Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በሚያገኙት ትርፍ ላይ ብቻ ያነጣጠሩ የሪልስቴት አልሚዎችን መንግሥት አንድ ይበልልን!

ጥቂት የማይባሉ ፕሮጀክቶች ግንባታ መስተጓጎላቸው እውነት ቢሆንም በግንባታ ላይ የሚገኙ የመንግሥትም ሆነ የግል ግንባታዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ተደራራቢ ጫናዎች ያሉበትም ቢሆንም አቅም በፈቀደ መጠን ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ በግል ዘርፉ እየተካሄዱ ካሉ ሥራዎች መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጎልቶ ዕየታየ ያለውን የሪልስቴት ግንባታ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በርካታ የሪልስቴት ማስታወቂያዎች አየሩን መያዛቸውም የሚነግረን ነገር አለ፡፡ በሚያማልሉ ቃላት የተዋቀሩት የሪልስቴት ማስታወቂያዎችና መሬት ላይ ያለው እውነታ ምን ያህል ይጣጣማል የሚለው ጥያቄ ግን ብዙ ሊያነጋግር ይችላል፡፡

ከዚህ ባሻገር ግንባታቹ አልሚውና ቤት ገዥው በተዋዋሉት ውል በመሠራት የተባለውን የጥራት ደረጃ ይዘው በተዋዋሉት ውል መሠረት በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ያለመተላለፋቸው ጉዳይ የዘርፉ ያልተፈታ ችግር ሆኖ ዘልቋል፡፡ 

ሰሞኑን ከአንድ ዘርፉን በደንብ ያውቃል ከሚባል አንድ የምህንድስና ባለሙያ ጋር ስናወጋ የሪልስቴት ዘርፉ በርካታ ችግሮች ያሉበት መሆኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡ የሪልስቴት ግንባታውን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የኮንስትራክሽን ግንባታዎች የጥራት ደረጃ አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ መድረሱን እንድገነዘብ አድርጎኛል፡፡ ከግንባታ ጥራት ጋር ተያይዞ ያለው ችግር በርካታ ምክንያቶች እንዳሉትም ገልጾልኛል፡፡ ለግንባታዎች ጥራት መጓደል አንዱ የግንባታ ዕቃዎች እጥረትና የዋጋ መወደድ ነው፡፡

በተለይ የሲሚንቶ ጉዳይ የግንባታ ዘርፉን በእጅጉ ጎድቷል፡፡ ሲሚንቶ የጥቂቶች መከበሪያ መሆኑ አሁንም ያልተቀረፈ በመሆኑ አንዳንድ አልሚዎች ግንባታዎቻቸውን ከደረጃ በታች እንዲገነቡ ሰበብ እየሆናቸው መምጣቱንም እንድገነዘብ አድርጎኛል፡፡ እንኳን እጥረት ኖሮ በደናውም ጊዜ ግንባታዎች በሚጠይቀው መሥፈርት ልክ ግብዓቶችን በአግባቡ ያለመጠወቀም ችግሮች ይታዩ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን የሲሚንቶና የሌሎች ምርቶች ዋጋ መናር ችግሩን አብሶታል፡፡

ይህ ችግር በተለይ በግል እየተገነቡ ባሉ ሪልስቴት አልሚዎች ላይ የሚታይ መሆኑን ከሥራው ባህሪ አንፃር የገጠሙትን ‹‹አሳፋሪ›› ያላቸውን ተግባራትም ይኸው መረጃ በምሳሌ እየጠቀሰ ሁሉ ሲያብራራልኝ በዚህ አገር የማይሸፈንበት የሥራ ዘርፍ የለም ማለት ነው? እንድንል አድርጎናል፡፡

ዛሬ እንደ አሸን የፈሉትና በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ማስታወቂያዎቻቸው ከሚሰሙ የሪልስቴት አልሚዎች መካከል ጥቂት የማይባሉት የግንባታ ሒደት፣ የሚያስነግሩትን ማስታወቂያና የሚጠየቁትን ገንዘብ የሚመጥን አይደለም፡፡

አንድ ቤት ገዥ ይገነባል ተብሎ የሚሰጠው ዲዛይንና የግንባታው በምን ያህል የጥራት ደረጃ እንደሚገነባለት የሚገለጽለት በውሉ ውስጥም ይኸው የሚካተት ቢሆንም አንዳንድ አልሚዎች ግን ይህንን አይተገብሩትም፡፡ 

ትልቁ ሥጋት ግን ችግሩ ቤት ገዥዎቹ በላይ ነው፡፡ ከሙያ ሥነ ምግባር ያፈነገጠ ተግባር ላይ የተሠማሩት እነዚህ የሪልስቴት አልሚዎች የሚያካሂዱት ግንባታ የጥራት ደረጃውን ያልጠበቀ መሆን ወደፊት ትልቅ ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም የሚል ነው፡፡ 

ቤት ገዥዎች የሚጠየቁትን ከፍተኛ ያውም የተጋነነው የሚባል ዋጋን የሚመጥን ቤት አለማግኘታቸው በራሱ አግባብ ባይሆንም ደረጃውን ባልጠበቀ መንገድ እየተካሄዱ ያሉ ግንባታዎች ጉዳቱ ለሌሎችም የሚተርፍ መሆኑ ሊያሳስበን ይገባል፡፡

ኃላፊነት በማይሰማቸውና የሚያገኙትን ትርፍ ላይ ብቻ ያነጣጠሩ ናቸው የሚባሉት እነዚህ የሪልስቴት ገንቢዎች የግንባታ ሒደታቸውን የሚቆጣጠር ያለ አይመስልም፡፡ 12 ሚሊ ሜትር ፌሮ ያስፈልገው የነበረ ኮንክሪት በስድስት ሳንቲ ሜትር ሊሠራ ይችላል፡፡

በዲዛይኑ መሠረት አሥር ኩንታል ይጠይቅ የነበረ አንድ የኮንክሪት ሙሌት በአምስት ኩንታል ሊሞላ የሚችልበት ሁኔታ ሁሉ እያጋጠመ ነው፡፡ ብራንድ ተመርጦ በዚህ ይሠራ የተባለ የግንባታው ክፍል ደረጃውን ባልጠበቀ ተመሳሳይ ምርት እንዲተካ ሁሉ ይደረጋል፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር ብዙ ቦታ የሚስተዋል ሲሆን የግብዓቶች መወደድና እጥረት ችግሮችን አብሷል ቢባልም የቁጥጥሩ መጓደል ደግሞ በአግባቡ ይሠራሉ የሚባሉትንም ወደዚህ ያልተገባ ተግባር እንዲገቡ እያደረጋቸው ነው፡፡

የሲሚንቶ እጥረት ጎልቶ በታየባቸው ጊዜያት አንዳንድ ግንባታዎች ሲሚንቶን ለማብቃቃት ሲጠቀሙበት የነበረው ያልተገባ ተግባር በቅርብ ተረድቶ ዕርምጃ የወሰደ የለም፡፡  ይህ ያለመሆኑ ደግሞ በዚህ መንገድ የተገነባ ሕንፃ ዕድሜ ሊኖረው አለመቻሉ ብቻ ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑ ሲታሰብ ጉዳቱን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ 

ለዚህም ነው የግንባታ ቁጥጥር ሥራ የቅርብ ክትትል ሊደረግበት ይገባል የሚባለው፡፡ ግንባታዎች በየደረጃው በገለልተኛ ባለሙያዎች ተፈትሸው ቀጣይ ሥራቸው እንዲቀጥል ይህንኑ መስጠት ሲገባው ይህ እየተደረገ አይደለም፡፡

ከባለሙያው የተረዳሁትም ይህንኑ ነው፡፡ የጉዳዩን አሳሳቢነት አጉልቶ ያሳየኝ ደግሞ በቅርቡ በሁለት የሪልስቴት አልሚዎችና በሠራተኞቻቸው መካከል እየተፈጠረ ያለው ችግር ነው፡፡

ሠራተኞቹ እየገነቡት ላለው ሪልስቴት መጠቀም ያለባቸው የሲሚንቶ መጠን ከሚያውቁት ልኬት በታች ሲሆንባቸው ሌላ አፈር መሰል ግብዓት ደባልቀው እንዲጠቀሙ በመታዘዛቸው ምክንያት የተፈጠረው አለመግባባት ሥራ እስከማቆም ያደርሳቸዋል፡፡

በተነገራቸው መንገድ መሥራት አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ አንሠራም ይላሉ፡፡ ይኼኔ አሠሪዎች ከሥራ ሲያግዷቸው ሠራተኞቹ ጉዳዩን በማኅበራቸው በኩል ይመለከተዋል ላሉት አካል በማቅረብ እየተሟገቱ ነው፡፡ ጉዳዩ አሁንም በእንጥልጥል ላይ እንደሆነም አስረዳኝ፡፡

የግንባታ ሥራዎች እንዲህ ባለ ደረጃ እየተገለጹ ከሆነ በእርግጥም አደጋ ውስጥ ነን፡፡ የግንባታ ሥራዎችን የሚቆጣጠሩ ተቋማት የሚመለከታቸው አካል ከዚህ በኋላ እጅን አጣምረው መቀመጥ የሌለባቸው መሆኑንም ይጠቁመናል፡፡ ከተኙበት መንቃት አለባቸው፡፡ አውቀው ተኝተው ከሆነም ትልቅ ስህተት እየሠሩ መሆኑን ሊያውቁ ይገባል፡፡ ይህንን ካደረጉ ደረጃውን ባልጠበቀ ሁኔታ የሚካሄዱ ግንባታዎች ለሚያደርሱት አደጋ ተጠያቂዎች ይሆናሉ፡፡ 

የግንባታ ጥራት በሪልስቴት ላይ ብቻ የሚንፀባረቅ አይደለም፡፡ የቆየ ችግር ነው፡፡ ሌሎች ግንባታዎችም በተመሳሳይ መንገድ የሚገለጹና እነሱም ቁጥጥር የሚያሻቸው ናቸው፡፡ የግል ሕንፃ ስለሆነ በዲዛይኑ ከሚጠበቀው ደረጃ በታች በሆኑ ግብዓቶች እንዲገነቡ የሚፈቅድ ሕግ የለም፡፡

ሕንፃው የግል ቢሆንም ግልጋሎት የሚሰጠው ለሕዝብ እስከሆነ ድረስ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ መገንባት አለ፡፡ የግንባታ ቁጥጥርን የተመለከተ ሕግ የወጣው፣ ተቋም የተደራጀውና ባለሙያዎች የተመደቡት ጉዳዩ የወል በመሆኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ በኃላፊነና በአግባቡ የሚሠሩ አልሚዎች እንዳሉ ግን መግለጽ ያስፈልጋል፡፡

ነገር ግን ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር ሁሉም ግንባታዎች ሕግን መሠረት ያደረገ፣ የከተማዋንም ገጽታ ከግምት ያስገባ እንዲሁም ተገልጋይን ሥጋት ላይ በማይጥል መልኩ ስለመሥራታቸው ማረጋገጥ ግዴታ ነው፡፡ በዚህም አሠራር ችግር ያለበትን ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲገነባ ማድረግ በአግባቡ የሚሠራውን ደግሞ ዕውቅና መስጠት ቢቻል ነገ የሚገጥመንን ችግሮች መቀነስ ወይም ማስቀረት ይቻላል፡፡ 

ከሪልስቴት አልሚዎች ከፍተኛ ገንዘብ አውጥቶ የሚገዛው ቤት ፈላጊም ገንዘቡን ትክክለኛ ቦታ እንዲያውል ያግዛል ስለዚህ አሁን ላይ የግንባታ ሥራዎች ቁጥጥር የተዘነጋ ይመስላልና ትኩረት ይደረግበት፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት