Sunday, February 25, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ባንኮቻችን ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ያስፈልጋቸዋል!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሚመሰገንባቸው ተግባራት መካከል አንደኛው፣ በውስጣዊ ትርምስ ለመፍረስ ይንገዳገዱ የነበሩ ባንኮችን በጠንካራ ቁጥጥር መታደግ መቻሉ ነው:: ከዚህ ቀደም በተለያዩ ነባር የግል ባንኮች ውስጥ የተፈጠሩ አለመግባባቶች ከቁጥጥር ውጪ ከመውጣታቸው በፊት፣ በአፋጣኝ በመድረስ ብሔራዊ ባንክ የተጫወተው አዎንታዊ ሚና ዛሬ ለደረሱበት ትልቅ ቁመና አስተዋፅኦ እንደነበረው አይዘነጋም:: የፋይናንስ ዘርፉ የአገሪቱ ኢኮኖሚ አከርካሪ አጥንት ስለሆነ የሚያንዣብበትን አደጋ ማስወገድ የሚቻለው፣ ከብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር በተጨማሪ በባለአክሲዮኖችና በደንበኞች ትብብር ነው:: የብሔራዊ ባንክ ሚና ግን ከሁሉም የላቀ ነው:: ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን በንብ ባንክ የቀድሞ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ላይ የወሰደው ዕርምጃም ባንኩን ከመታደግ ባሻገር፣ የአገሪቱ የፋይናስ ዘርፍ ጤናማ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ የሚያግዝ በመሆኑ ድጋፍ ሊቸረው ይገባል:: ባንኮቻችን በአገልግሎት አሰጣጣቸው፣ በአደረጃጀታቸው፣ በዘመናዊነትም ሆነ በካፒታል አቅማቸው ብዙ ይቀራቸዋል:: ከሕዝብ በአደራ የተቀበሉትን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብና የውጭ ምንዛሪ ስለሚያስተዳድሩ፣ በጠንካራ የቁጥጥር ማዕቀፍ መመራት አለባቸው::

ባንኮች ጥብቅ በሆነ ዲሲፕሊን መመራታቸው አስፈላጊ የሚሆነው፣ የውጭ የፋይናንስ ተቋማት አገር ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ ሲፈቀድላቸው ሊገጥማቸው በሚችለው ፉክክር ምክንያት ነው:: ከውጭ የሚመጡት በፋይናንስ፣ በአደረጃጀት፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በተለያዩ አገልግሎቶቻቸው፣ ደንበኞችን ለማማለል ይዘዋቸው በሚመጡ አማራጭ ዕድሎችና በመሳሰሉት የሰላ ፉክክር ይጠብቃቸዋል:: በተለይ የአገር ውስጥ ባንኮች በአመራር፣ በሙያዊ ብቃትና በአዳዲስ አሠራሮች ራሳቸውን ማብቃት ካልቻሉ ከውድድሩ ተገፍትረው ይወጣሉ:: ባንኮቹ በተመቻቸላቸው ዕድል ተጠቅመው የአገር ኢኮኖሚን፣ ባለአክሲዮኖችንና ደንበኞችን ማርካት የሚችል አሠራር ሊኖራቸው ይገባል:: በከፍተኛ ድካም የሚገኝን የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ ካላስተዳደሩ፣ በዝቅተኛ ወለድ ተቀማጭ ገንዘብ በመሰብሰብ በከፍተኛ ወለድ እያበደሩ ትርፍ የሚያገኙበትን የተመቻቸ ዕድል ካልተጠቀሙበት ችግር ይከተላል:: የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱ ሲስፋፋ ተፈላጊነታቸው ይቀንሳል:: በውስጣቸው በከፍተኛ ቅራኔ የተሞላ ፍትጊያ ምክንያት ሕገወጥ ድርጊቶች እየተበራከቱ ነው:: ከእነዚህም መካከል በቡድን ተደራጅቶ ባንኮችን በማገት የጥቂቶች መጫወቻ ለማድረግ ያለመ እንቅስቃሴ በብዛት ይስተዋላል:: ብዙኃኑ ተገፍተው የጥቂቶች መበልፀጊያ መሆናቸው ሊቆም ይገባል::

