Wednesday, May 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልበደጋ ሰው የመጣችው የማ

በደጋ ሰው የመጣችው የማ

ቀን:

ጎልታ የምትታወቀው በመድረክ ስሟ ‹‹የማ›› ሲሆን፣ የመጠሪያ ስሟ ግን የማርያም ቸርነት ነው፡፡ የስሟን የመጀመሪያ ሁለት ፊደሎችን በመውሰድ የማ (YEMa) የሚለው ቅፅል ስም፣ አሐዱ ባለችው የሙዚቃ አልበም ሥራዋ ላይ በጉልህ ተመልክቷል፡፡ የመጀመሪያው አልበሟ አገር በቀል የሆነውን የሙዚቃ ትውፊትና ባህል ከምዕራብና ከሰሜን አፍሪካ የሙዚቃ ሥሪት ጋር በማዛመድ የተሠራ መሆኑ ይነገራል፡፡ ስለሙዚቃ ሕይወቷ የማነ ብርሃኑ አነጋግሯታል፡፡   

በደጋ ሰው የመጣችው የማ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሪፖርተር፡- የማርያም ቸርነት (የማ) የት ተወለድሽ? አስተዳደግሽስ ምን ይመስላል?

- Advertisement -

የማርያም– የተወለድኩት አዲስ አበባ ‹‹ቀበና›› በሚባል አካባቢ ነው፡፡ በቤተሰቦቼ ውስጥ ሦስተኛና የመጨረሻ ልጅ ስሆን፣ አስተዳደጌም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጅ እንደሚያድገው ሆኜ ነው ያደግኩት፡፡ ከሠፈር ልጆች ጋር አንድ ላይ በመጫወት ያሳለፍኩት የልጅነት ጊዜ ብዙ ትዝ አይለኝም፡፡ ከቤት ርቄ ወደ ውጪ እንድወጣ አይፈቀድልኝም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የትምህርት ቤት ቆይታሽስ ምን ይመስላል? ትምህርትሽንስ የተከታተልሽው የት ነው?

የማርያም– የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን የተማርኩት ቅድስት ማርያም ካቶሊክ ትምህርት ቤት ሲሆን፣ ሁለተኛ ደረጃ  ትምህርቴን በፊውቸር ትምህርት ቤትና በማክ ሚላን አካዴሚ ተከታትያለሁ፡፡ በትምህርት አቀባበሌም ጎበዝና ውጤታማ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል የምመደብ ነበርኩ፡፡

ሪፖርተር፡- የሙዚቃ ፍላጎትሽ ከየት መነጨ? የሙዚቃ አጀማመርሽስ ምን ይመስላል?

የማርያም– ከልጅነቴ ጀምሮ ሙዚቃ ማድመጥም ሆነ መጫወት በጣም ደስ ይለኝ ነበር፡፡ አብዛኛውን የማደምጠው የእንግሊዝኛ ዘፈኖችን ነው፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ. በ1990 እና በ2000 አካባቢ የወጡ የእንግሊዝኛ ዘፈኖችን ማዳመጥ ያዝናናኛል፡፡ አልፎ አልፎ ዘመናዊ የሚባሉ የአማርኛ ዘፈኖችንም እሰማለሁ፡፡ የሙዚቃ ጅማሮዬን በተመለከተ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ክለብ ተቀላቅዬ መጫወት ስጀምር የተሰጠሁት ለዚህ ሙያ ነው ብዬ በማመን ልገፋበት ችያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በመድረክ የእነማንን ሙዚቃ በይበልጥ መጫወት ትመርጫለሽ?

የማርያም– በባንድ ደረጃ ሙዚቃን መጫወት በጀመርኩ ጊዜ እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ አካባቢ የተዜሙ የእንግሊዝኛ ዘፈኖች ምርጫዎቼ ነበሩ፡፡ ከአማርኛ የጋሽ ባህታ ገብረ ሕይወትና የእጅጋየሁ ሽባባው ዘፈኖች የምጫወታቸው ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የ‹‹ደጋ ሰው›› አልበምን ከማውጣትሽ በፊት ከሕዝብ ጋር አስተዋውቆኛል የምትዪው ሥራ የትኛው ነው?

የማርያም– የአገራችን አንጋፋና ታዋቂ ሙዚቀኞች ከሆኑት ከእነ ፀጋዬ እሸቱ፣ ንዋይ ደበበ፣ ሠርፀ ፍሬ ስብሐትና ኃይልዬ ታደሰ ጋር ‹‹ቅኔ ነው አገሬ›› የሚል በኅብረት የሠራነው ሙዚቃ ከሕዝብ ጋር በተወሰነ መልኩ ያስተዋወቀኝ ሥራ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የ‹‹ደጋ ሰው›› አልበምን ሠርቶ ለማጠናቀቅ ምን ያህል ጊዜ ወሰደ? ከገንዘብስ አንፃር?

የማርያም– አልበሙን አጠናቅቆ ለሙዚቃ አፍቃሪያን ጆሮ ለማድረስ ሁለት ዓመታት ያህል ወስዷል፡፡ ብዙ ድካም፣ ብዙ ልፋትም ነበረው፡፡ አጠቃላይ ለአልበሙ የወጣው ገንዘብ ይህ ነው ብዬ ለመናገር ባልችልም ኢዩኤል መንግሥቱ (ፕሮዲውሰር) መኪናውን እስከመሸጥ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ ከገንዘቡ፣ ከልፋቱና ከድካሙ በላይ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘቱና በደንብ እየተደመጠ መሆኑ ብቻ ለእኛ እንደትልቅ ስኬት የምንቆጥረው ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ከፕሮዲውሰር ኢዩኤል ጋር እንዴት ተገናኛችሁ? አልበሙንስ ለመሥራት ምን አነሳሳችሁ?

የማርያም– ከኢዩኤል ጋር የተዋወቅነው እሱና ጓደኞቹ የመሠረቱት የሙዚቃ ባንድ ጋር ሙዚቃ ለመጫወት በተቀላቀልኩና ‹‹ራማዳ›› ሆቴል በምጫወትበት ወቅት ነው፡፡ የደጋ ሰው አልበምን ለመሥራት ያነሳሳን በክለብ ለምንጫወታቸው ከምናጠናቸው ዘፈኖች አንዱን ሪከርድ  በምናደርግበት ወቅት ኢዩኤል ድምፄንና ስታይሌን ስለወደደው አንድ አልበም በጋራ እናዘጋጅ በሚል ተነሳስተን ይህንን የሙዚቃ አልበም ልንሠራና ለሕዝብ ጆሮ ልናበቃ ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- የሙዚቃ አልበሙን ለማዘጋጀት ከአዲስ አበባ ውጪ የቀሰማችሁት ምንድነው?

የማርያም– በመጀመሪያ ለዚህ አልበም መነሻ የሆነው የኢዩኤል ከጋሞ ብሔር፣ ‹‹የሶንኬ› ማኅበረሰብ የሙዚቃ ጥናት ጉዞ ነው፡፡ እሱ በዚያ ጉዞው የተመለከተው አገረ ሰብ ሙዚቃ አዲስ ለምናዘጋጀው አልበም መሠረት ይሆናል ብሎ በማመን፣ ወደ ጋሞ ሶንኬ ማኅበረሰብ ተጉዘናል፡፡ የደጋ ሰው አልበም መጠሪያ የሆነው የደጋ ሰው ዘፈን ግጥሙ የደጋ አካባቢን የሚዳስስና የሚገልጽ በመሆኑ፣ ብርዱንና ቅዝቃዜውን በይበልጥ ለመረዳትና ሙዚቃውንም በዚያ ስሜት ለመሥራት ወደ ባሌ የተጓዝንበትም አጋጣሚ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በዜማ፣ በግጥምና የሙዚቃ መሣሪያ በመጫወት እነማን ተሳትፈውበታል?

የማርያም– በዚህ የሙዚቃ አልበም ሥራ ላይ የአገራችን አንጋፋና ወጣት የሙዚቃ ሰዎች ተሳትፈውበታል፡፡ ኢዩኤል መንግሥቱ የአልበሙን ሙሉ ቅንብር ከመሥራት ባሻገር 11 ዜማዎችንና ሁለት ግጥሞችን አበርክቷል፡፡ ይልማ ገብረአብና በጋሞ ጉዟችን ያገኘናት ዓይናለም አዞ የተባለች የሶንኬ ማኅበረሰብ ሙዚቃኛ አንድ አንድ ግጥም ያበረከቱ ሲሆን፣ ጎላ ጎሕ (የብዕር ስም) ስምንት የሙዚቃ ግጥሞችን ጽፏል፡፡ የሙዚቃ መሣሪያ በመጫወት ኢዩኤል መንግሥቱ፣ አክሊሉ ዘውዴ (ረዳት ፕሮፌሴር)፣ ዕዝራ አባተ (ዶ/ር)፣ ተፈሪ አሰፋና እንድሪስ ሐሰን የሚገኙበት ሲሆን፣ ሰባት የውጭ አገር ዜጎችም የሙዚቃ መሣሪያ በመጫወት ተሳትፈዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በደጋ ሰው አልበም ለሙዚቃ አድማጩ ማኅበረሰብ ልታስተላልፉ የፈለጋችሁት መልዕክት ምንድነው ነው?

የማርያም– የዚህ አልበም ዋና ዓላማው የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም መድረክ ከፍ አድርጎ ማሳየት ነው፡፡ ውብና ድንቅ ባህላችንን ከማጉላት አንፃርም አልበማችን የራሱ የሆነ አበርክቶ እንዲኖረው ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት አድርገናል፡፡ በዚህም ተሳክቶልናል ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ለዚህ ሙዚቃ አልበም ስኬት ድጋፍ ያደረጉልሽና ልታመሠግኚያቸው የምትፈልጊያቸው እነማንን ነው?

የማርያም፡- በቅድሚያ ለዚህ ስኬት ያበቃኝ እግዚብሔርን አመሠግናለሁ፡፡ በመቀጠል ማመሥገን የምፈልገው ፕሮዲውሰር ኢዩኤል መንግሥቱን ነው፡፡ ለዚህ የሙዚቃ ሥራ መርጦኝ፣ ዕድሉን ሰጥቶኝና ጥሩ መሪ ሆኖኝ ትልቁን ሚና በመጫወቱ አመሠግነዋለሁ፡፡ በግጥም፣ በዜማና የሙዚቃ መሣሪያ በመጫወት በአልበሙ ላይ ተሳትፎ ያደረጉ የአገራችንና የውጭ አገር ባለሙያዎችንም እጀግ አድርጌ አመሠግናለሁ፡፡ ከእነርሱ ጋር መሥራት በራሱ ለእኔ ትልቅ ክብር ነው፡፡ ከልጅነቴ ጀምረው በመደገፍና በማበረታታት እዚህ ደረጃ እንድደርስ ላበቁኝ ቤተሰቦቼና በአልበም ሥራዬ ወቅት ዕገዛ ላደረጉልኝ ሁሉ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...