Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶች ዋጋና የወለድ ምጣኔ ፍትሐዊ ይደረግ!

የዲጂታል የባንክ አገልግሎቶች ፈጣን በሚባል ደረጃ ዕድገት እየታየባቸው ነው፡፡ አገልግሎቱ ብዙዎችን እየደረሰ ነው፡፡ በዲጂታል የባንክ አገልግሎት የሚፈጽሙ ግብዓቶች መጠን እየጨመረ መጥቷል፡፡ ከባንክ ወደ ባንክ የሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮች አሠራራቸው ተለውጧል፡፡ ቀናት ይወስዱ የነበሩ ከባንክ ወደ ባንክ የሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮች አሁን በደቂቃዎች መከወን እየቻሉ ነው፡፡ የፋይናንስ ተቋማት አሁናዊ መረጃዎች የሚመሰክሩትም አብዛኛው የገንዘብ እንቅስቃሴ ዲጂታላይዝ ሆኗል፡፡ አገልግሎቱን ከዛሬ አራትና አምስት ዓመታት በፊት የነበረበትንና አሁን ከደረሰበት ደረጃ ጋር እናነፃፅር ከተባለም ልዩነቱ እጅግ ሰፊ እየሆነ መጥቷል፡፡ በዚህ አገልግሎት ዙሪያ እየታየ ያለው ለውጥ ከፍተኛ ቢሆንም፣ አሁንም በጥሬ ገንዘብ የሚደረግን ግብዓት ከማስቀረት ወይም ከመቀነስ አኳያ ከዚህም በኋላ ብዙ የሚሠራበት ዘርፍ ነው፡፡ 

ከተማ ቀመስ በሆኑ አካባቢዎች በይበልጥ ጎልቶ የሚታየውን የዲጂታል የባንክ አገልግሎት ማስፋት ይጠይቃል፡፡ በአጠቃላይ ግን በዚህ ዘርፍ እየታየ ያለውን ለውጥ ልናደንቅ ይገባል፡፡ በአገልግሎቱ ዙሪያ የሚታዩ አንዳንድ እክሎች መኖራቸውን ሳንዘነጋ በአጭር ጊዜ የተደረሰበት ደረጃ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ከአንዳንድ መረጃዎች መገንዘብ እንደሚቻለው የዲጂታል የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች መጨመርና የሚንቀሳቀሰውም ገንዘብ በእጅጉ እያደገ መምጣት የፋይናንስ ተቋማት ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እየሆናቸውም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ባንኮችና የዲጂታል የክፍያ ኩባንያዎች እንዲህ ላለው አገልግሎታቸው እየጠየቁ ያሉት የአገልግሎት ክፍያ መጠን ግን ብዙ እያነጋገረ ነው፡፡ ተጠቃሚዎች የአገልግሎት ዋጋው ግነት እየታየበትም መሆኑን እየገለጹ ነው፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገንዘብ ከአንድ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ ለማዘዋወር የሚያስከፍሉት የአገልግሎት ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል ከእጥፍ በላይ ዋጋቸውን ያሳደጉም አሉ፡፡

በኤትኤም ገንዘብ ለማውጣት ሲከፈል የነበረው የአገልግሎት ዋጋ በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍ ብሏል፡፡ በሌሎች የዲጂታል የክፍያ አገልግሎቶች ላይም የባንኮች በክፍያ መጠን ጭማሪ እያሳየ ነው፡፡ በቅናሽ ሳንቲም ይከፈልባቸው የነበሩ የተለያዩ የአገልግሎቶች ዋጋ አሁን ቀርተዋል፡፡ ከአንድ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ አንድ ሺሕ ብር ለመላክ እስከ አሥር ብር ይጠይቃል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 200 ብር ወደ ቴሌብር የሚያዘዋውር ደንበኛ ባንኩ ለዚህ አገልግሎቱ አሥር ብር የሚቆርጥበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡ ከአንድ ባንክ ወደ ቴሌ ብር ለማሻገር ሰባት ብር የሚጠይቅ መሆኑ ደግሞ የአገልግሎት ዋጋው በምን ያህል እንደጨመረ ያስገነዝበናል፡፡ አነስተኛና ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ ለመላክ የሚጠየቀው ዋጋ የሚለያይበት አጋጣሚ አለ፡፡

ስለዚህ ገንዘብ ከአንድ ባንክ ወደ አንዱ ባንክ ለማዘዋወር የሚጠየቀው የአገልግሎት ክፍያ ለቁጠባ ከሚከፍሉት ወለድ ምጣኔ በላይ እየሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ዋጋው ግነት አለበት ቢባል ከእውነት የራቀ አይሆንም፡፡

ዋጋው ተጋንኗል ሊባል የሚችልበትን አንድ ሁለት ምሳሌ እንጥቀስ፡፡ አንዱ የአገልግሎት ተጠቃሚው በበዛ ቁጥር የአገልግሎት ዋጋን ቀንሶ ከብዛት ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበት ዕድል ስላለ ነው፡፡ አነስተኛ ተጠቃሚ በነበረበት ወቅት አነስተኛ ወይም ተመጣጣኝ ክፍያ ሲያስከፍሉ ቆይተው በአገልግሎቱ መስፋት የሚያገኙት ገቢ እያደገ ሲሄድ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ ተገቢ ነው ተብሎ አይታመንም፡፡ ጤናማ የቢዝነስ ዕሳቤም አይደለም፡፡ ሁለተኛው ተቋማቱ ይህንን አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ወጪ ያወጡ መሆኑ ቢታመንም ይህ ወጪ ግን አንዴ የሚወጣ ነው፡፡ በየዓመቱም ሊያወጡ የሚችሉት ወጪ እንዳለ ቢታወቅም፣ ይህ ወጪ ከመጀመያው ኢንቨስትመንት የማይበልጥ በመሆኑ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያወጡት ወጪ እየቀነሰ የሚሄድ ከመሆኑ አንፃር አሁን እያደረጉ ያሉት የዋጋ ጭማ ግነት አለው ሊባል ይችላል፡፡ 

ለአገልግሎቱ የሚያገለግሉ ግብዓቶች ወጪም አለባቸው፡፡ በየአንዳንዷ የገንዘብ ዝውውርም ቢሆን የሚጠይቋቸው ወጪ ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉ ወጪዎቻቸው አሁን ካለው ክፍያቸው አንፃር ሲታይ ዕርምጃቸውን መልሰው ቢያጤኑት እንድንል ያስገድዳል፡፡

በተመሳሳይ ከዲጂታል የባንክ አገልግሎት ጋር ተያይዞ አነስተኛ የብድር አቅርቦቶችን ማሳለጥ የሚያስችሉ አሠራሮች በተለያዩ ባንኮች እየተተገበረ ነው፡፡ በተለይ ኢትዮ ቴሌኮም የዚህ አገልግሎት ፈር ቀዳጅ በመሆን የተለያዩ ባንኮች ተመሳሳይ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ዝግጅት ላይ ያሉም አሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት የሚሰጣቸውን ብድሮች ዲጂታል ወደ ማድረግ እየተሸጋገሩ ነው፡፡ 

ይህ የሞባይል ስልክን በመጠቀም በዲጂታል የታገዘ አነስተኛ ብድሮች በተመጣጠነ ሁኔታ እየተለመዱ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሚሊዮኖችን መድረስ ተችሏል፡፡ ነገር ግን በዲጂታል የባንክ አገልግሎት እንደታየው ሁሉ ለእነዚህ አነስተኛ ብድሮች የሚጠየቀው የወለድ መጠን ከፍተኛ ስለመሆኑ እየታዘብነው፡፡ አንዳንዶች ተመጣጣኝ የሚባል የብድር ወለድ ሲተገብሩ፣ ብዙዎቹ ብድሮች ግን የወለድ ምጣኔ ከመደበኛው የባንኮች ብድር ወለድ በላይ ናቸው፡፡ ከ20 በመቶ በላይ ወለድ የሚጠይቅባቸው ሆነዋል፡፡ የአገልግሎቱ መጀመር የሚሰጠው ወይም እየሰጠ ያለው ጠቀሜታ የማይጠይቅ ቢሆንም ስድስት ሺሕ ብር ተበድሮ ይህንን ብድር በሦስት ወር ለመመለስ ከስድስት መቶ ብር በላይ ወለድ መጠየቅ በፍፁም አግባብ አይሆንም፡፡ አንዳንዶችም የብድር ወለድ በጥንቃቄ ከተሠላ ከዚህም የሚበልጥ ነውና እንዲህ ያለው አካሄድ ያዘልቃል ወይ? 

በአጠቃላይ በዲጂታል የታገዘ የክፍያ ሥርዓትና የገንዘብ ዝውውር እንዲሁም አነስተኛ የብድር አቅርቦት ከጥሬ ገንዘብ ንክኪ ለማላቀቅ ከተፈለገ የአገልግሎቶቹ ዋጋና ወለድ ፍትሐዊ መሆን አለበት፡፡ አጠቃላይ አሠራሩም በሕግ ሊደገፍ ይገባል፡፡ በአገራችን የተቀማጭ ገንዘብ የወለድ ምጣኔ እንጂ የብድር ወለድ ምጣኔ ገደብ ያልተበጀለት በመሆኑ ተቋማት የብድር ወለድ ምጣኔያቸውን እንደፈለጉ ቢለጥጡት የሚጠየቁበት አሠራር ያለመኖሩ አንዱ ምክንያት መሆኑን መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት