Monday, April 15, 2024

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ፈተናዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በ54ኛው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ የቀረቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ተለዋዋጭነት በበዛበት የዓለም ፖለቲካ መድረክ የአፍሪካን ብሎም የኢትዮጵያን ሚና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አቅርበዋል፡፡ በዓለም አቀፍ መድረኮችም ሆነ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች የአፍሪካ ብሎም የኢትዮጵያ ድርሻ ምን እንደሆነ አቶ ደመቀ ዝርዝር ሐሳቦች አንስተዋል፡፡

ብዙ ኃያላን አገሮች ባሉበት ዓለም ኢትዮጵያና አፍሪካ ምን መጫወት ይችላሉ ተብለው አቶ ደመቀ ሲጠየቁ፣ ‹‹ያለንበት ዘመን ብዙ አገሮች በዓለም መድረክ ያላቸው ተፅዕኖ እየጎላ የመጣበት ነው፣ ይህንን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ በደኅንነት አቅም፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አቅም፣ በኢኮኖሚ አቅም የሚገለጽ ነው፡፡ በየዘርፉና በየፈርጁ ጠንካራ አቅም የፈጠሩ አገሮች አሉ፡፡ አፍሪካ ዕምቅ አቅም ያለው አኅጉር ነው፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ደግሞ ልቀው እየወጡና በዓለም መድረክ ተፅዕኗቸውን እያሰፉ ነው፡፡ ይህ ለውጥ በሁለቱ መካከል ማለትም በአፍሪካና እየገዘፉ ባሉ ፈጣን አዳጊ አገሮች መካከል የደቡብ ለደቡብ ግንኙነት ለማጠናከር ወቅቱም ሆነ ሁኔታው የተመቸ ነው፡፡ አፍሪካ ለመጭው ዘመን ዓለም አቀፍ ፉክክር መዘጋጀት አለባት፡፡ በዲጂታል ቴክኖሎጂም ሆነ በኢኮኖሚ ራሷን አጠናክራ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖዋን ማሳደግ መቻል አለባት፤›› በማለት ነበር አቶ ደመቀ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በነበረው ታሪኳ ከራሷ አልፋ የአፍሪካዊያንን ጥቅም ለማስከበር በዓለም መድረክ ተሟጋች እንደ ነበረች በስፋት ይነገራል፡፡ ሆኖም ዛሬ አገሪቱ እንኳን የአፍሪካ አኅጉርን ቀርቶ የራሷን የዲፕሎማሲ ጥቅሞች በዓለም አደባባዮች ለማስጠበቅ እየተፈተነች መሆኑም ይተቻል፡፡

ከሰሞኑ በኢጋንዳ ካምፓላ በተደረገው የኢጋድ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ሳትችል የቀረችው ኢትዮጵያ፣ ሌላው ቀርቶ በቀጥታ የራሷን ጥቅሞችና ጉዳዮች በተመለከተ እንኳን በዓለም መድረክ ቀርቦ ለመሟገት ወኔና አቅሙን እያጣች መጥታለች በሚል እየተተቸች ነው፡፡

የኢጋዱ ስብሰባ ያውም የወቅቱ የሶማሊያና የኢትዮጵያን ፍጥጫ የተመለከተ ሆኖ ሳለ፣ ኢትዮጵያ በዚህ ስብሰባ ተገኝታ አቋሟን መግለጽ ያልቻለችበት አጋጣሚን እንደ ሽንፈት የቆጠሩት ብዙዎች ናቸው፡፡

አንጋፋው የሚሊታሪና የዲፕሎማሲ ሰው ፍሰሐ አስፋው (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ እንደ ኢጋድ ካሉ ቀጣናዊ የዲፕሎማሲ መድረኮች መቅረቷን በዲፕሎማሲ ስህተትነት ያወሱታል፡፡ ‹‹በቀደም የኢጋድ ስብሰባ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ግን አልሄድም ብላ ቀርታለች፤›› በማለት ያስታወሱት ፍሰሐ (ዶ/ር)፣ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ብቻ ሳይሆን በቀጣናዊ መድረኮች ጭምር ተሰሚነትና የቀደመ ሚናዋን እያጣች እንደመጣች ተናግረዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የድሮዋ ኢትዮጵያ ብትሆን ኖሮ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችን ባሸማገለች ነበር፡፡ አሁን እኮ ኢትዮጵያ ካለች አንደራደርም የሚሉ ኃይሎች በአካባቢያችን ተፈጥረዋል፤›› የሚሉት ፍሰሐ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተሰሚነቷንና ተደማጭነቷን ማጣቷን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት በዲፕሎማሲው ረገደ ከባድ ፈተና እንደገጠማት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔርና አንጋፋ ዲፕሎማት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጭምር በቅርቡ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ‹‹የቀደመ የዲፕሎማሲ ታሪካችን አንፀባራቂ ገድል ያለው ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ በቀደመ ታሪክ ከመኩራራት በዘለለ በነበረው ላይ ጠንካራ ሥራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ባለፉት ዓመታት ዲፕሎማሲው ፈተና እነዳጋጠመው በማውሳትም ይህን መቀየር ይገባል ብለዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም (አምባሳደር) ከሰሞኑ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ ይህንኑ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የገጠመውን ፈተና አንስተው ነበር፡፡

