Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአፍሪካ ፕሮግራሞች ላይ ትኩረት ሰጥተው በሚሠሩ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና የግል ተቋም በሆነው የግብርና እርሻ ልማት ሥራ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ሰፊ ልምድ እንዳካበቱ ያስረዳሉ፡፡ በመስከረም 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊነትን ከመረከባቸው በፊት፣ በምክር ቤቱ ውስጥ ለ13 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ ነበረኝ ይላሉ። ስለንግድ ምክር ቤቱ  በብቃት ደረጃና ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር እየተጋረጡ ስላሉት ማነቆዎች ይናገራሉ። በተጨማሪም የምክር ቤቱን የአሠራር ግልጽነት፣ ለንግድ ድርጅቶች የሚሰጠው ድጋፍ እየቀነሰ ስለመጣበት ምክንያት፣ በቅርቡ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ስለሚኖሩ ጥርጣሬዎችና ሌሎች በርካታ አንገብጋቢ ጉዳዮችን በሚመለከት ከአብርሃም ተክሌ ጋር ጸሐፊው ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል።

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በሕግ የተሰጡትን ኃላፊነቶች፣ ግዴታዎችና የተቋቋመባቸውን መሠረታዊ ዓላማዎች በግልፅ ይታወቃሉ። ምክር ቤቱ በሕግ የተሰጡትን ኃላፊነቶች ተጠቅሞ በሙሉ አቅሙ እየሠራ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ሺበሺ፡- በመጀመሪያ ንግድ ምክር ቤቱ በሕግ የተሰጡትን ኃላፊነቶች በአጭሩ ላስቀምጥና ለጥያቄህ መልስ ልስጥ፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት እንደ አንድ የንግዱ ማኅበረሰብ ወኪል በ1939 ዓ.ም የተመሠረተ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ካሉ ተመሳሳይ ተቋማት ጋር የጋራ የሆኑ ዓላማዎችን ያሉት ነው፡፡ የንግድ ምክር ቤታችን ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ውስጥ የንግድና የኢንቨስትመንት ዕድገትን ማጎልበት ሲሆን፣ ዘርፎችን ከማስፋፋት በተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ለአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ አጠቃላይ አገራዊ ልማትን ማረጋገጥ ላይ ያለመ ነው። የንግድ ምክር ቤቱ ሁለተኛው ቁልፍ ኃላፊነት የንግዱን ማኅበረሰብ ማደራጀትና አንድ ማድረግ ነው። የተደራጀነረ የንግዱን ማኅበረሰብ አቅም በብቃት መጠቀምና ከመንግሥት ጋር ትርጉም ያለው ውይይት ማድረግ ይችላል። በአንፃሩ የማኅበረሰቡ ቅልጥፍና አናሳ ሲሆን፣ ከመንግሥት ጋር እኩል የሆነ የግንኙነት መስመር ለመዘርጋት ይቸገራል። ስለዚህ ዋናው ዓላማችን ለንግዱ ማኅበረሰብ ጥብቅና መቆም፣ ዘላቂ ንግድ፣ ልማትና ጠንካራ ኢንቨስትመንት ማረጋገጥ ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ ካሉ አቻ ምክር ቤቶች ጋር ያለንን ሰፊ ኔትወርክና ታሪካዊ ግንኙነት በመጠቀም የኢትዮጵያ የንግድ አፈጻጸምን የሚያሳዩ የንግድ ኤግዚቢሽኖችን በማመቻቸት ምክር ቤታችን የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናል። የእኛ የአሠራር ሥልቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ ደንቦችንና ሥልቶችን ስለሚያከብሩና ስለሚከተሉ፣ ከዓለም አቀፉ ገበያ ጋር ስንገናኝ ትይዩ አቀራረብን እንከተላለን።

በተጨማሪም፣ ለንግድ አጋሮቻችን ሁሉን አቀፍ ሥልጠና በመስጠት ታዋቂ ነን። በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ ውጤታማ የሥልጠና ተቋሞቻችንንና ለሁሉም ተደራሽ የሆኑ የሥልጠና ፕሮግራሞችን በመጠቀም፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ3,000 በላይ የሚሆኑ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የቀረቡ ሠልጣኞችን ጨምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ በርካታ የግል ድርጅቶችን ያካተተ ሥልጠናዎችን ሰጥተናል። በተጨማሪም የንግድ ድርጅቶች ከመንግሥት፣ ከውጭ ላኪዎች ወይም ከአገር በቀል የንግድ ማኅበረሰቦች ጋር የተያያዙ ሕጋዊ ተግዳሮቶች ሲያጋጥሟቸው የሕግ ድጋፍ እንሰጣለን። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛ የግልግል ተቋም ያለን ስለሆነ የንግድ ድርጅቶችን ሕጋዊ፣ እንዲሁም ውስብስብ ጉዳዮችን በመከታተልና ፍትሐዊ ውሳኔዎችን መስጠት በመቻላችን ኩራት ይሰማናል።

ንግድ ምክር ቤት በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ኃላፊነቱን በትጋት እየተወጣ ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት ከፍተኛና ዝቅተኛ የአፈጻጸም አሳይቷል። ሆኖም የንግዱ ማኅበረሰብን የመደገፍ ተቀዳሚ ዓላማችንንና በዘርፉ የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች በንቃት እንድንፈታ አስችሎናል። ሌላው የ‹‹አድቮኬሲ›› ሥራ በቂ የሆነ ማኅረሰብ አቀፍ የውይይት መድረክ ያስፈልገዋል። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ውስን ወይም በቂ ያልሆነ ደረጃ ላይ ነው ያለው። አሁን ያሉትም መድረኮች ቢሆኑ እንኳ በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይተዋል። በመሆኑም ያቀረብናቸው ሐሳቦች በመንግሥት ውድቅ የተደረጉባቸውና ጥቃቅን ጉዳዮች በየጊዜው የተከሰቱባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ቢሆንም ከእነዚህ መሰናክሎች በተጨማሪ ተግባራችንን በትጋት እየተወጣን ነው። የእኛ አፈጻጸም እንከን የለሽ እንዳልሆነ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ችግሮች በተከሰቱ ጊዜ ለመፍታት እንተጋለን። በዚህ አጋጣሚ አገሪቱን ወክለን በተገኘንበት የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት መድረክ ላይ በመሳተፍ የአጎዋ ዕድል ወደ ነበረበት እንዲመለስ በመምከር ያደረግነው ንቁ ተሳትፎ እንደ አንድ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል።

ሪፖርተር፡- ነገር ግን ምክር ቤት ቀደም ሲል የነበረው ተፅዕኖና ውጤታማነት አንደቀነሰ የሚጠቁሙ አስተያየቶች ይሰማሉ። ብዙውን ጊዜ እነዚህ አስተያየቶች የሚሰጡት ደግሞ የምክር ቤቱን ውስጣዊ አሠራር በሚያውቁ ግለሰቦች ነው። ከዚህ አንፃር ለእነዚህ አስተያየቶች የእርስዎን ምላሽ ምንድነው? ከዚህ ባለፈም የንግድ ምክር ቤቱ በንግዱ ማኅበረሰብ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት አላደረገም የሚል አስተያየትም ይሰማል። ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው ይላሉ?

አቶ ሺበሺ፡- በዚህ ዓውደ ሐሳብ ውስጥ ትክክለኛ መመዘኛ አለመኖሩን የሚያሳይ ብዥታ ስላለ፣ ይህን በተመለከተ የተፈጠረውን ብዥታ ለማፅዳት የተነሳው ጥያቄ ተገቢ ነው። እንደሚታወቀው ተቋማችን ከዚህ በፊት የነበራትን 20 ያህል ሠራተኞች ወደ 86 በማሳደግ ከፍተኛ የሰው ኃይል ዕድገት እንዳስመዘገበ ማስገንዘብ አስፈላጊ ነው። ይህ ለውጥ ከተቋም ዕድገት አንፃር መታየት አለበት። ሌላው ነገር ምክር ቤቱ ቀደም ሲል ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸው ድምፆች ነበሩት፣ እዚህ ጋር ግን እኔ አሁን መሪ እንደ መሆኔ ተገቢው የትምህርት ደረጃ እንዳለኝና የምክር ቤቱ የቦርድ አባላትም እንዲሁ በቂ ችሎታ እንዳላቸው ልብ ሊባል ይገባል። ይሁን እንጂ ሁኔታዎች ተለውጠዋል። የቀደሙት መሪዎች የአገሪቱን ርዕዮተ ዓለም ከሶሻሊዝም ወደ ካፒታሊዝም ሲያሸጋግሩ ያንን ለውጥ መንግሥትም ሆነ የግሉ ዘርፍ በደንብ ደግፏል። ይህ ለግሉ ዘርፍ የተሰጠውን የዕውቅና ደረጃ ያሳያል።

ከዚህ ቀደም የነበሩት ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮች አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የመንግሥትና የግል ተቋማት የምክክር መድረክን ሲመሩ የነበረ ቢሆንም፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አልተደረገም። ሆኖም እኔ አሁን አፅንኦት ሰጥቼ የምናገረው ነጥብ ምክር ቤቱ የአስተዳደርና የመምራት አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ ማጠናከሩን ነው። በየጊዜው የምንሰበስበው የአባልነት ክፍያ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት አባሎቻችንን መደገፍ አልቻልንም ሲሉ የሚከሱንን ቅሬታዎች መስማት አስደናቂ ነው። እንዲያውም ከሹመቴ በፊት ምክር ቤቱ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ የአባልነት ክፍያ ሰብስቦ አያውቅም፣ ባለፈው ዓመት ግን ከአባሎቻችን ብቻ 34 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ችለናል። ስለዚህ የተቋሙ አፈጻጸም ሲገመገም በአፈጸጸሙ ወድቋል ወይም አልወደቀም የሚለውን ማጤን በጣም አስፈላጊ ነው። አንድ ተቋም የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ጠንካራ ተቋማዊ መዋቅር ወሳኝ ነው። ይህ እንደ የቦርድ ስብሰባዎች ቅልጥፍና፣ በሰዓቱ ሥራዎቹን ማካሄዱንና የመሳሰሉትን ሁኔታዎች መገምገምን ያካትታል።

ሌላው ነገር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ችግሮች ቢያጋጥሙንም፣ ባለፈው ዓመት ጉባዔያችንን በተሳካ ሁኔታ ማካሄድ መቻላችን ኃላፊነታችንን ለመወጣት ቁርጠኝነታችንን ማሳየታችን አይዘነጋም። በሌላ በኩል ለግል የንግዱ ማኅበረሰብ በብቃት ለመሟገት ችግሮች እንዳጋጠሙን እንገነዘባለን። ይህ በዋነኛነት ከመንግሥት ጋር ባለን የተሳትፎ መንገዶች ውስንነት በመሆኑ፣ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ያለን አቅም አነስተኛ መሆኑ እንቅፋት ስለሆነ ጭምርም ነው። በተጨማሪም ጥረታችን እንደ ቀድሞው ጎልቶ ሊወጣ አልቻለም የሚባለው ምክንያቱም ከሌላው ወገን የቅቡልነት እጥረት ስላለም ጭምር እንደሆነ መታወቅ አለበት።

ሪፖርተር፡- እርስዎ የጠቀስኳቸው ፈተናዎች ቢኖሩምምክር ቤቱ ለውን ሙሉ አቅም ተጠቅሞ ኃላፊነቶቹን እየተወጣ ነው እያሉ ነው?

አቶ ሺበሺ፡- ከማንኛውም ጊዜ በላይ እየተመጣ ነው። ለምሳሌ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ፕሮግራም የሚመራበት ለአምስት ዓመታት የሚቆይ አጠቃላይ የፖሊሲ ዕቅድ ያዘጋጀንበት ጊዜ ነበር። ይህ የተከናወነው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከመተግበሩ በፊት ነበር። ሌላው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ሰላማዊና ፖለቲካዊ ይዘት የሌላቸውን መንገዶችን በመጠቀም ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግቧል። ሆኖም የተቻለንን ጥረት ብናደርግም፣ እስካሁን ያገኘናቸው ስኬቶች በቂ እንዳልሆኑ እንገነዘባለን። ለዚህ በቂ አለመሆን ዋነኛው ምክንያት በየቀኑ የሚገጥሙን ተግዳሮቶች እየጨመሩ በመምጣታቸው ነው። በዋና ከተማው በግልጽ እንደሚታየው በተለያዩ ዘርፎች ያሉ የግልም ሆኑ መንግሥታዊ የንግድ ተቋማት ከቁጥጥርና ከአካባቢያዊ የንግድ ሥራ ጋር የተያያዙ ብዙ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። እነዚህ ተግዳሮቶች ከታክስ ሥርዓቱ ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ የፋይናንስ ችግሮችና በየጊዜው አዳዲስ ፖሊሲዎች መምጣት ጋር የተያያዙ ናቸው። ስለሆነም መንግሥት እነዚህን ተግዳሮቶች በብቃት የሚፈቱ ጠንካራ ፖሊሲዎችን መተግበር የግድ ይለዋል።

ሆኖም እኛ እንደ ንግድ ምክር ቤት እነዚህ አስፈላጊ ለውጦች እንዲመጡ በመደገፍ በትጋት እየሠራን ቢሆንም፣ ጥረታችን ግን በቂ አለመሆኑን እንገነዘባለን።  የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የግሉ ዘርፍ ጥቅም ለማስጠበቅ የተቋቋመ ምክር ቤት እንደመሆኑ መጠን የዘርፉን አሠራር ለማሳደግ የሚያስፈልጉ ፖሊሲዎችን እስካሁን ከመንግሥት አላገኘንም። ስለዚህ በዚህ ረገድ የበለጠ ቁርጠኝነትና ትግል ማድረግ አለብን።

ሪፖርተር፡- የግል ኢንዱስትሪዎችና የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የሚያነሷቸውን ችግሮች በተመለከተ ድርጅታዊ ግልጽነት እንዴት እየተፈታ ነው? እነዚህ ድርጅቶች ከምክር ቤቱ በቂ ድጋፍ አላገኘንም ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ችግሮቹ ምንድን ናቸው ይለሉ?

አቶ ሺበሺ፡- በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ያሉ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች እናውቀዋለን፣ ቅሬታቸውንም እንገነዘባቸዋለን። እኛ የንግዱ ማኅበረሰብ ተሟጋቾች እንደ መሆናችን መጠን ሥጋታቸውንም እንጋራለን። በሥራ ላይ ያሉት ፖሊሲዎች የንግዱ ማኅበረሰብ እያጋጠሙት ያሉትን በርካታ ችግሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት የባለድርሻ አካላትን ፍላጎት ለሟሟላትና ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ እንዲያስችል የፖሊሲዎቹን ውጤታማነትም እንጠይቃለን፣ እንመረምራለንም። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ችግሮች በንግድ ምክር ቤታችን አቅም ማነስ ጋር ብቻ ሊወሰዱ እንደማይችሉ ልብ ሊባል ይገባል። በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ፣ እነዚህ የንግዱ ማኅበረሰቦች ለሚገጥሟቸው ጉዳዮች ድምፅ ለመሆንና ለመደገፍ ቆርጠን ተነስተናል፡፡ ችግሮቻቸውንም በብቃት ለመፍታት እንጥራለን። ሆኖም ቅሬታዎቻቸውንም እየተቀበልን በፍጥነት መፍትሔ ለመስጠት ያልቻልንባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ለምሳሌ በቅርቡ ብሔራዊ ባንክ ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ኤልሲን በተመለከተ ያወጣው ፖሊሲ አንዱ ነው። ይህንን በተመለከተ ሥጋታችንን የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፈን፣ እንደ ዕድል ሆኖ ከሦስት እስከ አራት በፈጁ ቀናት ውስጥ እንደገና በማስተካከል ዕርምጃ ወስደዋል፡፡

በተጨማሪም በሕግ ክፍላችን የዳኝነትና የሕግ ድጋፍ የሚፈልጉ አስራ ሦስት የንግድ ድርጅቶችን ለይተናል። አስፈላጊ ከሆነም የተሻሉ መፍትሔዎችን ለማምጣትና መንግሥትንም እንኳን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል ሕጋዊ ዕርምጃንም ለመውሰድ ዝግጁ ነን። ይሁን እንጂ መፍትሔ ለማግኘት የሁለቱም ወገኖች ትብብር እንደሚያስፈልግ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ችግሮቹን በብቸኝነት መፍታት አንችልም፡፡ ከመንግሥት ጠንካራ ድጋፍና ለጥረታችን ዕውቅና መስጠትን ይጠይቃል።

ሪፖርተር፡- ከጠቅላላ ጉባዔ ጋር በተያያዘ ችግሮች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤን በተመለከተ እያጋጠሙት ስላሉት መሠረታዊ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ምን ይላሉ?

አቶ ሺበሺ፡- ንግድ ምክር ቤቱ የመጨረሻውን ጠቅላላ ጉባዔ አድርጎ ያደረገው በ2011 ዓ.ም. ነበር፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ተግዳሮቶች ተከታታይ ጉባዔዎች እንዳይደረጉ አግደዋል፡፡ ለምሳሌ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትና የትግራይ ጦርነቶች ዋነኞቹ ነበሩ። እነዚህ ተግዳሮቶች ጠቅላላ ጉባዔውን ላለማካሄድ ትክክለኛ ምክንያትም ይሁኑ ወይም ሰበብ ግልጽ የሆነ ነገር የለም። ሆኖም በመስከረም 2015 የዋና ጸሐፊነት ቦታን ከያዝኩ በኋላ 15ኛውን ጠቅላላ ጉባዔ በተሳካ ሁኔታ አዘጋጅተናል። በዚህ ጉባዔ እንደ አገር ያጋጠሙንን ሁነቶችና ክስተቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት የቀደሙትን የሦስት አመታት አጠቃላይ ሪፖርቶችና የኦዲት ሪፖርቶችን ገምግመናል። እዚህ ጋር ጠቅላላ ጉባኤው የንግድ ምክር ቤቱ ልብ እና እስትንፋስ ሲሆን ለድርጅቱ እንደ አንድ የበላይ አካልም ሆኖ ያገለግላል። ያለ ጠቅላላ ጉባኤው ንግድ ምክር ቤቱ ማንነት የሌለው ብቻ ሳይሆን ራሱን ማቆየት አይችልም። አንዳንዶች የንግዱ ማህበረሠብ ተቋማት የተቋቋሙበት ሕግ ሥልጣን እንደሚሰጣቸው ይከራከራሉ ነገር ግን ጠቅላላ ጉባዔውን ሳያካሂዱ ሥራቸውን ለመወጣት የሚያስችል ሕጋዊ ምክንያትም ሆነ ድጋፍ የላቸውም፡፡

ስለዚህ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት በ2015 ዓ.ም. ጉባዔውን አካሂደን አዲስ የቦርድ አባላት አስመረጥን። ይህንን ተመሳሳይ ሒደት ከሁለት ወራት በፊት በዚህ ዓመት ደግመናል። የጠቅላላ ጉባዔው ዋና ዓላማ አባላት ተሰብስበው በምክር ቤታቸው ጉዳይ የሚወያዩበት ነው። ስለዚህ በጉባዔው ወቅት ጠቃሚ አስተያየቶችን ተቀብለናል፡፡ በተጨማሪ አነስተኛ የቢዝነስ ተቋማትን ለመደገፍ፣ ከግብር አከፋፈል ጉዳዮች ጋር ያሉባቸውን ድክመቶች ጨምሮ ማሻሻያ የሚሹ ጉዳዮችን ለይተናል። በተጨማሪም ጉባዔው የንግዱ ማኅበረሰብ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች፣ በተለይም ከፀጥታ ጉዳዮችና ከፖሊሲ እክሎች ጋር በተያያዘ የተዘጉ የንግድ ሥራዎችንም ጉዳይ ተመልክቷል። እነዚህ ተግዳሮቶች ያሉብንን የአቅም እክሎችና የተጨማሪ ጥረቶች አስፈላጊነትን አጉልተው አሳይተዋል። በምላሹም በራሱ የቦርድ አባላት የሚመራ የቅስቀሳ ዘመቻ ጀምሯል። ይህ ዘመቻ የእነዚህን ችግሮች መንስዔዎች በመለየት በየአሥራ አምስት ቀናት ዓውደ ጥናት በማዘጋጀት የንግዱን ማኅበረሰብ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚረዱ ጥናቶችን ማድረግ ይጀምራል።

ሪፖርተር፡- ከአንድ ወር በፊት ጠቅላላ ጉባዔያችሁን ብታደርጉም ጉባዔው የተካሄደው በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ትዕዛዝ እንደነበር ይታወቃል። ይህ ለምን ሆነ? ያጋጠሟችሁ ተግዳሮቶች ምንድናቸው?

አቶ ሺመሺ፡- እዚህ ጋር ግልጽ ለመሆን በዕቅዳችን ይዘነው የነበረውን የመሰብሰቢያና የኦዲት ዕቅዶቻችንን የሚገልጽ ሰነድ ላካፍላችሁ እችላለሁ። በመጀመሪያ ጉባዔውን ለማካሄድና ኦዲት የምናጠናቅቅበት ቀን ለጥቅምት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ወስነን ነበር። ሆኖም በእኛና በከተማ መስተዳደሩ ኃላፊነት ሥር የሚገኘውን የኤግዚቢሽን ማዕከል በተመለከተ አንድ ችግር ገጠመን። የከተማ መስተዳደሩ ማዕከሉን ለማደስ በመፈለጉ፣ መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም. እንድናስረክባቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ ልኮልናል፡፡ ይህ ሁኔታ የተፈጠረው ማዕከሉን ለመጠቀምና ትርፉን በጋራ ለመጋራት ከአስተዳደሩ ጋር ሽርክና ስለፈጠርን ነው። በመቀጠልም ማዕከሉን የሚመለከቱ የፋይናንስ ጉዳዮችን ለመፍታት ኦዲተር መቅጠር ያስፈልገን ነበር። የእኛ ኦዲተር ሥራውን እንደጨረሰ የጋራ የፋይናንስ ጉዳዮችን ለመፍታት በአስተዳደሩ ከተሾመው ኦዲተር ጋር በትብብር መሥራት ያስፈልግ ነበር፡፡ በመሆኑም በኦዲት ሒደቱ መዘግየት ምክንያት ጥቅምት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ለማካሄድ የታሰበውን ጉባዔ ማድርግ አልተቻለም። በወቅቱ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ኦፊሴላዊ ደብዳቤ እጃችን ላይ ከመድረሱ በፊት፣ ጉባዔውን ለሚቀጥለው ወር ተለዋጭ ቀጠሮ በመያዝ ጉዳዩን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ አሳውቀናል። ከንግድ ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተላከው ኦፊሴላዊ ደብዳቤ ጉባዔው ታኅሳስ 11 ቀን እንዲካሄድ የሚገለጽ ቢሆንም፣ እኛ ጉባዔውን በታኅሳስ 12 እንዲካሄድ ወስነናል። ስለዚህ በጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ላይ የንግድ ሚኒስቴር ተፅዕኖ እንዳልነበረው ግልጽ ሲሆን የእኛንም ዝግጅት ያሳያል።

ሪፖርተር፡- ሌላው ጉዳይ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር በተሰጣችሁ ቦታ ላይ የዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ ለምን ሳታካሂዱ ቀራችሁ? የተሰጣችሁን መሬት በማጣታችሁ በንግድ ምክር ቤቱ አባላት ላይ ቅሬታ ፈጥሯል። በግንባታው ላለመቀጠል ምክንያታችሁ ምን ነበር? አማራጭ ቦታ አግኝተናል ብትሉም ወደ እዚያ ያደረጋችሁት ሽግግርም የለም፡፡ ለምን?

አቶ ሺበሺ፡- በጥያቄዎችህ ላይ ያነሳሃቸውን ሦስት ነጥቦችን በዝርዝር ላስቀምጥልህ። የመጀመሪያው ነጥብ ከሰባት ዓመታት በፊት የተከሰተ ሲሆን፣ አቶ ኤልያስ ገነቲ (የቀድሞ ፕሬዝዳንት) በቦታው ላይ በነበሩበት ወቅት ነው። በዚያን ጊዜ ድሪባ ኩማ የከተማው ከንቲባ ነበሩ። ምክር ቤቱ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት እንደሚያስፈልገው ተገንዝቦ በቦሌ ክፍለ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኝ 3,000 ሔክታር መሬት አስተዳደሩ ተሰጥቶታል። ነገር ግን ክፍለ ከተማው 160 ሔክታር የሚሆነውን መሬት ለራሱ አስቀርቶ ቀረውን ለንግድ ምክር ቤቱ አስረክቧል። በመቀጠልም በወቅቱ በኃላፊነት ላይ የነበሩት ግለሰቦች መሬቱን ወስደው ለንግድ ምክር ቤቱ ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻ እንዲጀምር ዕቅድ አዘጋጁ። ከዚያ በ12ኛው ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ዋና ጸሐፊው ለጠቅላላ ጉባዔው ዕቅዱን በማቅረባቸው ከሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴዎች በተጨማሪ፣ እያንዳንዱ አባል ለዋናው መሥሪያ ቤት ግንባታ የሚሆን 10,000 ብር እንዲያዋጣ ጠይቀው፣ እያንዳንዱ አባል የተጠየቀውን አዋጥቷል። ሆኖም በጠቅላላው መሰብሰብ የቻሉት ግን ሁለት ሚሊዮን ብር ብቻ ሲሆን፣ ይህም የመሬቱንና የአጥሩን ወጪ ብቻ የሚሸፍን ነው።

በተጨማሪም የንግዱ ማኅበረሰብ በገቢ ማሰባሰቢያ ጥረቶቹ ላይ በቂ ተሳትፎ ካለማድረጉ ጋር በተያያዘና ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ጋር ተዳምሮ በቂ የገንዘብ አቅም ባለመኖሩ፣ የግንባታ ፕሮጀክቱ እንዲቆም አድርጓል። ነገር ግን ለፕሮጀክቱ አለመቀጠል ዋነኛ ምክንያት የሆነው ንግድ ምክር ቤቱ ዋና መሥሪያ ቤቱን አለመገንባቱ ሳይሆን፣ የከተማ መስተዳደሩ ለንግድ ምክር ቤቱ ሰጥቶት የነበረው ቦታ የመገናኛ አካባቢ ያለውን የትራንስፖርት ማሳለጫ መንገድን ለማስገንባት በሚል አስቀድሞ የወሰደው ቦታ አካል ስለነበር ነው። ሆኖም ዋና መሥሪያ ቤቱን ለመገንባት በታቀደው ንድፍ መሠረትና ከመስተዳደሩ ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረት ምትክ ቦታ ተሰጥቶት ተቀብሏል፡፡ ምትክ ቦታውን በተመለከተ በአሁኑ ወቅት እዚያ የሚኖሩ ግለሰቦች ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩና ለአዲሱ ዋና መሥሪያ ቤታችን ግንባታ የሚውል የገንዘብ ድልድል እየጠበቅን ነው።

ሪፖርተር፡- የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በኢንዱስትሪና በንግድ ማኅበራት ሥር ለሁለት የተለያዩ አካላት እንዲከፈል የቀረበውን ሐሳብ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ቢሰጡን? በተጨማሪም ውሳኔው ምክር ቤቱን ከቀድሞው የዘርፍ መዋቅር መለየትን በተመለከተ ምን ይላሉ?

አቶ ሺበሺ፡- አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ የኢትዮጵያን ፌዴራላዊ ሥርዓትን መሠረት ያደረገ ነው። ነገር ግን በሴክተርነት ቢፈረጅም ሴክተርን መሠረት ባደረገ አካሄድ አይሠራም። ከዚህም በላይ ለኢኮኖሚ ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸውን ዘርፎች ሙሉ በሙሉ አያካትትም። በእኔ እምነት በአዋጁ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎች ቢደረጉና በአብዛኞቹ የዓለም አቀፍ አገሮች በስፋት ጥቅም ላይ የዋለውን አሠራር መሠረት በማድረግ ሴክተሮችን ማስተዳደር መቀጠል ይኖርበታል እላለው። ስለዚህ ንግድና ኢንዱስትሪን በአንድ መዋቀር ውስጥ ማጣመሩ ይበልጥ ተገቢ ይሆናል። እንደሚታወቀው የግሉ ዘርፍ በተወሰነ ደረጃ የተከፋፈለ ነው፡፡ ነገር ግን የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም፡፡ በመሆኑም በእኔ እምነት አዲስ አዋጅ መተግበር ውጤታማነቱን ያዳክመዋል እንጂ አያጠናክረውም። ስለዚህ ጠንካራና የተስተካከለ መሠረት ያለው የኢኮኖሚ ከባቢን ለመፍጠር ሁሉንም የግሉ ሴክተሮች በአንድነት በማዋሀድ ሊፈጠሩ የሚችሉትን መሰናክሎች በጋራ እንዲወጡ ማስቻል አስፈላጊ ነው። ይህ ሲተገበር በዘርፉ ያሉትን የተለያዩ ሴክተሮችን በማሰባሰብ የሚከሰቱ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያበረታታ አንድና ጠንካራ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መፍጠር እንችላለን።

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ለኢትዮጵያ የሚበጀው ኮስተር ብሎ የባህር በር ጥያቄውን መግፋት ብቻ ነው›› ብሩክ ኃይሉ (ፕሮፌሰር)፣ አንጋፋ የዲፕሎማሲና የሚዲያ ባለሙያ

ለረጅም ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተምረዋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፈረንሣይና በአሜሪካ ተመድበው በዲፕሎማትነት አገልግለዋል፡፡ ዳያስፖራው በ‹‹ኖ ሞር›› ንቅናቄ ሲያደርግ በማስተባበር ተሳትፈዋል፡፡ መንግሥትና ዳያስፖራው ለአንድ...

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...