Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አያዛልቅም!

ሰላም! ሰላም! ሰላም በራቃት ዓለም ውስጥ እየኖርን ሳምንት አልፎ እንደገና ስንገናኝ ሰላምታ እየተለዋወጥን ሲሆን ደስ ይላል፡፡ ሰላም እየተባባሉ ሰላምታ መለዋወጥ መልካም ነው፡፡ ‹‹ቅዳሜና እሑድ አበባ እያጠጡ፣ ከሰኞ እስከ ዓርብ ከሕይወት ማሳ አረም እያጨዱ፣ ጨመተ ይሉኛል እንዴት ልጨምት፣ ከፊቴ አስቀምጬ እርጅናና ሞት…›› ብለው የድሮዎቹ ክራር ከርክረዋል ሲባል ሰምቼያለሁ።  በደህናው ጊዜ አትሉም? ዘንድሮማ  አስቀድሞ በመጨመት ላላበደ እንዲሁ በዋዛ እርጅናና ሞት አይታደለውም የተባለ ይመስላል። ባይመስልም ነገሩ እንደዚያ ነው። ደግሞ ምን ሰማህ ካላችሁኝ፣  ‹‹የማልሰማው የለም ዘንድሮስ እንጃልኝ፣ ትምባሆ ያቦናል ዝንጀሮን እዩልኝ…›› የሚለውን በቅርቡ የሚወጣ ዜማ ጋብዣችኋለሁ። የግጥሙ ደራሲ ‹ልጅ እከሌ› ሲሆን ዘፈኑን ውብ አድርጎ የተጫወተልን ደግሞ ‹ራስ ማንትሴ› ነው። ደግሞ ‹ራስ› እና ‹ልጅ› በዛ ብላችሁ ኪነ ጥበብም ላይ አብዮት አፈንዱ አሉዋችሁ፡፡ ‹‹ወይ ጊዜ….›› አሉ አዛውንቱ ባሻዬ። መቼ? በቀደም በቴሌቪዥን ዓለም ጤና አጣች ተብሎ ከዩክሬን እስከ ጋዛ፣ ከዚያም እስከ ቀይ ባህር መተላለፊያ የሚካሄደውን ውጊያ ዜና ብሎ ሲተነትነው ሰምተው። እውነታቸውን ነው!

እኔ ደግሞ ችግርን ሁሉ በልኬ እያሰብኩ ከቤት፣ ከምግብና ከልብስ ሌላ ችግር ያለ አይመስለኝም ነበር። ለካ ከበሉ ከጠጡ፣ ከጠገቡና ከለበሱ በኋላ (በሌላ አባባል ልክ እንደ እነ አሜሪካ የለየለት ኢምፔሪያሊስት ከተሆነ ወዲያ) የችግር ያለህ ይመጣል። እናም እንደ ዜናው ዘገባ ዓለም ጤና ያጣችው በጦርነት ምክንያት ብቻ ከሆነ ተሳስተናል። በሁሉም ነገሮች ጤና የለም ማለት ይቻላል፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ስለዚህ ምክንያት ሲጠየቅ፣ ‹‹ምን ምክንያት አለው ደግሞ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አንዴ ዓይናችሁን ከድናችሁ ገለጥ ስታደርጉ፣ እጅግ ዘመናዊ ተብሎ የተዋወቀ ቴክኖሎጂ አሮጌ ይሆናል፡፡ ለግላጋ የፈረንጅ ሸበላ ቁመናውን ከሩቅ ዓይታችሁ ጠጋ ስትሉት ሴት ወይዘሮ መስሎ…›› ብሎ አንጠልጥሎ ተወው። ‹‹ምን ማለት ነው?›› አሉ ባሻዬ ቅር እያላቸው። ‹‹ወንድም ሴትም ያልሆኑ ሰው ይሁኑ አሻንጉሊት ብቻ በምድረ አውሮፓና አሜሪካ እየበዙ ነው…›› ብሎ ዝም አለ። ባሻዬ ቃል አልተነፈሱም። ጥቂት ሲያሰላስሉ ቆይተው፣ ‹‹በሥጋ ከመሞት ቀድሞ በቁም መሞት ነበረ የማውቀው። ለካ በቁም ከመሞት በፊት በቁም ማበድም አለ?›› ብለው ተነስተው ሄዱ። ይኼው እስከ ዛሬ አላየኋቸውም!

እንዲህ ዘይትና ውኃ ተቀላቅሎበት እያየን እኛ ግን የምናስበው ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም ድንበር መዝለል ይመስላል። ብቻ ከዚህ መራቅ። ለነገሩ ሐሜትና ወሬ ካልሆነ ትምህርታችንን ማስታወስ ስለሚያስቸግረን እንጂ፣ የሰው ልጆች ከቦታ ወደ ቦታ የመዘዋወር ተፈጥሯዊ ባህሪ እንዳላቸው የተማርነው ድሮ ሁለተኛ ክፍል ሳለን ነበር። ስለዚህ እዚህ ብቻ ያለነው ሳንሆን እዚያም ያሉት እዚህ መምጣት ይናፍቃሉ። ወደ ሞላለትና ወደ ጎደለበት መዘዋወሩ ላይ ነው ትኩረት ሚዛን የሚያስተው። አይደለም ነው? ሻሞ በሌለበት የአባቴ የእናቴ ብሎ ነገር አለ? ታዲያ በቀደም ዕለት አንድ ኢቬኮ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ያጋዛሁት ደንበኛዬ ውልና ማስረጃ መሄድ ነበረበት፡፡ አብረን እንሂድ ብሎኝ ሄድን፡፡ ጎበዝ ውልና ማስረጃ አንደኛው ቅርንጫፍ ስንደርስ አዳሜ ውክልና ለመስጠትና ለመቀበል መሰብሰቡን ሳይ፣ ደግነቱ ለንብረት ሆነ እንጂ ለሕመምና ለሞት ውክልና ቢቻል ኖሮ አካባቢው ጭር ይል ነበር ብዬ ብቻዬን ስስቅ ደንበኛዬ ደነገጠ፡፡ ለምን አይደነግጥ!

 ‹‹ለካ ከተማው ጭር የሚለው ሰው እዚህ ተሠልፎ እየዋለ ነው?›› ሲለኝ ደንበኛዬ አንድ ጎልማሳ ሰምቶት፣ ‹‹እንዴት ነው ነገሩ ከፒያሳ እስከ መገናኛ፣ ከስድስት ኪሎ እስከ አራት ኪሎ፣ ከአራዳ ጊዮርጊስ እስከ መሳለሚያ፣ ከአብነት እስከ መርካቶ አገሩ ሰው ብቻ አይደል እንዴ፡፡ እዚህ እኮ የተሰባሰበው ትንሽም ሆነ ትልቅ ንብረት የሚወካከል ‹ማይኖሪቲ› ነው…›› አለው። እኔ ታዛቢ እነሱ ተጫዋቾች ሆኑ። ደንበኛዬ ማብራሪያው እንዳልገባው ተናገረ። ‹‹እንዴት አይገባህም? ተመልከት እስኪ ከተማ ውስጥ የታክሲ ሠልፉን፣ ጎዳናው በሁሉም አቅጣጫ በእግረኞች ተወሮ እያየን ከሁለቱ የትኛው ነው ደምቆ የሚታየው?›› ብሎ ደንበኛዬ ላይ አፈጠጠበት። የሰውዬው ሁኔታ ስላላማረው ደንበኛዬ፣ ‹‹ካልክማ ከወንዱ ይልቅ ሴቱ ይበዛል እባክህ አለ…›› አለሳልሶ። ‹‹ምን ያድርጉ? የእህቶቻችን እንጀራ ከጉልት ችርቸራ እስከ አካል ሽያጭ ያለው ጎዳና ላይ ስለሆነ ነው…›› ብሎ ሰውዬው ሌላ ሰቆቃ ጀመረ። እንዲህ ፖለቲካውን ጋብ፣ ጭጋግ የበዛባቸውን የብሶት መዝሙሮቻችንን ጠበቅ ማድረግ ከጀመርንማ ፍትሕ ቀስ በቀስ በእግሯ ትቆማለች ማለት አይደል? ይበል ብለናል!

ሠልፉ እየተንፏቀቀ ያጥራል። ደንበኛዬ የልጅነት መዝሙር ትዝት ብሎት፣ ‹‹ኧረ አምሳለ… ኧረ አምሳለ…›› እያለ ሲጀምር፣ ‹‹ኧረ አምሳለ… ኧረ አምሳለ… ኧረ ወይ… ኧረ ወይ…›› እያልኩ አጀብኩት። ምነው እናንተ ሀብታም የምትባሉ የዘመናችን ከበርቴዎች ለሕዝባችን ትንሽ እንኳ አዘኔታ የማይሰማችሁ?›› አለው ደንበኛዬን የቅድሙ ሰውዬ። እኔ ትዝብት ብቻ ሆኗል ሥራዬ ብያለሁ። ዘንድሮ እኮ የጠፋው ጥሩ አድርጎ የሚያብራራ ብቻ ሳይሆን፣ ጥሩ አድርጎ የሚያዳምጥና የሚታዘብም ጭምር ነው። ለራስ ሲቆርሱ ከሆነም አይብዛብኝ አይደል? ይመቻችሁ፡፡ ወዲያው ሰውዬው የተጀመረውን የልጅነት መዝሙር እስከ ግማሽ ዘመረው። ‹‹…ንፁህ ደሃ ሆነሽ ምን በልተሽ ታድሪያለሽ …ባገኝም በልቼ ባጣም ተደፍቼ… የደጅሽ እንኮይ አልበሰለም ወይ… ቢበስል ባይበስል ትጠቅመኝ ይመስል…›› ብሎ ፀጥ አለ፡፡ ጎበዝ እንዴት ነው ነገሩ ዘንድሮ ሰው ሁሉ ትንሽ ንኩት እንጂ፣ ውስጡ የነበረው እሳተ ጎመራ እንደ ጉድ አይደል እንዴ እየተፍለቀለቀ የሚወጣው? እኔም እኮ እንዲህ ያደርገኛል!

 ወዲያው ግን ግጥሙን ቀይሮ ታዲያ፣ ‹‹በዚህ አድገን ዛሬ ‹ባገኝም በልቼ ባጣም ተሰድጄ… ቢበስል ባይበስል እጠብቅ ይመስል›፣ 365 ቀናት ወረዳና ክፍለ ከተማ፣ ውልና ማስረጃ፣ ፖሊስ ጣቢያና ፍርድ ቤት ስንሳለም ብንውል ምን ይገርማል?›› ከማለቱ መብረቅ እንደ ገነደሰው ዛፍ ተዝለፍልፎ ወደቀ። አካባቢው በአንዴ ቀውጢ ሆነ። አንዷ ትጮሃለች፣ አንዱ ውኃ፣  ሌላው ክብሪት ይላል። ‹ኧረ እናንሳውና ወደ ጥላ ወስደን እናሳርፈው› የሚልም ነበር። አንዳንዱ ደግሞ አንዴ ከሠልፉ ከወጣ ተራውን አሳልፎ የሚሰጥ መስሎት ፈራ ተባ ይላል። ‹‹ወይ አንቺ ኢትዮጵያ። ዕውን መይሳው ካሳ ሽጉጡን ጠጥቶ የወደቀው አንቺ እቅፍ ላይ ነው? ዕውን ያ ሁሉ አርበኛ አገሬን ብሎ ተምሞ ዓድዋ ላይ የረገፈው በአንቺ መሬት ነው?›› እያሉ አንድ አልፎ ሂያጅ አዛውንት ቁጣቸውን ሲያዥጎደጉዱት፣ ከደንበኛዬ ጋር ሩሁን ስቶ የወደቀውን ጎልማሳ ተጋግዘን አነሳነው። ወዲያው ቀዝቃዛ ውኃ ስንደፋበት ዓይኑን ገለጠ። ይብላኝ መቀደምን እየፈራን ትንሽ ትልቁን ሠልፍ በፉክክር ቃኝተን አጓጉል ስንተላለፍ ወድቆ ዓይኑን ሳይገልጥ ለቀረው፡፡ ዋ ጊዜ!

ባለፈው ሳምንት ቁርሴን በላልቼ ከቤት ከመውጣቴ በፊት በቅርቡ ያሻሻጥኩትን ቪላ ቤት የድለላ ኮሚሽን ልቀበል ወደ ደንበኛዬ ደወልኩ። ደወልኩ ሲባል ቀላል ይመስላል አይደል? ቋንቋ ገለባ ነው ያለው ማን ነበር? ታዲያ ያወቀበት ከገለባው መሀል ፍሬ ይለቅማል። ትርጓሜውን ስነግራችሁ ካርዱን በገለባ ኮሚሽኔን በፍሬው አስታወስኩት። ‹‹ብቻ እኔ የማዝነው በወርኃዊ ደመወዝ በካርድ ወጪ የሚንገፈገፈውን ወገን ሳስብ ነው…›› ብዬ ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ወሬ ሳስጀምረው፣ ‹‹ለወርኃዊ ደመወዝተኛ ሞባይል ካርድ ኬኩ እንጂ ዳቦው ስላልሆነ ብዙም አትወዝወዝ…› ብሎ ጢሜን አበረረው። በእርግጥ የእኔ ጢም ነው የበረረው ብዬ ራሴን የጠየቅኩት ውዬ አድሬ ነው። ምን ነበር የጀመርኩት? አዎ የድለላ ኮሚሽኔን ልቀበል ደንበኛዬ የቀጠረኝ ሥፍራ ስሄድ፣ ‹‹ካልቸኮልክ አንዴ ውልና ማስረጃ ገባ ብለን እንውጣና ልሸኝህ…›› አለኝ። አሁንም ያ ሰቆቃ ሊደግመኝ ነው እያልኩ በሥጋት ውስጥ ሆኜ፣ ‹ምን ይደረግ ይሁን› አልኩ። ክፍያ አላጣምና ተያይዘን ሄድን። ተራው ደርሶ ጉዳዩን አብራርቶ እየተስተናገደ ሳለ ጉዳዩን የምታስፈጽምለት አስተናጋጅ ስሙን በአማርኛና በእንግሊዝኛ እንዲጽፍላት ጠየቀችው። በነገራችን ላይ ይኼኛው ደንበኛዬ ዳያስፖራ ነው። እንዳጫወተኝ ከሆነ ለ30 ዓመታት አሜሪካ ኖሯል። ጻፈና ሰጣት። ‹‹ስምህ አብራም ነው ወይስ አብረሃም?›› አለችው መልሳ። እሱም ነገራት። ‹‹ታዲያ በእንግሊዝኛ የጻፍከው እኮ የሚነበበው አብራም ተብሎ ነው አስተካክለው…›› ብላ ተቆጣች። ‹‹ግድ የለም የእኔ እመቤት ፓስፖርቴም ላይ መኖሪያ ፈቃዴም ላይ የተጻፈው እንዲያ ነው። ስለዚህ ዝም ብለሽ ሙይው…›› ቢላት ልትለቀው ነው። ቋንቋ አስተማሪ ሆና አረፈችው። ቢጨንቀው፣ ‹‹ይኼውልሽ የእኔ እመቤቴ ስሙ ዓለም አቀፋዊ ነው። ከፈለግሽ ዲክሸነሪ ላይ ማየት ትችያለሽ…›› አላት። በዚህ አይረቤ ሙግት ወረፋ ጠባቂዎች ሳይቀሩ ተበሳጩ። ፈርዶብን ብስጭት መቼም አይጠፋም!

‹‹ያለ ሙያ፣ ችሎታና ፍላጎት መቀመጥ ማለት እኮ ይኼ ነው። አሁን ይህች ልጅ አወቀችውም አላወቀችውም መምህር መሆን ነው የምትፈልገው። ግን እነሱ እዚህ ነሽ አሉዋት። ምን ታድርግ ስም ታርም እንጂ…›› ብሎ በደምሳሳው ከኋላችን ቆሞ ተራውን የሚጠብቀው ባለጉዳይ ሲያጉረመርም ደንበኛዬ ወደ እኔ ዞሮ፣ ‹‹ከባህር ወጥታ ጤዛ ላሰች ይሉሃል እንግዲህ የእኔ ታሪክ ነው…›› እያለ በራሱ ቀለደ። በተውሶ ስሞች እንዲህ ከተጨቀጨቅን በአገር በቀሉማ ምን ልንባል ይሆን? ቆይ ግን እናንተ ፍሬ ነው ገለባ ለቀማ የሚቀናን? እኔ በበኩሌ፣ ‹‹ልፋ ያለው ገለባ ይወቃል›› የሚለው አባባል እኛን በደንብ የሚገልጸን ይመስለኛል፡፡ ፍሬውን ትተን ንፋስ የሚያበራየው ገለባ ላይ ስናተኩር ዓይናችን ውስጥ ተሞጅሮ ሥቃይ ይለቅብናል፡፡ ወሬና ንፋስ የሚያገላብጠው ገለባ አንድ መሆናቸውን መረዳት አቅቶን፣ ከፍሬው ይልቅ ገለባ ስናባርር ችጋር ይጫወትብናል፡፡ ይህንን ሁሉ ፍልስፍና መሰል ነገር የምነግራችሁ ከራሴ የአዕምሮ ጓዳ አፍልቄ ሳይሆን፣ ዕድሜ ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ ከእሱ የቀሰምኩት መሆኑን ስነግራችሁ በታላቅ አክብሮት ነው፡፡ ክበሩልኝ!

በሉ እንሰነባበት። ኮሚሽኔን ተቀብዬ ለአንዳንድ ተጨማሪ የድለላ ሥራ እንደሚፈልገኝ ደንበኛዬ ነግሮኝ በቀጠሮ ተለያየን። ይኼን መንፈቅ ዓመት ደግሞ ቀኑ ረዥም ሌሊቱ አጭር ስለሚሆን ብር ብር ስል ከቤቴ እንዳልባረር ሰዓቴን አየሁና ወደ ቤቴ ተጣደፍኩ። ገና ከመግባቴ፣ ‹‹ባሻዬ ከሄዱበት ፀበል ተመልሰውልሃል…›› ብላ ውዴ ማንጠግቦሽ ነገረችኝ። ‹‹አንድ ብርጭቆ ውኃ በቁሜ አጠጭኝና አይቻቸው ልምጣ…›› ስላት፣ ‹‹የታሸገ ውኃ ገዝተህ ጠጣ የውኃ እናት ሞታለች…›› ብላ አሾፈችብኝ። የታሸገ ውኃንና የሬስቶራንት ምግቦችን ዋጋ ዝርዝር ባሰብኩ ቁጥር እውነቴን ነው የምላችሁ ደላላ ባልሆን ይቆጨኝ ነበር። ይብላኝ ምድር ለምድር ለሚሳበው እንጂ እኛስ ከአየር ተቀብለን አየር ላይ እንቀለዋለን። ውኃዬን ገዝቼ ባሻዬ ቤት ስደርስ ከሄዱበት ቅዱስ ሥፍራ ይዘውት የመጡትን ቅዱስ ውኃ ፊታቸው ላይ፣ ወለሉ ላይ፣ ሶፋው ላይ፣ ፎቶግራፎቹ ላይ፣ ቴሌቪዥኑ ላይ፣ ጋዜጣው ላይ፣ ሬዲዮናቸው ላይ እየረጩ፣ ‹‹ለፍላፊውን ቀንሰው፣ አስተማሪውን አብዛው፣ ምሬተኛውን አፅናናው፣ አማራሪውን ልብ ስጠው…›› እያሉ ይፀልያሉ። ጥላዬ ከብዷቸው ዘወር ሲሉ ሲያዩኝ ሳቅ ብለው፣ ‹‹ነብር ዥንጉርጉርነቱን ሳይቀይር ምነው እኛ ኢትዮጵያውያን የሌለብን ነገር በዛ ልጄ?›› ብለው አቅፈው ስመው እንድቀመጥ ጋበዙኝ። እውነታቸውን ነው አይደል ባሻዬ? ‹‹አውቃለሁ ባይነት፣ ግትርነት፣ አጉል ጉልበተኝነት፣ ስንፍና፣ አድርባይነት፣ አስመሳይነት፣ ተላላኪነት፣ ዕውቀትና ማስተዋል ተፀያፊነት ዕውን የእኛ ናቸው? ወይስ ከመጀመሪያው እኛ ራሳችንን አልነበርንም? ከአቅም በላይ መኖር ቢያቅተን እንዴት በልክ መኖር ያቅተናል? በተውሶ ስሞች ከመጨቃጨቅ እስቲ ራሳችንን እንምሰል፡፡ የተውሶ ነገር አያዛልቅም…›› አሉኝ፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት