Sunday, April 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው የዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ በሰላምና በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ነው፡፡ ዜጎች በፈለጉበት ቦታ የመንቀሳቀስ፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብታቸው በሕግ የተረጋገጠ ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ በየቦታው ራሳቸውን ከሕግ በላይ ባደረጉ ታጣቂዎችና አጋቾች ምክንያት ከፍተኛ ችግር ተፈጥሯል፡፡ ለእዚህ ችግር መቀረፍ ከማንም በላይ መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነት ሲኖርበት፣ በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚሳተፉ በሙሉ ይመለከታቸዋል፡፡ በዜጎች ሰላምና ደኅንነት ላይ አደጋ የፈጠረው ችግር ከበስተጀርባው የተለያዩ ፍላጎቶችን ያነገበ በመሆኑ፣ መንግሥትም ሆነ ሌሎች አካላት ችግሩ በፍጥነት ተቀርፎ ሰላም እንዲሰፍን የሚፈለግባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ ማንኛውም ዓይነት ቅሬታም ሆነ ቅራኔ መፍትሔ ማግኘት ያለበት በሰላማዊ መንገድ እንጂ፣ አሁን እንደሚታየው አገርን የግጭት አውድማ በማድረግ መሆን እንደሌለበት መተማመን ያስፈልጋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ መቀመጫቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ያደረጉ የተለያዩ አገሮች ኤምባሲዎች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አካላት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተዋካዮችና በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣ ብለው መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ምክንያት ደስተኞች አይደሉም፡፡ ይህ መከፋት ውሎ ሲያድር ሌሎች ሰበቦች እየተጨማመሩበት አማራጮችን ማየት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ሰላም የሌለበት አገር ውስጥ መሥራት አልቻልንም ብለው ወደ ሌሎች አገሮች ማማተር ቢጀምሩ ጉዳቱ ለአገር እንደሆነ ነጋሪ አያስፈልግም፡፡ ቱሪስትም ሆነ በሥራ ምክንያት ኢትዮጵያ የሚመጣ የማንኛውም አገር ዜጋ ከምንም ነገር በፊት የሚያሳስበው ደኅንነቱ መጠበቁ ነው፡፡ ሰላም የሌለበት አገር ውስጥ ማንም መምጣትም ሆነ መኖር ስለማይፈልግ ሌሎች አማራጮችን ቢፈልግ አይደንቅም፡፡ አሁን በውጭ ዜጎች ላይ የሚስተዋለው ሁኔታ ይህንን ሥጋት ነው የሚያንፀባርቀው፡፡ እንኳንስ ቱሪስቶችንና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ መቀመጫቸውን እዚህ ያደረጉትን ማሳመን ካቃተ፣ ኢትዮጵያ ምን ያህል ጉዳት ሊያጋጥማት እንደሚችል ለመረዳት ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡

የአገር ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝነት ሊጠበቅ የሚችለው ለሕግ የበላይነት መከበር ቁርጠኝነት ሲኖር ነው፡፡ መንግሥት ሕግ ሲያስከብር ራሱ በአርዓያነት አክባሪነቱን ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ ሕግ በማስከበር ስም የመንግሥት ሹማምንትና የፀጥታ አስከባሪዎች የሚወስዱት ዕርምጃ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል፡፡ ብዙ ጊዜ በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ቅሬታና ቁጣ የሚቀሰቅሱ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ዝም ስለሚባል፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ሊኖር የሚገባው መተማመን ይጠፋል፡፡ ጥቂት ግለሰቦችና ግብረ አበሮቻቸው ራሳቸውን ከሕግ በላይ አድርገው ሕገወጥ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ ዝምታ ሲበዛ፣ ሕግና ሥርዓት ከሌለ ለምን ራሳችንን ጉዳት ላይ እንጥላለን የሚሉ አማፂያን እየበረከቱ ችግሮች ከቁጥጥር ውጪ ይሆናሉ፡፡ በብዙ አካባቢዎች ግጭቶች እንዲበራከቱ፣ ዕልቂትና ውድመት እንዲስፋፋና የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት እንዲጣስ የሚደረገው በአመዛኙ ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት እንደሆነ ማስተባባል አይቻልም፡፡ በቀላል ንግግርና ውይይት መፍትሔ ሊያገኙ የሚገባቸው ችግሮች ችላ በመባላቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ ነፃነት ተገፏል፡፡ በዚህ ሁኔታ መቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይም ተደርሷል፡፡

ሌላው ለዜጎችም ሆነ ለውጭ ሰዎች በጣም ሥጋት የፈጠረው ጉዳይ የአጋቾች በየቦታው መብዛት ነው፡፡ ትጥቅ ያነገቡ አጋቾች ዜጎችን አግተው ከአቅማቸው በላይ የሆነ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ይጠይቃሉ፡፡ ክፍያው ካልተፈጸመላቸው ደግሞ ንፁኃንን ይገድላሉ፡፡ እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ እጅግ በጣም ከፍተኛ መጠን ያለው የፀጥታ ኃይል (የአካባቢ ሚሊሻ፣ የከተማ ፖሊስ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት፣ ወዘተ) ከረቀቁ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ጋር ሥምሪት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የዚህ ኃይል ተቀዳሚ ተግባርም ዜጎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ቀድሞ መከላከል ሲሆን፣ ምናልባት ችግር ሲያጋጥም በፍጥነት የመፍትሔ ዕርምጃዎችን ወስዶ ዕፎይታ መስጠት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አስተማማኝ ኃይል ባለበት አገር ውስጥ አጋቾች በዜጎች ላይ የደቀኑት አደጋ ማቆሚያ ማጣቱ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ነገር ግን መንግሥት ከሕዝብ ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ፈቃደኛ ቢሆን ኖሮ አጋቾች የአገር ችግር አይሆኑም ነበር፡፡ መንግሥት ውስጡን አጥርቶ ከሕዝብ ጋር ቢቀራረብ አገር የሕገወጦች መፈንጫ አትሆንም፡፡

ለአገር ሰላምና ደኅንነት መከበር ዋናው ባለቤቱ ሕዝብ በመሆኑ፣ መንግሥትን የሚመራው ብልፅግና ፓርቲም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች አሁን ያለው አሳሳቢ ሁኔታ እንዲቀየር ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የመጀመሪያው ጉዳይ የሚያጋጥሙ ችግሮች በትጥቅ ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ንግግር ይጀምሩ፡፡ ንግግር ለማድረግ በርካታ እንቅፋቶች እንዳሉ ቢታወቅም፣ ራስን ከአገርና ከሕዝብ በታች ዝቅ አድርጎ ለመቀራረብ መሞከር ተመራጭ ይሁን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን የተደረጉ የእርስ በርስ ትንቅንቆች ያተረፉት ቢኖር የዜጎች ዕልቂት፣ መፈናቀል፣ መራብ፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት፣ የአገር አንጡራ ሀብት ውድመትና ተስፋ መቁረጥ ናቸው፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት ብቻ በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በትግራይ፣ በአማራና በሌሎች አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶችና ጦርነቶች የዘመኑን ትውልድ በታሪክ ፊት የሚያሳፍሩ ዕልቂቶችና ወድመቶች ደርሰዋል፡፡ ይህ ሁሉ ጥፋት አልበቃ ብሎ በአገር ህልውና ላይ አደጋ ተጋርጧል፡፡ ችግሩን በጋራ ተገንዝቦ መፍትሔ አለመፈለግ ከባድ ዋጋ ያስከፍላል፡፡

ዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ በሰላም መንቀሳቀስ ሲሳናቸው በገጠሪቱ የአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተመረቱ ምርቶች እጥረት ይፈጠራል፡፡ ምርቶችን ወደ ገበያ ማውጣት ሳይቻል ሲቀር አርሶ አደሮች ገቢ ስለሚያጡ ለሚቀጥለው ምርት መዘጋጀት ይሳናቸዋል፡፡ በከተሞች የሚኖሩ ዜጎች በምርቶች አቅርቦት እጥረት በሚከሰት የዋጋ ንረት ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ ሰላም ሲጠፋ የሰዎችና የምርቶች እንቅስቃሴ ስለሚገደብ ዜጎች ለችግር ይጋለጣሉ፡፡ የምግብና የሌሎች መሠረታዊ አቅርቦቶች ዋጋ ንረት ከሚችሉት በላይ ይሆንባቸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ሥፍራዎች በሚካሄዱ ጦርነቶች ምክንያት በነዳጅ፣ በምግብና በሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ላይ ከሚታየው ጭማሪ ባሻገር፣ በአገር ውስጥ ያለው የሰላም ዕጦት ዜጎችን ለከፍተኛ ፈተና ዳርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በርካታ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች ታግተው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እንዲከፍሉ ሲገደዱ፣ ገንዘቡን ማግኘት ያልቻሉ ደግሞ ተገድለዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አስነዋሪ ድርጊት ሲባባስ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ሊቆሙ እንደሚችሉ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል!

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ (ክፍል አንድ)

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...

የአገሪቱ ባንኮች የመጭበርበር ተጋላጭነት እየጨመረ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ2 ቢሊዮን ብር መጭበርበሩን ገልጿል ቀሲስ በላይ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

እንደገና ያገረሸው ግጭት መፍትሔ ይፈለግለት!

ሰሞኑን በራያና አካባቢው እንደገና ያገረሸው ግጭት አስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጠው፣ አድማሱ ሰፍቶ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስ አያጠራጥርም፡፡ በራያ በኩል የተጀመረው ትንኮሳ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተዛምቶ ተጨማሪ...

ስልታዊ መፍትሔን የሚሻው የኪነ ጥበቡ ዘርፍ

የኪነ ጥበቡ ዘርፍ በተለይም ፊልምና ሙዚቃ በውስብስብ ችግሮች ውስጥ እያለፈ ይገኛል፡፡ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ሲስተም በአግባቡ አልተበጁለትም፡፡ ስለሆነም ይህ ችግር ከመሠረቱ እየተፈታና እየተቀረፈ ካልሄደ ከዓመት...

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...