Sunday, April 21, 2024

የአማራ ክልል ቀውስና የውይይት መፍትሔ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን መርአዊ ከተማ በፋኖ ኃይሎችና በመከላከያ መካከል ውጊያ መካሄዱን ተከትሎ፣ በንፁኃን ዜጎች ላይ ግድያ ተፈጸመ መባሉ ከፍተኛ ድንጋጤን የፈጠረ ጉዳይ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ጉዳዩን ከአካባቢው ነዋሪዎች አጣራሁት ብሎ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ከ80 በላይ ሰዎች በግጭቱ መሞታቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ ከውጊያው ጋር በተያያዘ በነበረው ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ብቻ ሳይሆን፣ ከውጊያው በኋላ ቤት ለቤት በመዘዋወር ጭምር ግድያው መፈጸሙን በመግለጫው አክሏል፡፡ 

የአማራ ክልል ቀውስና የውይይት መፍትሔ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በመሀል ሳይንት የተደረገው ስብሰባ

ኢሰመጉ ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ነዋረዎች ምስክርነት በማስደገፍ ጉዳዩን የዘገቡ ሚዲያዎች ጭምር ቁጥሩ የተለያየ አኃዝ ቢሆንም፣ ከውጊያው በኋላ የመንግሥት ኃይሎች ሰላማዊ ዜጎችን መግደላቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎችን ሲያሠራጩ ሰንብተዋል፡፡

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ዘግይቶም ቢሆን በጉዳዩ ላይ እየተነጋገረ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ዓርብ የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ ጉዳዩ አሜሪካንን እንደሚያሳስባት ተናግረዋል፡፡ አሜሪካ ዓለም አቀፍ ገለልተኛ አጣሪ ቡድን በአስቸኳይ ወደ ሥፍራው ገብቶ ጉዳዩን እንዲያጣራና አጥፊዎች ለፍትሕ እንዲቀርቡ እንደምትፈልግ፣ አምባሳደሩ በመልዕክታቸው ግልጽ አድርገዋል፡፡ በአማራም ሆነ በኦሮሚያና በሌሎች አካባቢዎች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተደጋጋሚ እንደሚሰሙ በመጠቆም፣ ይህ ችግር የሚቆመው በአስቸኳይ ወደ ውይይት መፍትሔ ሲገባ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ይህ ጉዳይ ሳይረግብ ጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የተጣለውንና እንደ አስፈላጊነቱ በመላ አገሪቱ ተፈጻሚነት ይኖረዋል ተብሎ ከስድስት ወራት በፊት የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት አራዝሞ ነበር፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘሙ በተለያዩ ወገኖች በሥጋትነት እየታየ ነው፡፡ ኢሰመጉ አዋጁ መራዘሙ በተለይ የአማራ ክልልን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ የበለጠ ፈታኝ ሊያደርገው ይችላል የሚል ሥጋቱን፣ በጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. መግለጫው አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ ሁኔታው በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ ሊፈጥር የሚችለው ተፅዕኖ እንደ ሚያሳስባቸው በይፋ ገልጸዋል፡፡ በግጭቱ ሰለባ የሚሆኑ ቁጥር፣ የሚፈጠረው የሰብዓዊ ቀውስ፣ እንዲሁም ከፍርድ ሒደት ውጪ የሚካሄደው እስራት በዚህ መሀል አሳሳቢ እንደሚሆን ነው በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው የገለጹት፡፡

ይህን የተጋራው የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮም፣ አሜሪካ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም ያሳስባታል ሲል ገልጿል፡፡ ሰብዓዊ መብት መከበር አለበት፣ ሲቪሎች ከጥቃት መጠበቅ አለባቸው፡፡ ቀውሱን ለማስቆም በፍጥነት ንግግር መጀመሩ እጅግ አስፈላጊ ነው ሲል ነበር ቢሮው መልዕክቱን ያስተላለፈው፡፡ 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም ሥጋት ቢስተጋባበትም በማግሥቱ በነበሩት የሳምንት መጨረሻ ቀናት ደግሞ መንግሥት ወደ አማራ ክልል ባለሥልጣናትን በመላክ በ15 ከተሞች ሕዝባዊ ውይይት ማካሄድ መጀመሩን አስታውቆ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘሙ የአማራ ክልል ቀውስን ከማባባስ በዘለለ ችግሩን መፍታት አያስችልም ከሚሉ ወገኖች በተጨማሪ፣ የሕዝባዊ ውይይት መርሐ ግብሩም የሚፈይደው ነገር የለም የሚሉ ስሞታዎች መስተጋባት ቀጠሉ፡፡

በአማራ ክልል ካለፈው ሐምሌ ወር የጀመረው ጦርነት ከባድ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት እያስተናገደ ስድስት ወራትን ተሻግሯል፡፡ ግጭቱ በተጀመረ በጥቂት ጊዜ ልዩነት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ በአጭር ጊዜ የክልሉን ሰላማዊ ሁኔታ መመለስ መቻሉን ተናግረው ነበር፡፡ በጊዜው መከላከያ በክልሉ ሙሉ አቅሙን ለውጊያ አለማዋሉንና ‹‹አሥር ፐርሰንት እንኳን አልተዋጋንም፤›› ሲሉ የገለጹት ፊልድ ማርሻሉ፣ ጽንፈኛና ሥልጣን በኃይል ለመጨበጥ የሚሞክር ያሉትን ኃይል በፍጥነት ማፅዳት ስለመቻሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡  

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግጭቱ ከጀመረ ገና ሁለተኛ ወሩ ሳይገባደድ ነሐሴ ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት እስከዚያን ጊዜ ድረስ፣ በግጭቱ በአማራ ክልል ከ200 በላይ ተገድለዋል የሚል መረጃ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ በጊዜው የመከላከያ ሠራዊት የድሮን ጥቃት ጭምር ስለመፈጸሙ ሪፖርቶች ይፋ ሲያደርጉ ነበር፡፡ ግጭቱ አሁን ስድስት ወራትን ያገባደደ ሲሆን፣ በዚህ ረጅም ጊዜ ሊደርስ የሚችለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት እጅግ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ነው የሚገመተው፡፡ ሌላው ቀርቶ በአንድ ቀን በመርአዊ ከተማ በተፈጸመው ጥቃት ከ50 በላይ መገደላቸው እንደሚገመት በመጠቆም፣ የደረሰው ውድመት ከፍተኛ ነው ሲሉ ብዙዎች ተናግረዋል፡፡

ይህም ሆኖ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማራዘም መንግሥት ባለሥልጣናትን በክልሉ አሠማርቶ ሕዝባዊ ውይይት አደረግኩ ማለቱ በጥርጣሬ ነው ሲታይ የሰነበተው፡፡ መንግሥት የየክልሉ ባለሥልጣናትንና የብልፅግና ሹሞችን ከአማራ ክልል አመራሮች ጋር እየቀላቀለ በተለያዩ ከተሞች ከሕዝብ ጋር መምከሩን በራሱ መገናኛ ብዙኃን ይፋ ሲያደርግ ነው የሰነበተው፡፡ በእነዚህ ተካሄዱ በተባሉ የውይይት መድረኮች ሕዝቡ ይመለሱልኝ የሚላቸውን ጥያቄዎችን በሰፊው ስለማንሳቱና መድረኩን የሚመሩት ባለሥልጣናቱም የተነሱ ጥያቄዎችን አፈታት በተመለከተ፣ እንዲሁም የመንግሥትን አቋም በተመለከተ፣ ሰፊ ማብራሪያ ስለመስጠታቸው በተለያዩ ዘገባዎች እየተመጠኑ ሲሠራጩ ሰንብቷል፡፡

