Thursday, February 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ በቀድሞ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የቦርድ አባላት ላይ የስድስት ዓመታት ዕግድ ጣለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ለገጠመው ችግር ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን የቀድሞዎቹን 12 ቦርድ አባላት፣ በትኛውም የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ በማንኛውም የኃላፊነት ደረጃ እንዳያገለግሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማገዱን ታወቀ፡፡

ብሔራዊ ባንክ በቀድሞ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የቦርድ አባላት ላይ የስድስት ዓመታት ዕግድ ጣለ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ለእያንዳንዱ የቦርድ አባላት በተናጠል እንዲደርሳቸው በተደረገ የዕግድ ደብዳቤ፣ ባንኩ ገጥመውታል ተብለው በዝርዝር ለቀረቡት ችግሮችና የአሠራር ግድፈቶች እያንዳንዱ የቦርድ አባል በጋራና በተናጠል ተጠያቂ መሆናቸውን ባካሄደው ምርመራ በማረጋገጡ የወሰደው ዕርምጃ መሆኑንም አስታውቋቸዋል፡፡

በሕግ አግባብ የተሰጣቸውን ኃላፊነትና የባንኩን ባለአክሲዮኖች አደራ በአግባቡ ባለመወጣት የገንዘብ አስቀማጮችን ጥቅምና ባንኩን ለአደጋ እንዲጋለጥ ማድረጋቸውን ጭምር የሚጠቅሰው ደብዳቤው፣ ነበሩ የተባሉትን ችግሮችም በዝርዝር አመላክቷል፡፡  

የዕግድ ደብዳቤው በዋነኛነት በባንኩ ኩባንያ አስተዳደር (Corporate Governance) እና የገንዘብ አከል ንብረት አስተዳደር (Liquidity Management) ላይ ትኩረት ያደረገ ተደጋጋሚ ምርመራ ማካሄዱን በማስታወስ የሚጀምር ነው፡፡ ምርመራውን ተከትሎም በምርመራው ግኝቶች ላይ ከቦርዱ ጋር ውይይቶች ማድረጋቸውና አስፈላጊውን የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወስድ በተደጋጋሚ ለቦርዱ አቅጣጫ መሰጠቱን ይጠቅሳል፡፡

ይሁን እንጂ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተገቢው ዕርምት ባለመወሰዱ፣ በባንኩ ላይ በተካሄደው ምርመራ ተገኘ ያለውንም ውጤት ዘርዝሯል፡፡ በተለይ የገንዘብ አስቀማጮችን ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ የባንኩን ጤናማነት የሚጎዱ፣ እንዲሁም በባንኩ የሥራ አመራር ላይ ከባድ ድክመት መከሰቱን የሚያሳዩ የአሠራር ግድፈቶች መፈጸማቸውን ለማረጋገጥ መቻሉን አስታውቋል፡፡

ከዚህም ሌላ በባንክ አሠራር ውስጥ ከሚጠቀሱ ቁልፍና ወሳኝ ተግባራት መካከል አንዱ፣ ሊያጋጥም የሚችልን የገንዘብ አከል ንብረት ዕጥረት ሥጋት ጤናማና ብቃት ባለው ሁኔታ ማስተዳደር የሚያስችል ሥርዓት (Effective Liquidity Management Risk System) ዘርግቶ ተፈጻሚ ማድረግ ቢሆንም፣ የቦርዱ አባላት ይህንን ባለማድረጋቸውም ተጠያቂ አድርጓቸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር የተያያዘውን የብሔራዊ ባንክ መመርያ ቁጥር 602/2021 እና 607/2021 መሠረት ይህንን ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አልቻለም ብሏል፡፡

 በዚህም ምክንያት ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የሚቀርቡለትን የክፍያ ጥያቄዎች ብሔራዊ ባንክ ባወጣው ‹‹Ethiopian Automated Transfer System (EATS) System Rule›› መሠረት በአግባቡ ማስተናገድ ባለመቻሉ፣ የባንኩ ጤናማ አሠራር ለአሉታዊ ተፅዕኖ እንዲዳረግ መደረጉንም ደብዳቤው ያመለክታል፡፡ ይህም ተደጋጋሚ የደንበኞች ቅሬታ እንዲፈጠር ከማድረጉም በተጨማሪ፣ በብሔራዊ ባንክ መመርያ ቁጥር 943/2022 መሠረት ባንኩን ለከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ሊዳረግ መቻሉንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕግዱን በተመለከተ ለእያንዳንዱ ቦርድ አባል በጻፈው ደብዳቤ ላይ አመልክቷል፡፡

 የባንኩን ዘለቄታዊ ጥቅም መሠረት ባደረገ መልኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ የዓላማ አንድነት ፈጥሮ ከባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ የተሰጠውን ኃላፊነት፣ እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ መመርያ ቁጥር 607/2021 እና በሌሎቹም አግባብነት ባላቸው ሕጎች የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ሲገባው፣ ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መንገድ በቦርድ አባላት መካከል የእርስ በእርስ መከፋፈል መፈጠሩን ተከትሎ፣ በባንኩ የሥራ አመራር ላይ ከባድ ድክመት ተስተውሏልም ብሏል፡፡ 

ከዚህ ሌላ ቦርዱ በብሔራዊ ባንክ መመርያ ቁጠር 607/2021፣ በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 እና በሌሎችም አግባብነት ባላቸው ሕጎች፣ እንዲሁም በሥራ ላይ ባለው የባንኩ መመሥረቻ ጽሑፍ ላይ በተለያየ መልኩ በተጣለበት ኃላፊነት መሠረት፣ የባንኩን የአደጋ ሥጋት በአግባቡ አለማስተዳደራቸውን ደብዳቤው አመልክቷል፡፡

አያይዞም፣ ‹‹ባንኩ ሕግን አክብሮ እንዲሠራ በማስቻል፣ እንዲሁም የማኔጅመንቱን የሥራ አፈጻጸም በቅርበት በመከታተልና በመገምገም ተገቢ የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ፣ ተጨባጭ የሆነ የሥራ አፈጻጸም ለውጥና መሻሻል እንዲመጣ ማድረግ ቢጠበቅበትም፣ ቦርዱ ይህን ማድረግ አልቻለም፤›› የሚለው የዕግድ ደብዳቤው በዚህም መሠረት ችግሮችና የአሠራር ግድፈቶች እንደ አንድ የቦርድ አባል በጋራና በተናጠል ተጠያቂ መሆናቸውን በምርመራው መረጋገጡን አስታውቋቸዋል፡፡ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክን በቦርድ አባልነት ሲያገለግሉ የቆዩት 12ቱ የቦርድ አባላት ላይ የተጣለውን ዕግድ ምክንያት፣ እንዲህ ባለው መንገድ የዘረዘረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሰጠው ውሳኔ የዕግድ ደብዳቤው ከደረሳቸው ዕለት ጀምሮ፣ ለስድስት ዓመታት በየትኛውም የፋይናስ ተቋማት ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ላይ እንዳይሠሩ የሚል ነው፡፡

ስለሆነም ‹‹በሕግ አግባብ የተሰጠዎትን ኃላፊነትና የባንኩን የባለአክሲዮኖች አደራ በአግባቡ ባለመወጣት፣ የገንዘብ አስቀማጮችን ጥቅምና ባንኩን ለአደጋ እንዲጋለጥ በማድረግዎ፣ በባንክ ሥራ አዋጅ ቁጥር 592/2000 አንቀጽ 31 (4) መሠረት ዕርምጃ ተወስዶቦታል›› በማለት ደብዳቤው ገልጿል፡፡

በማጠቃለያውም ‹‹ይህ ደብዳቤ ከተጻፈበት ቀን ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ በማንኛውም የፋይናስ ተቋማት ውስጥ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና/ወይም ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚ ሆነው እንዳያገለግሉ የተወሰነና ዕገዳ የተጣለብዎት መሆኑን አስታውቃለሁ›› በሚል ውሳኔው ተገልጿል፡፡ ደብዳቤው የተጻፈው በብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሲሆን፣ ዕግድ የተጣለባቸው የንብ ባንክ የቀድሞዎቹ የቦርድ አባላት አቶ ወልደ ተንሳይ ወልደ ጊዮርጊስ (የቦርድ ሊቀመንበር)፣ አቶ ዓለሙ ደነቀው፣ አቶ ሙሉጌታ አስፋው፣ አቶ ሙሉጌታ ወልደ ሚካኤል፣ አቶ ለማ ኃይለ ሚካኤል፣ ዶ/ር ዓለማየሁ ጉርሙ፣  ኮሚሽነር መላኩ ወልደ ማርያም፣ አቶ ሥዩም አስፋው፣ አቶ ክፍሌ ሰብጋዘ፣ አቶ አማረ ለማ፣ ዋልታ ኢትዮጵያ አ.ማ. (አቶ እንግሊዝ ብያን) እና ሙለጌ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (ወ/ሮ ሐያት ሙስጠፋ) ናቸው፡፡

በእነዚህ የቦርድ አባላት ምትክ የባንኩ ባለአክሲዮኖች አዲስ የቦርድ አባላት መምረጣቸው ይታወቃል፡፡

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የ2015 የሒሳብ ዓመት ጠቅላላ ጉባዔውን ታኅሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲያካሂድ፣ በዕለቱ የተደረገውን የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስፈጻሚነት የተካሄደ መሆኑም ይታወሳል፡፡

የባንኩን የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ በብሔራዊ ባንክ አስፈጻሚነት እንዲካሄድ ከውሳኔ ላይ የደረሰበትን ምክንያት ለጠቅላላ ጉባዔው በማስታወቅ፣ በተደረገው ምርጫ የተመረጡትን የ12ቱን አዳዲስ የቦርድ አባላትን ምርጫ ብሔራዊ ባንክ ያፀደቀላቸው በመሆኑ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር ባገኘው መረጃም አዲሱ ቦርድ ከትናንት በስቲያ ከነበሩ ቦርድ ኃላፊነቱን ተረክቦ ሥራ ጀምሯል፡፡ በዛሬ ዕለትም 12ቱ የቦርድ አባላት ከመካከላቸው የዳሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር የሚመርጡ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ቀድመው ከተቀላቀሉ ባንኮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ አሁን ገጠመው በተባለው ችግር ሳቢያ በብሔራዊ ባንክ ምርመራ ሲደረግበት ቆይቷል፡፡ ችግሩን ለመፍታትና ነገሮች እንዲስተካከሉ ብሔራዊ ባንክ የተለያዩ ዕርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል፡፡

ብሔራዊ ባንክ በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ላይ እያደረገ ካለው ለወራት የዘለቀ ምርመራ ምክንያት፣ እንዲሁም የገጠሙ ችግሮችን ለመፍታት በወሰዳቸው ዕርምጃዎች፣ በአሁኑ ወቅት ከተፈቀዱ የብድር ዓይነቶች ውጪ ባንኩ ብድር እንዳይሰጥ ተደርጓል፡፡

አዳዲስ ቅርንጫፎችን የመክፈትና አዲስ የሠራተኞች ቅጥር እየተካሄደ እንዳልሆነ፣ ይህም ለወረት የቆየ ሒደት የባንኩን እንቅስቃሴን የተጫነው በመሆኑ አዲስ የተመረጠው ቦርድ ሥራ ሲጀምር እነዚህ ዕገዳዎች ይነሳሉ ተብሎም እየተጠበቀ ነው፡፡

የ2015 የሒሳብ ዓመት ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው፣ አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 77 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ አጠቃላይ የብድር ክምችቱ 53.3 ቢሊዮን ሲሆን፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት ብቻ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ አዲስ ብድር መፈቀዱም ተጠቅሷል፡፡  

በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት 1.77 ቢሊዮን ብር፣ ከታክስ በኋላ ደግሞ 1.5 ቢሊዮን ብር ማትረፍ እንደቻለም አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ባንኩ አጋጠመው ከተባለው የአሠራር ችግርና ተግዳሮት ጋር በተያያዘ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ ለባለአክሲዮኖች ይከፋፈላል ተብሎ ታቅዶ የነበረው የትርፍ ድርሻ ክፍፍል ታግዶ እንዲቆይ ውሳኔ መስጠቱ ታውቋል፡፡ ይህ ውሳኔ ብሔራዊ ባንክ በባንኩ ላይ እያደረገ ያለው ምርመራ እስኪጠናቀቅ ድረስ ተፈጻሚ የሚሆን ነው፡፡

ሪፖርተር ካሰባሰባቸው የተለያዩ መረጃዎች፣ ብሔራዊ ባንክ የወሰደው ውሳኔ ባንኩን ለመታደግ ያስቻለ ሲሆን፣ አዲሱ ቦርድም የተፈጠሩትን ክፍተቶች ከመድፈን ባለፈ ከሠራተኞችና ከደንበኞች ጋር እንደ አዲስ በመምከር ጭምር ሊሠራ እንደሚገባ ነው፡፡ ባንኩ ጠንከራ መሠረት ያለው በመሆኑ፣ መሃል ላይ ተፈጠረ የተባለውን ክፍተት ለመድፈንም የአዲሱ ቦርድ ይወስዳቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ዕርምጃዎች መካከል የባንኩን ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት በአዲስ መተካት እንደሚሆን ምንጮችን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ታኅሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ሥራ ላይ የነበረውን ቦርድና ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት ባንኩን በመምራትና ለውጥ ያመጣሉ ብሎ እንደማያምን በግልጽ ማስታወቁ፣ በባንኩ ውስጥ በርካታ ለውጥ ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይታመናል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች