Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህል‹‹የደጋ ሰው›› አልበም ሲመነዘር

‹‹የደጋ ሰው›› አልበም ሲመነዘር

ቀን:

በየማነ ብርሃኑ

የማርያም ቸርነት (የማ) ትባላለች፡፡ ወጣት ድምፃዊት ናት፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት የምትታወቀው የእንግሊዝኛ ዘፈኖችን በመጫወት ነው፡፡ በቅርቡ በአልበም ደረጃ የመጀመርያዋ የሆነና ‹‹የደጋ ሰው›› የሚል ስያሜ የተሰጠው – እንደ ሙዚቃ ሐያሲያን ጆሮ ገብና ጥበባዊ እሴቱ የላቀ የሙዚቃ ስብስቦቿን ለአድማጭ ጆሮ አድርሳለች፡፡

‹‹የደጋ ሰው›› አልበም ሲመነዘር | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

- Advertisement -

ጥር 18 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ፣ በብላቴን ጌታ ኀሩይ ወልደ ሥላሴ ሥነ ጥበባት ማዕከል ታዋቂ የሙዚቃ ሰዎች፣ የሙዚቃ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት፣ የ‹‹ደጋ ሰው›› በተሰኘው በድምፃዊቷ የሙዚቃ አልበም ላይ ያተኮረ ሒስ ተካሂዶ ነበር፡፡

በመድረኩ ላይ በመገኘት በአልበሙ ዙሪያ ሒሳቸውን ያቀረቡት የሙዚቃ ባለሙያና የሙዚቃ ሐያሲ ሠርፀ ፍሬ ስብሐት እንደተናገሩት፣ የድምፃዊት የማርያም ቸርነት (የማ) ‹‹የደጋ ሰው›› አልበም ጥቅል ቅርፅ የዓለም ሙዚቃ ዘውግ (World Music Genre) ውስጥ ሊመደብ የሚችል ነው፡፡ የአልበሙ አጠቃላይ ሙዚቃዊ ፍልስፍና፣ የሥልት አመራረጥ፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች አሰናኘት፣ የቅማሬ (ኮምፖዚሽን) አስተሳሰቡ ሁሉ የዓለም ሙዚቃ ዘውግ ውስጥ የሚሠራባቸውን አስተሳሰቦች ይዞ ተገኝቷል፡፡

ይህ ማለት ግን፣ በአልበሙ ውስጥ የተሠሩት ሥራዎች በየራሳቸው የተሸከሟቸውን የአፍሪካ፣ የጃዝ፣ የአንደርግራውንድ ሚውዚክ ፍልስፍናዎችን ወደ ጎን አድርጓቸዋል ወይም የሉም ማለት አይደለም ሲሉም ባለሙያው ይናገራሉ፡፡

የዓለም የሙዚቃ ዘውግ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው፣ የብዙዎችን ጆሮ መማረክ የቻለ ትልቅ የሙዚቃ ዘውግ መሆኑንና በኢትዮጵያም ወደ እዚህ የሙዚቃ ዘውግ ገብቶ ሙዚቃዊ ሥራ ለማበርከት የተደረገው ጥረት የቀደመና በ1980ዎቹ አካባቢ መወጠኑን ሐያሲው ጠቅሰዋል፡፡

አስቴር አወቀ ከእነ አበጋዝ፣ ሔኖክና ከለንደን ሙዚቀኞች ጋር የሠራችው ‹‹ካቡ›› የተሰኘው አልበሟ፣ የእጅጋየሁ ሽባባው ‹‹ጉድፈላ›› አልበም የዓለም ሙዚቃ ከፍታና አስተሳሰብ የነበራቸው ሲሆኑ፣ ከእነሱም በኋላ ዣን ሥዩም ሔኖክ፣ ምኒሹ ክፍሌ፣ ሳሙኤል ይርጋ (በዳብ ክሎስስ አልበሙ፣ በጉዞ አልበሙ በጥቂቱ) ተጠቃሽ ጥረት ማድረጋቸውን ሠርፀ ፍሬ ስብሐት ይገልጻሉ፡፡

‹‹የደጋ ሰው›› አልበም ከእነዚህ ሁሉ በኋላ የመጣና ከላይ የተጠቀሱት አልበሞች ሊያገኙ የሚችሉትን ዕድሎች ለማግኘት በማይመች ቦታ (በአገር ውስጥ) ተሠርቶ ውጤታማ መሆን የቻለ መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያው፣ አስቴር በአሜሪካ የተዋወቀቻቸውን ታላላቅ ዓለም አቀፍ ሙዚቀኞችን በመጠቀም ለንደን ላይ የሠራችው፣ እጅጋየሁም በተመሳሳይ የውጭ ኑሮዋና ቢልላስዌል የቅርቧ ሰው መሆኑ ነገሮች ሁሉ እንዲሳኩ የማድረግ የራሱ ዕድል የነበረው ሲሆን፣ የምኒሹና የዣን ሥዩምም በተመሳሳይ የሚታይ ዕድል እንደነበራቸው አውስተዋል፡፡

‹‹የደጋ ሰው›› አልበም ግን ይህን ዓይነቱን ዕድል ሳያገኝ፣ አጠቃላይ የሥራው ሒደት በአገር ውስጥ ከመሠራቱ አንፃር ለ‹‹ዓለም ሙዚቃ›› ቅጂ አስፈላጊ የሆኑ የስቱዲዮ ደረጃዎችንና የቅማሬ ሐሳቡን ‹በኢንስትሩሜንታል ኢንተርፕሪቴሽን› ሊተረጉሙ የሚችሉ የባህሉን ሙዚቀኞች ማግኘት በማይቻልበት ድባብ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሥራ መሥራት አይደለም ማሰቡ እንኳን ከባድ እንደሆነ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡

የዓለም ሙዚቃ ዘውግ፣ በሙዚቃ መሣሪያዎች የታወቀ ወይም (Standard Timber and Technical) አጨዋወት ላይ ብቻ ተመሥርቶ የሚሠራ ሥራ አለመሆኑን፣ ብዙ ኤክስፐርመንታል ድምፆችን ከተፈጥሮ መቅዳትን የሚጠይቅና አንዳንዴም ባህሪው ወደ ፊልም ‹ስኮሪንግ ሳውንድ› የሚያደላ መልክ ሁሉ አለው፡፡ አዳዲስ ፍብርክ ድምፆችን ፕሮዲውሰሮች የሚፈጥሩበትና ያ አዲስ ፍብርክ ድምፅም የአልበሙ መለያ ብቻ ሳይሆን፣ የዓለም ሙዚቃ ልዩ ባህሪ ተደርጎም ስለሚወሰድ፣ እዚህ ደረጃ ድረስ ሊደርስ የሚችል ጥረትና ከፍታ ያለው ቅጅ ለመሥራት መወሰንን የሚጠይቅ ድፍረት የሚፈልግ በመሆኑ፣ ከዚህ አንፃር ኢዩኤል መንግሥቱ (የአልበሙ ፕሮዲውሰር) የወሰደው ኃላፊነትና አልበሙን ሊገመት በማይችል ሁኔታ በአገር ውስጥ ቀድቶ፣ የሰባት አገሮች ሙዚቀኞችን ከእኛ አገር ታላላቅ ሙዚቀኞች ጋር አቀናጅቶ የቀዳበት ሁኔታ እጅግ ሊደነቅ የሚገባው ከፍ ያለ ጥረት መሆኑን ሠርፀ ፍሬ አብራርተዋል፡፡

እንደእሳቸው አገላለጽ፣ በ‹‹ደጋ ሰው›› አልበም የተደረሱት ዜማዎች ለሚውዚካል ስትራክቸር ምቹ በሆነ መልኩ ሆን ብለው የተቀመሩና ከበርካታ የሙዚቃ አደራረስ ጥንቃቄዎችና ስሜቶች አንፃር በጣም የተዋጣለት፣ የድምፃዊቱን የማርያም ብቃት፣ ቮካል ሬጅስተርና የግጥም ድርሰቱን ባህሪ ጥንቅቅ አድርጎ መሸከም በሚችል መልኩ የተሰናዱ ሥራዎችን መስማት ችለናል፡፡

የድምፃዊቷ የማብራራት ብቃትና ሙዚቃዊ አረዳዷ ምን ያህል ጥልቅ መሆኑን የተረዳንበት፣ ድምፃዊቷ ማዜም የምትችል፣ ሶኖሪቲ፣ ቲምበር የምንለውን ከለዛ ጋር የሚያያዝ ጥራት (ኳሊቲ) ማሟላት የምትችልና በዚያ ላይ እጅግ የተገራ ሙዚቃዊ አረዳድ ያላት መሆኗን የሚገልጹት ባለሙያው፣ ድምፃዊቷ የሥልት ውስንነት (የስታይል ሊሚቴሽን) ሳይኖርባት በርካታ ሥራዎች መሥራት እንደምትችል፣ ለዚህ ደግሞ በመድረክም በስቱዲዮም የተፈተነ ብቃት ያላት በመሆኑ ከዚህ አንፃር የተደረሱት ዜማዎች ለሷ ብቃት ምቹ ሆነው መገኘታቸውንም ይናገራሉ፡፡

በይዘት በኩል አልበሙ ለዓለም ሙዚቃ ከፍታ የሚመጥን ግጥም እንዳገኘ፣ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች በሰፊው የሚራቀቁበት ብዙ ቁምነገር ያለው አልበም መሆኑን የሚገልጹት ሠርፀ ፍሬ ስብሐት፣ ሙዚቃ የተራ ተርታ ሐሳቦች መጠራቀሚያ አለመሆኑን ለማሳየትና እነ ኤልያስ መልካ የደከሙት ድካም በሚገባ የዘመኑ ፍልስፍና እየሆነ መምጣቱን፣ ሙሉጌታ ተስፋዬና እጅጋየሁ ሽባባው ታሪክን፣ ባህልንና ምሰላን ተጠቅመው የዘፈን ግጥምን ከፍ ያደረጉበትን የኢሉዥን ወይም የንቡር ጠቃሽ ቴክኒክ በሰፊው መታየቱን፣ የኢሞሽንና የኢንተሌክት ውህደት በሙዚቃ ላይ ትልቅ ውጤት እንደሚያመጣ በዚህ አልበም መመልከታቸውን ይገልጻሉ፡፡

የ‹‹ደጋ ሰው›› አልበም ፕሮዲውሰር አቶ ኢዩኤል መንግሥቱ በመድረኩ ላይ በሰነዘሩት አስተያየት ከጋሞ ብሔር የቦንኬ ማኅበረሰብ ሙዚቃን ከሚውዚካል አንትሮፖሎጂ (ከሙዚቃዊ ሥነ ሰብዕ) አንፃር ለማጥናት የተጓዘው ጉዞና በዚህ የጥናት ሒደት ውስጥ ተለምዷዊው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ የማይገኙ፣ ልዩ የሥልተ ምት፣ የዜማና የሚውዚካል ቴክስቸር አስተሳሰቦችን ከማኅበረሰቡ ሙዚቃ ውስጥ በማየቱ፣ ይህን አዲስ የሙዚቃ ባህል ቀድሞ ከነበረው የሙዚቃ ዕውቀትና ሳይንስ ጋር በማዋሀድ አልበሙን ለመሥራትና ለማዘጋጀት ተነሳሽነትን እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡

የጋሞ ጉዞ ‹‹ለደጋ ሰው›› አልበም ጥንስስ እንደሆናቸው የሚናገሩት አቶ ኢዩኤል፣ በአገሪቱ ለአገር በቀል ሙዚቃ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን በመረዳት ሙዚቃዎቻችንን ከተለያዩ አገሮች ባህል ጋር በማዋሀድ አገርኛ ዜማውን ሳይለቅ የኢትዮጵያን ሙዚቃ አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግና ለማሳደግ ይህ አልበም ሊዘጋጅ መቻሉንም ይናገራሉ፡፡

በሙዚቃው ሕይወትን፣ ተፈጥሮንና ተስፋን ለማንገሥና ለማጉላት ጥረት መደረጉን፣ ከተለመደው የሙዚቃ ባህላችን ወጣ ያለና ለውጥ እንዲያመጣ ተደርጎ ለአገር ውስጥና ለውጭ የሙዚቃ አፍቃሪያን በሚመጥን ልክ መዘጋጀቱንና ከጠበቁትም በላይ ሙዚቃው በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትን እንዳገኘ ባለሙያው አብራርተዋል፡፡

‹‹ብዙ ጊዜ ያልተለመደና አዲስ ሥራ ይዘህ ስትመጣ የምታገኘው ምላሽ አርኪ አይደለም፡፡ እኛ ይህን አልበም ስንሠራ ቅድሚያ የሰጠነው ለስሜታችንና በአገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ አንዳች ነገር እናበረክታለን ብለን አስበን ስለነበር፣ ልፋታችን፣ ድካማችንና ያወጣነው ወጪ አላሳሰበንም፤›› ያለችው ድምፃዊት የማርያም ቸርነት (የማ) ናት፡፡

እስካሁን ባለው ሁኔታ ሥራችን በአገር ውስጥና በውጭ እየተደመጠ እንዳለና አልበሙም በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትን እንዳገኘ፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች የምናገኛቸው ሰዎች ይነግሩናል፣ ይህ ደግሞ ለቀጣይ ሥራችን ስንቅና ተስፋ ነው ስትልም ድምፃዊቷ ገልጻለች፡፡

በደጋ ሰው የሙዚቃ ስብሰብ ከሰባት አገሮች፣ ከሃያ በላይ ሙዚቀኞች የተሳተፉበት ሲሆን፣ በሙዚቃ ድርሰትና በሁለት የዘፈን ግጥሞች፣ በቅንብርና በፕሮዲዩሰርነት ኢዩኤል መንግሥቱ መከወኑ ተገልጿል፡፡

አንጋፋና ታዋቂ የሙዚቃ ሰዎች እንደ እነ እዝራ አባተ (ዶ/ር)፣ አክሊሉ ወልደ ዮሐንስ፣ እንድሪስ ሐሰንና ሌሎችም በዜማና በሙዚቃ መሣሪያ ተሳትፈውበታል፡፡ ከአልበሙ ውስጥ የሚገኙ ስምንት የሙዚቃ ግጥሞችን በብዕር ስሙ ‹‹ጎላ ጎሕ›› የተባለ ገጣሚ የጻፋቸው ሲሆን፣ ይልማ ገብረአብም ያበረከተ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የደጋ ሰው አልበም፣ ‹‹ራያ ራዩማ››፣ ‹‹ሎሚዬ››፣ ‹‹ጋሻዬ ካርኑ››፣ ‹‹ደግዬ››፣ ‹‹ሳህሌ ሌቦ››ን ጨምሮ አሥራ ሁለት ዘፈኖች ተካተውበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...