካከል የሚያስከትል ነው፤›› በማለት መናገራቸው ታውቋል፡፡

ከሰሞኑ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የባህር በር ስምምነት መፈረሟን ተከትሎ በጉዳዩ ተናደናል ያሉት ሶማሊያውያኑ ብቻ ሳይሆኑ፣ ያደፈጡ ኃይሎችም ጎራ ለይተው መቆም መጀመራቸው እየተነገረ ነው፡፡ ከሶማሊያ ጋር በግልጽ የመቆም ዝንባሌ ያሳየችው ኤርትራ በሱዳን ጉዳይ ደግሞ የበለጠ እየገባችበት መሆኗን እያሳየች ነው፡፡

ከሰሞኑ ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ምክትል ኃላፊ ከማሊክ አጋር ጋር ኤርትራ ውስጥ የተገናኙት የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ለሱዳን ፀጥታና ደኅንነት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ ሱዳንና ኤርትራ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ወደ አልጀዚራ ግዛት መግባቱ፣ እንዲሁም በምሥራቃዊ ሱዳን ግዛቶች ጥቃት ማፋፋሙ እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል፡፡

ኤርትራ ከሱዳን ጋር የምትዋሰንባቸው እንደ ገዳሪፍና ከሰላ ያሉ አካባቢዎች የፀጥታ ሥጋት እየገጠማቸው መሆኑን በአሳሳቢነት ታወሳለች፡፡ ይህን የሚጋሩት የሱዳን ባለሥልጣናትም ከኤርትራ ጋር በፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ተባብሮ መሥራትን እንደመረጡ ተናግረዋል፡፡ 

በአንዳንድ ሪፖርቶች ኤርትራ የሱዳን መንግሥት ኃይሎችን በወታደራዊ ሥልጠና እየደገፈች መሆኗን እይገለጹ ነው፡፡

ሱዳን ከሰሞኑ ከኢራን ጋር አቋርጣው የነበረውን ግንኙነት ዳግም ለመቀጠል መስማማቷ ታውቋል፡፡ ሁለቱ አገሮች ኤምባሲዎቻቸውን ዳግም ለመክፈት መስማማታቸውም ተነግሯል፡፡

በሱዳን በሁለቱ ተፋላሚ ኃይላት ማለትም በሱዳን ጦር መሪ ጄኔራል አብዱልፈታ አል ቡርሃንና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በጄኔራል መሐመድ ሀምዳን ደጋሎ (ሄሜቲ) ጦርነት በቀጠለበት በዚህ ወቅት፣ እንደ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ግብፅና ሳዑዲ ዓረቢያ የመሳሰሉ የውጭ ኃይሎች  ጎራ እየለዩ ከተፋላሚዎቹ ጀርባ መቆማቸው ይነገራል፡፡ በሱዳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጦርነቱ ኤርትራና ኢትዮጵያን በምትዋሰንበት ምሥራቃዊ ክፍል እያጋደለ ነው ይባላል፡፡

በዚህ የሱዳን ምሥራቃዊ ክፍል ደግሞ ለወትሮም ከማዕከላዊው የሱዳን መንግሥት ጋር ልል ግንኙነት ያላቸውና ከፊል ራስ ገዝነት ይዘው የቆዩ የቤጃ ሕዝቦች የሚኖሩበት ነው፡፡ እንደ ቤኒ አሚ፣ አል ሀባብ፣ አል ቢሻሪ፣ አል ደማር፣ አል ዲባኒያ፣ አል ሱሌይሀብ፣ አል ባዋዳል፣ አል ላህዊንና አል ጀሚላብ የመሳሰሉ የቤጃ ሕዝቦች በምሥራቅ ሱዳን የሚኖሩ ሲሆን፣ ወቅት እየጠበቁ በሦስቱ አገሮች ድንበሮች የሚዘዋወሩ አርብቶ አደሮች መሆናቸው ይነገራል፡፡

የውጭ ኃይሎች በሱዳን ጦርነት እያደረጉ ያሉት ጣልቃ ገብነት ተጨምሮበት በሱዳን፣ በኤርትራና በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ እየጨመረ የመጣው ውጥረት  ቀጣናዊ ግጭት ያስከትላል የሚል ሥጋት ተፈጥሯል፡፡

በሌላ በኩል ኤርትራም ሆነች ሱዳን  ከኢትዮጵያ ጋር ሆድና ጀርባ መሆናቸው፣ እንዲሁም ኤርትራ የሱዳን ኃይሎችን ማሠልጠንና ማስታጠቅ መጀመሯ ተጨምሮበት ቀጣናዊ ቀውስ በአካባቢው እንዳይቀሰቀስ እየተሠጋ ነው፡፡

ያም ቢሆን ግን ከሰሞኑ ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ ለሆነ የውጭ ወታደራዊ አታሼዎች፣ የወቅቱን የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ ጉዳይ በተመለከተ ገለጻ ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዋ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) የኢትዮጵያን አቋም ግልጽ አድርገዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ የባህር ኃይል ትንሳዔ በቀይ ባህር ላይ በሚገነባው የባህር ኃይል ጦር ሠፈር ይበሰራል፤›› ሲሉ የተናገሩት ሬድዋን (አምባሳደር) ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ለመስማማት የማንንም ፈቃድ እንደማትጠይቅ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሱዳን በተፈጠረው ቀውስና ከሶማሊያ ጋር የተፈጠረውን ፍጥጫ ተከትሎ በኢትዮጵያና በዙሪያዋ የእጅ አዙር ጂኦ ፖለቲካዊ ቀውስ ይከሰታል ተብሎ እየተሠጋ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የመጣው ይምጣ ያለ ይመስላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -