Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከአስተዳደር ወሰን ጋር የተያያዘው ውዝግብ በሕዝበ ውሳኔ እንዲፈታ አለመስማማቱን የትግራይ ክልል አስታወቀ

ከአስተዳደር ወሰን ጋር የተያያዘው ውዝግብ በሕዝበ ውሳኔ እንዲፈታ አለመስማማቱን የትግራይ ክልል አስታወቀ

ቀን:

‹‹ሁለቱ ክልሎች ከዚህ የተሻለ መፍትሔ ካመጡ መንግሥት ተባባሪ ይሆናል››

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል የተነሳው የአስተዳደር ወሰን ይገባኛል ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ እንዲፈታ ስምምነትም ሆነ መግባባት አለማድረጉን አስታወቀ። 

ሕወሓት ከሳምንት በፊት የፕሪቶርያ ስምምነት እንዲከበር የሚጠይቅ መግለጫ ማውጣት የሚታወስ ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ደግሞ ለዚህ የሕወሓት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ መግለጫ ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም. አውጥቶ ነበር። በመግለጫውም የፌዴራል መንግሥት የፕሪቶሪያውን ስምምነት በቁርጠኝነት እየተገበረ መሆኑን ማሳያዎችን ጠቅሷል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ካቀረባቸው ማሳያዎች መካከል የፌዴራል መንግሥት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረትም ተፈናቃዮችን ወደ መደበኛ መኖሪያቸው ለመመለስ እንዲቻል የሚመለከታቸው አካላትን አቀናጅቶ ሥራ መጀመሩንና በአንዳንድ አካባቢዎችም ‹‹ትክክለኛ ተፈናቃዮችን›› ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ማድረጉን ያትታል።

በሌላ በኩል ደግሞ የአከራካሪ ቦታዎችን ሁኔታ በዘላቂነት ለመፍታት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ጉዳዩ በዋናነት ከሚመለከታቸው ከአማራና ትግራይ ክልሎች ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር አመላክቷል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ደግሞ ለፌዴራል መንግሥት መግለጫ ምላሽ ሰኞ ጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ፊርማ ይፋ የተደረገ መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫውም የተነሳው የአስተዳደር ወሰን ውዝግብ በሕዝበ ውሳኔ እንዲፈታ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምንም ዓይነት ስምምነት አለማድረጉን አስታውቋል።

‹‹ከትግራይ ሉዓላዊ ግዛት መረጋገጥ ጋር በተያያዘ ጉዳዩን በሪፈረንደም ለመፍታት መረዳዳት ተደርሶ ነበር በሚል የቀረበው መግለጫ ፍፁም የተሳሳተና ጊዜያዊ አስተዳደሩም ሆነ የፌዴራል መንግሥቱ ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ፣ ጉዳዩን ለመፍታት ካደረጉት የፕሪቶሪያው ስምምነትም ሆነ ካላቸው ሥልጣን ውጪ የሆነ ተግባር መሆኑን በተደጋጋሚ ያነሳነው ስለሆነ፣ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን መግለጽ እንወዳለን፤›› ብሏል።

ይህ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምላሽ የሰጠበት መግለጫ በወጣ ማግስት ትናንት ማክሰኞ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ሌላ ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽም ‹‹ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚቻለው በአካባቢው ማኅበረሰቦች መካከል ውይይትና ምክክር ተደርጎ ነዋሪው ራሱ በሕዝበ ውሳኔ ወደ ፈለገው አካባቢ እንዲካለል ይደረግ ብለን ለሁለቱም ክልሎች አሳውቀን ወደ ሥራ ልንገባ ስንል አሁን በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭት አጋጠመን፤›› ብለዋል።

በዚህ ላይ ልዩነት ካለ ደግሞ የአማራም ሆኑ የትግራይ ምሁራን የተሻለ ነው የሚሉትን፣ ሕዝብን ከሕዝብ የማያጋጭ መፍትሔ ማምጣት እንደሚችሉና ካመጡም የፌዴራል መንግሥት ተባባሪ እንደሚሆን ተናግረዋል። 

ከዚህ ውጪ ግን የፌዴራል መንግሥት አንዱን የሚደግፍ ሌላውን የሚጎዳ ውሳኔ ለመወሰን እንደማይችል የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥት ሁሉንም ሕዝቦች በእኩል ማየት ስላለበት ያንን ማድረግ ይቸገራል። ይህንን መገንዘብ አስፈላጊ ይመስለኛል፤›› ብለዋል።

ውይይትና ሕዝበ ውሳኔ እስኪካሄድ ድረስ ግን አንኳር አንኳር ጉዳዮች እንዲመለሱ መወሰኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ከእነዚህ አንኳር ጉዳዮች መካከል አንዱ የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደ ቀዬአቸው መመለስ እንደሆነ ገልጸዋል። ሌላኛው አንኳር ጉዳይ ደግሞ የወሰን ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎችን ሕዝብ በውክልና ማስተዳደር ስለማይቻል የአካባቢው ነዋሪ በቀበሌ ወይም በወረዳ ደረጃ ምርጫ አካሂዶ ራሱን በራሱ ያስተዳድር የሚል እንደሆነ ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል ከረር ያሉ የመግለጫ ልውውጦች እየተስተዋሉ ሲሆን፣ ሁለቱ አካላት በልዩነቶቻቸው ዙሪያ ለመነጋገርና የፕሪቶሪያው ስምምነትን አጠቃላይ አፈጻጸምን ለመገምገም በቅርቡ በአካል ለመገናኘት ቀጠሮ መያዛቸው ታውቋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ (ክፍል አንድ)

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...