Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ንግድና ኢንዱስትሪ በአዋጅ ተለያይተው ሁለት ምክር ቤት መሆናቸው በመካከላቸው ያለውን ፍትጊያ ያስቀራል›› አቶ አበባየሁ ግርማ፣ የኢትዮጵያ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ ሲያወዛግብ ቆይቷል፡፡ አዋጁ መሻሻል አለበት ተብሎ ሲሞገት የነበረው አዋጅ ከወጣበት ማግሥት ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ላለፉት 20 ዓመትም አዋጁ ይሻሻል የሚለው ጥያቄ ያለ ማቋረጥ ሲቀርብ ነበር፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን አዋጁ መሻሻል እንዳለበትም ታምኖ የረቂቅ አዋጅ ዝግጅቱ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ይሁንና የሚሻሻለው አዋጅ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት በሚል መጠሪያ ረቂቁ ተዘጋጅቶ ቢያልቅም፣ አሁን ላይ ንግዱንና ኢንዱስትሪውን ለየብቻ በማድረግ ተለያይተው መሥራት አለባቸው ተብሎ ለሁለቱም ዘርፎች የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች ተዘጋጅተዋል፡፡ ይህ አደረጃጀት ግን ብዙ ጥያቄዎች እያስነሳ ነው፡፡ ሁለት ምክር ቤቶች እንዲፈጠሩ ማድረግ፣ ንግድ ምክር ቤቶችን ያደክማል የሚሉ አስተያቶች ጎልተው እየተሰሙ ነው፡፡ የጉዳዩ ባለቤት ነኝ የሚለው የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ግን፣ መንግሥት የኢንዱስትሪ ምክር ቤት ለብቻው እንዲቋቋም መወሰኑ አግባብ መሆኑን ያምናል፡፡ የኢትዮጵያ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበባየሁ ግርማ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ይህንኑ ሐሳብ አንፀባርቀዋል፡፡ በዚህ አወዛጋቢ በሆነው ጉዳይ ዙሪያ ዳዊት ታዬ ከአቶ አበባየሁ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡   

ሪፖርተር፡- አሁን ሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ከሁለት አሠርት ዓመታት በላይ ሲያወዛግብና ሲያጨቃጭ የቆየ ነው፡፡ አዋጁን ለማሻሻል ሲደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎች በቶሎ ወደ ተግባር ሊለወጡ አልቻሉም፡፡ ይህንን ያህል ከባድ የሆነበት ምክንያት ምንድነው? አዋጁ ያለመሻሻሉ ያጎደለው ነገር ምንድነው?

አቶ አበባው፡- እውነት ለመናገር ይህንን አዋጅ ለማሻሻል ከባድ መሆኑን እኔም ራሴ የምገረምበት ጉዳይ ነው፡፡ የንግድ ምክር ቤቶችን ማጠናከር ለመንግሥትም፣ ለሕዝብም ሆነ ለአገር የሚጠቅም ነው፣ መሠረቱ ይህ ነው፡፡ አደረጃጃችንን እያሳመርን ስንሄድ አገርን የማሳደግ ዕድላችን ከፍ እያለ ይሄዳል፡፡ ሌላው ዓለም ላይ የንግድ ምክር ቤቶች ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ አብዛኛው የወጪና የገቢ ንግድ ሥራዎች ስምምነቶች የሚደረጉት ከንግድ ምክር ቤቶች ጋር ነው፡፡ የአንድ አገር ኩባንያ ከሌላ አገር ጋር የንግድ ስምምነት ሲደረግ ከስምምነቱ ውጪ የሆነ ተግባር ተፈጽሞ አለመግባባት ቢኖር እንኳን በንግድ ምክር ቤቶች በኩል እደራደራለሁ ነው የሚባለው፡፡ ለምሳሌ እኔ በግሌ ኤክስፖርት ሥራ ላይም ያለሁ በመሆኔ የእኔን ምርት ከሚቀበለው ውጭ ኩባንያ ጋር ባልስማማ በንግድ ምክር ቤት ሕግ እንዳኛለን የሚል ስምምነት ተፈራርመናል፡፡ የንግድ ስምምነቶች ችግር ቢያጋጥማቸው እንዲህ ባለው ሁኔታ መልኩ እንዲፈቱ ንግድ ምክር ቤቶቹ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ስለዚህ የንግድ ምክር ቤቶች እየተጠናከሩ ሲመጡ የንግድ ሲስተሙን እንዲሳለጥ ያደርጋል፡፡ አንዳንድ አገሮች ላይ እኮ የንግድ ምክር ቤቶች ከመጠንከራቸው የተነሳ መንግሥት የመቀየርና ማስመረጥ ደረጃ ላይ ሁሉ የደረሱ አሉ፡፡ የእኛ ግን ብዙ ይቀረናል፡፡ አዋጁን ለማሻሻል እንኳ ብዙ ጊዜ ወስዶብናል፡፡ አሁን ሥራ ላይ ያለው የንግድ ምክር ቤቶቹ ማቋቋሚ አዋጅ መሻሸል በሚገባው ደረጃ አለመሻሻሉም ንግድ ምክር ቤቶቻችን የሚፈለግባቸውን ያህል ሊሠሩ አልቻሉም፡፡ ኢኮኖሚያችን ትልቅ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞም ንግድ ምክር ቤቶች ብዙ ጊዜ ፖለቲካ ውስጥ የመግባት አዝማሚያ ነበር፡፡ መንግሥትም መጥቶ ንግድ ምክር ቤቶች እንዳያድጉ አስሮ የመያዝ ነገርም ይስተዋል እንደነበር ሲነገር ቆይቷል፡፡ መንግሥት ለንግድ ምክር ቤቶች ተስማሚ ሕግ ቢያወጣም የራሱን ፍላጎት እንዲያስፈጽሙለት ይደረግ ነበር፡፡ ስለዚህ አሁንም ከአደረጃጀት ጋር የገጠመው ችግር ቀድሞ ከነበረው ሁኔታ ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ የንግድ ምክር ቤቶች አደረጃጀት ወደ 80 ዓመታት ታሪክ ያለው ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን ብዙ ነገሮች የንግድ ምክር ቤቶች ሳይኖሩ በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች ተመሥርተው ይሠሩ ነበር፡፡ ንግድ ምክር ቤቶችን ጥንካሬ ስትመለከት ግን ከእኛ በኋላ ብዙ ዓመታት ዘግይተው የተቋቋሙ የሌሎች አገሮች ንግድ ምክር ቤቶች ጠንካራ ሆነው ስታይ ያስቆጫል፡፡  

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች እንዲህ የሆኑበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ አበባው፡- ምክንያቱም ሥራቸውን ገለልተኛ ሆነው የሚሠሩበት ዕድል ስለተፈጠረላቸው ነው፡፡ በእርግጥ የእኛ አገር የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጁ የንግድ ምክር ቤቶች ገለልተኛ ሆነው እንዲሠሩ ይፈቅዳል፡፡ ግን አንዳንዴ በተግባር ላታየው ትችላለህ፡፡ እርግጥ ነው እንዲህ ባሉ ተቋማት ውስጥ የመንግሥት ፍላጎት ሊኖር ይችላል፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ግን በቀጥታ ለመግባት ፍላጎቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከ1995 ዓ.ም. በፊት ሁሉንም የቢዝነስ ዘርፍ ያሰባሰበና ንግድ ምክር ቤት በሚል ይታወቅ ነበር፡፡ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ግን በንግድ ምክር ቤቶችና በመንግሥት መካከል ያለ መግባባት ይፈጠራል፡፡ ከቀደምት አመራሮች እንደሰማነውም መንግሥትን ደግፉ የሚል ነገር ይዞ ይመጣል፡፡ የንግድ ምክር ቤቶች አመራሮች ይህንን አንቀበልም ይላሉ፡፡ በጎን ሌላ አደረጃጀት እንዲፈጠር ይደረጋል፡፡ መጀመሪያ ዘርፍ ምክር ቤት በሚል ንግድ ምክር ቤቶችን የሚቀላቀሉ ተቋማት እንዲፈጠሩ ተደረገ፡፡ ይህ የሚሆነው ንግድ ምክር ቤቱ አመራር ዕንቢ ቢል ከእነዚህኞቹ ጋር በመሆን የምንፈልገውን እናደርጋለን የሚል አመለካከት ተይዞ እንደነበርም ለመረዳት ይቻላል፡፡ ንግድና ዘርፍ የሚለው አደረጃጀት ከተፈጠረ በኋላ ግን ዘርፉም እኔ በአዋጅ ነው የተቋቋምኩት እንዲህ ያለው ነገር ውስጥ አልገባም ይላል፡፡ ከዚህ በኋላ መንግሥት ንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶችን ወደ ጎን በማድረግ የነጋዴ ፎረም የሚል አደረጃጀት እንዲፈጠር አደረገ፡፡ ልማታዊ ነጋዴ የሚሉና የመሳሰሉት መጠሪያ ያላቸው አደረጃጀቶች መፈጠርና ሌሎች  ነገሮች ተደማምረው አሁን ንግድና ዘርፍ የምንለው ምክር ቤት ጠንካራ እንዳይሆን ምክንያት እስከመሆን ደረሰ፡፡ ከዚህ የዘለለ ነገር አለ ብዬ በግሌ አላምንም፡፡

ሪፖርተር፡- እንግዲህ እንዲህ ያሉ ነገሮች ከታለፉ በኋላ አላሠራ አለ የተባለውን አዋጅ ለማሻሻል አዎንታዊ ምላሽ ተገኝቶ ወደ ሥራ ከተገባ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አዋጁን ለማሻሻል መጀመሪያ የተሰናዳው ረቂቅ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት በሚል ነው፡፡  ብዙ ውይይት ሲደረግበት ከቆየና በአመዛኙ ስምምነት ላይ ተደርሶበት ነበር፡፡ ቆየት ብሎ ግን ንግዱ ለብቻ፣ የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እንዲኖረው ለብቻው ረቂቅ ተዘጋጀ፡፡ ከዚያም በተመሳሳይ መንገድ ለብቻ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ እንዲኖረው ይደረጋል ተባለ፡፡ ይህም ኢንዱስትሪውን ለብቻ፣ የንግዱን ዘርፍ ደግሞ ለብቻው እንዲሆኑ የሚያደርግ ነውና እንዲህ ባለው አደረጃጀት ዙሪያ እንደ ዘርፍ ምክር ቤቶች መሪነትዎ ያለዎት ምልከታ ምንድነው? የግል አመለካከትዎስ?

አቶ አበባው፡- በመጀመሪያ ደረጃ ግልጽ መሆን የሚያስፈልገው ከአንድ ዓመት በፊት አሁን ያለውን አዋጅ ለማሻሻል የተሰናዳው ረቂቅ አዋጅ የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ በሚል የተዘጋጀ ነው፡፡ በነባሩ አዋጅ ንግድና ዘርፍ  በሚለው አደረጃጀት ዘርፍ በሚል የሚጠቀሰው ወይም ኢንዱስትሪውን የሚወክለው አካል የዘነጋ ነው ማለት ነው፡፡ በረቂቁ ውስጥ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ትኩረት ያልሰጠ ረቂቅ በመሆኑ በወቅቱ ተቃውሞዎችንን እንድናቀርብ አስገድዶናል፡፡ ያለንን ቅሬታ ለመንግሥት ጭምር አቅርበን ጥያቄያችን ተቀባይነት አግኝቶ ረቂቅ አዋጁ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት በሚል እንደገና ተስተካክሎ እንዲሰናዳ ተደረገ፡፡ እኛም ይህንን እንቀበላለን ብለን ተስማምተን ነበር፡፡ ከወራት በኋላ ግን የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ የሚለው ረቂቅ ፍትሕ የንግድና ሚኒስቴር ሲደርስ የዓላማ መደራረብ አለው በሚል እንደገና ተስተካከለ፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር መስመር አስምሩና ሥሩ ብሏልና ረቂቁ የንግድ ምክር ቤት ብቻ በሚል እንዲዘጋጅ ስለመወሰኑ ሰማን፡፡ ኢንዱስትሪውም የራሱ አዋጅ ይኖረዋል ተብሏል የሚል ቀጥተኛ ያልሆነ መረጃ መጣ፡፡ በዚህም ምክንያት ኢንዱስትሪ የሚለው ወጥቶ የንግድ ምክር ቤት በሚል ብቻ ረቂቁ እንዲያዘጋጅ ተደረገ፡፡ ይህ መሆኑን ካረጋገጥን በኋላ ኢንዱስትሪን ሚኒስቴር ስለጉዳዩ መረጃ ጠየቅን፣ አዎ የኢንዱስትሪ ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ረቂቅ እኛ እናዘጋጃለን አለን፡፡ በዚሁ መሠረት ኮሚቴ ተቋቁሞ ባለድርሻ አካላትንም በማሳተፍ ንዑስ ኮሚቴዎች ተደራጅተው የኢንዱስትሪ ምክር ቤት አዋጁ ረቂቅ እንዲሰናዳ ሆኗል፡፡ በእኛ በኩል ይህንን ካረጋገጥን በኋላ በዚህ አዋጅ ዙሪያ አባሎቻችንንና ባለድርሻ አካላትን ሁሉ በማወያየት ግብዓቶችን ወስደን ያገኘነውን ግብዓት ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አቅርበናል፡፡      

ሪፖርተር፡- ከአባሎቻችሁ ያገኛችሁት ምላሽ ምንድነው? ኢንዱስትሪው ምክር ቤት ለብቻው እንዲቋቋም የሚል ነው፡፡

አቶ አበባው፡- አዎ የኢንዱስትሪ ምክር ቤቱ መቋቋም የሚደገፍ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  የኢንዱስትሪ ምክር ቤት አዋጅ ረቂቅ መነሻ የሰጣችሁት እናንተ ናችሁ? በረቂቁ ላይ የነበራችሁ ተሳትፎስ?

አቶ አበባው፡- እኛ ግብዓት ነው የሰጠነው የረቂቁ መረጃ የመነጨው ከመንግሥት ነው፡፡ እኛ በውይይት አዳብረነዋል፡፡ የዛሬ ወር አካባቢም ባለድርሻ አካላት ረቂቅ አዋጁን እንዲያውቁት በሚል ውይይት ተደርጓል፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሉ አካላትም ስለረቂቁ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢንዱስትሪውንና ንግድ ዘርፉን ለሁለት በመክፈል ይወጣሉ የተባሉት አዋጆች ንግድ ምክር ቤቶችና የንግድ ኅብረተሰቡን ለሁለት የሚከፍል ነው በሚል የሚቃወሙ አሉ፡፡ ነባር የንግድ ምክር ቤቶች አመራሮች ሳይቀሩ እንዲህ ያለው አካሄድ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ዕርምጃው ንግድ ምክር ቤቶችን ያዳክማል በማለትም እየሞገቱ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የእርስዎ ምልከታ ምንድነው?

አቶ አበባው፡- አዎ ለሁለት የሚከፍል ነው፡፡ ነገር ግን ንግድና ኢንዱስትሪው አንድ ሆነው ባሉበት ሁኔታ እኮ ኢንዱስትሪው የተለየ ለውጥ አላገኘም፡፡ በግሌ እየተሰማኝ ያለው ነገር አደረጃጀቱን እንዲህ ባለው መንገድ ለማካሄድ መወሰኑ መንግሥት ለኢንዱስትሪው ትኩረት መስጠቱን ነው፡፡ ኢንዱስትሪው አውቶነመስ ሆኖ በራሱ መንገድ እንዲሄድ ማድረግ ጠቀሜታ እንዳለው ታምኗል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ሱቅ መክፈት በጣም ቀላል ነው፣ ብዙ አይከብድም፡፡ ኢንዱስትሪ ገንብቶ ሥራ ለማስጀመር ግን ሦሰትና አራት ዓመታት ሊፈጅ ይችላል፡፡ ይህም ፈጣን ከሆነ ማለት ነው፡፡ ለመነገድ ግን ሰኞ ፈቃድ አውጥተህ ማክሰኞ ወደ ሥራ ትገባለህ፡፡ ስለዚህ ሁለቱ ዘርፎች ከባህሪያቸው አንፃር የሚያስፈልጋቸውም አደረጃጀት የተለየ ቢሆን የሚጠበቅ ነው፡፡ አሁን ያለው አዋጅ ችግር አለበት፣ አዋጁ መቀየር አለበት፣ ስንል ተጨባጭ ምክንያቶችን ይዘን ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን ያለው አዋጅ መጠሪያው ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት የሚል ነው፡፡ እኛ ‹‹ዘርፍ›› የሚለው አገላለጽ ኢንዱስትሪውን የሚገልጽ ስላልሆነ መለወጥ አለበት በማለት ጭምር ነበር ስንሞግት የነበረው፡፡ ስለዚህ ኢንዱስትሪው ለብቻ እንዲወጣ መደረጉ አግባብ ነው፡፡ እስካሁን በነበረው አሠራር በዘርፉ (ኢንዱስትሪው) እና በንግዱ መካከል አብሮ ከመሥራት ይልቅ መገፋፋትንና አለመግባባትን ነው የፈጠረው፡፡ የንግድ ዘርፉ ለኢንዱስትሪው ምንድነው የሠራው? ካልክ ደግሞ ይህ ነው ብለህ የምትገልጸው ነገር የለም፡፡ ሠርቶም ከሆነ ደግሞ ንግድና ዘርፉ ተቀላቅሎ ስላለ መስመር ስለሌለ ውጤቱን ለመመዘን አይቻልም፡፡ ከዚህም ሌላ በባህሪም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ንግዱ ፈጣን ነው፡፡ ኢንዱስትሪውን ዶሚኔት አድርጎታል፡፡ ሌላው ቀርቶ እስከ ዛሬ ንግድ ምክር ቤታችንን የሚመሩ ፕሬዚዳንቶች ከኢንዱስትሪው የወጡ አይደሉም፡፡ ስለዚህ የኢንዱስትሪውን ችግሮች ሊቀርፉ አልቻሉም፡፡ እንዲህ እንዲህ ያሉ ነገሮች ጭምር ኢንዱስትሪው ያለበትን ችግር ሊታደግ አላስቻለም፡፡ የእኛ ትግል ደግሞ የኢንዱትሪ ዘርፉ ለብቻው ሆኖ ኢንዱስትሪያሊስት ሆነው፣ ትክክለኛ አምራች የሆነው አካል ይምራው ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የኢንዱስትሪው ዘርፍ የራሱን ምክር ቤት ለማቋቋም የተጀመረውን እንቅስቃሴ ትደግፋላችሁ ማለት ነው? ምክንያታችሁ ምንድነው?

አቶ አበባው፡- ይህንን የመንግሥት ሐሳብ መቶ በመቶ ነው የደገፍነው፡፡ ለመንግሥትም ለእኛም ጥሩ ነገር ነው፡፡ ለአገር ከፍተኛ ጠቀሜታ ይሰጣል፡፡ ከዚህም ባሻገር ኢንዱስትሪው ብዙ ውስብስብ ነገሮች ያሉበት ነው፡፡ ብዙ ነገር ችሎ ነው ያለው፡፡ የራሱ ምክር ቤት ኖሮት ራሱ የሚያወያይበትና የሚመካከርበት ተቋም ሲኖር ለመንግሥትም ይቀለዋል፡፡ አሉ የሚባሉ ችግሮችን ለማቅረብና መፍትሔ ለማምጣትም ቢሆን አሁን የታሰበው ነገር ውጤት ሊያመጣ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የጣራና የግድግዳ ግብር ምክንያት ከፍተኛ ጫና ያረፈው ኢንዱስትሪው ላይ ነው፡፡ ይህንን ጫና ተመልክቶ ማነው ሲናገርለት የነበረው? የጣራና የግድግዳ ግብር ችግር ያስከተለው መኖሪያ ቤና ሕንፃ  ላይ ብቻ ይወሰናል፡፡ በእነሱ ላይ ያጠነጠነ ሐሳብ ብቻ ሲሰጥ ነበር፡፡ ኢንዱስትሪውን ያስታወሰ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ለባለ ኢንዱስትሪው የሚሞግት ተቋም ያስፈልገዋል፡፡ ለብቻው የእሱ ተቋም ቢኖር ለባለኢንዱስትሪው ትልቅ ነገር ነው፡፡ እንዲህ ያለው አደረጃጀት መፈጠሩ ሌላው ጠቀሜታ በንግድና በዘርፍ (ኢንዱስትሪው) መካከል ያለውን ፍትጊያ ያስቀራል፡፡ ስላለንበት እናውቃለን፡፡ በሁለቱ መካከል መገፋፋትና መናናቅ ሁሉ አለ፡፡ ዘርፉ እንዲህ ነው፣ ንግዱ እንዲህ ነው፣ በመባባል ነው የቆዩት፡፡ በመሆኑም መስመር ይዘው የሚሠሩ ከሆነ ሁለቱንም ዘርፍ በየራሳቸው መንገድ ለመገምገም ውጤታቸውን ለመመዘን ዕድል ይሰጡታል፡፡ እኛ ኢንዱስትሪው ባለሀብቶችና እንደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አመራር ሆነን ስናየው፣ አዲሱ አሠራር ጠቃሚ በመሆኑ ሁሉም አባሎቻችን አዋጁ እስኪፀድቅ በጉጉት እየጠበቁ ነው፡፡     

ሪፖርተር፡- የእናንተ ምልከታ ይህ ቢሆንም፣ ንግድ ምክር ቤቶችን ይመሩ የነበሩ አንዳንድ ታዋቂ ሰዎች ሳይቀሩ ንግድና ዘርፉ ለሁለት ተከፍሎ መዋቀሩን አጠቃላይ የንግደ ምክር ቤቶችን ያዳክማል የሚል ሥጋታቸውን እያንፀባረቁ ነው፡፡ ይህ ሥጋት ትክክል ነው ብለው ያምናሉ?

አቶ አበባው፡- እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ላንሳ፡፡ አሁን ያለን ንግድ ምክር ቤት ጠንካራ ነው? አይደለም፡፡ ስለዚህ ምኑ ነው የሚዳከመው? አሁንም እኮ ደካማ ንግድ ምክር ቤቶች ናቸው ያሉን፡፡ ደካማ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ምናልባትም ሁለት የማይገናኙ አካላት አንድ ላይ ሆነው በግድ እንዲሠሩ በመደረጉ ነው፡፡ ይህንን ሥጋት አልጋራም፡፡ በየራሳችን እንሥራ የምንልበት ምክንያት በመስመራችን መመዘን ስላለብን ጭምር ነው፡፡ ይህ ከሆነ በየዘርፋችን ጠንካራ ተቋም ሊኖረን ይችላል የሚለውንም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ አዎ አሁን ላይ ያሉን ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ጠንካራ ቢሆኑ ሥጋቱ ሊያስኬድ ይችላል፡፡ የትኛው ንግድ ምክር ቤት ጠንካራ ሆኖ ነው የዚያን ያህል የምንሠጋው? በኢትዮጵያ መሠረታዊ የሚባሉ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አሉ፡፡ እንደ ምክር ቤት በዚህ ረገድ መንግሥትን ሳፖርት ማድረግ ነበረብን፡፡ ግን እያደረግን ነው ወይ? አንዳንዱ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያለው ነው፡፡ አንዳንዱ ኢንዱስትሪው ሳይኖረው ኢንዱስትሪ እየመራ ያለ ነው፡፡ ስለዚህ ጠንካራ ንግድ ምክር ቤት ኖሮን ቢሆን የሚባለው ሐብሳ ሊያስኬድ ይችላል፡፡ ጠንካራ ንግድ ምክር ቤት ስለሌለን ጠንካራ እናድርገው መባል አለበት፡፡ አሁን በታሰበው አደረጃጀት እኮ በፉክክር የተሻሉ ተቋማትን መፍጠር የሚቻልበትም ዕድል ሊኖር እንደሚችል ቢታሰብ ጥሩ ነው፡፡ አዋጁ መስተካከል አለበት፡፡ ክፍተቶች አሉበት፡፡ አዋጁ ሲስተካከል ግን ሌላ ራስ ምታት የሚሆኑ ነገሮች ሊኖሩት አይገባም፡፡ ይህ ከሆነ ዋጋ የለውም፡፡ መንግሥት እንደፈለገ ሊሠራው ከፈለገም ዋጋ የለውም፡፡ ግለሰቦች እንደ ፈለጉት የሚያደርጉት ከሆነ ዋጋ የለውም፡፡ ለሁሉም ዘርፍ ጠቃሚ አዋጅ ሊኖረው የሚገባው፡፡ አሁን እንኳን ኢንዱስትሪው ለብቻው ይወጣል ሲባል ያልተመቻቸው ብዙ አሉ፡፡ እኔ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቦርድ አባል ነኝና እዚህ ውስጥ እንኳን ብዙዎቹ የንግድና ምክር ቤት በሚል አዋጁ እንዲወጣ ይፈልጋሉ፡፡ እነሱ ሐሳብ ይህ ከሆነ እኛ ደግሞ ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ይኑረን ስንል ለምንድነው የምንከለከለው? የእኛ መዘጋጀት ለምን ለድክመት ምክንያት ይሆናል? እኔ የራሴ ምክር ቤት ይኑረኝ ስል ለምን ልታዳክም ነው ይባላል? እንዲህ ያሉ ነገሮች መቅረት አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የአምራች ኢንዱስትሪው ምክር ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጁ አሁን ምን ደረጃ ላይ ነው?

አቶ አበባው፡-      ረቂቁ አሁን ሚኒስትሮች ምክር ቤት ደርሷል፡፡ ቅድም ባልኩህ አግባብ አባሎቻችንና ባለድርሻ አካላትን አወያየተን የሕግ ባለሙያዎች አስተያየት የእኛ የምክር ቤት አባላት የሚሆኑትም 100 በመቶ ኢንዱስትሪያሊስቶች ናቸው፡፡  

ሪፖርተር፡- ኢንዱስትሪያሊስቶች ተብለው የሚለዩት የትኞቹ ናቸው? መሥፈርት አለው ወይ? አንድ የብረት መበየጃ የያዘ ድርጅት የኢንዲስትሪ ባለቤት ተብሎ ሊታቀፍ ይችላል? አሁን ባለው አደረጃጀት ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ምን ያህል አባሎች አላቸው? የዘርፉ ለብቻ የንግዱ ለብቻ ምን ያህል ይሆናል?

አቶ አበባው፡- አዋጁ ላይ ሁሉ ነገር ላይጠቀስ ይችላል፡፡ መሠረታዊ ጉዳዮችን ይዞ ነው የሚቀረፀው፡፡ አዋጁ ሁሉ ነገር ጨርሶ ይወጣል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ አንድ አዋጅ ጥንቅቅ ብሎ ቢወጣ ኖሮ አሁን እኛ አዋጅ ይሻሻልልን አንልም ነበር፡፡ የኢንዱስትሪ አዋጅም ኖሮን አያውቅም፡፡ ስለዚህ ‹ዋናው አዋጅ ከወጣ በኋላ አፈጻጸሙን በተመለከተ የጠራ መረጃ ለመስጠት ያስቸግራል፡፡ በመመርያ ሊያብራሩ የሚችሉ ነገሮች ይኖሩታል፡፡ ኢንዱስትሪ የምንለው ማንንን ነው? ከተባለ ም በንግድ ሕጉ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ኢንዱስትሪ የሚባለው አምራቹ ነው፡፡ አንደኛው በቀን አሥር ወንበሮች ሌላው ደግሞ በቀን 100 ወንበሮች ሊያመርት ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር ከታየ ሁለቱም አምራች ናቸው፡፡ የአባላት ቁጥርን በተመለከተ እንዲህ ያሉ ነገሮች ናቸው ፓራዶክስ የሚሆንብህ፡፡ አንደኛው ቁጥሩ ፍላክቹዌት ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ ጉባዔዎቹ ሲያካሂዱ የአባላቶቻቸውን ቁጥር ላኩ ይባላል፡፡ መረጃው ሲታይ አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ዝቅ ይላል፡፡ ምክንያቱም የንግድ ፈቃድ የሚመልስ አለ፡፡ አዲስ የሚገባ አለ፡፡ ስለዚህ ወጣ ገባ ነው፡፡ አጠቃላይ የአባላቱ ቁጥር አንዴ 300 ሺሕ ሌላ ጊዜ 500 ሺሕ ይባላል፡፡ ዘንድሮ ባለው መረጃ አንዱ ክልል ብዙ አባላቶች አለኝ ብሎ ያስመዘገበ አለ፡፡ እንደ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ግን በአገር አቀፍ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ውስጥ 21 መቀመጫዎች አሉት፡፡ ይህ ማለት አገር አቀፍ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ኢንዱስትሪውን እየመራ ያለው የመቀመጫ ብዛት አነስተኛ ነው፡፡ ለውሳኔ እንኳን የሚበቃ አቅም የለውም፡፡ ነገሩን ጠቅለል ስናደርገው እስካሁን የነበረው አሠራር ብዙ ማሻሻያዎች የሚያስፈልጉት መሆኑን ነው፡፡ ከጊዜው ጋር የተራመደ አደረጃጀትና አሠራር ያስፈልገናል፡፡ አሁን ከሚዲያ የዘለለ ነገር አድርገናል ወይ? ኢንዱስትሪዎችን አበረታትተን እናውቃለን ወይ? መንግሥት ላይ ጣታችንን ከመቀሰር ውጪ ተቋማትን የተቋቋመለትን ዓላማ እያስተገበሩ ነው ወይ? አብዛኛው ኢንዱስትሪ እኮ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምን እንደሆነ አያውቁም፡፡ ይህ ማለት ታች ድረስ አደረጃጅት የለውም ማለት ነው፡፡ አየር ላይ ነው ማለት ነው፡፡ በአዲሱ አዋጅ እንዲህ ያለው ነገር እየተስተካከለ ከመጣ ተጠያቂነቱም ያመጣል፡፡ ሌላው ዓለም የምናያቸውንም አሠራሮች ለመተግበር ያስችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ሁለቱ ዘርፎች በተነጣጠለ ምክር ቤቶቹ እንዲዋቀሩ መደረጉ ችግር ሊያስከትል ይችላል ተብሎ የሚጠቀሰው ሌላው ጉዳይ ከአባልነት ጋር ተያያዘ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው ላይ የተሰማራ ባለሀብት አምራችም የመሆኑን ያህል ነጋዴም ነው፡፡ ስለዚህ አባል የሚሆነው ንግዱ ምክር ቤት ላይ ነው ወይስ ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ላይ ነው የሚለው ጉዳይ አዋጁ ሲተገበሩ አፈጸጸም ላይ ችግር ይፈጥራል የሚል መከራከሪያም እየተነሳ ነውና በእርግጥ ይህ ሥጋት ተገቢ አይደለም?

አቶ አበባየሁ፡- አፈጻጸም ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል የምንለውን ነገር ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት በመመርያ የሚስተካከል ነው፡፡ እውነት ነው አንድ ኢንዱትሪያሊት አምራችም ነው ነጋዴም ነው፡፡ ሁለቱንም አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ አንድ ነጋዴ ግን አምራች አይደለም፡፡ በንግድና ዘርፍ ውስጥ ሁለቱንም አጣምረን ይዘን መቆየታችን ድምፃችን እንዳይሰማ አድርጎታል፡፡ እኛ የንግድ ምክር ቤቱም አባል ልንሆን እችላለን፡፡ ምክንያቱም አምራችም ነጋዴም ስለሆንን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ስለሆንን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህም ጉዳይ ተቃርኖ የለውም፡፡ የአባላቱን ጉዳይ የሚመለከተውም ጉዳይ ችግር የለውም፡፡ የእኛ ዋና ጉዳይ ግን ኢንዱስትሪው በባለኢንዱስትሪዎች ይመራ የሚል ነው፡፡.   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች