Sunday, April 21, 2024

የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ ስምምነት የሶማሊያን ቀውስ አባብሷል የሚለው ስሞታ ተዓማኒነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከሰሞኑ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ወታደሮች በሶማሊያው የሽብር ቡድን አልሸባብ የደረሰባቸው ጥቃት መነጋገሪያ ጉዳይ ነበር፡፡ በሞቃዲሾ ከተማ የሶማሊያ ፀጥታ ኃይሎችን የሚያሠለጥኑ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ወታደሮች የጥቃቱ ዒላማ ነበሩ፡፡

ጄኔራል ጎርደን የጦር ካምፕ ላይ በደረሰው የሽብር ጥቃት ሦስት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ወታደሮችና አንድ የባህሬን ወታደር ሲገደሉ፣ ሁለት ተጨማሪ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ወታደሮች ደግሞ መቁሰላቸው ታውቋል፡፡

ቅዳሜ የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. የደረሰው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ወታደሮችን ዒላማ ያደረገው የአልሸባብ ጥቃት ብዙ መላምቶች እየተሰጠበት ነው፡፡ ጥቃቱን በተመለከተ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ የሐዘን መግለጫ አውጥተዋል፡፡ አንዋር ጋርጋሾ የተባሉ አንድ ከፍተኛ የተባበሩት ኤምሬትስ ዲፕሎማት በበኩላቸው፣ ‹‹ምንም ዓይነት ጥቃት ቢፈጸም ደኅንነትና ጥበቃ እንዲጠናከር ካለማድረግም ሆነ ሽብርተኝነትን ከመዋጋት የሚያስቆመን ኃይል አይኖርም፤›› ብለው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ ስምምነት የሶማሊያን ቀውስ አባብሷል የሚለው ስሞታ ተዓማኒነት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ በአዲስ አበባ የመግባቢያ ስምምነት
በተፈራረሙበት ወቅት

ለጥቃቱ ሙሉ ኃላፊነቱን የወሰደው አልሸባብ በበኩሉ፣ ‹‹ዓረብ ኤምሬትስ የእስልምና ሕጎችን የጣሰች ፀረ እስላም አገር ናት፤›› በማለት ፈርጇታል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥቃቱን ማጠናከሩ የሚነገረው አልሸባብ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ፣ በሞቃዲሾ በአንድ የተጨናነቀ ገበያ ባደረሰው ጥቃት አሥር ሰዎችን ገድሎ 20 ማቁሰሉ ተዘግቦ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ አልሸባብ ዓረብ ኤምሬትስን ዒላማ ያደረገው ያለ ምክንያት እንዳልሆነ በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሶማሊያ ወደቦች አካባቢ መጠነ ሰፊ ኢንቨስትመንት ማካሄዷ ለጥቃት እንዳጋለጣት በርካቶች በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ ግንኙነት መፍጠሯ፣ በሶማሊያዊያን ዘንድ እንድትጠላ እያደረጋት መሆኑ በሰፊው እየተዘገበ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው የባህር በር የመግባቢያ ስምምነት በሶማሊያ የፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ ተቃውሞ ሲነሳበት መቆየቱ ይታወቃል፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከኢትዮጵያ ጀርባ በመሆን ስትተባበራት ቆይታለች የሚል ክስ ሲቀርብባት ነበር፡፡ ኢትዮጵያን በመደገፍ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያንና የሶማሌላንድን ስምምነት በመደገፍ የሶማሊያ ሉዓላዊነት እንዲጣስ ምክንያት እየሆነች ነው ብለው በከሰሷት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ላይ፣ የሶማሊያ ፖለቲከኞች ከፍተኛ የጠላትነት ስሜት ሲያንፀባርቁ ነው የሰነበቱት፡፡

የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነትን ተከትሎ በኢትዮጵያ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጀርባ ቆመዋል በሚል በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ላይ ሲንፀባረቅ የቆየው ጥላቻም አልሸባብ እነዚህ አገሮችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት እንዲከፍት እንደገፋፋው በሰፊው እየተዘገበ ነው፡፡ ከሰሞኑ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ወታደሮች ላይ የእሩምታ ተኩስ በመክፈት ጥቃት የፈጸመው ወታደር፣ ከአልሸባብ ቡድን አባልነት የወጣ እንደነበር ተሰምቷል፡፡ ከአልሸባብ ወጥቶ የሶማሊያ መደበኛ ጦርን የተቀላቀለ መሆኑን፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ድጋፍ የሚሰጠውን ወታደራዊ ሥልጠናም በጦር ካምፑ ሲከታተል መቆየቱ ታውቋል፡፡ ይህን ሁሉ ካለፈ በኋላ ግን በድንገት ወደ አልሸባብነት ተቀይሮ ሲሠለጥንበት በቆየው የጦር ካምፕ፣ ሲያሠለጥኑት በቆዩት ወገኖች ላይ ጥቃት ማድረሱ አስገራሚ ነው ተብሏል፡፡

የሶማሊያ መንግሥት ጥቃቱ በደረሰ ማግስት እሑድ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ብለን ነበር›› የሚል ይዘት ያለው መልዕክት አስተላልፏል፡፡ የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ ስምምነት ቀጣናውን ቀውስ ውስጥ ይከታል ብለን ስናሳስብ መቆየታችን ይታወሳል የሚል ይዘት ያለው የሶማሊያ መንግሥት መግለጫ፣ አልሸባብ ከስምምነቱ በኋላ ጥቃቱን ማጠናከሩን አጉልቶ ለማሳየት ሞክሯል፡፡

‹‹ሶማሊያ በአልሸባብ የሽብር ቡድን ላይ የተሳካ ዘመቻ ስታካሂድ ቆይታለች፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ቁልፍ የሚባሉ ቦታዎችን የሶማሊያ መንግሥት ከአልሸባብ ማስለቀቅ ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት ተጋፍታ ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟ ለአልሸባብ የመጠናከር ወርቃማ ዕድል ፈጥሮላታል፡፡ ይህ ደግሞ በሽብር ቡድኑ ላይ የተቀናጀ ነው ድል እንዲከሽፍ የሚያደርግ ነው፤›› በማለት ነበር የሶማሊያ መንግሥት በመግለጫው ያተተው፡፡

ይህ ደግሞ የሶማሊያ መንግሥት መግለጫ የአገሪቱ ፖለቲካ ልሂቃን የኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ስምምነት ከአልሸባብ መጠናከር ጋር በቀጥታ እያገናኙት መሆኑን የሚያመለክት ነው ተብሏል፡፡ ከሰሞኑ በሮም በአፍሪካና በጣሊያን የመጀመሪያ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ሰፊ ገለጻ ያደረጉት የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ፣ ይህንኑ የበለጠ የሚያጠናክር አስተያየት ሲሰጡ ነበር፡፡

 የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን ለአልሸባብ መጠናከር ምክንያት አድርገው ሲያቀርቡ ተደምጠዋል፡፡ ሶማሊያ አልሸባብን አደጋ የማይፈጥርበት ደረጃ ለማድረስ ብዙ ስትሠራ ብትቆይም፣ ኢትዮጵያ ግን ይህን የሚያደናቅፍ ሥራ ሠርታለች ሲሉ ተናግረዋል፡፡ እሳቸው ወደ ሥልጣን ከመጡበት ከግንቦት እ.ኤ.አ. 2022 ጀምሮ ሰላምና መረጋጋትን መፍጠር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ በማድረግ ሶማሊያ ሽብርተኞችን ስትዋጋ መቆየቷን ገልጸዋል፡፡

‹‹ሶማሊያ በአፍሪካ ረጅም የባህር ጠረፍ ያላት አገር ናት፡፡ ይህን የባህር ጠረፍ በአግባቡ መጠበቅ ካልቻልን የስደተኞች ፍልሰትንም ሆነ የሽብርተኞችን እንቅስቃሴና የባህር ላይ ዝርፊያን መከላከል ትቸገራለች፡፡ ይህ በአሁኑ ጊዜ እንኳ የዓለምን ግማሽ ያህል ኢኮኖሚ የሚፈታተን ችግር መሆኑን እየተመለከትን ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

ሶማሊያን መደገፍ ብዙ ዓለም አቀፍ ችግሮችን መቅረፍ እንደሆነ አበክረው ያስገነዘቡት ፕሬዚዳንቱ፣ ሶማሊያ ታጣቂዎችን እንድታሸንፍ አግዙን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ሀሰን ሼክ በተለይ ኢትዮጵያን የተመለከቱ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን፣ ሶማሊያ ወዳና መርጣ የኢትዮጵያ ጎረቤት እንዳልሆነች በመጠቆም 1,700 ኪሎ ሜትር ድንበር የሚጋሩ አገሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ከኢትዮጵያ ጋር ለ600 ዓመታት በጉርብትና ኖረናል፡፡ እነዚህ 600 ዓመታት ደግሞ በቀውስ የተሞሉ ነበሩ፡፡ አንዱ ጂሀድ ሌላው የመስቀል ጦርነት ሲያውጅ በግጭት ነው የኖሩት፡፡ ይህ በቀውስ የተሞላ ጉርብትና ግን እ.ኤ.አ. በ1990 የሁለቱም አገሮች መንግሥታት ሲፈራርሱ አበቃ፡፡ የሶማሊያው ዚያድ ባሬና የኢትዮጵያው መንግሥቱ ኃይለ ማርያም መንግሥታቸው ፈርሶ አገር ጥለው ፈርጥጠዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች ብዙ የእርስ በርስ ጦርነት ካስተናገዱ በኋላ ነው ዛሬ ላይ የደረሱት፡፡ አሁን በሶማሊያ ሪፐብሊክ እንደ አዲስ መሥርተን መምራት ጀምረናል፡፡ ያለፈውን ትተን በአዲስ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትብብር ጉርብትናችንን ለማስቀጠል ጥረት ጀምረናል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ይህን የሚያደናቅፍ ሥራ እየሠራች ነው፤›› በማለትም ወቅሰዋል፡፡

ለሶማሌላንድን ማንም የዓለም አገር ዕውቅና እንዳልሰጠ የገለጹት ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ፣ አሁንም ቢሆን የሶማሊያ ሉዓላዊ ግዛት አካል መሆኗን ተከራክረዋል፡ ‹‹ሶማሌላንድን ልክ እንደ ሉዓላዊ አገር ቆጥረው ኢትዮጵያውያን የወደብ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ለሶማሌላንድ የአገርነት ዕውቅና እንደሚሰጡና የባህር ኃይል ማስፈሪያ ካምፕ በባህር ጠረፍ ላይ እንደሚገነቡ እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ የማይሆን ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ወደብም፣ የባህር ኃይልም፣ የትራንስፖርት ኮሪደርም የመገንባት አቅም እንደሌላት አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ፡፡ ከኢትዮጵያ ጀርባ ጉዳዩን የሚያበረታታና የሚደግፍ ኃይል መኖሩን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል፤›› ሲሉ ኢትዮጵያን ወንጅለዋል፡፡

ይህን ጉዳይ የሶማሊያን ሉዓላዊነት ከመድፈር፣ ዓለም አቀፍ ሕጎችና ስምምነቶችን ከመጣስ ጋር ያገናኙት ፕሬዚዳንቱ መላው ዓለምም የኢትዮጵያን እንቅስቃሴ እንዲቃወም ነው የጠየቁት፡፡

ኢትዮጵያ በየጊዜው በሶማሊያ ጉዳዮች ጣልቃ መግባቷ የሶማሊያን ችግር ከማባባስ በስተቀር የፈየደው ነገር አለመኖሩን ሀሰን ሼክ በይፋ ተናግረዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2006 የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት ሲቋቋም ኢትዮጵያ ተቻኩላ ወደ ሞቃዲሾ ጦሯን በማስገባቷ የተነሳ የሶማሊያ ችግር ከድጡ ወደ ማጡ እንደገባ በመጠቆም ተችተዋል፡፡ ‹‹በጊዜው ኢትዮጵያ 50 ሺሕ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ አስገባች፡፡ በዚህ የተነሳ ቡድኑ ተጠናከረ፡፡ ጂሀድ ማወጅ አለብን የሚሉ ፅንፈኛ የሃይማኖት አክራሪ ቡድኖች ተጠናከሩ፡፡ እንደ አልሸባብ ያሉ የሽብር ቡድኖች ተፈጠሩ፡፡ በርካታ ወጣቶችን ለጦርነት ማሠለፍም ቻሉ፡፡ ይህ ሁሉ አልፎ ሶማሊያን ማረጋጋትና ዳግም ሰላም መገንባት ጀመርን፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ አሁን ይህንን ጥረታችንን የሚያደናቅፍ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረች፤›› ብለዋል፡፡

ሀሰን ሼክ ሲቀጥሉ አልሸባብ የሽብር ቡድንን ከ16 ዓመታት ልፋት በኋላ  በከፍተኛ ደረጃ አቅሙን እንዳዳከሙት ይናገራሉ፡፡ ‹‹አልሸባብን ልናጠፋው በተቃረብንበት በዚህ ወቅት ግን ኢትዮጵያ በድንገት ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመች፡፡ ይህ ስምምነት ደግሞ አልሸባብን ከመጥፋት የሚታደግ አጋጣሚ ሆነ፡፡ ስምምነቱ ‹ስንል ነበር›፣ ‹ኢትዮጵያ ተመልሳ ልትወረን ነው›፣ መንግሥታችን በውጭ ኃይል ሊያስወርረን ነው የሚል ቅስቀሳ ለማድረግ ምክንያት ሆናቸው፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

ለሶማሊያ መንግሥት ዕውቅና ባንሰጥም ነገር ግን አገራችንን ኢትዮጵያ ስትወር ዝም ብለን አናይም በማለት፣ አልሸባቦች ጉዳዩን ለፖለቲካ መቀስቀሻነት እየተጠቀሙበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ‹‹አልሸባብ ላይ በከፈትነው ሁሉን አቀፍ ዘመቻ ቡድኑን የርዕዮተ ዓለምና የፖለቲካ መሠረት አሳጥተነው ነበር፡፡ ቡድኑ ከውኃ የወጣ ዓሳ ሆኖ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የወደብ ስምምነት መፈረሟ ግን ይህን አበላሽቶታል፡፡ ቡድኑ ተፋላሚዎችን ለመመልመልና ጥቃት ለማጠናከር የኢትዮጵያ ዕርምጃ ጠቅሞታል፡፡ ኢትዮጵያ ያደረገችው ነገር ሩሲያ በዩክሬን ከፈጸመችው ጥፋት ጋር የሚነፃፀር ነው፡፡ ሩሲያ በዶምባስ ግዛት ጣልቃ ባትገባ ኖሮ የዩክሬን ጦርነት ባልነበረ፡፡ ኢትዮጵያም በሶማሊያ ጉዳይ ጣልቃ ገብታ አልሸባብ እንዲጠናከርና ተጨማሪ ቀውስ እንዲፈጥር ምክንያት ሆናለች፤›› በማለት ነበር ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ የኢትዮጵያን ጥፋት አጉልተው በዓለም መድረክ ለማቅረብ የሞከሩት፡፡

ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክና የሶማሊያ ፖለቲከኞች ሶማሊያ በአልሸባብ ላይ የምታደርገውን ውጊያ፣ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት እንቅፋት እየሆነበት ነው የሚለውን ውንጀላ ጎልቶ እንዲሰማ የፈለጉ ይመስላል፡፡ ጉዳዩን የታዘቡ ወገኖች ኢትዮጵያ እንደ አልሸባብ ያሉ ኃይሎችን ለመዋጋት በሺሕ የሚቆጠር ጦር በሶማሊያ ማሥፈሯ፣ በሶማሊያ ፖለቲከኞች ዘንድ የተረሳ ነው የሚመስለው ይላሉ፡፡

ከሰሞኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በሺሕ የሚቆጠሩ ወታደሮች በሶማሊያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ተሰማርተው ባሉበት የሕይወት መስዋዕትነት መክፈላቸውን አውስተው ነበር፡፡ ‹‹ከሰሞኑ እንኳን በሁርሶ ማሠልጠኛ ማዕከል የሶማሊያ ወታደሮችን አሠልጥነን ልከናል፤›› ሲሉ የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም፣ መረጋጋትና እንደ አገር መቆም የከፈለችው መሰዋዕትነት በዋጋ የሚተመን እንዳልሆነ ገልጸው ነበር፡፡

‹‹ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው›› እንደሚባለው የሶማሊያ ፖለቲከኞች ጭምር በቅጡ የሚገነዘቡት ሀቅ ቢሆንም እንኳን፣ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ለአልሸባብ መጠናከር ዋና ምክንያት እየሆነች ነው የሚለውን ክስ አጉልተው ማሰማት የመረጡ ነው የሚመስለው፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የባህር በር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ የሶማሊያ ቀውስ ምንጭ በሚል በሶማሊያ ፖለቲከኞች ስትፈረጅ ቆይታለች፡፡ ሌላው ቀርቶ እንደ አልሸባብ ያሉ የሽብር ቡድኖች ጭምር ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ዒላማ ሲያደርጉ እየታየ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -