Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የችኮላ መዘዝ!

ጉዞ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹ጥረህ ግረህ ትኖራለህ…› በሚለው ትዕዛዝ መሠረት ከባዱን የኑሮ ትግል ተያይዘነዋል። የሕይወትን ትርጉምና የመኖርን ጣዕም አጥርተን ሳንረዳ በአልሞትባይ ተጋዳይነት እንጓዛለን። መነሻውን ባልደረስንበት የጉጉት ሰቀቀን ጎዳና ላይ ወዲያና ወዲህ እንመላለሳለን። ግራ የገባው፣ በከፊል የገባው የመሰለው፣ ምንም ያልገባው፣ የሚሄድበትን የሚያውቀው፣ እግሩ በዘፈቀደ የሚመራው፣ መድረሻውን የወሰነው፣ እንኳን መድረሻ መነሻ የሌለው ሁሉ ከዚያም ከዚህም እየተግተለተለ ይተራመሳል። የትናንቱ አሰልቺ እንግልት ዛሬ በአዲስ ጉልበት ሊደገም ጎህ ቀዷል። ለአንዳንዱ ደግሞ ገና ሳይነጋ መሽቶበታል። አስቀድሞ የክስረት ሒሳቡን ላወራረደ የሰማይ ዓይን መግለጥና የምድር ዓይን መክደን ትርጉም አይኖራቸውም። ብቻ ጎዳናው የተሸናፊውም የአሸናፊውም መድረክ ስለሆነ፣ ይኼኛው ከዚያኛው እኩል ትከሻ ለትከሻ ተጠባብቀው የታክሲ ወረፋ ይጠብቃሉ። ሕይወት እንዲህ ናት!

ከረጅም ጥበቃ በኋላ የተገኘው አሮጌ ሚኒባስ ላይ በቅደም ተከተል ገብተን ተሳፍረናል። አስቀድሞ ራሱ በከፋፈታቸው መስኮቶች በኩል አንገቱን ያስገባው ወያላ ተሳፈሪዎችን ይለክፋል። ‹‹እሺ እዚህ ጋ… አንቺኛዋ ትንሽ ጠጋ በይ… እዚያ ጋ ሄይ ጩጬ ተማሪዎች… አዎ እስክሪብቶአችሁን ቦርሳችሁ ውስጥ ክተቱ። ነግሬያለሁ ወንበር ላይ ብትጽፉ… በተለይ ፖለቲካን በተመለከተ አንድ ነገር ጻፉና እናንተን አያድርገኝ። አዎ ይኼን ጊዜ ስንት ያልሠራችሁት የቤት ሥራ አለ…›› ይላል። በዋናው በር በኩል ዞሮ ደግሞ፣ ‹‹ገና በጠዋቱ እንዳንለካከፍ ዝርዝር ብር አዘጋጁ። አዳሜ በብላክ ማርኬት እየዘረዘርሽ አገር ማራቆት ለምደሽ እኔ መልስ ብትሉኝ አልሰማችሁም…›› ይላል። ‹‹ዛሬ ቁርስ የበላኸው የፍየል ምላስ ነው እንዴ ፍሬንድ? ይልቅ ሞልቷል ሳበው በለው…›› የቸኮለ ወጣት ተናገረ፡፡ ይኼኔ ታክሲያችን መንቀሳቀስ ጀመረ። የግድ ነው!

