Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢዜማ 185 አባላቱ ያለ በቂ ምክንያት መታሰራቸውን አስታወቀ

ኢዜማ 185 አባላቱ ያለ በቂ ምክንያት መታሰራቸውን አስታወቀ

ቀን:

  • የዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት አሳስቦኛል ብሏል

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ከመስከረም 2016 ዓ.ም. ወዲህ 185 አባላቱ ያለ በቂ ምክንያት መታሰራቸውን አስታወቀ፡፡

ኢዜማ ይህንን የገለጸው የዜጎች የሰላም ደኅንነት፣ የሰዎች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይዞታ፣ እንዲሁም በአገሪቱ የተከሰቱትን ግጭቶችና ድርቅ አስመልክቶ ሐሙስ ጥር 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ 

መንግሥት የጠራ አቋም ይዞ ሰላም ባለማስከበሩ ምክንያት ዜጎች በተለያዩ አካባቢዎች እየሞቱና ለእስር እየተዳረጉ መሆኑን፣ ኢዜማ በተጨባጭ ለመለየት መቻሉን አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

መንግሥት ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ አፅንኦት ሰጥቶ መከታተል እንዳለበት የገለጸው ፓርቲው፣ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን ዜጎች ያለ ምንም ምክንያት ታፍሰው ለእስር መዳረጋቸውን ካሰባሰብኩት መረጃ ለማወቅ ችያለሁ ብሏል፡፡

በኢትዮጵያ በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መሆናቸውን፣ መንግሥትም ሰላምን ለማስፈን የሚያደርገው ጥረት ቁርጠኝነት የሚታይበት እንዳልሆነ የኢዜማ ድርጅት ጉዳይ መምርያ ኃላፊ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት፣ ድርቅና ሌሎች ችግሮች የተፈጠሩት ከሰላም ዕጦት እንደሆነ ኃላፊው ጠቅሰው ሰላም ሳይኖር ስለልማት፣ ስለኢኮኖሚና ስለዴሞክራሲ ማውራት ከቅንጦት እንደማይተናነስ አስረድተዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው መሥራት የማይችሉበት፣ ሃይማኖታዊ በዓላትን እንኳን ማክበር የተቸገሩበት ሁኔታ መፈጠሩን አክለው ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶችም ቢታዩ ዜጎች ምን ያህል በአስጨናቂ የሰላምና ደኅንነት ዕጦት አደጋ ውስጥ እንዳሉ መገንዘብ እንደሚቻል፣ ለአብነትም በጋምቤላ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎችና በሌሎች አካባቢዎች ግጭት በመፈጠሩ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን ወደ ሰላም መቀየር ካልተቻለ አሸናፊ እንደሌለ ገልጸው፣ መንግሥት በዘፈቀደ ግጭቶችን አስቆማለሁ ካለ የበለጠ እንደሚስፋፉ ጠቁመዋል፡፡

በትግራይ ክልል ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ማሳወቁን፣ ነገር ግን መንግሥት ለችግሩ ዕውቅና ሰጥቶ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ቁጥር ላይ መሠረት በማድረጉ፣ ከክልሉ አስተዳደር ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ መግባቱን ኢዜማ በመግለጫው ገልጿል፡፡

መንግሥት በኃይል ግጭትን መፍታት እንደማይችል ከዚህ በፊትም የነበረው ግጭት ማሳያ እንደነበር የገለጹት አቶ ዋስይሁን፣ እስካሁን የተከፈለው ዋጋ እንደሚበቃና መንግሥት ችግሮችን በድርድር መፍታት አለበት የሚል አቋም ፓርቲው መያዙን ተናግረዋል፡፡

ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋተፅኦ ከሚኖራቸው ጉዳዮች መካከል ሰላም አንዱ እንደሆነ መንግሥት ተረድቶ፣ ግጭቶችን በውይይት መፍታት ይኖርበታል ያሉት የኢዜማ ሕግና ደኅንነት መምርያ ኃላፊ አቶ ሥዩም መንገሻ ናቸው፡፡

መንግሥት በፀጥታ መዋቅር ውስጥ ያለውን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ በሚገባ መርምሮ፣ አስቸኳይ የመፍትሔ ሐሳቦችን ይዞ መቅረብ እንዳለበት አክለው ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 172፣ በኦሮሚያ ክልል 11፣ በአዲስ አበባ ከተማ አንድ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አንድ፣ በአጠቃላይ 185 የኢዜማ አባላቱ መታሰራቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...