‹‹የዲፕሎማሲ ሥራችን ውጤት የሚለካው በአንድ ነገር ነው፡፡ ብሔራዊ ጥቅማችንን በማስጠበቅ ረገድ በምናገኘው ውጤት ነው፤›› በማለት የተናገሩት መለስ (አምባሳደር)፣ በዚህ ረገድ ትጋት ያለውና ውጤታማ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በቅርቡ የገጠማትን የዲፕሎማሲ ፍጥጫ ለመፍታት ለንግግር ዝግጁ እንደሆነች ማስታወቋን ቃል አቀባዩ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ይህ አገር ትልቅ አገር ነው በሲኒ ውስጥ ባለ ማዕበል አይናጥም፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ያለፍንበትን ሁኔታ ሌሎች አገሮች ያለፉበታል ብላችሁ እንዳትገምቱ፤›› ሲሉም አገሪቱ የገባችበትን የውጭ ጫናና የዲፕሎማሲ ፈተና ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልል ጦርነት ከፈነዳ ጊዜ ጀምሮ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለ14 ጊዜያት በታላቁ ህዳሴ ግድብና በጦርነቱ ጉዳዮች እየተከሰሰች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ፊት የቀረበችው ኢትዮጵያ፣ በዲፕሎማሲው ባለፉት ዓመታት ፈተና አጋጥሟታል የሚለውን ብዙዎች ይጋሩታል፡፡ ከሶማሊያ ጋር በገባችበት የወቅቱ ፍጥጫም በድጋሚ በዓለም ፍትሕ አደባባይ ኢትዮጵያ ልትቀርብ ትችላለች የሚል ግምት እየተሰጠ ነው፡፡

ከሰሞኑ የብልፅግና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ስለስብራት ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ስለዲፕሎማሲ ፈተናዎችና ሊያስከትል ስለሚችለው ተፅዕኖ በጉልህ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ውስብስብ ዓለም ነው ያለው፣ በተናጠል አንወጣውም፡፡ የሌሎች ትብብር ካልታከለበት ውስብስብ ችግሮችን መፍታት ያስቸግራል፡፡ ችግሩ የብቸኝነት ጉድለት ያስከትላል፡፡ ያ ብቸኝነት ደግሞ ሁሉን አልቦና ሁሉ የማይሳካለት ያደርገናል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዓለም ጋር ተባብራ እንጂ ተናቁራ መኖር እንደማትችል ዓብይ (ዶ/ር) በግልጽ አስቀምጠዋል፡፡ ‹‹ዲፕሎማሲያችን ፉክክርን ሳይሆን ትብብርን ያስቀደመ ዲፕሎማሲ ነው፤›› ሲሉ የገለጹት ዓብይ (ዶ/ር)፣ በሁሉም ረገድ ከሌሎች ጋር መተባበሩ እንደሚያዋጣ ነው ያብራሩት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን በወጡባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በዲፕሎማሲው ረገድ በድንገት አስመራ እስከ መጓዝ ያሉ ደፋር ዕርምጃዎች ስለመውሰዳቸው ይወሳል፡፡ በዓለም አቀፍ ትብብር ረገድም ቢሆን አፍሪካ በተመድ የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ ተወካይ እንዲኖራት ጥሪ ሲያቀርቡ ተሰምተዋል፡፡

ከሁሉ በላይ በደሃ አገሮች ዘንድ ትልቅ ዋጋ በተሰጠው የዓለም ፋይናንስ ተቋማት የብድርና ዕዳ ሽግሽግ እንዲያደርጉ በመጠየቁ በኩል ከቀደሙ ሰዎች አንዱ ተብለው ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ የኮሮና ወረርሽኝ ዓለምን በተፈታተነ ወቅት እንደ ‹‹ፋይናንሺያል ታይምስ›› ባሉ ጋዜጦች ላይ ጭምር ጽሑፍ በማሳተም የደሃ አገሮች የዕዳ ሸክም እንዲሸጋሸግና ዕፎይታ እንዲሰጣቸው ሰፊ ጥረት ያደረጉበት ጊዜ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ በሒደት መንግሥታቸው በዲፕሎማሲው በኩል ክፉኛ መፈተን መጀመሩን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ምናልባትም አገሪቱ የቀደመ የካበተ የዲፕሎማሲ ሀብት ባይኖራት ኖሮ ሊገጥማት የሚችለው ፈተና ካጋጠማትም በላይ ከባድ ሊሆን እንደሚችል አንዳንዶች ያስታውሳሉ፡፡ የአንዳንድ ተፅዕኖ ፈጣሪ አገሮች ድጋፍ ታክሎበት ዜጎች በአገር ቤትም በውጭም በራስ ተነሳሽነት ባካሄዱት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዘመቻ፣ ኢትዮጵያ ያን የከፋ ጊዜ እንዳለፈች በብዙዎች ዘንድ ይወሳል፡፡

ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል ጦርነትን ተከትሎ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ የገጠማት ፈተና ከባድ መሆኑ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን ድምፅ ስትሆን ብትቆይም በዓለም አደባባይ በተፈተነችበት ጊዜ የአንዳንድ አፍሪካ አገሮችን ድጋፍ እስከማጣት የደረሰችበት ሁኔታ ማጋጠሙ በታሪክ መዝገብ የሚሰፍር አጋጣሚ ስለመሆኑ ብዙዎች ያስታውሱታል፡፡

አፍሪካዊያን በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ላይ ትወክለን ያሏት ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት በዓለም መድረኮች ስሟ በክፉ መነሳቱን ብዙዎች በቅሬታ ሲያነሱት ነው የቆዩት፡፡ ዳቮስ ስዊዘርላንድ በየዓመቱ በሚካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ስብሰባ ላይ ደጋግማ በመገኘት አፍሪካ ነክ አጀንዳዎችን በማንሳት የምትታወቀዋ ኢትዮጵያ፣ በኢጋድ ስብሰባ ላይ አልሳተፍም ማለቷን እንደ ታላቅ የዲፕሎማሲ መንሸራተት ነበር የቆጠሩት፡፡

ይህ በሆነ ማግሥት ዳቮስ በዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም የተካፈሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ግን በብዙዎች እምነት የተቀዛቀዘውን የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የዓለም አቀፍ መድረኮች ተሳትፎ እንቅስቃሴ የሚያነቃቃ ጥረት ሆኖ ነው የታየው፡፡

በዚህ መድረክ ስለኢትዮጵያ ብሎም ስለአፍሪካ አጀንዳዎች በርካታ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ጥያቄዎች የምዕራቡ እንዲሁም የምሥራቁን ዓለም የሚያቻችልና የአገርን ጥቅም አደጋ ላይ የማይጥል ምላሽ የሚጠይቁ ጥያቄዎችንም ሚኒስትሩ አስተናግደው ነበር፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ፣ የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ማዕከል ስትሆን፣ በአፍሪካ ጉልህ ሚና ያላት አገር ናት፡፡ ሁለቱን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ዕድሎች በምን መንገድ ነው ለውጭ ዲፕሎማሲያችሁ የምትጠቀሙት የሚል ጥያቄ ለአቶ ደመቀ ተነሳ፡፡

‹‹የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ብቻ እኮ አይደለንም፣ መሥራችም ጭምር እንጂ፡፡ በዚህ እንኮራለን፡፡ ከተጠቀሱት ተቋማት በተጨማሪም በቅርቡ ብሪክሰን ተቀላቅለናል፡፡ በብሪክስ ውስጥም ጉልህ ሚና መጫወት እንፈልጋለን፡፡ ዓለም አሁን የገጠመውም ፈተና፣ ፉክክሩም ሆነ ዓለም አቀፉ ነባር ሥርዓት እንደኛ ላለ ታዳጊ አገር የማደግና የመለወጥ ፍላጎት ምቹ ሁኔታ ያለው አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ባለ ብዝኃ የግንኙነት አማራጮችን ትሻለች፡፡ ኢትዮጵያ ላላት የማደግና የመለወጥ ፍላጎት በሁሉም አቅጣጫ ከሁሉም ወገን ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ ግንኙነት ማጠናከርን ትመርጣለች፤›› በማለት ነበር አቶ ደመቀ የተናገሩት፡፡

በተለያዩ አቅጣጫዎች መናጥ በሚጠይቀው፣ የልዕለ ኃያላን አገሮች ጂኦ ፖለቲካዊ ግብግብ ከፍተኛ በሆነበት በአሁኑ የዓለም ሁኔታ ኢትዮጵያ ሚዛኑን በጠበቀ አቻቻይ መንገድ መጓዙ እንደሚያዋጣት ነው በዚህ መድረክ የሞገቱት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -