Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍን ተጠቃሚ የሚያደርግ ባንክ እንዲቋቋም መታሰቡ ተሰማ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባንኮች ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚያቀርቡት ብድር ዝቅተኛና ምቹ ባለመሆኑ፣ ዘርፉ ራሱን የቻለ ባንክ እንዲኖረው ውሳኔ ላይ መድረሱንና በቅርቡም እንዲቋቋም መታሰቡን የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ይህንን ያስታወቀው፣ ማክሰኞ ጥር 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት በተፈራረመበት ወቅት ነው፡፡

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተሠርቶ ታኅሳስ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ላይ፣ ባንኮች በዘርፉ ለተሰማሩ ተቋማት የሚያቀርቡት ብድር ዝቅተኛ ስለሆነ ዘርፉ ራሱን የቻለ ባንክ እንዲኖረው መጠቀሱ ታውቋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ምልኬሳ ጃጋማ (ዶ/ር)፣ ‹‹በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ውስጥ የተሰማሩ ተቋማት ከባንኮች የሚያገኙት የብድር መጠን 12 በመቶ ብቻ ነው፤›› መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከባንኮች የሚያገኙት ብድር ከፍ እንዲል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አቅጣጫ መስጠታቸውን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ያስቀመጡትን አቅጣጫ አምራች ኢንዱስትሪዎች 24 በመቶ ብድር ማግኘት እንደሚችሉ የሚገልጽ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በቅርቡ የወጣው ፖሊሲ አምራች ኢንዱስትሪዎች በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል፣ በግብርና፣ በብድር፣ በጥናትና ምርምር፣ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸው ሚና ከፍ እንዲል የሚያደርግ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ባንክ እንዲቋቋም በፖሊሲ ውስጥ ቢካተትም፣ ‹‹ባንኩ መቼና በምን ያህል ካፒታል ይቋቋማል?›› የሚለው አለመታወቁን ጠቅሰው፣ ባንኩ ሲቋቋም የአምራች ኢንዱስትሪዎች ችግር በቀላሉ ይቀረፋል ብለዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በርካታ አምራች ኢንዱስሪዎች ቢኖሩም፣ የዕድገት ደረጃቸው ሲታይ ግን ዝቅተኛ የሚባል እንደሆነ ገልጸው፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተቋሙ በጋራ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ማዕቀፍ ውስጥ እያንዳንዱ ተቋም የራሱን ተልዕኮ እንዲወጣ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸው፣ ክልሎች ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የመሬት አቅርቦት እንዲያመቻቹ፣ ባንኮች የብድር አገልግሎት እንዲሰጡ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ሥልጠናዎችን በማመቻቸት የተቋማትን አቅም ማሳደግ እንደሚገባው ተመላክቷል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የኢኮኖሚ ዕድገቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስና ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ብቁ ባለሙያዎች ለማቅረብ ዩኒቨርሲቲው እየሠራ እንደሆነ፣ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ለሚ ጉታ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በኢትዮጵያ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች በተለየ ሁኔታ በመሥራት፣ በሳይንስና በኢንጂነሪንግ የተሰማሩ ተማሪዎችን በማብቃት የተሻለ ቦታ እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች