Sunday, April 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የሕፃናት ጤና ሲታሰብ

በሳህሉ ባዬ

ብዙ ጊዜ ስለ ሕፃናት ጤና ስናስብ አካላዊ ዕድገት ላይ ብቻ ስናተኩር ይስተዋላል። ይህ ዕይታ ብቻውን በቂ አይደለም። የሕፃናት አዕምሮም በቂ ትኩረት ሊያገኝ ይገባል። ስለ ሕፃናት ጤና ስናነሳ ስሜታቸውን መግለጽ፣ መምራትና ማስተዳደር ስለሚችሉና ችግር ስለገጠማቸው ታዳጊ ሕፃናት ማሰብ ይኖርብናል።

ሕፃናት ለስሜትና አካላዊ ጉዳቶች ሲጋለጡ፣ ሲገለሉ፣ ሲረሱ፣ ፍቅር፣ ጨዋታና እንክብካቤ ሲነፈጉ በሰውነታቸው ውስጥ የአዕምሮ ሴሎች የሚገድል ከፍተኛ የኮርቲሶል ሆርሞን ይመረታል። ይህ ጎጅ ሆርሞን በውጤቱ የአዕምሮ ዕድገት መቀጨጭ (20%-30%)፣ የእዕምሮ ዝግመት፣ የመማር ችግር፣ ደካማ ማህበራዊ ግንኙነት፣ ግዴለሸነት፣ ጥላቻና የተዛባ የአንጐል ሴሎች ግንኙነት ያስከትላል፡፡

የሕፃናትን አዕምሮ ጤና መጠበቅ የሚቻለው ቤተሰባዊ ቅርበት፣ አስተማማኝ ምላሽ ሰጪ ግንኙነት፣ እንክብካቤ፣ የተረጋጋ ሕይወት፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ ጨዋታ፣ መዳሰስና ማሰስ የሚያስችል ስሜት አዳባሪ አካባቢ መፍጠር ሲቻል ነው።

በተለይ በቅድመ ወሊድና በመጀመሪያዎቹ 2-3 ዓመታት ምቹ አካባቢ መፍጠር አስፈላጊ ነው። በእነዚህ ዓመታት በጄኔቲክ ቅድመ ዝንባሌና በአካባቢ መካከል በሚፈጠር መስተጋብር የሚከሰት ተጽዕኖ ለጤናማ አዕምሯዊ ዕድገት መሠረት ናቸው። ተፅዕኖው በጎልማሳነት ዕድሜ ጐልቶ ይታያል። ስለዚህ ከሕፃናት አስተዳደግ ጋር ግንኙነት ላላቸው ባለድርሻ ሰዎች ትምህርትና ተከታታይ ሥልጠናዎች መስጠትና ግብዓቶችን ማሟላት ጠቃሚ ነው።

 ሕፃናት ምቹ የመማሪያ አካባቢ ሲገጥማቸው፣ ከጎልማሶች ጋር ሲሠሩና አዳዲስ ክህሎቶችን ሲለማመዱ፣ የረጅም ጊዜ የትምህርት ስኬትን የሚደግፍ ጠንካራ የአዕምሮ ውቅር እየገነቡ እንደሆነ ቀደም ሲል ተረጋግጧል። አሁን ደግሞ አዲስ ምርምር ምስጋና ይግባውና እነዚህ ቀደምት ልምምዶች የዕድሜ ልክ ጤንነታቸውን በመቅረፅ ረገድ አስፈላጊ መሆናቸው ታውቋል።

ሕፃናትን መንከባከብ ግዴታ ነው!

በሕፃናት አስተዳደግ ሒደት ላይ ጥናት ባደረጉ ባለሙያዎች አገላለጽ፣ ሕፃናት በአካል፣ በአዕምሮ፣ በስሜትና በማኅበራዊ ለጋና ታዳጊ ስለሆኑ የሚያዩት፣ የሚሰሙት፣ የሚዳስሱትና የሚያሸቱት ሁሉ ከህልውናቸው ጋር በፍጥነት ይዋሃዳል፡፡ ሕፃናት መንቀሳቀስ የሚወዱና በአንድ ሥራ ላይ ብቻ ለረዥም ጊዜ ተጠምደው መቆየት የማይችሉ ናቸው፡፡ ጨዋታ ይወዳሉ፡፡

ጨዋታ ሲባል ቧልት፣ ፌዝና ቀልድ ሳይሆን የአካል ቅልጥፍናን፣ የአዕምሮ ንቃትን፣ በሥራ መደሰትን፣ በዕቅድ መመራትን፣ ግምትን፣ ፈጠራን፣ መውድድንና መወደድን፣ ማኅበራዊ ግንኙነትንና ባህልን ሊያስተምር የሚችል በቁም ነገር የተሞላ ጨዋታ ማለት ነው፡፡ ሕፃናት በጨዋታ ደስታንና ዕርካታን ያገኛሉ፡፡

ሕፃናት ጭንቀትና ድብርት ማርከሻ ፀጋ አላቸው። ሳቅና ፈገግታቸው ለአዋቂዎች ጥሩ መድኃኒት ነው። ይህን ሰብዓዊ መግነጢሳዊ ኃይል መጋራት ደግሞ የአዋቂዎች ድርሻ ነው።
እኛ ወልደን ለመሳም እንጓጓለን እንጂ ሕፃናት ውለዱን ብለው አይጠይቁም።

ስለዚህ ወልደን የመሳም ምኞታችን ከመሳካቱ በፊት ወደንና ፈቅደን ለወለድናቸው ሕፃናት በጤና፣ በሰላምና ፍቅር የሚያድጉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ግድ ይላል። ጊዜ ሰጥተን በጋራ ለመጫወት፣ ለመንከባከብ፣ ‹ክንፎችና ሥሮች› በመሆን ከፍ ብለው እንዲበሩና በረው ሲመለሱ ማረፊያ ለመሆን ዝግጁ መሆን አለብን።

በትምህርት ፍልስፍናዋና የምርምር ሥራዎቿ የምትታወቀው ኢጣሊያዊቷ ሐኪምና አስተማሪ ማሪያ ሞንቴሶሪ ‹‹ልጆች የዋህ፣ ባለ ንፁህ ህሊና እና ወደፊት የሚገጥሟቸው ዕድሎች ከእኛ የተሻሉ ስለሆነ ትኩረት ሊያገኙ ይገባል›› ስትል መክራለች።

ስለዚህ ሕፃናት በሰላምና በጤና የማደግ፣ በጋራ የመልማትና የመኖር ዓለም አቀፍ መብት አላቸው። በመሆኑም ከተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች ሊጠበቁ ይገባል።

ሕፃናት በማኅበራዊ ችግሮች ሲጠቁ ለመርዛማ ጭንቀት (Toxic stress/ PTSD) ለተባሉ የአዕምሮ ሕመሞች ይጋለጣሉ። ጤናቸው ተዛብቶ ሕይወታቸው ለዘላቂ ችግር ይጋለጣል። ስለዚህ የማኅበረሰብ ዕድገት አንዱ መለኪያ የሕፃናት ልማት በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። የሕፃናትን አዕምሯዊ ጤንነት ችላ ካልን የመማር፣ የመሥራት፣ ጤናማ ማኅበራዊ ግንኙነት የመገንባትና ለዓለም አስተዋፅዖ የሚያደርጉበትን አቅም አሳጣናቸው ማለት ነው።

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ፣ በዓለማችን ዕድሜያቸው ከ10-19 ዓመት የሆኑ ከ13% በላይ ወጣቶች በተረጋገጠ አዕምሯዊ መታወክ የተጠቁ ናቸው። ከእነዚህ ሕመሞች ውስጥ 40% ያህሉን ጭንቀትና ድብርት ይይዛሉ። ቀሪዎቹ ትኩረት ማጣትና ቅብጥብጥነት፣ የባህርይ መታወክ፣ የአዕምሮ ውስንነት፣ ኦቲዝም፣ የስሜቶች መለዋወጥ (ባይፖላር ዲስኦርደር)፣ የምግብ ፍላጐት የሚያስከትለው ችግር፣ ስኪዞፍረኒያ እና የሰብዕና ቀውስ ናቸው። በእነዚህ ችግሮች ምክንያት በየ11ደቂቃው አንድ ወጣት ራሱን እንደሚያጠፋ ጥናቶች ገምተዋል።

 ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ከሆኑ ሕፃናት መካከል 20% ያህሉ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሕይወት ውስጥ ይኖራሉ። ድህነት ለአዕምሮ ሕመም አጋላጭ ሲሆን የአዕምሮ ሕመም ለድህነት ምክንያት ነው። ተመጋጋቢ ናቸው።

 ስለ አዕምሯዊ ጤና ለማስተማርና ለማከም የሚደረግ ኢንቨስትመንት እጅግ በጣም አናሳ ነው። የአንዳንድ አገሮች መንግሥታት የአዕምሮ ጤናን ለመንከባከብ  ለአንድ ሰው የሚበጅቱት ከአንድ ዶላር በታች ነው።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles