Thursday, February 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ዳይኖሰርስ ከእነ ነፍሱ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ብትል ሰላም ከሌለ ማንም ሊጎበኝ አይመጣም›› አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በ2002 ዓ.ም. በሐዋሳ የመጀመሪያ ሆቴሉን ገነባ፡፡ አሁን 14 ዓመታት የደፈነው የአትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የሆቴል ድርጅት ከሰሞኑ ዘጠነኛ መዳረሻውን በወላይታ ሶዶ ከተማ አስመርቋል፡፡ በ1.1 ቢሊዮን ብር ከተገነባው ባለ107 መኝታ ክፍሉ የወላይታ ሶዶ ሆቴል በተጨማሪ፣ በመጪው አንድ ዓመት በኮንሶ፣ ደብረ ብርሃን፣ ጅማና ወልቂጤ አዳዲስ ሆቴሎች እንደሚያስመርቅ ይፋ አድርጓል፡፡ ወደ 1,800 ሠራተኞችን የቀጠረው የኃይሌ የሆቴል ድርጅት በሻሸመኔ በግጭት የወደመውን ሆቴሉን በድጋሚ እያስገነባ ሲሆን፣ ለውድመቱ መንግሥት አንዳችም ካሳ እንዳላደረገለት አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ ከዚህ በተጨማሪም ወደ ውጭ ወጣ በማለት በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የመሥራት ዕቅድ እንዳለው አስታውቋል፡፡ የወላይታ ሶዶ ሆቴሉን ለማስመረቅ በተገኘበት ወቅት የድርጅቱ ባለቤት አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ዙሪያ ከዮናስ አማረ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

‹‹ዳይኖሰርስ ከእነ ነፍሱ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ብትል ሰላም ከሌለ ማንም ሊጎበኝ አይመጣም›› አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሪፖርተር፡- ይህንን የሆቴል ግንባታ ለመሥራት የገጠማችሁ እንቅፋት ምን ነበር?

አትሌት ኃይሌ፡- የኮንስትራክሽን ግብዓት አቅርቦት ከባድ ፈተና ነበር፡፡ ሁሉንም ነገር ከአዲስ አበባ ማጓጓዝ ይጠበቅብን ነበር፡፡ ቡልኬት ጭምር ከአዲስ አበባ ያመጣንበት አጋጣሚ ነበር፡፡ የውኃ ችግር ሁሉ ገጥሞናል፡፡ ውኃ ለማጓጓዝ ቦቴ በብዛት እንጠቀም ነበር፡፡ መብራት መቆራረጡም እንዳለ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ለግንባታው መሠረታዊ የሆኑ ችግሮች ነበሩ፡፡ እነዚህን ሁሉ እንዴት ተወጣችሁ ያልከኝ እንደሆነ በየቢሮው ያሉ የክልሉ አመራሮች ቅንነት ነው፡፡ ነገሮች ቢጓተቱ እንኳን እንቢ የሚል ነገር እነሱ ጋር የለም፡፡ በተቻለ መጠን ግድ የለም አይዟችሁ እያሉ ረድተውናል፡፡ ስለዚህ ግንባታው እክል እንኳ ቢገጥመው ለዚህ ሕዝብማ እሞታለሁ ብለህ ትጽናናለህ፡፡ ለምሳሌ ትንሽ ተጨማሪ መሬት ለማግኘት የነበረው ሒደት በጣም ፈታኝ ነበር፡፡ ሒደቱ ቢጓተትም ተስፋ እንዳትቆርጥ ግን ያደርጉሃል፡፡ ግድ የለም እንከውናለን ስለምንባል የነበሩ ችግሮችን ተቋቁመን ለዚህ በቅተናል፡፡ በአጠቃላይ የነበረው የሥራ ሒደት መጥፎ አልነበረም፡፡

ሪፖርተር፡- የሆቴል ዘርፍ ከቀረጥ ነፃ መብት የመጠቀምን ጨምሮ ብዙ ማበረታቻዎች ሲደረጉለት የቆየ ዘርፍ ነው፡፡ እናንተ በዚህ ግንባታ በአጠቃላይ በዚህ ዘርፍ ስትሠሩ ድጋፍና ማበረታቻ ይደረግላችሁ ነበር? የዘርፉ አሠሪነትና ምቹነት ምን ይመስላል?

አትሌት ኃይሌ፡- ከቀረጥ ነፃ መብት ነበር፡፡ ሆኖም ከቀረጥ ነፃ መብት ብቻውን ግን በቂ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሚያስፈልግህ ዶላር የለም፡፡ የሆቴል ዕቃዎችን እዚህ አገር ውስጥ ለመግዛት ደግሞ ዋጋቸው በሺሕ ፐርሰንት የጨመረ ይሆንብሃል፡፡ የዛሬ አራትና አምስት ዓመታት በ450 ብር የምንገዛው ዕቃ፣ ዛሬ በ3,400 ብር ሲሉኝ ስንት ዕጥፍ ነው የጨመረው፣ ፐርሰንቱ ስንት ነው ማለት ጀመርኩኝ፡፡ ይህንን መሰሉ ሁኔታ በጣም ፈተና ነበረ፡፡ ሆቴል ደግሞ ከሌሎቹ የተለየ ባህሪ አለው፡፡ የምታሟላቸው ቁሳቁሶች በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ከእነ ማንኪያ፣ ሹካ፣ ሰሐን ጀምረህ ድስት እያልክ ከማብሰያ እስከ መኝታ ዕቃዎች ብዙ ቁሳቁስ ትገዛለህ፡፡ ለሌሎችም ለአንተም እንዲጠቅምህ የተወሰኑትን ነገሮች እዘረዝራለሁ፡፡ ለምሳሌ ከጃንዋሪ አንድ ጀምረህ እስከ 29 ባለው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ አንድ መቶ ሚሊዮን ብር ነው ያወጣነው፡፡ ምን ገዝተህ ነው ብለህ ብትጠይቀኝ ሲኒው፣ ሹካው፣ ማንኪያው፣ ሲስተሙ፣ የውኃ ማሞቂያ፣ ላውንደሪው፣ የኪችኑ ዕቃ፣ ፎጣዎች፣ አንሶላዎች የመሳሉት በአጠቃላይ ውድ ሀብት ይፈስበታል፡፡ የዕቃ ግዥ ቅጽ የሚቀርበው ራሱ ዳጎስ ባለ ወረቀት ነው፡፡ አንድ ዓይነት ዕቃ ራሱ በብዛት ነው የሚገዛው፡፡ አንድ የአትክልት ማቅረቢያ ሳህን ለምሳሌ አንድ ሺሕ ተብሎ ሊታዘዝ ይችላል፡፡ አንድ የፍራፍሬ ማስቀመጫ ሳህን ስንት ነው ስትል ደግሞ ከ400 እስከ 500 ብር ትባላለህ፡፡ ብርጭቆ ይታዘዝ ሲባል ደግሞ ምን ዓይነት ተብሎ የሻይ፣ የውኃ፣ የወይን፣ የጁስ፣ የለስላሳ የማይጠሩብህ ነገር የለም፡፡ እነዚህ ሁሉ ጥቃቅን የሚመስሉ ነገሮች ቀላል ነገሮች አይደሉም፡፡ በሆቴል ዘርፍ መሳተፍ ከባድ እንደሆነ እኔ በደንብ እረዳለሁ፡፡ እከሌ ሆቴሉን አልጨረሰም ስትባል ብዙም አትገረም፡፡ ምክንያቱም ሆቴል መገንባቱና ቁሳቁሱን አሟልቶ ሥራ ማስጀመሩ ከባድ ሥራ ነው፡፡ እኛ ለምሳሌ የአዲሱ ሆቴላችን መዋኛን ገና አልጨረስንም፡፡ ምክንያቱም ለዋና የሚሆነውና ታች ኮንክሪት ላይ የሚቀበረው ዕቃ ኬንያ ነው የሚሠራው፡፡ ግድ የለም እሱ አያስቸኩለንም ፣ ሆቴሉን ለአገልግሎት ብናውለው የተሻለ ነው በሚል ነው ያስመረቅነው፡፡ እነዚህን መሰል ነገሮች የሆቴል ግንባታን ወደኋላ የሚጎትቱት ናቸው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአገር ቤት ምርቶች ቁሳቁሱን ለሟሟላት አልተሞከረም?

አትሌት ኃይሌ፡- ከበር ጀምሮ ብዙ ፈርኒቸሮችን በአገር ውስጥ በተመረቱ ቁሳቁሶች ነው ያሟላነው፡፡ ይሁን እንጂ የአገራችን የግንባታ ዘርፍ ብዙ ግብዓቶች ከውጭ በሚመጣው ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በተቻለ መጠን እያቻቻልን ለመሥራት ሞክረናል፡፡ ቢኖረንና ብናገኝ ሙሉ ለሙሉ የአገር ውስጥ ምርቶችን ብንጠቀም ደስ ባለን፡፡ ከውጭ የሚመጣውንም ቢሆን እኮ ገንዘቡ ኖሮህ በአግባቡ የሚያቀርብልህ ገበያው ላይ ልታጣ ትችላላህ፡፡ ለምሳሌ አንድ መብራት ዓይነቱንና ብዛቱን ዘርዝረህ ወደ ገበያ ትወጣለህ፡፡ ዑራኤል አካባቢ ሄደህ ይህንን ዓይነት መብራት 30 እፈልጋለሁ ስትል ያለን 12 ብቻ ነው የሚል መልስ ልታገኝ ትችላለህ፡፡ በተቻለ መጠን የጎደለውን እየሞላን ነው የምንሠራው፡፡ ይህ እኔ የምናገረውን ሆቴል የሚሠሩ ሰዎች እንዴት እንደሚቸገሩ ያውቁታልና ኃይሌ አፌ ቁርጥ ይበልልህ እያሉ እንደሚሰሙት አውቃለሁ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ሆቴል ግንባታ ‹‹ገበታ ለአገር›› እየተባለ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩ ፕሮጀክቶች ጭምር ሲደገፍ ይታያል፡፡ ብዙ ሪዞርቶችና ሎጆች ሲሠሩ ይታያል፡፡ ግን ደግሞ በተቃራኒው ከአገሪቱ ሰላም ዕጦት ጋር በተገናኘ የሆቴል ሥራ ንግድና ገቢ መዳከሙ በሰፊው ይነገራል፡፡ ይህንን እንዴት ነው ማስታረቅ የሚቻለው?  

አትሌት ኃይሌ፡- ይህ በጣም ከባድ ነው፡፡ እንደምትሰማው እንዲያውም በአሁኑ ሰዓት ሆቴሎች እየተዘጉ ነው፡፡ ይህ ማለት ቱሪስት ወይም ተጠቃሚ እየጠፋ ነው ማለት ነው፡፡ ተጠቃሚው በአንድ በኩል በቱሪስትነት ነው የሚመጣው ወይም ደግሞ በስብሰባ ነው የሚመጣው፡፡ የፈለገውን ያህል በወርቅ ለብጠን ሆቴል ወይም ሪዞርት ብንሠራ ሰላም ከሌለ ማንም መጥቶ አይጠቀምም፡፡ ሌላው ይቅርና ኢትዮጵያ ውስጥ ዳይኖሰርስ አለ ብትል እንኳ ሰላም ከሌለ ማንም መጥቶ መጎብኘት አይፈልግም፡፡ የዛሬ ስንት ሚሊዮን ዓመት የጠፋው እንስሳ ዳይኖሰርስ ከእነ ነፍሱ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ብትል ሰላም ከሌለ ማንም አይመጣም፡፡ አንድ ቱሪስት መጀመሪያ የሚያስቀምጠው መጀመሪያ ለመቀመጫዬ እንዳለችው እንስሳ ሕይወቱን ነው፣ ይህንን መገንዘብ አለብን፡፡ እንደ ሕዝብም፣ እንደ መንግሥትም ይህንን ካላደረግንና ሰላምን ካላረጋገጥን እንኳን ቱሪስት ለማምጣት ቀርቶ አንተም እኔም ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስም አንችልም፡፡

ከሰሞኑ ዓይተናል ሁላችንም ከአዲስ አበባ ለመውጣት እንኳ እየተሳቀቅን ነው፡፡ እኔ ለምሳሌ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው እዚህ ሶዶ በአውሮፕላን የመጣሁት፡፡ በአውሮፕላን መጥቼ አላውቅም፡፡ መኪናዬን እየነዳሁ ከሶዶ አልፌ አርባ ምንጭ ደርሼ ሥራዬን ሠርቼ እመለሳለሁ፡፡ ሰሞኑን ግን ያሠጋል፡፡ በመኪና መሄድ አትችልም አሉኝ፡፡ እንዴት የማውቀውን መንገድ ትከለክሉኛላችሁ ብልም በፍፁም አይሆንም አሉኝ፡፡ ሐዋሳ በአውሮፕላን ለመሄድ ? ኧረ ባካችሁ ግፍ ነው ነበር ያልኩት፡፡ እንዲህ ባለው አስገዳጅ ሁኔታ ግን በመኪና መሄድ የሚቻሉ ቦታዎችን በአውሮፕላን ለመሄድ ትገደዳለህ፡፡ ይህ ሁኔታ ቱሪስቱን ብቻም ሳይሆን፣ የብዙ ሺሕ ሠራተኛ ኃላፊነት ያለበት እንደ እኔ ያለውን ሰው እንቅስቃሴም ይገድባል። ይህንን ቆም ብለን ሁላችንም ልናስብበት ይገባል፡፡

መንግሥትም እንደ መንግሥት፣ ሕዝብም እንደ ሕዝብ ቆም ብለን ብናሰብበት፡፡ ካልሆነ ግን በስተመጨረሻ ሁላችንም እንከስራለን፡፡ መንግሥት አባት ነው፡፡ አባት ደግሞ ሁል ጊዜ ልጆችን አስቀምጦ መምከርና መመካከር ነው ያለበት፡፡ ሕፃን ልጅ ወደ እሳት ሲሄድ ኡፍ ነው ይባላል፡፡ ኡፍ ነው እያልን ማስተማር ነው እንጂ አልተመለሰም ብለህ እሳት ውስጥ አትጨምረውም፡፡ 

እኔ የማወራው እንደ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ እንደ ኢንቨስትመንት ሳወራ ደግሞ ታክስ ከፋይ ነኝ፡፡ መንግሥት ታክስ ከእኔ እንደሚጠብቀው ሁሉ፣ እኔም ደግሞ ከመንግሥት የምጠብቀው ነገር አለ፡፡ እሱም ሰላም ነው፡፡ እኔ ሰላምን የምጠይቀው ለእንግዶቼና ለሠራተኞቼ ነው፡፡ ግን ደግሞ የእኔስ? አሁን እኮ የእኔም የሰላም ዋስትና ችግር ሊሆን ነው ማለት ነው፡፡ ይህችን ነገር በደንብ ትኩረት ልናደርግባት ይገባል፡፡ 

እዚህ አገር ውስጥ አንዱ ትልቅ ችግር ምንድነው መሰለህ ? በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ታክስ እየከፈልክ መብትህን ስትጠይቅ በሌላ ይተረጎማል፡፡ ለምሳሌ የእኛ ድርጅቶችን እንመልከት። የኃይሌ ድርጅቶች አሉ፣ የኃይሌና የዓለም ድርጅቶች አሉ፣ የማራቶን ሞተርስ አለ፣ ያያ እና ሌሎች ድርጅቶቻቾን አሉ ፤ እንዲህ እያልን ብንደማምራቸው በእነዚህ ድርጅቶች በዓመት ውስጥ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር እንገብርባቸዋለን፡፡ ይህ የተሠራው ከምንም አይደለም፡፡ የመንግሥት ኃላፊነት ይህንን መጠበቅ ነው፡፡ ይህንን ለምን ተናገርህ ወይም ለምን እንዲህ አልክ የሚለኝ ካለ ደግሞ እኔ በጣም እቸገራለሁ፡፡ ብዙ ዓመታት ማለትም 30 ዓመት በአገሬ ውስጥ ስሠራ አሳልፌያለሁ፡፡ በውጭ ደግሞ አውሮፓንም አሜሪካንም አውቀዋለሁ፡፡ ግዴታዬን መወጣት ብቻ ሳይሆን መብቴንም እፈልጋለሁ፡፡ ግዴታዬን በአግባቡ እወጣለሁ በተመሳሳይ መልኩ መብቴም እንዲከበር እፈልጋለሁ፡፡ መብቴን ለማስከበር ደግሞ አይ አላውቅልህም የሚለኝ ካለ ይህ በጣም ከባድ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ኃይሌ የሆቴል ቢዝነሱን ከኢትዮጵያ ውጭ ለማስፋፋት አቅዷል ይባላል። ወዴት ልታሰፉት አሰባችሁ?

አትሌት ኃይሌ፡- ወደ ምሥራቅ አፍሪካ አስበናል። እንግዲህ እነ ዑጋንዳና ሩዋንዳ ላይ ጥሩ ነገሮች አሉ፡፡ ኬንያም አስበናል፡፡ ሆኖም ኬንያ ውድድሩ ጠንከር ያለ ስለሆነ በሒደት እንገባለን፡፡ ወደ እዚያ ስንገባ ግን እንደ ኃይሌ ብቻ መታሰብ የለበትም፡፡ ለዚህ የኮሪያዎችን ምሳሌ ልስጥህ፡፡ ኮሪያዎች እነ ሀዩንዳይን፣ ሳምሰንግንና ኤልጂን ዛሬ የሚገኙበት ደረጃ ያደረሱት በግል ጥረት ብቻ ሳይሆን፣ የአገራቸው መንግሥትም ድርሻ ይዞ በጋራ ኢንቨስት በማድረጋቸው ነው፡፡ የኮሪያ መንግሥትና ሕዝብ ሼር ይዞ አሳድጎ ነው ተወዳዳሪ ሲሆኑ ድርጅቶቹን ለብቻቸው የለቀቃቸው፡፡ ኢትዮጵያም በዓለም ተፎካካሪ የሆኑ ድርጅቶችን በማገዝ ማንሳት አለባት፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመንግሥት ሥር ሆኖም ከድሮ ጀምሮ ተፎካካሪ ነው፡፡ እኛም በሆቴልም ሆነ በግብርና ወይም በሌላ ዘርፍ ወደ ዓለም ተፎካካሪነት ልንወጣ ስንዘጋጅ መንግሥት ድጋፍ ማድረግ አለበት፡፡ 

ድጋፍ ማለት ገንዘብ ብቻ አይደለም፡፡ ሞራልም ድጋፍ ነው፡፡ ለምሳሌ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እየሠራ ያለው ምንድነው ? በየቦታው አምባሳደሮች አሉ፣ ኤምባሲዎችም አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ምን እየሠሩ ነው፡፡ ቢዝነስ ማስተዋወቅ ካልሠሩ የኢትዮጵያና የዑጋንዳ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማለት ብቻቅን ምን ዋጋ አለው ? የዲፕሎማሲ አንዱ ተልዕኮ ኢኮኖሚ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት መሆን አለበት፡፡ በጥቅም የተሳሰሩ አገሮች ሁል ጊዜ ጤናማ ግንኙነት ነው ያላቸው፡፡ ምክንያቱም ጥቅማቸው እንዲቀርና ግንኙነታቸው እንዲፈርስ አይፈልጉም፡፡ የእገሌ መንግሥትን እንዲህ ብናገረው ኩባንያውን ዘግቶ ይሄዳል በሚል ሥጋት አገራት በመካከለቸው መቻቻልን ወይም ማመቻቸመችን ይመርጣሉ።

ኢትዮጵያን ወክለው ወደ ተለያየ አገር የሚመደቡ ዲፕሎማቶች ቢዝነስ መር አስተሳሰብ ያላቸው ቢሆኑ እላለሁ፡፡ ምክንያቱም ለዲፕሎማሲ የሚወጣው ቀላል ወጪ አይደለም፡፡ አንድ አገር ሩዋንዳ ወይም ኬንያ ለተቀመጠ አምባሳደሩ የሚያወጣው ወጪ (ያውም በውጭ ምንዛሪ) ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ በማተኮር ሥራቸው መገምገም አለበት፡፡ ሌሎች አገሮችም ልክ እንደዚህ ሲሠሩ ነው ያየናቸው፡፡ 

ሪፖርተር፡- አንተ በተለያዩ አገራት ትዞራለህ፣ ብዙ ቦታዎች ሄደህ ትስተናገዳለህ፣ በሆቴሎች ታርፋለህ፣ በተለያዩ ዓለማት የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ምን ማለት እንደሆነ ብዙ የማየት ልምድ አለህ፡፡ ይህን ከእኛ አገር ጋር በማነፃፀር ምን መማር አለብን ትላለህ? ይህ ዘርፍ በኢትዮጵያ ምን ዓይነት ፈተናዎች ተጋርጠውበታል?

አትሌት ኃይሌ፡- ሆቴልና ቱሪዝም (ሆስፒታሊቲ) ቢዝነስ ከመሠረታዊው የእንግዳ አቀባበልና የማስተናገድ ባህላችን ነው የሚጀምረው፡፡ እኛ አገር ሕዝባችን ቤቱ ስትሄድ አፈር ልሁንልህ ብሎ ነው የሚያስተናግድህና የሚጋብዝህ፡፡ ወደ ሆቴል ስትሄድ ግን መስተንግዶ ለመስጠት ትንሽ ክብር የመጠበቅ ቁጥብነት ታያለህ፡፡ ይህ በአገልግሎቱ ዘርፍ ያለው ችግር ነው፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ ሆቴሎችን ለመክፈት ያለው የምቹነት ሁኔታና የፋይናንስ አቅርቦት ችግሮች አሉ። ገና ብዙ የሚቀረው ነው፡፡ ባንኮችም ቢሆኑ ሁል ጊዜ ምን ይዞ ይመጣል? የሚለውን ነው የሚያዩት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሆቴል ዘርፍ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወዲህ ብዙ ሆቴሎች በጣም ተመተዋል፡፡ ባለው የፖለቲካ ችግርም የተነሳ ብዙ ተጎድተዋል፡፡ ሆቴል ዘርፍ በጣም በቀላሉ ተጎጂ (ሴንሴቲቭ) ነው፡፡ ሆቴልና ቱሪዝም የተሳሰሩ ዘርፎች ናቸው። ለቱሪዝም አመቺ ሁኔታ መፍጠር ግዴታ ነው፡፡ ቱሪስቱ ደግሞ ቅድም እንዳነሳሁት ሰላም ይፈልጋል፡፡ ጭስ አልባውን ኢንዱስትሪ ለማሻሻል መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን ካሟላን ግን ውጤታማ መሆን እንችላለን፡፡ አንዳንዱ ቀለል አድርጎ ለምን ታማርራለህ ይለኛል፡፡ ሆቴል ዘርፍ ችግር ቢኖረው ኖሮ ከሆቴል ሆቴል መቼ ትከፍት ነበር ይለኛል፡፡ እኔ ግን ሌላ ዘርፍ ውስጥም ገብቼ ቢሆን ኖሮ እንደዚሁ ነበር የምሄደው፡፡ አንዳንድ ጊዜም ሰዎች እየዘጉ እንዴት አንተ ትከፍታለህ ይሉኛል፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ አንዳንድ ትልልቅ ሆቴሎች ቢዝነስ አጥተው አዲስ አበባ ውስጥ እየተዘጉ ነው፡፡ ይህ ለእኛ ትልቅ ድንጋጤ ነው፡፡ አምባሳደርን የሚያህል ትልቅ ሆቴል ተዘጋ ሲባል ሁላችንም ደነገጥን፡፡ በእርግጥ ሁላችንም ችግሩን እናውቀዋለን፡፡ ሆቴል እየተዘጋ ያለው አንተ አዋጥቶህ ሌላው ሳያዋጣው ቀርቶ አይደለም፡፡ ነገ ይመጣል ሥራው እያልን በተስፋ ነው እየሠራን ያለነው፣ ወደፊትም ተስፋ አልቆርጥም፡፡

ሪፖርተር፡- ከኃይሌ ወደፊት ምን እንጠብቅ፡፡ በሆቴል ሊሆን ይችላል በሌላ ዘርፍ ምን አዲስ ነገር ይዛችሁ ትመጣላችሁ?

አትሌት ኃይሌ፡- ሆቴሎቹ ከተማ ለከተማ የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ አንዱ ትልቁ ሀብቷ ግብርና ነው፡፡ እኔ ከድሮም ጀምሮ በግብርና ለመሰማራት ትልቅ ስሜት ነው ያለኝ፡፡ እንደምናወራው ሳይሆን ግብርና ግን የራሱ በጣም በርካታ ችግሮች አሉት፡፡ ብዙዎች ይህንን የዘርፉን ችግሮች ይሸፋፍናሉ፡፡ እኔ ግን ገብቼበት እያየሁት ነውና ልሸፋፍነው አልፈልግም፡፡ በተግባር ስትገባበት የሚገጥምህ የተለየ ነው፡፡ ሆኖም በሆቴል ዘርፍ ከተማ ለከተማ የሚሠራ ስለሆነ ያን ያህል ችግር አልገጠመንም፡፡ ነገር ግን በሁሉም ዘርፍ በዚሁ መቆም አንፈልግም ብዙ መሥራት ነው የምንፈልገው፡፡ በሆቴሉም ቢሆን ከአገር ወጣ ብለን መታየትና ልምድ መቅሰም እንፈልጋለን፡፡ እንደሚታወቀው ብዙ ሆቴል በማስፋፋት በዓለም ደረጃ ሒልተን ወይም ሸራተን ሳይሆኑ ፣ የእኛ ሰዎች ቀድመው የጀመሩት ሥራ ነበር፡፡ ቼይን ሆቴሎችን በመፍጠር (አንድ ብራንድ ሆቴልን በተለያዩ አካባቢዎች በማስፋፋት) አቶ በቀለ ሞላን የሚቀድም የለም፡፡ ሒልተንና ሸራተን ወይስ የበቀለ ሞላ ሆቴሎች የሚቀድሙት የሚለውን ታሪክ መፈተሽና ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ አንዳንድ የተደበቁ ብዙ ፈር ቀዳጅ ነገሮች አሉን፡፡ ለምሳሌ በቀደም ሰምቼ የማላውቀውን ፣ ኢትዮጵያ የዛሬ 85 ዓመት አውሮፕላን ሠርታለች የሚል መረጃ ሰምቼ በጣም ነው የገረመኝ፡፡ ይህ በእርግጥ ሊመረመር የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የሆቴል ብራንድን በየቦታው በመክፈትና በማስፋፋት የአቶ በቀለ ሞላ ሆቴሎች ከብዙ የውጭ አገሮች ሆቴሎች የቀደሙ ናቸው፡፡ ለእኔ በቀለ ሞላ እንጂ የውጭዎቹ ተምሳሌት አይሆኑኝም፡፡ የውጭዎቹ እኮ ያውም በተመቸና ያማረ ሥርዓት ባለው የቢዝነስ ከባቢ ውስጥ እየሠሩ ነው ዛሬ ለሚገኙበት ደረጃ የደረሱት፡፡ እኛጋ ግን መንገድ እንኳ በቅጡ በሌለበት ከአዲስ አበባ ጀምሮ ወደ ደቡብና ወደ ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ገብተው በሆቴል (በቀለ ሞላ ሆቴሎች) ያገናኙት አቶ በቀለ ሞላ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የዛሬ 80 እና 90 ዓመታት ታሪክን ኮፒ እያደረገ እንጂ ምንም እየሠራ አይደለም፡፡ ኃይሌ በሆቴል ማስፋፋት ታሪካዊ ነው አይባልም፡፡ ምክንያቱም አቶ በቀለ ሞላ ናቸው ከማንም ቀድመው የጀመሩት፡፡ በሩጫም ቢሆን የታሪክ መሠረት ማነው ከተባለ አበበ ቢቂላ ነው፡፡ እነ ማሞ ወልዴ፣ እነ ምሩፅ ይፍጠር እያለ እስካሁኑ ትውልድ የተሸጋገረ ነው፡፡ ነገር ግን የመጀመሪያዎቹ ሁሌም ቢሆን ፋና ወጊዎች ናቸው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች