Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹በሶማሊያ ወንድሞቻችን ላይ ምንም ዓይነት የከፋ ነገር ለመናገርም ለማድረግም ዝግጁ አይደለንም›› ...

‹‹በሶማሊያ ወንድሞቻችን ላይ ምንም ዓይነት የከፋ ነገር ለመናገርም ለማድረግም ዝግጁ አይደለንም›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹በሶማሊያ ወንድሞቻችን ላይ ምንም ዓይነት የከፋ ነገር ለመናገርም ለማድረግም ዝግጁ አይደለንም፤›› ሲሉ ለፓርላማ አባላት ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማክሰኞ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ማብራሪያ ሲሰጡ ነው፡፡

ከምክር ቤት አባላት ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ስገምት የሶማሊያ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የመጋጨት ፍላጎት ያለው አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች ሶማሊያን የውክልና ጦርነት ማካሄጃ ማድረግ ይፈልጋሉ፣ ለዚህ ደግሞ እኛ አንመችም፤›› ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ሶማሊያን የውክልና ጦርነት ማካሄጃ ለማድረግ የሚመኙ ኃይሎች ለአንዳንድ ዳያስፖራ ወንድሞች ሚዲያ እንደከፈቱላቸው ሁሉ፣ ለአንዳንድ ሶማሊያ ወንድሞችም የተወሰነ ነገር ሊያደርጉላቸው ይችላሉ፣ ሊያዋጉን ግን አይችሉም፣ በእኛ በኩል ቢያንስ አንዋጋም፣ አንፈልግም›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት በርካታ ዓመታት የሶማሊያን ሰላም ለማስከበር በሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን፣ የሶማሊያ ሕዝብ ወንድም በመሆኑ ከኢትዮጵያውያን በላይ ለሶማሊያ የሞተ አለመኖሩንና ወደፊትም እንደማይኖር፣ ነገር ግን ስለሶማሊያ መግለጫ የሚያወጣ በስም ያልጠቀሱት ስለመኖሩ ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ወራት በሺሕ የሚቆጠሩ የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች ሁርሶ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ሠልጥነው መላካቸውን አክለዋል፡፡

‹‹ለሶማሊያ አንድነት እንደዚህ መንግሥት የሠራ የለም፣ ሶማሌላንድና ሶማሊያን ለማገናኘት ብዙ ጥረት አድርገናል፡፡ ነገም ሁለቱ ቢስማሙ የመጀመሪያው ተደሳች አገር ኢትዮጵያ ነች፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሥጋት 120 ሚሊዮን ሕዝብ ጉዳይ ነው ያሉት ጠቅለይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ተረዱን እያልን ነው፣ ይህንን ዓለም ተገንዝቦት በዓለም ሕግ እንዲዳኘን፣ በቢዝነስ ሕግ እንዲዳኘን እንፈልጋለን፡፡ የማንንም ሉዓላዊነት መንካት ግን አንፈልግም›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ አቧራው ጨሰ የሚለውን ጩኸት ማብረድ ትፈልጋለች፡፡ በታሪኳ የማንንም አገር ወርራ አታውቅም፣ ማንም አገር ወሯት ግን አሸንፏትም አያውቅም፡፡ ሦስት አይደለም አሥር አገር ቢደመር ኢትዮጵያን ማሸነፍ አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እኛ አንዋጋም፣ ልንዋጋም አንፈልግም፡፡ ነገር ግን ወደዚህ የመጣ አይችለንም፣ እኛ ያሠጋን የሠፈር ጎረምሳ እንጂ ወራሪ አይደለም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሲያብራሩ የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ 1.2 ትሪሊዮን ብር መድረሱን፣ ባለፉት ስድስት ወራት 170 ቢሊዮን ብር ብድር መሰጠቱንና ከዚህ ውስጥ 83 ከመቶ የሚሆነው ለግሉ ዘርፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ጥቂት አገሮች አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፣ ዕድገት መኖሩን ነገር ግን የቆዩ ስብራቶች በመኖራቸው ኢኮኖሚው በማደግና በመፈተን መካከል እንዲወድቅ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዕድገት የሚታይ በመሆኑ፣ ልማቱ ምንም አስረጂ እንደማያስፈልገውና የመጣ ሰው ሁሉ የሚናገረው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹እናንተ በየቀኑ ስለምትኖሩበት ላይታወቃችሁ ይችላል፣ የመጣ ሰው ሁሉ ምን ተፈጠረ? ነዳጅ አግኝታችሁ ነው ወይ? ገንዘቡ ከየት መጣ? ማን ረዳችሁ?›› የሚለው ጥያቄ መብዛቱን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያውያንን መቼም ትችላላችሁና ሠራችሁት ማለት ኃጢያት ስለሆነ ከጀርባችሁ ማን አለ የሚል ጥያቄ ሁልጊዜም እንደሚነሳና ማን ዲዛይን አደረገው? ማን ፋይናንስ አደረገው? የሚል ጥያቄ ሁሌም አለ ብለዋል፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ሥራውን መካድ ስለማይቻል ባለቤቱን ለመቀየር የመሞከር ሒደት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በስድስት ወራት ውስጥ ከታቀደው 270 ቢሊዮን ብር ገቢ ውስጥ 265 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ ገቢ ከዓምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር የ17 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ከጋራ የክልሎች ገቢም በስድስት ወራት 27.8 ቢሊዮን ብር መከፋፈሉን አስታውቀዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም. 17 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሸቀጥ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን፣ በተያዘው ዓመት አምስት ወራት ብቻ 7.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሸቀጥ ወደ አገር ቤት እንደገባ አስረድተዋል፡፡

በአምስት ወራት የተመዘገበው የውጭ ኢንቨስትመንት 1.5 ቢሊዮን ደላር እንደሆነ፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድል መፈጠሩንና 150 ሺሕ ዜጎች ወደ ውጭ አገሮች ለሥራ መላካቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ 

በዶሮ ዕርባታ ልማት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጥሩ የዶሮ ዘሮች ማግኘት ችግር በመሆኑ ችግር ሲፈታ ግን፣ ‹‹በመቶ ማሊዮኖች ዶሮ በማምረት በየመንገዱ ዶሮ መጥበስና እየበሉ መሄድ ኢትዮጵያ ውስጥ ወግ ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

ከውጭ ብድር ጋር በተገናኘ ለተነሳው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ለመንግሥት ትልቁ ስኬትና የሚያኮራ ድል ያሉት ዕዳ ላይ ያለው አቋም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ስትቀበለው የነበረው ብድር ሳይሆን አራጣ ስለመሆኑ ጠቅሰው፣ ከነበረባት ብድር ከ2011 ዓ.ም. እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ 9.9 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ መክፈሏን ተናግረዋል፡፡

ለውጡ በፊት የመንግሥት የውጭ ዕዳ 32 በመቶ የአገር ውስጥ ሀብት ይይዝ እንደነበረ፣ አሁን ግን የውጭ ዕዳ ወደ 17 በመቶ መውረዱን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሠረት ድንጋይ እየተቀመጠላቸው ለዓመታት የሚጓተቱ ፕሮጀክቱን በተመለከተ ለቀረበ ጥያቄ ሲያብራሩ፣ ‹‹እኛ ድንጋይ አስቀምጠን ለመሥራት የማንፍጨረጨርበት ፕሮጀክት የለም፡፡ በተደጋጋሚ እንዳልኩት በሆነ ባልሆነ ጊዜ የተዘራ ድንጋይ ለመልቀም አልመጣንም፡፡ ዝም ብሎ በየሄዱበት ድንጋይ እያስቀመጡና ቃል እየገቡ ተሂዶ አሁን በጊዜ ተጀምሯል ቢባል አስቸጋሪ ነገር ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሥራ በበጀት የሚከናወን በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍላጎቱ ከፍተኛ መሆኑንና ለኤሌክትሪክ፣ ለግድብ፣ ለውኃና ለመሰል ፕሮጀክቶች የሚበቃ ሀብት የለም ብለዋል፡፡ ‹‹እየመረጥን ነው የምንሠራው፡፡ እኛም ጀምረናቸው በፀጥታ፣ በኮንትራክተሮችና በክትትል እጥረት ምክንያት የዘገዩ ፕሮጀክቶች በመኖራቸው እየገመገምን እናርማለን፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...