Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፓርላማው የወንጀል ክሶች እንዳይቋረጡ ለፍትሕ ሚኒስቴር ማሳሰቢያ ሰጠ

ፓርላማው የወንጀል ክሶች እንዳይቋረጡ ለፍትሕ ሚኒስቴር ማሳሰቢያ ሰጠ

ቀን:

  • ከእናቶቻቸው ጋር ታስረው የሚገኙ ሕፃናት በአስቸኳይ እንዲወጡ ተጠይቋል
  • ፓርላማው የግል መገናኛ ብዙኃን እንዳይዘግቡ ከልክሏል

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝብና የመንግሥት ጥቅምን የተመለከቱ የወንጀል ጉዳዮችን፣ በተለይም ከሙስና ጋር የተያያዙ ክሶችን አሳማኝ በሆነ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር መቋረጥ የለባቸውም ሲል ለፍትሕ ሚኒስቴር ማሳሰቢያ ሰጠ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንን ማሳሰቢያ የሰጠው ባለፈው ሐሙስ ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የፍትሕ ሚኒስቴርን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ካዳመጠ በኋላ ነው።

ሁሉም የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን የምክር ቤቱን መደበኛ ስብሰባዎች ሲከታተሉ የቆየ ቢሆንም፣ ባለፈው ሐሙስ የተደረገውን መደበኛ ስብሰባ ግን የግል መገናኛ ብዙኃን ተከታትለው እንዳይዘግቡ በምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ክልከላ ተጥሎባቸዋል። ምክር ቤቱ ይህንን ክልከላ ለምን እንደጣለ የሰጠው ምክንያት የለም። ሐሙስ ዕለት በተካሄደው መደበኛ ስብሰባ የፍትሕ ሚኒስቴር የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ከተደመጠ ሚኒስቴሩን የሚከታተለው የምክር ቤቱ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም የምክር ቤቱ አባላት ለፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ማብራሪያ የሚሹ ጥያቄዎችን ከማቅረባቸው ውጪ፣ ጥንቃቄ የሚፈልግ የተለየ ጉዳይ አለመነሳቱን ሪፖርተር በዕለቱ የነበረውን አጠቃላይ ውይይት በተመለከተ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመገንዘብ ችሏል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የፍትሕ ሚኒስትሩ የሙስና ወንጀሎችን የተመለከቱ እንዲሁም የተመዘበሩ የሕዝብና መንግሥት ሀብቶችን በማስመለስ ረገድ በስደስት ወራት ውስጥ ተከናወኑ ያሏቸውን ጉዳዮችን በሪፖርታቸው ያቀረቡ ሲሆን፣ የፍትሕ ሚኒስቴርን የሚከታተለው ቋሚ ኮሚቴም የተናወኑ ጉዳዮችን በአወንታ ተቀብሎ፣ በመንግሥት ተቋማት የሚፈጸም የሀብት ምዝበራን አስመልክቶ የፌዴራል ዋና ኦዲተር የሚያቀርባቸው የኦዲት ግኝቶችን መሠረት በማድረግ፣ የተቋማቱን መሪዎች በሕግ ተጠያቂ ከማድረግ አኳያ ክፍተት መኖሩን በጥያቄ አንስቷል።

ፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) የተጠቀሰው ክፍተት መኖሩን ተቀብለው በሰጡት ተጠማሪ ማብራሪያ፣ የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርትን መሠረት አድርጎ የሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ተጨማሪ የፎረንሲክ ምርመራ ማካሄድና በመንግሥት ላይ ለደረሰው ጉዳት ትክክለኛውን ተጠያቂ መለየት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ይህንን የፎረንሲክ ምርመራ ለማድረግ ደግሞ ጊዜና በቂ ባለሙያዎችን ማደራጀት እንደሚያስፈልግ፣ ይህ ባለመኖሩም ዕርምጃ ለመውሰድ ጊዜ መውሰዱን ነገር ግን ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። 

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ግብረ መልስ ያቀረቡት የምክር ቤቱ የሕግ ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዕፀገነት መንግሥቱ የቋሚ ኮሚቴውን ግምገማና ግብረመልስ ያቀረቡ ሲሆን፣ በወቅቱም በፌዴራል ዋና ኦዲተር የሚጋለጡ የሀብት ምዝበራዎች ትኩረት እንዲሰጠውና የተመዘበረው ሀብትም ሊሰበሰብ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። 

አክለውም፣ የሕዝብና የመንግሥት ጥቅምን የተመለከቱ የወንጀል ክሶች በተለይም ከሙስና ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንደሚቋረጡ በማንሳት ይህ አካሄድ እንዲስተካከል ጠይቀዋል።

‹‹የሕዝብና የመንግሥት ጥቅምን የተመለከቱ የወንጀል ጉዳዮችን በተለይም ከሙስና ጋር የተያያዙ ክሶችን አሳማኝ በሆነ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር መቋረጥ የለባቸውም›› ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ዕፀገነት፣ ‹‹በሕዝብ የተጠቆሙ ሙስናን የተመለከቱ ጉዳዮችን በተገቢው መንገድ መገምገምና ክስ መመስረት ይገባል፡፡ የተጀመሩ ምርመራዎችም ሳይቋረጡ ዕልባት እንዲያገኙና የተመዘበሩ ሀብቶችን ማስመለስ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ይህንን በማድረግ የሕዝብን አመኔታ ማሳደግ ተገቢ ነው፤›› ብለዋል።

በሌላ በኩል የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢዋ ወ/ሮ ዕፀገነት መንግሥቱ፣ ፍትሕ ሚኒስቴር በማረሚያ ቤቶች አካባቢ የሚስተዋሉ ፈርጀ ብዙ ችግሮችን ጠጋ ብሎ መመልከትና መደገፍ አለበት ብለዋል።

ቋሚ ኮሚቴው እነዚህን ተቋማት እንደጎበኘና በጉብኝቱ ወቅትም ሕፃናት ከእናቶቻቸው ጋር በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚቆዩበት ሁኔታ መኖሩን እንዳስተዋለ ተናግረዋል።

‹‹በማይመለከታቸው ጉዳይ ከእናቶቻቸው ጋር ታስረው የሚገኙ ሕፃናትን ቶሎ እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልጋል። ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ይህንን ሁኔታ ማስተካከል ያስፈልጋል፤›› ብለዋል። አክለውም፣ በማረሚያ ቤቶች የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታትና ማስተካከል እንደሚገባ ጠቅሰው፣ ‹‹ታራሚዎችን በተገቢው መንገድ ማረም ያስፈልጋል፤›› ብለዋል። 

ይህ ማሳሰቢያ ከመሰጠቱ ቀደም ብሎ፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)፣ የተሻሉ ማረሚያ ቤቶች ግንባታ በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ነበር። 

የአራት ትልልቅ ማረሚያ ቤቶች ግንባታ በድሬደዋ፣ በዝዋይ፣ በሸዋ ሮቢትና በአዲስ አበባ ከተማ እያካሄደ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በድሬዳዋና በዝዋይ የተገነቡት አዳዲስ ማረሚያ ቤቶች መጠናቀቃቸውን፣ የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤትም ወደ መገባደዱ እንደሆነ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የሚካሄደው የማረሚያ ቤት ግንባታም እየተጠናቀቀ በመሆኑ አሁን ባለው ማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች በዚህ ዓመት ውስጥ በአባ ሳሙኤል አካባቢ እየተገነባ ወደሚገኘው ማረሚያ ቤት እንደሚዘዋወሩና ነባሩ ማረሚያ ቤት ደግሞ ወጣት አጥፊዎችን ለማስተናገድ እንደሚውል ተናግረዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉት ታራሚዎች ብዛት 107,260 ሲሆን ከዚህ ውስጥ የሴት ታራሚዎች ብዛት 4,151 መሆኑን ሚኒስትሩ ካቀረቡት ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...