ተማሪ፣ ነጋዴ፣ ሸማች፣ አሠሪ፣ ሥራ ፈላጊ በታክሲያችን ጣሪያ ሥር ተሰባስበን ጉዞ ጀምረናል። መሀል መቀመጫ ላይ የተሰየመች ወይዘሮ በሞባይል ስልኳ፣ ‹‹…ይኼ የፖለቲካ ፓርቲ ከመደገፍ ወይም ከመቃወም ጋር የተያያዘ አይደለም…›› ስትል ፈዘዝ ብለን የነበርነው ተነቃቃን። ሁላችንም እርስ በእርስ ተያይተን ወደ ወይዘሮዋ አፈጠጥን። ወይዘሮዋ ቀጥላለች፣ ‹‹ነገር ግን መስዋዕትነት ተከፍሎበታል የተባለውን ዴሞክራሲና ነፃነት እንዳሻቸው ሲፈነጩበት ማየት ከምንም በላይ ስለሚያም ነው። አሁንም ድሮም ሆነ ወደፊት ሥልጣንን ተገን በማድረግ የሚፈጸሙ ኢሰብዓዊ ጥቃቶችን በፅኑ እቃወማለሁ…›› ብላ ስታበቃ እጇን ወደ ላይ ማንሳት ነበር የቀራት። ስልኳን ወዲያው ዘግታ አብሯት ከተመቀመጠ ጎልማሳ ጋር ማውራት ቀጠለች። መጨረሻ ወንበር ከተመቀጡ ተሳፋሪዎች አንዱ፣ ‹‹ባላሰብነውና ባልጠበቅነው ሰላማዊ ሠልፍ ስንሳተፍ ዝም ትላላችሁ? ሴትየዋን ኧረ አንድ በሏት…›› ከማለቱ፣ ‹‹ሰው ያለ ከልካይ የበላ የጠጣውን የሚለጥፍበት የፌስቡክ ግድግዳና ቲክቶክ አልበቃ ብሎት ደግሞ ጎዳናውን በብሶት ፖለቲካ ካላተራመስኩት ይላል። መተሳሰብ እኮ ትተናል…›› ስትል አንዲት ወጣት የእንኑርበት መልዕክቷን ታስተላልፋለች። ጎመን በጤና!

ወያላው በበኩሉ፣ ‹‹ሰው ለበላው ቁርስ አያዝንም? ምናለበት ምሳ ሰዓት ሳይደርስ በነገር እየተነቋቆረ ለረሃብ ባይቸኩል?›› እያለ በማያገባው ሲገባ ሾፌሩ፣ ‹‹ስለሰው ስለሰው ቀድጄ ልልበሰው ብላለች ዘፋኟ። ይልቅ ወሬውን ትተህ ስፖክዮውን አስተካክለው አይታየኝም…›› ብሎ ኩም ያደርገዋል። ከወገቡ በላይ በመስኮት ሾልኮ ሲወጣ ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ ሁለት መምህራን ተሳፋሪዎች ስለአፍሪካ ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ጨዋታ ያወራሉ። አላደርስ ብሎን ዜና ያልሰማን ማን ወደቀ ማን አለፈ የሚለውን ለመስማት ጆሯችንን ወደ እነሱ ቀና ስናደርግ፣ ‹‹ኑሯችን ትላለህ ፖለቲካው፣ ትዝብታችን፣ ሐዘናችን ሳይቀር ገና ከጥሎ ማለፍ ጨዋታ የማይወጣበት ምክንያት ነው እኮ የማይገባኝ። ተግዳሮታችንና ችግራችን ሁሉ የትናንት፡፡ እንዲያው መቼ ይሆን ነገራችን ሁሉ ወደ ጥሎ ማለፍ የሚሸጋገረው?›› የሚል ቀጭን ድምፅ ስንሰማ ግን የባከነ ሰዓት ላይ መድረሳችን ታወቀን። በስንቱ እንደምንባክን አልገባን አለ እኮ!

ወያላው ሒሳብ መሰብሰብ ጀምሯል። ጋቢና የተየሰሙትን ሴቶች ሾፌሩ እንዳትቀበል ስላለው ወያላው ተነጫንጯል። ‹‹በቃ አጠገቡ ሴት ከተቀመጠች እኮ በነፃ አላስካ ደርሶ ይመለሳል ምን አገባኝ እኔ?›› እያለ ለራሱ እያጉተመተመ መጨረሻ ወንበር ተጠባብቀው ወደ ተቀመጡት ሕፃናት ተማሪዎች ሲደርስ፣ ‹‹ሒሳብ!›› ብሎ ጮኸባቸው። ነገረ ሥራቸው ሁሉ ፈገግ የሚሰኝ እነዚያ ሕፃናት የሞባይል ስልካቸውን እየጎረጎሩ ቀና ብለው እንኳ ሳያዩት ዝም አሉት። ‹‹እነ ጩጬ አትከፍሉም?›› ወያላው ደገመላቸው። ‹‹ቆይ አንዴ ሪከርድ ልሰብር ስለሆነ ነው እሰጥሃለሁ…›› ብሎ አንደኛው መለሰ። ወይዘሮዋ አፏን ሸፍና ሳቀች። አጠገቧ የተሰየመች ቀዘባ ደግሞ ፈገግ ብላ፣ ‹‹አይ ኢትዮጵያ አገሬ በዱር በገደሉ ለነፃነትሽ የተዋደቁ አርበኞች ልጆችሽን ባየሽበት ዓይን ዛሬ የጌም አርበኞች ሲተኩዋቸው ስታይ ምን ትይ ይሆን?›› ብላ ወደ ሰማይ ቀና አለች። መሀል መቀመጫ ያለ ጎልማሳ ዘወር ብሎ፣ ‹‹እነሱ ምን ያውቃሉ? እኛ ነን እንደጠቀምናቸው እያሰብን በዚህ ዕድሜያቸው ያውም ወደ ትምህርት ቤት ይዘው እንዲሄዱ እየፈቀድን ሞባይል ገዝተን የምንሰጥ። ወላጆች ነን ልጆቻችንን እያበላሸናቸው ያለነው…›› ብሎ ተነፈሰ። ኡፍፍፍፍ…!

ሕፃናቱ ትምህርት ቤታቸው በራፍ ላይ ሲወርዱ አዲስ ተሳፋሪ ተጫነ፡፡ እሱም ከመግባቱ፣ ‹‹…ታክሲ አሁን አግኝቼ ገና ተደላድዬ አልተቀመጥኩም፡፡ ችግሩ ምንድነው ስል ‹አይ አንተ ከሄድክ ስለማትመለስ ኬዝህን አላመነበትም› አትለኝም አስተርጓሚዋ። ኧረ ድርጅት አለኝ ይኼው የባንክ ወጪና ገቢዬ ብል ማን ይስማኝ? ለነገሩ እነሱ ምን አለባቸው ለኮቴ የሚቀበሉት ብቻ እኮ በዓመት የትናየት ሚሊዮን ብር መሰለህ? በትንሹ በቀን በአሥር ሺሕ ብር ሒሳብ 100 ሰው ይገባል ብለህ አስላውማ፡፡ ማን መፅዋች ማን ተመፅዋች እንደሆነ እኮ ነው ግራ የሚገባህ። ግድ የለም ቆይ ብቻ…›› እያለ በብስጭት በሞባይል ስልኩ እያወራ ሰማነው። ‹‹የአሜሪካ ቪዛ ተከልክሎ ነው መሰለኝ…›› አለኝ ይኼን ያህል ሰዓት ዝምታ ውጦት የተቀመጠ አጠገቤ የነበረ ተሳፋሪ። አዲሱ ተሳፋሪ ስልኩን ከመዝጋቱ ደግሞ ይባስ ብሎ ያም ያም ያፅናናው ጀመር። ‹‹አይዞን ነገም ሌላ ቀን ነው…›› ሲል አንዱ ቆንጅት ቀበል አድርጋ፣ ‹‹ነገ ተመልሰህ ሄደህ ሌላ መስኮት ላይ እንዲደርስህ አድርገህ ብትጠይቅ ይሰጡሃል። ተስፋ አለመቁረጥ ነው ሞክር ዝም ብለህ…›› ትለዋለች። ግፋ በለው በሉት!

ከወደፊት የተቀመጠ ስለቢዝነስ አብዝቶ የሚያወራ ተሳፋሪ በበኩሉ፣ ‹‹የእኔም ወንድም እንዳንተ አጋጥሞት ነበር። ምን አደረገ መሰለህ? አንድ የአውሮፓ አገር ቪዛ ጠይቆ ከዚያ ላጥ አለና ዋሽንግተን ዲሲ ገባ እልሃለሁ። ዋናው ተስፋ ሳትቆርጥ በሩን ማንኳኳት ነው። ወጣ ወጣ እያልክ ካልሆነ የእኛን ነገር ታውቀዋለህ…›› ይለዋል። ሰውየው ከተከለከለው ቪዛ ይልቅ የሚሰማቸው የማፅናኛ ቃላት ብዛት ይባስ ራሱን እንዳሳመሙት ያስታውቃል። ታክሲያችን ጥቂት የሐዘን ድባብ ሰፍሮባት ቆየ። በዚህ አያያዛችን ምፅዓትን ጥሩ አድርገን ተለማምደነዋል አትሉም? ሾፌራችን ጋቢና ከተሰየሙት የሚያውቃቸው እህቶች ጋር አፍ ለአፍ ገጥሞ መቆየቱ ወያላውን ክፉኛ አበሳጭቶታል። ጨዋታውን ለማቆርፈድ ይመስላል፣ ‹‹ኮካ በስሜ አትጋብዝልኝም?›› ሲል ከወሬው ያደናቅፈዋል። ሾፌሩ ነገሩ ገብቶት፣ ‹‹ቀበሌ የማያውቅህ ወያላ ማን በአንተ ኮካ ይዳል?›› ብሎ አጠገቡ ካሉት ጋር ተጠቃቅሶ ፈገግ አለ። ወያላው ሴራው እንዳልተሳካለት አውቆ ዝም ሲል ጎልማሳው፣ ‹‹ምን ይሻለናል ዘንድሮ? የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳ የምርጫ ጊዜ ቅስቀሳ ይመስል በየራሳችን ፈተናዎች ጩኸት አበድን እኮ፡፡ የአንዱን ብሶት ሰምተን ሳንጨርስ ሌላው ደግሞ የእኔስ የባሰው ብሎ ይመጣል…›› እያለ ተብሰከሰከ። ብሶት ብቻ!

ወደ ካዛንችስ እየተቃረብን ነው፡፡ በጎልማሳው ትዝብትና ቁጭት እኛም ተብሰልስለን ሳንጨርስ ከየት መጣ ሳይባል ከኋላችን አንድ አይሱዙ መጥቶ ተላተመ። የታክሲያችን የኋላ መስታወት ሿ ብሎ መሬት ላይ ተበትኗል። ተሳፋሪዎች ‹የምን መዓት ነው?› እየተባባሉ እርስ በእርስ ይተያያሉ። ትንሽ ስንረጋጋ ተሽቀዳድመን ከታክሲያችን ወረድን። መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ተሳፋሪዎች ማንኛቸውም አለመጎዳታቸው ቢያስደስተንም፣ የገጨንን አይሱዙ አሽከርካሪ ጤንነትና ሕጋዊነት ለማጣራት ስንሰባሰብ ወጣቱ የአይሱዙ ሾፌር ጥምብዝ ብሎ ሰክሯል። ትራፊክ ፖሊስ ደርሶ መንጃ ፈቃድ ሲጠይቀው የኤቲኤም ካርዱን አውጥቶ ሰጠው። ለወሬ የተሰበሰበው መንገደኛ ሁሉ ይኼን ጉድ እያየ ዘና ይላል። ድንጋጤው አመድ ያስመሰላት ወይዘሮ፣ ‹‹አንተ ሰካራም በዚህ አያያዝህ እንኳን መኪና ልትነዳ ወግ ያለው ሞት ለማግኘትም ዕድል የምታገኝ ይመስልሃል?›› ብላው እያማተበች ራቀች። ‹‹ኑሮን ለማሸነፍ ቸኩለን፣ ለሞትም ቸኩለን እንዴት ይሆናል?›› ብላ ሁሉን አሳታፊ ጥያቄ የምትጠይቀው ደግሞ ሌላዋ ወይዘሮ ናት። የችኮላ መዘዝ አትሉም? መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት