Sunday, April 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን ያህል አገርን እየጎዱ እንደሆነ አመላካች ነበር፡፡ ተወካዮቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቧቸው ጥያቄዎችም ሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፅንኦት ሰጥተው ምላሽ የሰጡባቸው ጉዳዮች የሰላም ያለህ የሚሉ ናቸው፡፡ በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በሌሎች አካባቢዎች የሰላም ዕጦቱ ትሩፋት የሆኑት ዕልቂቶች፣ መፈናቀሎች፣ ውድመቶች፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳቶች ኢትዮጵያንና መላው ሕዝቧን ሰንገው የያዙ አደገኛ መከራዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ሰላም በመጥፋቱ ምክንያት ከጦርነትም ሆነ ከተለያዩ ግጭቶች ሕይወታቸው የተረፉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች፣ በየመጠለያው ሆነው የዕርዳታ ምግብ ማግኘት አልቻሉም፡፡ የመንግሥትንም ሆነ የዓለም አቀፍ ለጋሾችን ድጋፍ የሚሹ ወገኖች ከጦርነት በተጨማሪ፣ በድርቅ ምክንያት የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ለረሃብ እየተዳረጉ ነው፡፡ የሚበላ ምግብ አጥተው በረሃብ የሞቱ ወገኖች መኖራቸው ሪፖርት እየተደረገ ነው፡፡ ይህንን አሳዛኝ ሁኔታ በፍጥነት ማስቆም ካልተቻለ ሰብዓዊ ቀውሱ ይባባሳል፡፡

ሰሞኑን ከኦሮሚያ ክልል ተወካዮች ጋር ውይይት መደረጉን ከመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች መገንዘብ ተችሏል፡፡ በአማራም ሆነ በኦሮሚያ፣ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች የሚደረጉ ውይይቶች ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያስገኙ የሚችሉት፣ በትክክል የሕዝቡን ፍላጎት ለማንፀባረቅ ወደኋላ የማይሉ ተወካዮች በስፋትና በምልዓት ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሲደረግ ነው፡፡ እርግጥ ነው ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያ ቀደም ሲል በነበሩ ዓመታት ጭምር ሲንከባለሉ የነበሩ ችግሮች በርካታ ናቸው፡፡ የችግሮቹን መንስዔና የመውጫ መንገዶችን ሊያመላክቱ የሚችሉ የመፍትሔ ምክረ ሐሳቦችን የሚያቀርቡ በዕድሜ፣ በሥራ ልምድ፣ በትምህርት፣ በሥነ ምግባርና በማኅበረሰብ ተቀባይነት የሚታወቁ ተወካዮች ቢኖሩ ይመረጣል፡፡ የደረጁ ሐሳቦች ተሰናስለው ሲቀርቡ ችግሮቹ ብቻ ሳይሆኑ መፍትሔዎቹም አብረው ስለሚኖሩ፣ የሚደረገው ውይይት በመላው ሕዝብ ዘንድ የሚኖረው ተቀባይነትም ይጨምራል፡፡ የሚካሄደው ውይይትም የብዙዎችን ቀልብ ስለሚስብ ለስላቅና ለሐሜት የሚዳርጉ ነገሮች ይቀንሳሉ፡፡ በዚያው ልክ የሁሉንም ዜጎች ትኩረት ሊያገኝ የሚችል የሰላም ፍለጋ ጉዞ በጋራ ይጀመራል፡፡

በሰላም ዕጦት ምክንያት በአማራ ክልል በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ በየጊዜው መንገዶች ስለሚዘጋጉ ምርቶችና ለእርሻ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች አይንቀሳቀሱም፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንት በመስተጓጎሉ ገቢ ማመንጨት አልተቻለም፡፡ ከልማት ይልቅ ውድመት በመበራከቱ የዜጎች ተስፋ እየጨለመ ነው፡፡ ትርፍ አምራች የሆኑ አካባቢዎች ጭምር በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ዕርዳታ ፍለጋ እጃቸውን እየዘረጉ ነው፡፡ ክልሉ በውስጡ በተካሄደው ጦርነት ከተፈናቀሉ በተጨማሪ፣ የወለጋ ተፈናቃዮች ተጨምረውበት ለከፍተኛ ችግር ተዳርጓል፡፡ ዜጎች ሁሉም ነገር ጭልምልም ብሎባቸው ባለበት በዚህ አሳሳቢ ጊዜ፣ የሚደረጉ ውይይቶችም ሆኑ የሚቀርቡ የመፍትሔ ሐሳቦች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚረዱ መሆን አለባቸው፡፡ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ግን የችግሮቹን ስፋትና ጥልቀት የሚመጥኑ የውይይት መድረኮች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ዜጎች በሰላም ዕጦት ምክንያት ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉ፣ ሲራቡና ሲጠሙ በአገር ላይ ሊከተል የሚችለው ቀውስ ማሳሰብ አለበት፡፡ አሁን በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚስተዋለው አደገኛ ሁኔታ አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡ መፍትሔው በጋራ ተመክሮበት አስተማማኝ ሰላም እንዲያመጣ የጋራ ጥረት ይኑር፡፡

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት፣ በትግራይ ክልል አንድ ሺሕ ያህል ሰዎች በረሃብ ሳቢያ ሳይሞቱ እንዳልቀሩ መረዳቱን አስታውቆ ነበር፡፡ በአማራ ክልልም ቁጥሩ አይታወቅ እንጂ ሟቾች መኖራቸው ሲነገር ተደምጧል፡፡ የችግሩ ፅናት ከቦታ ወደ ቦታ ይለያይ እንጂ በበርካታ አካባቢዎች ዜጎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሳይቀር ምግብ አጥተው የሚራቡ ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በጦርነትና በግጭት ቀጣናዎች ውስጥ የሚገኙ ዜጎች መከራ ግን ለንፅፅር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶች የችግሩን ፅናት በተለያዩ መንገዶች እየገለጹ ነው፡፡ ሰሞኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ድጋፎች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ እስከሚቀጥለው መጋቢት ወር ድረስ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ካልተገኘ በኢትዮጵያ ድርቅና ረሃብ እንደሚባባስ አስታውቋል፡፡ የተጠቀሰው ገንዘብ ካልተገኘ ግን በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖች ለከፋ ቀውስ እንደሚጋለጡም አስጠንቅቋል፡፡ በአገር ውስጥ ያለው ችግር በዚህ መጠን በውጭ ሰዎች በሥጋት ሲገለጽ ካለስደነገጠ ምን ሊያስደነግጥ ነው?

ዓለም በከፍተኛ የዕድገት ግስጋሴ ላይ በሚገኝበት በዚህ ዘመን እንደ ጥንታዊ የጋርዮሽ ሥርዓተ ማኅበር ጊዜ፣ ዜጎች የሚቀምሱት አጥተው ሥራ ሥርና ቅጠላ ቅጠል ሲመገቡ ከማሳዘን አልፎ ያስቆጫል፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች አንፃራዊ ሰላም እያሰፈኑ የዕድገት ትልም በሚያወጡበት ዘመን፣ እንደ ዘመነ መሣፍንት ጊዜ በየአካባቢው ግጭት እየቀሰቀሱ መፋጀት ጤነኝነት አይደለም፡፡ የምዕራባውያን በተለይም የአሜሪካ ፖለቲከኞችና የጦር አማካሪዎች ሰላም ማስፈን ያልቻሉ አፍሪካ አገሮች ጉዳይ ግራ እያጋባቸው፣ ዘመናዊ ቅኝ አገዛዝ ያስፈልጋቸዋል እያሉ ምክረ ሐሳብ እየሰጡ መሆናቸው ካላሳሰበ ምን ሊያሳስብ ይችላል? በድሮ ጊዜ ኢትዮጵያውያን የውጭ ጠላት ሲመጣ ውስጣዊ ችግሮቻቸውን በማለዘብ በጋራ ይመክቱ ነበር፡፡ አሁን ግን ያን መሰሉ ስሜት ሊኖር የማይችልበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን እንዴት ማጤን ይከብዳል? እርስ በርስ መጨካከኑና መፋጀቱ በቀጠለ ቁጥር የጥንቱ አብሮነት ሊኖር ይችላል ተብሎ ይታሰባል ወይ? በጦርነት፣ በድርቅና በረሃብ የተዳከመ ሕዝብ አገሩን ከምንም ዓይነት ጥቃት መከላከል ይችላል ተብሎ አይታሰብም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሞኑ ስብሰባ መንግሥት ፋታ ካላገኘ ሥራ መሥራት እንደማይችል ጠቅሰው፣ ይቅርታ ተደርጎም ሆነ ካሳ ተከፍሎ ሰላም ቢሰፍን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ በመላ አገሪቱ ፋታ ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ዕፎይታ እንዲፈጠር መንግሥት በራሱ በኩል የሚጠበቅበትን ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በተገዳዳሪዎቹ በኩል የሚቀርቡለትን የመተማመኛ ጥያቄ ለመመለስም ዝግጁ ሊሆን ይገባል፡፡ አሁን የሚታየው እጅግ በጣም ጥልቅ የሆነ ክፍፍልና አለመተማመን በርካታ ጋሬጣዎች አሉት፡፡ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በሙስና፣ በብልሹ አሠራሮችና በመሳሰሉት ሳቢያ ለሰላም ጠንቅ የሆኑ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመሻገር ግን ሰፊና ጥልቅ የሆነ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ አላስፈላጊ ድርጊቶች በርካታ ብልሽቶችን ስለፈጠሩ፣ መንግሥት በጥልቀት ውስጡን በመፈተሽ ራሱን ከአላስፈላጊ ነገሮች ማፅዳት አለበት፡፡ ይህንን  በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ሲችል ያኮረፉ ብቻ ሳይሆኑ፣ ትጥቅ ያነገቡ ጭምር ወደ ንግግርና ድርድር የሚመጡበት ዕድል ይመቻቻል፡፡ አሁን ባለው አሳሳቢ ሁኔታ መቀጠል ስለማይቻል፣ ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ (ክፍል አንድ)

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...

የአገሪቱ ባንኮች የመጭበርበር ተጋላጭነት እየጨመረ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ2 ቢሊዮን ብር መጭበርበሩን ገልጿል ቀሲስ በላይ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

እንደገና ያገረሸው ግጭት መፍትሔ ይፈለግለት!

ሰሞኑን በራያና አካባቢው እንደገና ያገረሸው ግጭት አስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጠው፣ አድማሱ ሰፍቶ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስ አያጠራጥርም፡፡ በራያ በኩል የተጀመረው ትንኮሳ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተዛምቶ ተጨማሪ...

ስልታዊ መፍትሔን የሚሻው የኪነ ጥበቡ ዘርፍ

የኪነ ጥበቡ ዘርፍ በተለይም ፊልምና ሙዚቃ በውስብስብ ችግሮች ውስጥ እያለፈ ይገኛል፡፡ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ሲስተም በአግባቡ አልተበጁለትም፡፡ ስለሆነም ይህ ችግር ከመሠረቱ እየተፈታና እየተቀረፈ ካልሄደ ከዓመት...

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...