Monday, March 4, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያ የምትከበረው ዘመኑን በሚመጥን ተግባር ብቻ ነው!

ዓለም በሁሉም መስኮች በፍጥነትና በቅፅበት እየተለወጠች ነው፡፡ በፈጣን ግስጋሴ ውስጥ ካለችው ዓለም ጋር ቢቻል እኩል ካልሆነ እግር በእግር መከታተል ካልተቻለ፣ በሁሉም ዘርፎች ያሉ ፉክክሮችን ተቋቁሞ ካሰቡበት ለመድረስ ያዳግታል፡፡ ዘመን አፈራሽ ዕውቀቶችን በመቅሰም ከጊዜው ጋር የሚራመዱ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀምም ሆነ፣ እንዲሁም በራስ አቅም አምርቶ የጥቅም ተቋዳሽ ለመሆን የሚቻለው ለዘመኑ የሚመጥን ቁመና ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲ፣ በውትድርና፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በቴሌኮም፣ በትራንስፖርትና በተለያዩ መስኮች ውጤታማ ለመሆን ዘመኑን የሚመስል አቅም መፍጠር ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ በሁሉም መስኮች ጥራት ያለው ዕውቀትና ክህሎት ማዳበር የግድ ይላል፡፡ ዓለም በዕውቀትና በቴክኖሎጂ በፈጣን ግስጋሴ ላይ ሆኖ ወደፊት ሲመነጠቅ፣ ለዘመኑ አኗኗር ፋይዳ የሌላቸው ያለፈው ዘመን የታሪክ ትርክቶች ላይ ተቸክሎ መነታረክ ዋጋ የለውም፡፡ ዘመኑ የሚጠይቀውን አስተሳሰብ ታጥቆ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ ለመሆን መዘጋጀት አለመቻል፣ ለተመፅዋችነት ከመዳረግ ውጪ ጥቅም የለውም፡፡

በፖለቲካው ምኅዳር ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ተዋንያን ዘመኑን መምሰል የተሳናቸው ይመስላሉ፡፡ ዓላማ ብለው የያዙት ጉዳይ ባለፈው ዘመን የፖለቲካ ዕሳቤ ላይ ብቻ ስለሚንጠለጠል፣ ለዚህኛው ዘመን የሚመጥን ፉክክር ማሳየት እያቃታቸው ጊዜያቸውን የሚያባክኑት ስህተቶችን በመደጋገም ነው፡፡ የማንኛውም ፖለቲከኛም ሆነ ፓርቲ ዓላማ ሥልጣን መያዝ መሆኑ ጥያቄ የሚነሳበት አይደለም፡፡ ነገር ግን ከውስጥ አደረጃጀት እስከ ውጭ መስተጋብር ድረስ ያለው ሒደት በሥርዓት ካልተያዘ፣ ነጠላ ፓርቲም ሆነ ስብስብ ልክ እንደ ትናንትናዎቹ ፈራሾች ብትንትኑ መውጣቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ‹‹ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከንቢያው ላይ ቁጢጥ›› እንደሚባለው ዘመን ተሻጋሪ አባባል፣ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› ዓይነት የሥልጣን መንገብገብ ብዙዎችን ከጨዋታ ውጪ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች በስተቀር፣ የብዙዎቹ ገመና ‹‹ተከድኖ ይብሰል›› እንደሚባለው ነው፡፡ ፖለቲከኞች ዘመኑን የሚመጥን ቁመና ላይ ሳይገኙ፣ ፓርቲዎቹ የትም እንደማይደርሱ የታወቀ ስለሆነ ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡

በንግዱ ማኅበረሰብ ዘንድም የሚታየው ተመሳሳይ እውነታ ነው፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ እንደ ሥራ ዘርፉ የተደራጀባቸው ማኅበራትና እንደ ንግድ ምክር ቤት መሰል ተቋማት አሉ፡፡ ነገር ግን በጣም ጥቂት ከሚባሉት በስተቀር አብዛኞቹ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ለጤናማ የንግድ አሠራር የተመቹ አይደሉም፡፡ የሚወክሏቸው ማኅበራትም ሆኑ ተቋማት አባላቶቻቸው የመሬት፣ የባንክ ብድር፣ የውጭ ምንዛሪ፣ ከቀረጥ ነፃ ዕድል፣ የግብር፣ የጉምሩክና መሰል ችግሮች ሲያጋጥሟቸው በከፍተኛ ድምፅ ብሶት ሲያስተጋቡ በተደጋጋሚ ተሰምቷል፡፡ ማኅበራቱም ሆኑ ተቋማቱ የአባላቶቻቸውን አቤቱታና ብሶት ማስተጋባታቸው ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እዚህ ግባ የሚባል ሚና የላቸውም፡፡ ግብር የሚያጭበረብሩና የሚሰውሩ፣ ኮንትሮባንድ የሚነግዱ፣ በሐሰተኛ ደረሰኝ ግብይት የሚፈጽሙ፣ የአቅርቦት ሰንሰለቶችን አፍነው የሚይዙ፣ ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት የሚፈጥሩ፣ በሚዛን የሚያጭበረብሩ፣ ምርቶች ውስጥ ለጤና ጎጂ ባዕድ ነገሮችን የሚቀላቅሉና ሕዝቡን የሚያሰቃዩ እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ዘመኑን የማይመጥን አሳፋሪ ድርጊት ተሸክሞ መዞር ያሳፍራል፡፡

በአሁኑ ጊዜ እጅግ በጣም ጥቂት ከሚባሉ መንግሥታዊ ተቋማት በስተቀር ብዙዎች ባህላዊ ናቸው ቢባል አያንስባቸውም፡፡ ከወረዳ አስተዳደሮች ጀምሮ ብዙዎቹ አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ ሆን ብለው ተገልጋዮችን ለማስመረር ተዘጋጅተው የሚጠብቁ ነው የሚመስሉት፡፡ ተቋማቱ ብቃት ባላቸው አመራሮችና ባለሙያዎች ስለማይመሩ በደቂቃዎች ውስጥ ማለቅ ያለባቸው ሥራዎች ተገልጋዮችን ለሳምንታት ያንገላታሉ፡፡ የብዙዎቹ አሠራር በጥናት ላይ የተመሠረተ ሊመስል የሚሞክር የሥራ ፍሰት ቅደም ተከተል ቢኖረውም፣ ሥራ የሚከናወነው በግለሰቦች መልካም ፈቃደኝነት ላይ በመሆኑ ተገልጋዮች ለምሬት ይዳረጋሉ፡፡ አንዳንዶቹ ተቋማት ውስጥ የሥልጣን ተዋረዱ ሊጠበቅ ባለመቻሉ አለቃው የበታቹን ይፈራዋል፡፡ ይህ በግልጽ የሚያሳየው አንድም የመንግሥትና የፓርቲ ሥራ መደበላለቁን ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጥቅም ትስስር የፈጠረው መናናቅ ነው፡፡ ከዘመኑ ጋር መራመድ አለመቻል አዘቅት ውስጥ እየከተተ ነው፡፡ በሙስና የተበከሉ ግለሰቦችና ቡድኖች በየቦታው የበላይነቱን ሲይዙ፣ ተቋማቱ እንኳንስ ከዘመኑ ጋር ሊራመዱ የህልውናቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ይሆናል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰሞኑን የዓድዋ ዜሮ ዜሮ ፕሮጀክት የሥራ ክንዋኔ አስመልክቶ፣ ‹‹ሃያ አራት ሰዓት በመሥራት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል›› የታየበት መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ሃያ አራት ሰዓት በፈረቃ መሥራትና ማሠራት የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ቢቻል፣ ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ከምፅዋት ጠባቂነት ማውጣት እንደማያቅት ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በፌዴራል መንግሥትም ሆነ በከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረትና ክትትል እንደሚደረግላቸው ፕሮጀክቶች፣ መንግሥታዊ ተቋማትም በልዩ ክትትል ቢመሩ የሕዝባችን ምሬትና ሰቆቃ ጣሪያ አይነካም ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ በሁሉም መንግሥታዊ ተቋማት ሥራን ዓላማ ያደረገ ሹመት፣ ምደባና ሥምሪት ማድረግ ቢቻል በርካታ ብልሹ አሠራሮች መልክ ይይዙ ነበር፡፡ በየጊዜው ሥልጠና የሚሰጣቸው አመራሮችም ሆኑ ባለሙያዎች በየተቋማቱ ለውጥ ማምጣት ካልቻሉ፣ የሥልጠናው ፋይዳ በሚገባ መገምገም ይኖርበታል፡፡ የአገር ሀብት እየባከነ አመራሮቹና ተቋማቱ ካልተለወጡ፣ ከዘመኑ ጋር ሊራመድ የሚችል የአስተሳሰብ መሠረት መጣያ መደላድል መፈጠር ይኖርበታል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን የብዙዎቹ ተቋማት ጉዳይ ያሳስባል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዚህ ቀደም የነበራት ክብርና ተቀባይነት ማሽቆልቆል ከጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በተለይ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የምትታወቀው በጦርነት፣ በድርቅና በረሃብ፣ እንዲሁም በምግብ ተመፅዋችነት ነው፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አንገት አስደፊ ታሪክ በፊት ኢትዮጵያ ዕድሜ ለታላቁ የዓድዋ ድል የአፍሪካውያንና የመላው ጥቁር ሕዝቦች ጌጥ ነበረች፡፡ በታላቁ የዓድዋ ድል ምክንያት በርካታ አገሮች አንገታቸውን ቀና አድርገው ለነፃነታቸው ለመታገል ተነሳስተዋል፡፡ የኢትዮጵያን ባለሦስት ቀለማት ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች የተጋሩት፣ ኢትዮጵያ የነፃነት ተምሳሌት እናታቸው መሆኗን አምነው ስለተቀበሉ ነበር፡፡ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ይህንን የመሰለ የጋራ እሴት ተንከባክቦ በማስቀጠል፣ በታሪክ ያጋጠሙ መንገጫገጮችን ደግሞ እንደ መማሪያ በመውሰድ በዚህ ዘመን ታሪክ መሥራት ሲገባ እርስ በርስ መፋጀት ያሳፍራል፡፡ ዘመኑን የሚመጥን መልካም ሥራ እንጂ ጠላትነት አያስከብርም፡፡ ኢትዮጵያ የምትከበረው ዘመኑን በሚመጥን ተግባር ብቻ እንደሆነ ይታመን!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...

ምርጫ ቦርድ ፓርላማው ያፀደቀለትን 304 ሚሊዮን ብር አለማግኘቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ሰኔ 2016 ዓ.ም. በአራት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰብዓዊ ቀውስና በውድመት የታጀቡ ግጭቶች በአስቸኳይ ይቁሙ!

በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ተጀምሮ አማራና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው የሁለት ዓመቱ አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢገታም፣ ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል የተጀመረው...

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...