የፋይናንስ ተቋማት ጤንነት ሳይኖራቸው ሲቀር ኢኮኖሚው ይታወካል:: ብዙዎቹ ባንኮች ጤናማነት የጎደለው አሠራር እየተከተሉ ለመሆናቸው ማሳያ ከሚሆኑት መካከል የሚጠቀሱት እጅግ በጣም ጥቂት ለሚባሉ ባለሀብቶች አበዳሪ በመሆናቸው፣ እነዚህ ጥቂት ተበዳሪዎች ገበያውን በብቸኝነት በመቆጣጠር ዋጋ ወሳኝ መሆን በመቻላቸው፣ በውጭ ምንዛሪ አሰጣጥ አድሎአዊነት በመብዛቱ፣ የብሔርና የእምነት ትስስር ለብድርና ለውጭ ምንዛሪ መልቀቅ ብቻ ሳይሆን ለቅጥርና ለዕድገት መሥፈርት በመደረጉ፣ አዳዲስ ባንኮች ሲመሠረቱም በዚህ መሠረት እንዲደራጁ አስገዳጅ ሁኔታ መፈጠሩና የመሳሰሉት በአገር ኢኮኖሚ ላይ አደጋ እንዲደቀን ማድረጋቸው ነው:: እንዲህ ዓይነቱ አደረጃጀትና አሠራር በርካታ ሚሊዮን ቆጣቢዎችንና የውጭ ምንዛሪ የሚያፈሩ ምርቶችን የሚያመርቱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አግልሏል:: ጥቂቶች ተደራጅተው ባንኮችን የፍላጎታቸው ማርኪያ ማዕድ እያደረጉ ብዙኃኑ ሲገለሉ፣ ምን ዓይነት ውጤት ይገኛል ተብሎ መጠየቅና መሞገት ያስፈልጋል:: የባንኮች የቦርድ አባላትም ሆኑ የማኔጅመንት ሰዎች ለተሰጣቸው ሕዝባዊ ኃላፊነት ተጠያቂነት ሊኖርባቸው ይገባል::

ባንኮች በጤናማ መንገድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ብሔራዊ ባንክ ጥርጊያውን የበለጠ ማመቻቸት ሲኖርበት፣ የባንክ አመራሮችም የሚፈለግባቸውን ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል:: ለዚህም ከብልሹ አሠራሮች በመራቅ በከፍተኛ ዲሲፕሊን ለማገልገል የገቡትን ቃል መፈጸም አለባቸው:: ትርፍ ማግኘት ተቀዳሚ ዓላማቸው መሆኑ አነጋጋሪ አይደለም፣ ተገቢም አይሆንም:: ትርፍ ለማግኘት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ግን ሕግ መከበር አለበት:: ለሕገወጥ ድርጊቶች የሚያነሳሱ ፍላጎቶች መገታት ይኖርባቸዋል:: ባለአክሲዮኖችም የትርፍ ድርሻ ከመከፋፈል ባሻገር የባንኮቻቸውን ውሎና አዳር ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው:: ባንኮቹ ውስጥ ቡድንተኝነት ሲንሰራፋና የዘረፋ ርብርብ ሲደረግ በሕግ ማለት ይኖርባቸዋል:: የባንክ አመራሮችም ሆኑ ባለሙያዎች ሙያዊ ሥነ ምግባር ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል:: ጥቂቶች ተቧድነው ባንኮቹን ሲቆጣጠሩ እንዳላዩ ሆኖ ማለፍ አድርባይነት ብቻ ሳይሆን፣ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ጭምር ደንታ ቢስነትን ነው የሚያሳየው:: በጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ ባንኮች በትክክል ሥራቸውን እያከናወኑ መሆናቸው መታወቅ አለበት::

ሌላው ባንኮች የሚወቀሱበት ጉዳይ የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ነው:: ባንኮች በየዓመቱ ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በተመለከተ በአኃዝ አስደግፈው የሚገልጹት ነገር አለ:: የባንኮች ማኅበራዊ ኃላፊነት በጠባብ የዕርዳታ መስኮት ውስጥ የሚገለጽ መሆን የለበትም:: ባንኮች ትርፍ አግኝተው ለባለአክሲዮኖች የትርፍ ድርሻ ከማካፈል፣ ለመንግሥት የሚፈለግባቸውን ግብር ከመክፈልና ከመሳሰሉት ወጪዎች በተጨማሪ ለሕዝብ ኑሮ ዕድገት አጋዥ መሆን አለባቸው:: ለመሆኑ ምን ያህሉ ናቸው ለአስቀማጭ ደንበኞቻቸው ብድር የሚያመቻቹት? ምን ያህሉስ ናቸው ከንብረት መያዣ ውጪ አዋጭ ሐሳብ ለያዙ የፈጠራ ሰዎች ብድር የሚሰጡት? ምን ያህሉ ናቸው ሕዝብን ከድህነት ሊያላቅቁ ለሚችሉ ፕሮጀክቶች ድጋፍ የሚያደርጉት? ምን ያህሉ ናቸው በዝቅተኛ ወለድ ለቤት ፈላጊዎች ብድር የሚያመቻቹት? ምን ያህሉ ናቸው ተጨማሪ እሴት ሊፈጥሩ የሚችሉ ሥራ ፈጣሪዎችን በማገዝ አብረው ለመሥራት የሚፈልጉት ቢባል ተከድኖ ይብሰል ማለት ይቀላል:: እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባው ማኅበራዊ ኃላፊነት ከትርፍ ላይ ቆንጥሮ መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ አብሮ ሠርቶ የጥቅም ተጋሪ መሆን ጭምር መሆኑን ነው::

ቅጥ ያጣ ትርፍን ታሳቢ በማድረግና ጥቂቶችን ለማጥገብ በሚል ዕሳቤ ብቻ ባንኮችን ለመምራት መሞከር ተያይዞ መውደቅ ነው የሚያስከትለው :: ባንኮች የሚያስተዳድሩት ተቀማጭ ገንዘብም ሆነ የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ ድካም የሚገኝ ነው:: ይህንን ትልቅ የተደከመበት ሀብት ጥቂቶች እንዲፈነጩበት ለማድረግ ሲባል ብቻ ተደራጅቶ ማወክ ወንጀል ነው:: የብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር የሚያስፈልገው እንዲህ ዓይነቱን አጉራ ዘለልነት አደብ ለማስገዛት ነው:: ከዚያ ውጪ ባንኮቹ ለነገው አንገት ለአንገት ለሚያስተናንቀው ብርቱ ፉክክር ዝግጁ እንዲሆኑ፣ መሰናክሎችን በማስወገድ ሙያዊ ነፃነት መስጠት ተገቢ ነው:: ይህ ነፃነት ግን በኃላፊነት የሚጠቀሙበት እንጂ የሚቆምሩበት እንዳይሆን በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ተዋንያን ልብ ማለት አለባቸው:: መንግሥት የፖሊሲ ማሻሻያዎችን አድርጎላቸው በነፃነትና በልበ ሙሉነት ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን በተግባር ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል:: ያለ ባንክ ስለዕድገትም ሆነ ስለልማት ማሰብ እንደማይቻለው ሁሉ፣ በሥርዓት ስለሚመሩ ባንኮች ማቀድና ችግር ሲኖርም የእርምት ዕርምጃ መውሰድ አገራዊ ግዴታ መሆኑን መረዳት ይገባል :: ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...