ይህንን መርሐ ግብር ግን አንዳንዶች ከባድ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት እያስከተለ ላለ ቀውስ የታዘዘ የውይይት ፓራስታሞል ሲሉ፣ ሒደቱ መፍትሔ እንደማይሆን ተችተዋል፡፡ በሌላ በኩል ሒደቱ መንግሥት የአማራ ክልል ቀውስን በቅጡ ለመፍታት ዝግጁ ነው ወይ የሚል ጥያቄም ሲያስነሳ ሰንብቷል፡፡ የአማራ ክልል የሚገኝበትን ቁመናና የፖለቲካ ምስቅልቅል ያላገናዘበ፣ እንዲሁም ለችግሩ ፈውስ ሊሆን የማይችል ስለመሆኑ የሚተቹ ነበሩ፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት በተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፣ የአማራ ክልል ችግርን መንግሥታቸው ማጥናቱን አስታውቀዋል፡፡ ከከሚሴ በስተቀር በአማራ ክልል በሁሉም ዞኖች ከሕዝብ ጋር የመወያየት ዕድል እንደ ገጠማቸው የጠቀሱት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ከሕዝቡ የሚቀርበው ጥያቄ በሦስት ዋና ዋና ፈርጆች ሊቀመጥ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ አንደኛ ሕዝቡ የልማት ጥያቄ አለው፣ ሁለተኛ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጥያቄ አለው፣ በሦስተኛነትም የወሰን ጥያቄ አለው ብለዋል፡፡ ከእነዚህ ዋና ዋና ጉዳዮች በተጨማሪ እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ የሚለያይ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንዳለም ገልጸዋል፡፡

‹‹ታጥቀው ከሚታገሉ ሸማቂዎች ጋር መደራደር በኢትዮጵያ የተጀመረ ልምምድ አይደለም፡፡ እንግሊዝ ከአየርላንድ አማፂያን ጋር ስትደራደር ነበር፣ ኮሎምቢያም ከፋርክ አማፂያን ጋር ተደራድራለች፣ ከሁቲ አማፂያን ጋርም የሚደረጉ ንግግሮች አሉ፡፡ ከእንግዲህ በኢትዮጵያ በጠመንጃ አፈሙዝ ሥልጣን መያዝ አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡ 

በቅርቡ አዲሱ የአማራ ክልል አመራር ሕዝቡን ማወያየቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ ውይይትም ሕዝቡ ሁለት ወሳኝ ነጥቦችን ማንሳቱን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹አንደኛው የሰላም ጥያቄ (ሰላም እንፈልጋለን) የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛም የፌዴራል መንግሥቱ ያወያየን የሚል ጥያቄ ተነስቷል፡፡ የክልሉ መንግሥት እነዚህ ጥያቄዎች መቅረባቸውን ሲያቀርብ የሰላም ጥሪ ይደረግ ተብሎ በርካታ ሰዎች በዕድሉ በመጠቀም ወደ ሰላማዊ መንገድ ተመልሰዋል፡፡ ሁለተኛው የሁሉም ክልል አመራሮችና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አማራ ክልል ሄደው የክልሉን ሕዝብ ብሶት ያዳምጡ ተብሎ አመራሩ ተሠማርቷል፡፡ ያልገባን ወይም ያልመለስነው ነገር ካለ ውይይቱ ተገቢ ነው በሚል ሁሉም አመራር ሄዶ ሕዝብ ለማወያየት ሞክሯል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡  

በመንግሥት ሚዲያዎች በአጭሩ እየተመጠኑ በተለቀቁት የውይይት ዘገባዎች ላይ ‹‹ሰላም ይስፈንልን›› የሚል የሕዝብ አስተያየት ተደጋግሞ ሲደመጥ ታይቷል፡፡ መድረኩን ከሚመሩት አመራሮች በኩል ደግሞ ‹‹ስለተሳሳተ ትርክት›› ገለጻ የሚያደርጉ፣ እንዲሁም ‹‹ስለሕግ ማስከበር ዘመቻ ቀጣይነት›› አጠንክረው የሚጠቁሙ መረጃዎች ተደጋግመው ሲሰጡ ተሰምቷል፡፡

በሰቆጣ በተደረገ ውይይት ከመድረክ መሪዎቹ አንዱ የነበሩት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንትና የብልፅግና ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የፅንፈኞች ሥልጣን በኃይል የመያዝ ዓላማ አይሳካም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ እነዚህን ኃይሎች በሁለቱም መንገድ መታገል ያስፈልጋል ያሉት አቶ ሽመልስ፣ በሰላማዊ መንገድ በድርድር እንዲሁም በሕግ ማስከበር ዘመቻ ዕርምጃ በመውሰድ የሚሉ አማራጮችን ተናግረዋል፡፡

በጎንደር ውይይት ላይ መድረክ ከመሩት አመራሮች አንዷ የነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባና የብልፅግና ሥራ አስፈጻሚ አባል ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ‹‹ዕድሉ በእጃችሁ ነው ያለው፤›› በማለት ለሕዝቡ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ሰላም በክልሉ ቢሰፍን ኖሮ ይህን ጊዜ ሕዝቡን የወሰን ማስከበር ጥያቄ ለመመለስ ሕዝበ ውሳኔ ማካሄድ ይቻል ነበር ያሉት ወ/ሮ አዳነች፣ አሁንም ቢሆን ሕዝቡ የራሱን ሰላም ማስጠበቅ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ለሌላው እንደሚደረገው ትጥቅ ሳይፈቱ ቢደራደሩ ምን ችግር አለው ተብለው የተጠየቁት ወ/ሮ አዳነች፣ ትጥቅ ሳይፈቱ ወደ ድርድር መቅረብ የለም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በጎንደር ሌላኛው መድረክ መሪ የነበሩት የሲዳማ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው፣ መንግሥትም ሆነ ብልፅግና የፈጠሩት ችግር የለም የሚል ሐሳብ ሲያስተጋቡ ተደምጠዋል፡፡ አቶ ደስታ ባለፈው ዘመን ከተወረሰ የተዛባ ትርክት የመጣ ችግር አማራ እንደ ገጠመው ተናግረዋል፡፡

ደሴ ከተማ ሕዝብ ካወያዩት አንዷ የነበሩት የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፣ የታጣቂ ኃይሎች ያነገቡት ‹‹የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ስላልተመለሰ ነው ጫካ የገባነው›› የሚለው መነሻ ምክንያት ሀቅ የሌለው ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ብልፅግና ሲመሠረት ጀምሮ በኢትዮጵያ ያሉ ጥያቄዎች ምንድናቸው ብሎ ዘርዝሮ አስቀምጦ፣ ግልጽ ስትራቴጂም አውጥቶ ለመመለስ እየሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በአገሪቱ ያጋጠመው ግጭት እንቅፋት ሆነበት እንጂ ብልፅግና ጥያቄዎቹን በፕሮግራሞቹ አስቀምጦና አደረጃጀትም ፈጥሮ ለመመለስ እየሠራ ነበር፤›› ሲሉ ወ/ሮ ሙፈሪያት ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ አማሮች በዘራቸው እየተለዩ ጥቃት ይደርስባቸዋል፣ ይገደላሉ፣ ይፈናቀላሉ ብሎም ንብረታቸው ይወድማል የሚል ጥያቄ በበርካታ መድረኮች ከሕዝቡ ሲቀርብ ተደምጧል፡፡ በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ዙሪያና በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች አካባቢ ሕገወጥ ግንባታ በማፍረስ ስም የአማራ ተወላጆች ቤት ንብረታቸው ለውድመት እየተዳረገ ይገኛል የሚል ጥያቄም ተሰምቷል፡፡ በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ ዜጎች የሚደርስባቸው ግድያና ዕገታ ጉዳይ ተነስቶ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱ ሰዎች አዲስ አበባ ከተማ አትገቡም ተብለው የመመለሳቸው ጉዳይ ተጠይቆ ነበር፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን የአማራ ተወላጆች በተለያዩ ቦታዎች ይታሰራሉ፣ ይገደላሉ፣ ይፈናቀላሉ የሚል ጉዳይም ተደጋግሞ በየዘገባዎቹ ተስተጋብቷል፡፡ ይሁን እንጂ ለእነዚህና ለሌሎችም ጥያቄዎች አቶ ሽመልስም ሆኑ ወ/ሮ አዳነች ወይም ሌላ አመራር የሰጡት ምላሽ ምን እንደሆነ ሲዘገብ አልተሰማም፡፡    

በመንግሥት ዜና ማሠራጫዎች ከተለቀቁት ከእነዚህ የአማራ ክልል ውይይትን የተመለከቱ ዘገባዎች የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ሕግ እናስከብራለን የሚለውን የመንግሥትን አቋም አጠንክረው ማንፀባረቃቸውን ለመስማት ተችሏል፡፡ መንግሥት ለሰላም ዝግጁ መሆኑን ነገር ግን የታጠቁት ኃይሎች መሣሪያቸውን ጥለው ለሰላም ጥሪው ምላሽ ካልሰጡ፣ የሕግ ማስከበሩ ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በየውይይቱ መድረክ ተደጋግሞ ሲነሳም ተሰምቷል፡፡

ይህን የውይይት ሒደት የተከታተሉ አንዳንድ ወገኖች መርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ቀውስን ለመፍታት የሚያስችል ስለመሆኑ እየተጠራጠሩ ነው፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ አበባው ደሳለው በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፣ መርሐ ግብሩ ተጨባጭ መፍትሔ እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡ 

የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የቆየ ትርክት ብቻ ሳይሆን የግብርና ግብዓት (የማዳበሪያ) ይቅረብልኝ የሚልም እንደ ነበር አቶ አበባው ያወሳሉ፡፡ ሕዝቡ ይፈቱልኝ የሚላቸው በርካታ ጥያቄዎችን ሲያነሳ መቆየቱን የገለጹት አቶ አበባው፣ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት መንግሥት ማርፈዱን ገልጸዋል፡፡ 

‹‹አሁን ብዙ ነገሮች ተበላሽተዋል፡፡ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡ ንብረቶችና ተቋማት ወድመዋል፡፡ አስገድዶ መድፈር፣ ጅምላ እስር፣ የምክር ቤት አባላት ሳይቀር ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ታስረዋል፡፡ እነዚህ ውይይቶች ጦርነቱ ከመካሄዱ በፊት ቢካሄዱ ኖሮ ውጤታማ ሊሆኑ ይችሉ ነበር፡፡ አሁን ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከወጣቶችና ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር የሚደረገው ውይይት ብዙም ውጤት የለውም፡፡ አሁን ጠብመንጃ አንግቦ የሚታገል ኃይል አለ፡፡ ከእዚህ ኃይል ጋር ድርድር ቢደረግ ነው የሚበጀው፤›› ብለዋል፡፡ 

አቶ አበባው ውይይቶቹ አሁን የሚታየው ቀውስ ከመፈጠሩ በፊት ቢሆኑ ኖሮ ችግር ፈቺ ይሆኑ ነበር ይላሉ፡፡ ‹‹የአሁኑ ውይይት የተፈጠረውን ችግር ያሳንሰዋል፡፡ ምክንያቱም አሁን ያለው ሁኔታ የሠፈር ፀብ አይደለም፡፡ ከፍ ያለ አገራዊ ቀውስ ነው የተፈጠረው፡፡ ብዙ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎች የተፈጸሙበት ጉዳይ ነውና አሳንሶ ማየት አይቻልም፡፡ በግሌ እነዚህ ስብሰባዎች ለውጥ ያመጣሉ ብዬ አላስብም፤›› በማለት አክለዋል፡፡

ከሰሞኑ ስለዚሁ ውይይት አስተያየት የሰጡት አንጋፋው የኦሮሞ ፖለቲከኛ ህዝቅኤል ጋቢሳ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ አማርኛ ተናጋሪ የሆኑና ከአማራ የወጡ ፖለቲከኞች ያላረጋጉትን ጉዳይ ከሌላ ክልል አመራር በመላክ ችግሩን መፍታት ይቻላል ብሎ ማሰብ በራሱ ታላቅ ስህተት ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ በአማራ ልሂቃን ዘንድ በርካታ ስሞታ የሚሰማባቸው ሰው ናቸው፡፡ እሳቸው አማራ ክልል ሄደው ሕዝብ ስላወያዩ የአማራ ክልል ችግር ይፈታል ብሎ ማሰብ ከባድ ስህተት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የዚህ ሰሞነኛ ውይይት ግብ በዋናነት ሦስት ዓላማ ያለው ሊሆን እንደሚችል ሕዝቅኤል (ፕሮፌሰር) ተንትነዋል፡፡ ‹‹አንደኛው አማራ ክልል ሰላም ነው እንደሚባለው አይደለም ብሎ ችግሩን አቃሎ ለማሳየት የተደረገ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛም የአማራ ክልል አስተዳደር የለውም፡፡ ሕዝቡን ለማናገር የሚችል ፖለቲከኛም የለም፡፡ የፖለቲካውን ሥራ የያዙት የወታደራዊ አመራሮች ናቸው ብሎ ለማሳየት ሊሆንም ይችላል፡፡ በእርግጥም ይህ እውነትነት ያለው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በአብዛኛው ወታደራዊ አመራሮች ሕዝብ ሲያወያዩ አይተናል፡፡ በሦስተኝነት ደግሞ ይህ በወታደራዊ አመራሮች ሕዝቡን የማነጋገሩ ነገር ስላልሠራ አሁን ደግሞ በሲቪል አመራሩ በኩል ማወያየቱን እንሞክረው በሚል የተደረገ ሊሆን ይችላል፤›› በማለት ነው ፕሮፌሰሩ የተናገሩት፡፡

በሌላ በኩል ይህን የውይይት መርሐ ግብር የአንድ ሳምንት አጀንዳ ማስለወጫ ብሎ አሳንሶ መመልከት ተገቢ አለመሆኑን ነው ሕዝቅኤል (ፕሮፌሰር) የገለጹት፡፡ ውይይቱ የተዛባ ትርክት የሚል የተደጋገመ ሐሳብ የተስተጋባበት መሆኑን የጠቀሱት ተንታኙ፣ ‹‹የአማራና የትግራይ ክልሎችን ጠላትነት የማደስ ግብ ያለው፤›› ብለውታል፡፡ አሁንም የትግራይ ልሂቅ ነው የፖለቲካ ሥጋትህ ብሎ ሁለቱን ክልሎች በማጋጨት ለማስቀጠል የታለመ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አማራ የሕገ መንግሥት ይሻልልኝ ጥያቄ አለው በሚል የፌዴራል መንግሥቱ ጉዳዩን ገፍቶ ለማምጣትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለራሱ በሚጠቅም ሁኔታ ለመለወጥ ሊጠቀምበት እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

ውይይቶቹን በተመለከተ በመንግሥት ሚዲያዎች ከተሠራጩ ምጥን ዘገባዎች ውጪ ስለሒደቱ እንዲሁም በውይይት መድረኮቹ ስለነበረው ድባብ በተጨባጭ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡ ሪፖርተር በተለያዩ ከተሞች በተካሄዱ ውይይቶች የተሳተፉ አንዳንድ ሰዎችን ስለሒደቱ ለመጠየቅ የሞከረ ቢሆንም፣ ደፍሮ የውይይት ድባቡን የሚገልጽ ለማግኘት ሳይችል ቀርቷል፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአንድ ከተማ ውይይት ተሳታፊ ጥያቄ በመጠየቃቸው ማስፈራሪያ እንደገጠማቸው ተናግረዋል፡፡ ውይይቱን በተካፈሉና ጥያቄ ባቀረቡ ማግሥት ከአንድ የአካባቢያቸው አመራር፣ ‹‹እንዴት እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ታነሳለህ? እኛ ካንተ ይህን አንጠብቅም የሚል ቁጣ በስልክ ደረሰኝ፤›› የሚሉት እኚህ ግለሰብ፣ ስለውይይቱ ሁኔታ ለመናገር ለራሳቸው ደኅንነት ሲሉ እንደሚፈሩ በመጠቆም አጭር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ውይይቱ እየተካሄደ ባለበት ወቅት የአማራ ክልል ችግር በዘላቂነት በምን መንገድ ይፈታ በሚለው ነጥብ ላይ አንዳንድ ወገኖች ከዚህ ቀደም ያልተደመጡ የተለያዩ ሐሳቦችን ሲሰጡ ታይተዋል፡፡ ታዋቂው የሕግ ምሁር አደም ካሴ አበበ (ዶ/ር)፣ በኤክስ/በትዊተር ገጻቸው ላይ በአስቸኳይ ሁሉንም ወገን አካታች የሆነ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት በአማራ ክልል ውስጥ እንዲመሠረት፣ ከመንግሥት ጋርም በሕዝቡ ጥያቄዎች ዙሪያ እንዲደራደር ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ ስለዚሁ ሐሳብ የመፍትሔ አማራጭነት ሪፖርተር የጠየቃቸው የአብኑ የምክር ቤት ተወካይ አቶ አበባው፣ ጉዳዩ ብቸኛ ባይሆንም አንዱ አማራጭ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -