Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በአሁኑ ሰዓት እየፈተነን ያለው እንደ ልብ ተንቀሳቅሰን መሥራት አለመቻላችን ነው›› አቶ ልዑል ሰገድ መኮንንን፣ አይሲዳ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር

አይሲዳ አገር በቀል የዕርዳታ ድርጅት በኤችአይቪ ሥርጭት ቁጥጥር ላይ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከ1998 ዓ.ም. ወዲህ ራሱን እንደ አዲስ አዋቅሮ በተለይ ለሰው ሠራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ ይሠጣል፡፡ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ልዑል ሰገድ መኮንንን ናቸውለ፡፡ ድርጅቱ በሚያከናውናቸው ጉዳዮች ዙሪያ ታምራት ጌታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አይሲዳ እንዴት ተመሠረተ?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- አይሲዳ የተቋቋመው በ1998 ዓ.ም ሲሆን፣ በኤችአይቪ ዙሪያ ይሠራ ነበር፡፡ ቀጥሎም ራሱን በማሳደግ በተለያዩ ሥራዎች ተሰማርቷል፡፡ በዋነኛነት ሰው ሠራሽም ይሁን የተፈጠሮ አደጋ በሚከሰትበት ወቅት ፈጣን ምላሽ በመስጠት ተጎጂዎችን ማቋቋም ሲሆን፣ በንፁህ ውኃ አቅርቦት፣ በንፅህና አጠባበቅ፣ በትምህርት፣ በተመጣጠነ የምግብ ሥርዓት፣ በግብርናና በምግብ ዋስትና፣ በሰብዓዊ ድጋፍ፣ በአካባቢ ጥበቃና በአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም በጥናትና ምርምር ዘርፎች ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በየትኞቹ አካባቢዎች ትሠራላችሁ?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- አይሲዳ ሥራውን ሲጀምር በአፋር ክልል በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ውስጥ ነበር፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊት ጀምሮ ደግሞ ሥራውን በማስፋት በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን እየሠራ ይገኛል፡፡ በጦርነቱ የተጎዱ ሰዎችን በማገዝ፣ የፆታ እኩልነት ትምህርት በመስጠትና ጥሬ ገንዘብ ማቅረብ ከሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ በትግራይ ክልልም ጊዚያዊ ጣቢያ በመክፈት በተመሳሳይ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡  

ሪፖርተር፡- እስካሁን ምን ያህል የማኅበረሰብ ክፍሎችን ደርሳችኋል?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- አይሲዳ ከተመሠረተ ጀምሮ ከግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ መድረስ ችሏል፡፡ ዋናው ነገር ግን ቁጥሩ ሳይሆን ወቅታዊ ምላሽ ለማኅበረሰቡ ማድረስ መቻሉ ነው፡፡ ይህንን ባናደርግ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት ይችል ነበር፡፡ ድጋፍ የተደረገላቸው ሰዎች በሕይወት እንዲቆዩ፣ ከአካል ጉዳት እንዲያገግሙ፣ ከአዕምሮ ጉዳታቸው እንዲላቀቁና ጤናማ ሕይወት እንዲመሠርቱ ማስቻሉ ትልቁ ነገር ብዬ አስባለሁ፡፡ ድርጀቱ ከተመሠረተ ጀምሮ በጠቅላላው ለ769.091 አባወራዎች አገልግሎት ሰጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገር በቀል የዕርዳታ ድርጅቶች ላይ የሚታየው ትልቅ ችግር ምንድነው?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ድርጅቶች የሚሠሩት ሥራና የሚያገኙት ድጋፍ በፍፁም የሚመጣጠን አይደለም፡፡ ችግሩም ሰፊ ነው፡፡ በድርቅ፣ በጦርነት፣ በወባ፣ በተፈጥሮ፣ በሰው ሠራሽ የሚመጡ ችግሮች እየባሰባቸው እንጂ እየቀነሱ አልሄዱም፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ሲከሰቱ ቀድመን መድረስ ያለብን እኛ ነን፡፡ ሆኖም ከፍተኛ የሀብት ችግር አለብን፡፡ ሌላው ትልቁ ችግር፣ ችግሩን ቀድመን የምንጋፈጠው እኛ ብንሆንም፣ ዓለም አቀፍ ረጂ ግለሰቦችም ይሁኑ ድርጅቶች ገንዘቡን በቀጥታ ለእኛ አይሰጡም፡፡ ገንዘቡን ለዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ይሰጣሉ፡፡ እነሱ ወጪያቸውን ቀንሰው ነው ለእኛ የሚሰጡን፡፡ ይህ የሚደርሰንን ገንዘብ ይቀንሰዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገር ውስጥ ሀብት ለማሰባሰብ ያደረጋችሁት ጥረት አለ?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- በአገር ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ ደካማ ነው፡፡ በእርግጥ ከመቄዶንያ ከኅብረተሰቡ ማሰባሰብ እንደሚቻል ታይቷል፡፡ በዚህ በኩል እኛ ብዙም ገፍተን አልሄድንበትም፡፡ ወደ ፊት የምንሄድበት ይሆናል፡፡ ድርጅቱ 60 አባላት ያሉት ሲሆን፣ እንደ ፍላጎታቸው መዋጮ ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ ዓምና 32 አባላት ብቻ መዋጮ አድርገው፣ 42 ሺሕ ብር ብቻ አግኝተናል፡፡ ከአባላት የሚገኘው መዋጮ ለድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች፣ ለሠራተኞች ደመወዝና ለሥራ መስኬጃ የሚያግዝ ነው፡፡ ብዙ ተርፎ ለተረጂዎች የሚውል አይደለም፡፡ ሌላው በግለሰብ ደረጃ በቀጥታ ለተጠቃሚዎች እንዲውሉ የሚለግሱ አሉ፡፡ እኛ ከዚህ ምንም አንነካም፡፡

ሪፖርተር፡- አይሲዳን የፈተነው ችግር ምንድነው?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- እንደ ሌሎች አገር በቀል ድርጅቶች ያለው ፈተና በእኛ ላይ ያለ ሲሆን፣ የእኛን የሚለየው ግን ሁሉም ችግሮች ሲከሰቱ ቀድመን ፊት ለፊት ደራሾች መሆናችን ነው፡፡ አሁን ላይ ያለው የችግር ስፋት እየጨመረ በመምጣቱ የሀብት እጥረት እየገጠመን ይገኛል፡፡ ትልቁ እየጎዳን ያለው ደግሞ በድንገት የሚወጡ ፖሊሲዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ 20/80 የሚባለው አንዱ ነው፡፡ ለዕርዳታ ድርጅቶች ከቀረጥ ነፃ ተፈቅዶ ዕቃ ማምጣት ስንጀምር ድንገት ደግሞ የሚከለክል አዋጅ መውጣቱ ጎድቶናል፡፡ በዚህም ሁለት ላንድ ክሩዘር መኪናዎች ከቀረጥ ነፃ አምጥተን ጂቡቲ ከደረሱ በኋላ ቀረጥ ካልከፈላችሁ አይገቡም በመባሉና የምንከፍለው ባለመኖሩ ለሁለት የአፍሪካ አገሮች እንዲከፋፈሉ ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ እየፈተነን ያለው ባለችንም ሀብት ተጠቅመን እንደ ልብ ተንቀሳቅሰን መሥራት አለመቻላችን ነው፡፡ መድረስ ላለብን ማኅበረሰብ አገልግሎቶቻችንን ካላደረስን ሰብዓዊ ቀውሱን የበለጠ ሊያባብሰው ይችላል የሚልም ሥጋት አለን፡፡  

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በአፋር ክልል ተከስቶ ለነበረው የኮሌራ ወረርሽኝ የእናንተ ድርጅት ምን ሥራዎችን አከናወነ?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- የኮሌራ ወረርሽኝ እንደ አገር የተከሰተ ነው፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያ እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች የተስፋፋበት ሁኔታ ነበር፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ አፋር ክልል ነው፡፡ ወረርሽኝ በስፋት ያጠቃቸው በዞን ሦስት ውስጥ የሚገኙ አዋሽ፣ ፈንታሌና አሚባራ እንዲሁም ዱለቻ የሚባሉ ወረዳዎችን ነው፡፡ ከ245 በላይ የማኅበረበሰብ ክፍሎች በወረርሽኙ የተጠቁ ሲሆን፣ አራት ሞተዋል፡፡ በአካባቢው ያለው የንፁህ ውኃ አቅርቦትና የመሠረተ ልማት አነስተኛ መሆን ለችግሩ መንስዔ ናቸው፡፡ ያለውም የውሃ አቅርቦት ከአዋሽ በሚነሳ ጎርፍ በየወቅቱ ስለሚጠቃና መልሶ ጥገና ለማድረግ የአቅም ውስንነት መኖሩ ሕዝቡ የአዋሽን ወንዝ እንዲጠቀም አስገድዶታል፡፡ በዚህ ምክንያት ወረርሽኝ በመከሰቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ ሊጎዳ ችሏል፡፡ እኛ ወረርሽኙ እንደተከሰተ ዓለም አቀፍ ድርጅት ከሆነውና በአጋርነት ከምንሠራው አይአርሲ ጋር በመሆን፣ 350 ሚሊዮን ፓውንድ ለግሶን በሦስቱም ወረዳዎች ስለበሽታው ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን ሰጥተናል፡፡ ተጨማሪ የኮሌራ ማገገሚያ ክፍሎችን ሠርተናል፡፡ ንፁህ ውኃ በቦቲ ለማኅበረሰቡ ማቅረብ፣ የመፀዳጃ ቤቶችን ግንባታ፣ የመድኃኒት አቅርቦትና ርጭት ማካሄድ፣ የንፅህና መጠበቂያ አልባሳት ድጋፍ ማድረግ፣ የውኃ አጋር ሥርጭት፣ የንፁህ ውኃ መቅጃ ጀሪካኖችን ማደል ከሠራናቸው ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህም ከ25 ሺሕ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ የመድኃኒት አቅርቦት ካገኙ ሰዎች ጋር ወደ 64 ሺሕ የሚጠጉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከወረርሽኑ ጋር በተያያዘ ደርሰናል፡፡ ከክልሉ መንግሥት ጋር በሠራነው ሥራም ወረርሽኙ ከቁጥጥር ሳይወጣ ለማቆም ተችሏል፡፡  

ሪፖርተር፡- በክልሉ ይህ በሸታ ለሁለተኛ ጊዜ እንደተከሰተ ይታወቃል፡፡ በቋሚነት ለመፍታት ምን ጥረት እያደረጋችሁ ነው?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- የእኛ ሥራ ለድንገተኛ አደጋ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ነው፡፡ ግን እንዲህ ነው ብለን አንተውም፡፡ እኛ የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶች መንግሥት ተረክቦ እንዲያስቀጥላቸው የድጋፍ ሥራዎች አሉን፡፡ በቋሚነት ግን የመንግሥት ሥራ ነው፡፡ በዚህኛው ሥራ ለየት ያለ ዘዴ በመከተል ከተለያዩ ድርጅቶችና ከክልሉ መንግሥት ጋር በቋሚነት ለመፍታት ውይይት ጀምረናል፡፡ በተገኘው ድጋፍም ችግሩን ለማቃለል ይሠራል፡፡   

ሪፖርተር፡- አገር በቀል ድርጅቶች እንዲጠናከሩ ምን መሠራት አለበት ይላሉ?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- በመጀመሪያ ደረጃ የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ እንደሚባለው፣ የራሳችንን ችግር ራሳችን መፍታት አለብን፡፡ ለዚህም ትልቁን ድርሻ የሚወስደው መንግሥት ነው፡፡ ለእነዚህ ድርጅቶች የተለየ ፖሊሲ ማውጣት፣ ማበረታታት፣ ሥራዎቻችንን ማሳየት አለበት፡፡ ለምሳሌ የመንግሥት ሚዲያዎች ጥረታችንን እንዲዘግቡ ማድረግ፣ ራሱ መንግሥትም ያለንበትን ሁኔታ ወረዶ ማየት አለበት፡፡ ዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማትም ቀጥታ ወደ አገር በቀል ድርጅት ገንዘባቸውን ፈሰስ ቢያደርጉ ጥሩ ነው፡፡ በቅርቡ በኳታር በተካሄደው ጉባዔ ላይ በተደረሰው ስምምነት መሠረት 21 በመቶ ለአገር በቀል ድርጅቶች ቀጥታ ፈሰስ እንዲደረግ ብንስማማም እስካሁን 10 በመቶ እንኳን ተፈጻሚ አልሆነም፡፡ ይህ ተፈጻሚ እንዲሆን መንግሥት ግፊት ቢያደርግ መልካም ነው፡፡ ማኅበረሰቡም እነዚህ ድርጅቶች ከእኔ ወስደው ለእኔው ነው የሚያውሉት በማለት አስተዋጽኦውን ከፍ ማድረግ አለበት፡፡ እኛም የዕርዳታ ድርጅቶች የገባነውን ቃል መተግበር አለብን፡፡ እነዚህ የዕርዳታ ድርጅቶችን ሊያጠናክሩ ከሚችሉ በርካታ አበርክቶዎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡   

ሪፖርተር፡- አይሲዳ ወደፊት ምን ዕቅድ አለው?

አቶ ልዑል ሰገድ፡-  አይሲዳ ችግሮች ባሉበት ሁሉ የመድረስ፣ የመሥራት ፍላጎትና ግዴታ አለበት፡፡ ይህንንም አጠናክሮ በመቀጠል በቅርቡ ለመስፋፋት በነደፈው ዕቅድ መሠረት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዳዲስ ቢሮዎችን በመክፈት ሥራ ይጀምራል፡፡ ዋናው ነገር ግን በየቀኑ እየጨመረ የመጣውን የዕገዛ ፈላጊ ማኅበረሰብ ቁጥር በተለይ ሰላም በመፍጠር መቀነስ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችሉ አካላት ትኩረት በመስጠት ቢሠራ እኛም ትኩረታችንን ዘላቂነት ወዳላቸው የልማት ሥራዎች አዙረን ኅብረተሰቡን የበለጠ ተጠቃሚ ማድረግ እንችላለን፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...

‹‹ማንም ያለ ምክንያት አልተፈጠረምና ዜጎች እንዳይባክኑ እንሠራለን›› አቶ አብዱልፈታህ ሁሴን፣ የብሬክስሩ ትሬዲንግ ሥራ አስፈጻሚ

ብሬክስሩ ትሬዲንግ ‹ባለራዕይ፣ ቅን፣ ጤናማና ባለፀጋ ትውልድን ለመፍጠር የሚል ዓላማን ሰንቆ ቅን በተሰኘና አሥራ ስድስት አባላት ባሉት ቡድን ከአራት ዓመት በፊት የተመሠረተ ድርጅት ነው፡፡...