Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገደብ ከጣለ ሰባተኛ ወሩን ይዟል፡፡ የብሔራዊ ባንክ የጣለው ገደብ የአገሪቱ ንግድ ባንኮች የብድር መጠን ከቀደመው ዓመት ካበደሩት ከ14 በመቶ በላይ መብለጥ እንደማይችል የሚደነግግ ነው፡፡ መመርያው ባንኮች ሊያበድሩ ይችሉ የነበረውን ያህል እንዳያበድሩ ስለሚገድባቸው ጫና እንደሚያሳርፍባቸው ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ 

ዓመታዊ የብድር ምጣኔያቸው አነስተኛ የሆነ ባንኮች በተለይ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ተቋቁመው ወደ ሥራ የገቡ አዳዲስ ባንኮች በዚህ መመርያ በእጅጉ እንደሚጎዱ በመጥቀስ ብሔራዊ ባንክ በልዩነት እንዲያስተናግዳቸው እስከ መጠየቅ ደርሰዋል፡፡ መመርያው እነሱ ላይ የሚፈጥረውን የተለየ ጫና ብሔራዊ ባንክ ከግምት ውስጥ አስገብቶ የኢትዮጵያ ማሻሻያ እንዲያደርግላቸው አቤቱታ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል፡፡ የባንክ ኢንዱስትሪውን በቅርብ ዓመታት ውስጥ የተቀላቀሉት እነዚህ ባንኮች ከላይ የተመለከተውን ጥያቄ በጋራ ሆነው ለብሔራዊ ባንክ ቢያቀርቡም፣ ጥያቄያቸው ምላሽ ሳያገኝ የበጀት ዓመቱ ተጋምሷል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመሪያ የባንኮችን የብድር መጠን በመገደብ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ መጠን መቀነስ፣ በዚህም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰውን የሸቀጦች የዋጋ ዕድገት ባለበት ለማርጋት፣ ብሎም ለማውረድ የተለመ ነው። የመመሪያው መሠረታዊ ዓላማ ይህ ቢሆንም፣ በተለይ በባንኮች ትርፋማነት ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ተሠግቶ ነበር።

የባንኮችን እንቅስቃሴና ጥቅም ይነካል የተባለው መመርያ ሥራ ላይ በዋለ በመጀመርያው የ2016 ግማሽ ዓመት የባንኮች ጥቅል አፈጻጸም ሲታይ ግን ባንኮቹ አሁንም በትርፋማነት መዝለቃቸውን የሚጠቁም ነው፡፡ ሪፖርተር የተመለከተው ጥቅል መረጃ የባንኮቹ የተቀማጭ ገንዘብ መጠንም ሆነ የሰጡት ብድር እንደቀደሙት ዓመታት ሁሉ ዕድገት ላይ መሆኑን ይጠቁማል።

የ2016 ግማሽ ዓመት የባንኮች አፈጻጸምን የሚያመለክቱ መረጃዎች ሁሉም በሥራ ላይ ያሉ ባንኮች ከ124.2 ቢሊዮን ብር በላይ ብር አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ችለዋል፡፡ 

አዲስ የሰጡት ብድርም ከቀዳሚው ዓመት ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የትርፍ ምጣኔያቸውም ቢሆን በድምር ሲታይ ከቀዳሚው ዓመት ብልጫ እንዳለው ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

ይሁን እንጂ ባንኮቹ ቀደም ባሉት ዓመታት ሲያስመዘግቡ የነበረውን የዕድገት ምጣኔ ማስቀጠል እንዳልቻሉ የተመለከትናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ። 

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፋይናንስ ተቋማት ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች ባንኮቹ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ዕድገት ያስመዘገቡ ቢሆንም ቀደም ባሉት ዓመታት ያስመዘግቡ የነበረውን የዕድገት ምጣኔ ማስቀጠል እንዳልቻሉ ግን ከሥራ አፈጻጸማቸው መረዳት ይቻላል ብለዋል። በዋናነትም የብሔራዊ ባንክ መመሪያ በባንኮቹ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንዳሳደረ ጠቅሰዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ አገር ውስጥ ባሉ ተግዳሮቶች በኢኮኖሚው ላይ እያሳደሩ ያሉት ተፅዕኖዎች በተለያዩ ቢዝነሶች ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ በኢትዮጵያ በባንኮች ላይ ሳይንፀባረቅ የዘለቀ ቢሆንም አሁን ግን ባንኮችንም ሊነካ ይችላል የሚል አስተያየቶች እንዲሰነዘሩ እያደረገም ነው፡፡ በ2016 ግማሽ የሒሳብ ዓመት የባንኮች አፈጻጸምም ይህንኑ ሊጠቁም ይችላል ያሉት ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የባንክ ባለሙያ በግማሽ ዓመቱ የሁሉም ባንኮች የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም በጥቅሉ ሲታይ በብድርና በተቀማጭ ገንዘብ መጠን እንዲሁም በትርፍ ምጣኔ ዕድገት የሚታይበት ቢሆንም፣ ይህ ዕድገት እስከዛሬ ባንኮቹ ሲያስመዘግቡ ከነበረው የዕድገት ደረጃ ዝቅ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት የአገሪቱ ባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በዓመት በአማካይ ከ30 በመቶ በላይ እያደገ እንደነበር ለማሳያ የጠቀሱት እኚሁ የባንክ ባለሙያ፣ በዘንድሮው ግማሽ ዓመት ባንኮቹ ያስመዘገቡት የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት ግን ከዚህ ያነሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ ባንኮች ባልተለመደ ሁኔታ የተቀማጭ ገንዘባቸው ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ቀንሶ የመገኘቱ አንድ ምክንያት ከዚሁ የብሔራዊ ባንክ መመርያ ጋር የተሳሰረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከስድስት ወሩ የባንኮች አፈጻጸም መረዳት የሚቻለውም በግማሽ ዓመቱ ውስጥ ወደ አምስት የሚሆኑ ባንኮች ባልተለመደ ሁኔታ የተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸው ቀንሶ መታየቱ በራሱ በግማሽ ዓመቱ የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት በቀድሞው የዕድገት ምጣኔ ልክ አለማደጉን ነው፡፡ 

ብዙዎቹ ባንኮች በግማሽ ዓመቱ የተለሙትን ለማሳካት አለመቻለቸውና የትርፍ ምጣኔያቸው ላይም ተፅዕኖ ያሳረፈባቸው ባንኮች እንዳሉ ማመላከቱን እነዚሁ ያነጋገርናቸው የፋይናንስ ባለሙያዎች ጠቁመዋል፡፡ 

ስለዚህ በ2016 ግማሽ ዓመት የተመዘገበው የባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ፣ የብድር መጠንና የትርፍ ምጣኔ ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ዕድገት ማሳየቱ ባይታበልም የብድር ገደቡ ባይኖር ኖሮ ከዚህ በላይ ይገኝ የነበረውን ዕድገት ይዞታል ይላሉ፡፡ በተለይ መመርያው ያለው ተፅዕኖ ያሳርፍባቸዋል የተባሉት አዳዲስ ባንኮች ላይ ክፍተቱ ጎልቶ ታይቷል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የብድር ገደቡ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ መንግሥትም የፈለገው ይህንኑ እንደሆነ የጠቀሱት የባንክ ባለሙያው በተለይ የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገቱ ከዚህ ቀደም ሲያሳይ በነበረው የዕድገት ምጣኔ ልክ ስላለመሆኑ በመግለጽ የዘንድሮው የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት አንዳንድ ባንኮች የተቀማጭ ዕድገት ከፍ ያደረገው በመሆኑ እንጂ አጠቃላይ የዕድገት ምጣኔው ከዚህም በታች ሊቀንስ ይችል ነበር ይላሉ፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ለአራት ተከታታይ ዓመታት የአገሪቱ ባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ዕድገት በአማካይ ከ30 በመቶ እያደገ የመጣ ሲሆን የግማሽ ዓመቱ ዕድገት ግን ከዚህ ያነሰና ከ20 በመቶ ያልበለጠ መሆኑንም በመጥቀስ ይህ ያልተለመደ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡ 

‹‹ከተወሰኑት ባንኮች ውጪ አብዛኛዎቹ ባንኮች ያሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ አጥጋቢ የሚባል አይደለም›› የሚሉት ባለሙያው እንዲሁም አንዳንዶቹ የተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸው ስለማነሱም በማስረዳት እስካሁን በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሁሉም ባንኮች የቀማጭ ገንዘብ መጠናቸው ይጨምራል እንጂ ቀንሶ የታየበት ጊዜ ያለመኖሩን አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የሁሉም ባንኮች የተቀማጭ ዕድገት ዩኒፎርም ሆኖ ይታይ እንደነበርም በመጥቀስም በዘንድሮ ግማሽ ዓመት ላይ ግን በተወሰኑ ባንኮች ላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን መቀነስ ሊታይ የቻለበት ዋነኛ ምክንያት ከብሔራዊ ባንክ የ14 በመቶ የብድር ገደብ ጋር ሊያያዝ እንደሚችልም ያምናሉ፡፡

ብሔራዊ ባንክ በባንኮች ላይ የጣለው የ14 በመቶው የብድር ገደብ ባይኖር ትልልቅ የሚባሉትም ሆነ አዲስ ባንኮች ያሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ ከዚህም በላይ ሊሆን ይችል እንደነበር ጠቁመው የብድር ገደቡ ጫና በግልጽ እየታየ ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡  

አሁን እየታየ ያለው ሁኔታ ደግሞ በሁለተኛው ግማሽ የበጀት ዓመት ላይ በዚሀ ከቀጠለ የተወሰኑ ባንኮች የበለጠ ሊቸገሩ ይችላሉ፡፡ የትርፍ ግባቸው ብቻ ሳይሆን ሌሎች አፈጻጸማቸው ላይም ተግዳሮት ሊፈጥር እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

የኢኮኖሚ ባለሙያው አወት ተክኤ ግን ለባንኮች የተቀማጭ ገንዘብና የብድር ዕድገት መቀነስ ዋነኛ ምክንያቱ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ብሎ መደምደም እንደማይቻል ያስረዳሉ።

አቶ አወት እንደሚሉት የብድር ገደብ የተጣለበት ምክንያት በቀጥታ በባንኮች ላይ የራሱ ተፅዕኖ እንደሚያመጣ የሚታወቅና ተጠባቂ ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ በተፈለገው ደረጃ ማደግ ያልቻለው በሌሎች በተለይም ከፀጥታ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።

የፀጥታ ችግርና መረጋጋት ከሌለ ሰዎች ገንዘብ ከባንክ ሊያወጡ የሚችሉ መሆኑም የተቀማጭ ገንዘብ በሚፈለገው ደረጃ ላለማደጉ ምክንያት መሆኑን በቀዳሚነት አስቀምጠዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ደንበኞች ከባንክ ሒሳባቸው በቀን ከ50 ሺሕ ብር በላይ ማውጣት እንዳይችሉ ገደብ መጣሉም የራሱ ተፅዕኖ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ ውስጥ ያለው የፀጥታ ሁኔታ እንቅስቃሴን የሚገድብ ሆኖ ሳለ በዚህ ላይ በቀን ከ50 ሺሕ ብር በላይ ገንዘብ ከባንክ ማውጣት እንዳይቻል መደረጉ አስቀማጮች ገንዘባቸውን በእጅ በጥሬ ገንዘብ እንዲይዙ ያበረታታል፡፡ ይህም በባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳርፍ ገልጸዋል።

የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የሰዎች እንቅስቃሴ የተገደበ ስለሚሆን ወደ ባንክ ሊመጣ የሚችለው የገንዘብ መጠንም በዚሁ ልክ ያዝ ሊያደርገው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ 

ከሁሉም በላይ ግን አሁን ያለውም የዋጋ ንረት የባንኮች የቁጠባ መጠን በተፈለገው ልክ እንዳያድግ የሚያደርግ መሆኑንም አቶ አወት ገልጸዋል፡፡ ይህንንም ሲያብራሩ በምሳሌነት የጠቀሱት ደመወዝተኞችን ነው፡፡ ‹‹የዋጋ ንረት መኖር የደመወዝተኞችን የመቆጠብ አቅም ይቀንሳል፡፡ ሊያስቀምጡ ይችሉ የነበረውን የዋጋ ንረቱ ለሚፈጠረው ጭማሪ ስለሚያውሉት የመቆጠብ አቅማቸው ይሸረሸራል። የዚህ ውጤትም የባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በሚፈለገው ደረጃ እንዳያድግ ያደርጋል። በመሆኑም ይህም በባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ላይ ለታየው ቅናሽ አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል፤›› ገልጸዋል፡፡ 

አንዳንዴ ደግሞ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ ወጪ የሚጨምርባቸው ወቅቶች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ አወት እንዲህ ያሉት ጉዳዮችም ከባንኮች ቁጠባ መጠን መቀነስ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ጠቁመዋል። ለዚህ የወጪ መጨመር ከጠቀሷቸው ምክንያቶች መካከልም አንዱና ዋነኛው የሕገወጥ ንግድ እንቅስቃሴን ነው። ሕገወጥ የንግድ በሚጨምርበት ወቅት በባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ ድርሻ ላይ ወይም ባንኮች በሚሰበስቡት የተቀማጭ መጠን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንሚኖረው አስረድተዋል።

በሌላ በኩል፣ ብሔራዊ ባንክ ተግባራዊ ያደረገው የገንዘብ ፖሊሲ ወይም በባንኮች የብድር መጠን ላይ የጣለው ገደብ ኢኮኖሚ ውስጥ አዎንታዊ የዋጋ ለውጥ እያስከተለ እንደሆነ ከባለሙያዎቹ ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

በተለይ በገበያ ውስጥ ያልተቋረጠ የዋጋ ዕድገት ሲታይባቸው የነበሩ የመሬት ይዞታና በሪል ስቴት ዘርፉ የሚገነቡ መኖሪያ ቤቶች ዋጋ ባለፉት ወራት ቅናሽ እያሳዩ መምጣታቸው በቀጥታ ከብድር ገደቡ ጋር የተያያዘ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በተለይ በዚሁ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያው የቤቶች የቦታና የመሳሰሉት ንብረቶች ዋጋ መቀነስ በቀጥታ ከዚህ የብድር ገደብ ጋር የሚገናኝ መሆኑን ነው፡፡ ይህ የሚጠበቅ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ አንድ መኖሪያ ቤት 50 እና 60 ሚሊዮን ብር በደረሰበት ወቅት ያለ ባንክ ብድር ይህንን ያህል ገንዘብ አውጥቶ የሚገዛ ማግኘት የማይታሰብ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

አሁን ባለው የብድር ገደብ ውስጥ ባንኮች የረዥም ጊዜ ብድር ለመስጠት የሚቸገሩ በመሆኑ የሪል ስቴት ዘርፉ ቤት የሚገዛው አጥቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የመኖሪያ ቤቶች የሽያጭ ዋጋ እንዲቀንስ ማድረጉን ባለሙያው ገልጸዋል። ይህም ብሔራዊ ባንክ ያወጣው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማነት ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል። ከዚህ የገንዘብ ፖሊሲ ዕርምጃ የሚጠበቀው አንድ ነገር የንብረት ዋጋዎች እንዲቀንሱ ማድረግ በመሆኑ በዚህ ረገድ ፖሊሲው ውጤት እንደሆነ ገልጸዋል።

አቶ አወት በበኩላቸው አሁን ለታየው የቤትና መሰል ንብረቶች ዋጋ መቀነስ ከ14 በመቶው የብድር ገደብ ጋር ሊያያዝ ቢችልም ቀድሞም ቢሆን በተለይ የቤትና መኪና ዋጋ ያልተገባ ዋጋ የተሰጣቸው እንደነበር ግን ሊሰመርበት ይገባል ይላሉ፡፡ 

እነዚህ ንብረቶች ያልተገባ ዋጋ ሲሰጣቸው ለኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ሁኔታው በዚያው እንዲቀጥል ከተፈቀደ ለአገራዊ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ሊሆን እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህን ንብረቶች ባልተገባቸው ዋጋ ብዙ ሰዎች ብድርም ጭምር በመውሰድ ይገባቸው ስለነበር ያልተገባ ዋጋ እንዲገነባ አድርጎ ቆይቷል፡፡ ስለዚህ አሁንም የታየው የዋጋ ቅናሽ የታየው ቀድሞም ያልተገባ ዋጋ ተሰጥቷቸው የቆዩ በመሆናቸው አሁን ብድር ባንኮች ላይ የተጣለው የብድር ገደብ መመርያ ሲቀዛቀዝና ለእነዚህ ንብረቶች የሚሰጠው ብድር ያዝ ሲደረግ ዋጋቸው መቀነሱ የሚጠበቅ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ 

‹‹በአሁኑ ወቅት መንግሥት ጠበቅ ያለ ሞኒተሪ ፖሊሲ መከተል ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ የባንኮች መገደብም የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የገንዘብ ፖሊሲው ገንዘብ የበለጠ ወደ ባንክ እንዲሰበሰብ የሚያደርግና ከባንክ የሚወጣውም ገንዘብ እንዲመጠን የሚያደርግ በመሆኑ ብድሮችን አያበረታታም›› በማለትም አብዛኛው ባንኮች የሚሰጡት ብድር ለዋና ዋና ደንበኞቻቸው ስለሚያደርጉትና ለመኪና ገዥ ብድር መስጠትን እያገቱ በመሆኑ አሁን ለታየው ቅናሽ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡ 

ይህ አንድ ጉዳይ ሆኖ ሌላ ለምሳሌ መኪናን በተመለከተ አጠቃላይ የባንክ ኢንዱስትሪውን ከሚመለከቱ አኃዛዊ መረጃዎች መገንዘብ እንደሚቻለውም በተለይ በተቀማጭ ገንዘብ በብድርና በትርፍ ምጣኔ በቀደመው ልክ ዕድገት ያልተመዘገበ መሆኑ ነው፡፡ 

በ2015 ግማሽ ዓመት መጨረሻ ላይ ሁሉም የአገሪቱ ባንኮች አጠቃላይ ተቀማጭ 1.93 ትሪሊዮን ብር ነበር በ2015 መጨረሻ ላይ ደግሞ ወደ 2.12 ትሪሊዮን ብር ከፍ ብሏል፡፡ በ2016 ግማሽ ዓመት ላይ ደግሞ ይህ ተቀማጭ ገንዘብ 2.29 ትሪሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል፡፡ ይህ አኃዝ ዕድገት ያለ መሆኑን ያሳያል፡፡ ሆኖም በእነዚህ ሦስት የግማሽ ዓመት የተሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ መጠን እየቀነሰ መምጣቱን ያሳያል፡፡ 

የብድር ክምችታቸውም ሲታይ በ2015 ግማሽ ዓመት 1.78 ትሪሊዮን ብር በሰኔ 2015 መጨረሻ 1.95 ትሪሊዮን ብር ነበር፡፡ በ2016 አጋማሽ ይህ የብድር ክምችት 2.08 ትሪሉዮን ብር ደርሷል፡፡  ይህም ዕድገት የሚያሳይ ሲሆን በሦስቱ ስድስት ወሮች የታየው የብድር ዕድገት ሲታይ የ2016 ግማሽ ዓመቱ የዕድገት ምጣኔው በቀድሞ ልክ ያለመሆኑን እንደሆነ ከባለሙያዎቹ ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

የሚወጡ መመርያዎች፣ ታክስ ፖሊሲዎች ያልተረጋጉ መሆንም ገበያው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ የሚችል መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ 

እርጋታ የሌላቸው መመርያዎች ሲወጡ ሰዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ ስለሚያደርግ በዚህ መሀል የዋጋ ቅናሽ ሊያሳይ የሚችልበት ዕድል እንዳለም ጠቅሰዋል፡፡ 

ከተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ አንፃር ሌላው ተፅዕኖ ፈጥሯል ተብሎ የተገለጸው የገንዘብ ፖሊሲው ሲወጣ ታስቦ የነበረው ከ270 ቢሊዮን ብር በላይ በውጭ ያለ ገንዘብ ወደ ባንክ ይገባል የሚል ቢሆንም ይህ በተሰጠው መልክ ያለመግባቱን የባንክ ባለሙያዎቹ ጠቅሰዋል፡፡ 

በአጠቃላይ ግን የገንዘብ ፖሊሲው የተወሰኑ ምርቶች ላይ በተለይ ንብረቶች ላይ የዋጋ መቀነስ እያሳየ ቢሆንም ፖሊሲው ባንኮችን እየተጫነ ስለመሆኑና የተመረጡ ብድሮች ላይ እንዲያተኩሩ መደረጉ አጠቃላይ የአፈጻጸማቸውን ዕድገት እየገደበው ነው፡፡ ይህ ገደብ ምን ያህል ተፅዕኖ እያሳረፈ መሆኑንና በዚሁ መቀጠሉ ሊኖረው የሚችለው ችግር ከፍ እንዳይል የፖሊሲው እስካሁን ያለው አፈጻጸም መገምገምና ማስተካከያ ሊደረግበት እንደሚገባም የባለሙያዎች ምክረ ሐሳብ ያመለክታል፡፡ 

አሁን በአንዳንድ ንብረቶች ላይ የሚታየው የዋጋ መረጋጋት ግን የመንግሥት የገንዘብ ፖሊሲ ሊወጣ ታስቦ የነበረውን ግብ ወደ ማሳካት እየገባ ስለመሆኑ አመላካች እንደሆነ ግን ለዚህ ዘገባ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ያምናሉ፡፡ ችግሩ የዋጋ ንረቱን በተፈለገው ደረጃ በተለይም መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ላይ እየታየ ያለ መሆኑ ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች